የአንጋፋው ስፖርት ክለብ መቻል 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ከሰኔ 01 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቶ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በክብር እንግድነት በተገኙበት ትናንት በአዲስ አባባ ስታድየም በድምቀት ተጠናቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስታዲየም ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት “መቻል አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴን፣ ምሩፅ ይፍጠርን፣ ጌጤ ዋሜንና አልማዝ አያናን ለሀገር ያበረከተ ባለውለታ ክለብ ነው፡፡ በመቻል 80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ዛሬ ተገኝተናል፡፡ የመቻል ስፖርት ክለብ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩራት ያስጠሩ ዕንቁ ስፖርተኞችን ያፈራ የሕዝብ ክለብ ነው፡፡ይህ ድንቅ ክለብ የክብር ዘባችን የሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን የድል አድራጊነት ምልክታችንና ተምሳሌታችን ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ገናና የስፖርት ክለብ የቀድሞ ታሪኩን አድሶና በውጤት ታጅቦ የሠራዊቱ የሥነ-ልቦና ጥንካሬ መሠረት ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡” ብለዋል።
“መቻል ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ከአንድ ወር በላይ ሲከበር በሰነበተው ክብረ በዓል የፓናል ውይይት፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን፣ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታዎችና ልዩ ልዩ ጉብኝቶች እንዲሁም መሠል ክዋኔዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ከነዚህ መርሐግብሮች መካከል በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊው የዩጋንዳው ክለብ ኪታራ ከመቻል ጋር የሚያደርጉት የወዳጅነት ጨዋታ ነው። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ትናንት 10:00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲከናወን እንግዳው ክለብ ሁለት ለዜሮ ማሸነፍ ችሏል። የክለብ ኪታራን የማሸነፊያ ሁለት ግቦች ዴኒስ ኦሜዲ 24 እና 73ኛ ደቂቃዎች ላይ ከመረብ አሳርፏል።
በዚህም ክለብ ኪታራ ለመቻል 80ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓል የተዘጋጀውን ዋንጫ አንስቷል። ኪታራ ልዩ የክብር ዋንጫና ሜዳለያ ሲበረከትለት ለመቻል ደግሞ የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷል። በጨዋታው ድንቅ ብቃት በማሳየት ሁለት ግቦች ላስቆጠረው የኪታራ ተጨዋችም ሽልማት ተበርክቷል።
የመቻል የቴክኒክ ዳይሬክተር የካፍ ኢሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ ክለብ ኪታራ ከወዳጅነት ጨዋታው በኋላ ወደ ሀገሩ ከመመለሱ በፊት በሁለቱ ክለቦች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት እና የትብብር ስምምነት ለመፈራረም ከመቻል ስፖርት ክለብ ቦርድ አመራሮች ጋር እንደሚወያይ መግለፃቸው ይታወሳል።
የኪታራ እግር ኳስ ቡድን ፕሬዚዳንት ካሶዚ ዲኦ ለቡድኑ ለተደረገው ደማቅ አቀባበል ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸውም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምስረታ በዓሉ የማጠቃለያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ስታድየም በድምቀት ሲካሄድ የባለሥልጣናት ቡድን የባለሀብቶችን ቡድን በወዳጅነት ጨዋታ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በተመሳሳይ የወዳጅነት ጨዋታ የአርቲስቶች ቡድን የቀድሞ የመቻል ተጫዋቾችን 3ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ለሁለቱም ተሳታፊ ቡድኖች ልዩ የክብር ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል።
ፖርቹጋላዊው የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ኮከብ ሉዊስ ናኒ እና ናይጄሪያዊው የቀድሞ የአርሰናል ኮከብ ንዋንኮ ካኑ የመቻልን የምስረታ በዓል ለማድመቅ ተጋባዥ ሆነው ከቀናት በፊት አዲስ አበባ መግባታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በትናንቱ የማጠቃለያ መርሐግብርም በስቴዲየም መገኘታቸው ክለቡ በተለይም እግር ኳሱ ላይ የበለጠ ትኩረት ለመስጠትና ለማነቃቃት እገዛ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።
የመቻል ክለብ የቦርድ አመራር ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለው ዓላማም ክለቡን ወደ ነበረበት ታላቅነት መመለስና ከራሱ አልፎ የኢትዮጵያን ስፖርት መቀየር እንዲችል የማገዝ፣ የማደራጀት፣ ከሠራዊቱ ጋር የማቆራኘት ሥራዎች ይከናወናሉ። በቀጣይም ከትልልቅ የምዕራብና የሰሜን አፍሪካ የሚሊተሪ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
የገዘፈ ስም እና ዝና የነበረውን መቻል ወደ ቀደመ ታሪኩ ለመመለስ የተሠራው ሥራ መቀዛቀዝ የሚያሳየውን የስፖርት ዘርፍ የሚያነቃቃ እና ወጣቱ ስፖርት ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግም የራሱ የሆነ አዎንታዊ ገፅታ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የስፖርት ጉዞ ለኢትዮጵያ የስፖርት እድገት የራሱ የሆነ ድንቅ አሻራ እያሣረፈ የመጣ ስለመሆኑ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በየጊዜው ከክለቡ ተመልምለው ሀገር በመወከል አንፀባራቂ ውጤት ያስመዘገቡ ስፖርተኞች ምስክሮች ናቸው።
መቻል የስፖርት ክለብ በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቮሊቦል፣ እጅ ኳስ እና ቅርጫት ኳስን የመሳሰሉ ስፖርቶችን በማቀፍ በተለያዩ አገር አቀፍ ውድድሮች እየተሳተፈ ሲሆን፤ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል 80ኛ ዓመቱን ተንተርሶ ትልልቅ እቅዶችን ለማሳካት ወጥኗል። በአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያንና አፍሪካን ማኩራት ከቻሉት ከሻምበል አበበ ቢቂላ እና ማሞ ወልዴ አንስቶ በርካቶችን በማፍራት እስካሁን ዘልቋል። በቦክስ ስፖርትም ትልልቅና ሀገርን መወከል የቻሉ ቦክሰኞችን አፍርቷል። በእግር ኳስም ጠንካራ የሴቶችና ወንዶች ክለብን በመገንባት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም