አስተሳስረውና አጋምደው ካመጡን የወል ስሞች መሀል ብዙና አንድ መልክ የሚለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ብዙ እና አንድ መልክ በህብረብሄራዊነት ተምጦ ኢትዮጵያዊነት የተወለደበት፣ አብሮነት ያበበበት የማንነታችን ቀለም ነው። ቀለሙ በዘርና ብሄር የማይደበዝዝ፣ በፖለቲካ ትርክት የማይጠኸይ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የቃል ኪዳን ውርስ ነው። ይሄ የአብሮነት ቀለም አባቶቻችን ከቀደምቶቻቸው የወረሱት እኛም ከአባቶቻችን የተቀበልነውና ለመጪው ትውልድ የምናስተላልፈው የኢትዮጵያዊ ትውፊት ነው።
የሶስት ሺህ ዘመን የታሪክ አውራ ስንባል፣ የጀግንነትና የሉዓላዊነት አርማ ስንሆን፣ የነጻነትና የብኩርና፣ የፍትህና የእኩልነት፣ የሥልጣኔና የዘመናዊነት፣ የሥርዓትና የግብረገብነት ፊተኛ ምድር ስንባል ከላይ በተጠቀሰው በብዙሃነት ውስጥ ባለው የአንድነት ቀለሞቻችን ነው። ነጋችንን በሰላምና በእርቅ፣ በመከባበርና በመቻል ለመቀበል የህብረብሄራዊነት ቀለማችን በጥላቻ መልኩን እንዳይስት ከሃላፊነት ጋር መታገል አለብን። በራዕይና በተስፋ የኳልነው መጪው ጊዜ የሁላችን እንዲሆን ዛሬ ላይ ከሁላችን የተዋጣ ሰላም፣ ፍቅር፣ እርቅ፣ ትቅቅፍ ያስፈልጋል።
የዛሬ መከራዎቻችን የትናንት ውጤቶች እንደሆኑ እያወቅን ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬን አለመረባረባችን የሚያሳዝነው የታሪካችን አካል ነው። ዛሬ ላይ እርቅና ምክክር ብለን መነሳታችን ነገን የተሻለ ለማድረግ ድርሻው የላቀ ነው። ትናንት ላይ ለእርቅና ለፖለቲካ ስምምነት መድረክ ኖረውን ቢሆን፣ ለአብሮነትና ለኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ምክክር ኖሮ ቢሆን የዛሬ ችግሮቻችን ባነበሩ ነበር። ዛሬን በአግባቡ መጠቀም ማለት ነገን የተሻለ ማድረግ ማለት ነው። አሁን ላይ ብሄራዊ ምክክርን እንደብሄራዊ ድልና እንደህብረብሄራዊ አርማነት ቆጥረን መጪውን በጎ ለማድረግ የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል።
ብሄራዊነት ብዙሃነት ነው። ብዙሃነት ደግሞ የብዙ አስተሳሰብ፣ የብዙ ምክክር አስተዋጽኦ ነው። ስለሀገራችን ከሆነ የምንመክረው የእኔ የአንተ በሌለው የጋራ ሃሳብ ስር የአብሮነት ህልም ያስፈልገናል። በእኛ ሀገር የአርቅና ምክክር ታሪክ ላይ እንደትልቅ ችግር የሚነሳው ሀገርን ከፊት አድርጎ ለተግባቦት አለመቀመጥ ነው። የምንሰባሰበው ለማሸነፍ አሊያም ደግሞ የበላይነታችንን ለማንጸባረቅ ነው። እንዲህ አይነቱ ሞገደኝነት ብዙ ዋጋ አስከፍሎን ያውቃል። በሀገር ጉዳይ ላይ ማንም አሸናፊ የለም። ከብዙሃነት ውስጥ አንድ በላጭ ሃሳብ ተመርጦ ለትውልዱ ቅርስ፣ ለማህበረሰቡ ደግሞ ውርስ ሆኖ ታሪክ ይቀጥልበታል። ይሄ ማለት ሃሳቡ የአንድ ወገን ወይም የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን ከብዙሃነት ውስጥ የተውጣጣ ነው ማለት ነው።
ጋን በጠጠር እንደሚደገፍ የእኛ ሃሳብ የሆነ ቦታ ላይ የሀገር ቀዳዳ መድፈን የሚችል ነው። ጋንን የሚያክል ትልቅ ነገር ትንሽዬ ጠጠር ስትደግፈው፣ ስታቆመው መግረሙ አይቀርም። ግን አይገርምም ትንሽዬዋ ጠጠር ትልቁን ጋን ያቆመችው በትክክለኛው ቦታ ለትክክለኛ ዓላማ ስለዋለች ነው። ሃሳብም እንደዚህ ነው። በትክክለኛው ቦታ ለትክክለኛው ነገር ከተሰባሰብን ለውጥ እናመጣለን።
በቅንነትና በትዕግስት ከተሰባሰብን ሃሳቦቻችን ቀዳዳዎቻችንን መድፈን አያቅታቸውም። ችግሩ ትዕግስት የለንም። ላለመግባባትና ላለመስማማት ስለምንሰባሰብ ሃሳቦቻችን አስቀድመው ይከሽፉብናል። ሃሳቦቻችን በትክክለኛው ጊዜ ለትክክለኛው ዓላማ ከዋሉ ተአምር መፍጠር የሚችሉ እንደሆኑ እያወቅን ግን በገዛ እጃችን ነውጥና መከራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ እያደረግናቸው ነው።
በጥላቻና በትዕቢት ተሞልተን፣ በዘርና በብሄር ተቧድነን እንዴት ነው ሀገር የምናሻግረው? በእኔነትና በራስ ወዳድነት ጎልምሰን እንዴት ነው ትውልድ የምናርቀው? በሀሰት ትርክት በልጽገን ጎራና ድንበር ከፍለን እንዴት ብለን ነው ኢትዮጵያዊነትን የምናስቀጥለው? እውቀቶቻችን የትምክህት ሆነው፣ ዲግሪና ዶክተሬቶቻችን የጥላቻ ሆነው በምን አቅማችን ነው አስታራቂና መካሪ የሚወጣን?።
እልህና ሃይል የፖለቲካችንና የፖለቲከኞቻችን መገለጫ ሆነው፣ ለትውልዱ ቁብ በማይሰጥ ራስ ወዳድነት እንዴት ነው አርነት የምንወጣው? ሥልጣንና ጌትነት በጦር ሜዳ ጀብድ ተስለው፣ ማዕረጎቻችን ወንድሞቻችንን ገለን ያገኘናቸው ሆነው እንዴት ነው ከጥላቻ የምንጸዳው? ፈርሃ ፈጣሪ በሌለበት የእርስ በርስ ሽኩቻ መቅደሶቻችን ተንስኦን አስተጓጉለው፣ መስኪዶቻችን አዛን ማለት ፈርተው እንዴት ነው ጨዋነትነ የምናስቀጥለው?።
መጀመሪያ ራሳችንን እንመልከት። የሀገር ሥልጣኔ ያለው በግለሰብ ሥልጣኔ ውስጥ ነው። የትውልድ ተስፋ በእኔና በእናተ አሁናዊ አስተሳሰብ ውስጥ ያለ ነው። በአስተሳሰባችን ሀገር እየሠራን፣ ትውልድ እየፈጠርን ነው። አሁን ላይ የምንሆነው የትኛውም ነገር የትውልዱ የነገ ውርስ ነው። ለዛም ነው ስለሰላም እናውራ፣ ስለአብሮነት እንነጋገር የምንለው። እኛ ሥላልሠለጠንን፣ እኛ ስላልበቃን፣ እኛ ስላልነቃን ነው ሀገራችን ከጦርነት ወደጦርነት የሆነችው። ራሳችንን ገዝተን ከስሜት ወደስሌት፣ ከፉክክር ወደምክክር ስንሄድ ነገሮች በራሳቸው ጊዜ ይስተካከላሉ።
ሃሳቦቻችን መፍትሄ እንዳይሰጡን በጥላቻ መርዝ ያደበናቸው እኛው ነን። ተነጋግረን ለመግባባት ንጹህ ልብ ያስፈልገናል። በአንድነት ስለአንድነት ለመወያየት ከእኔ ከአንተ አስተሳሰብ መላቀቅ ግድ ይለናል። ሃሳቦቻችን ትርፍ ያልሰጡን፣ ከጦርነት ወደጦርነት የሆነው በዚህ ነው። እስኪ ሃሳቦቻችንን እንግራ። ከእርግማን ወደምርቃት፣ ከጥላቻ ወደፍቅር እንሸጋገር። ከራስወዳድነት ወደአጋሪነት፣ ከጦርነት ወደሰላም እንመለስ።
የደም መንገዶች ካልተዘጉ የሕይወት መንገድ አይከፈትም። የጥላቻ መንገድ ካልተሻረ የፍቅር ሰርጥ አያብብም። የብሄር ፖለቲካ ሁሉን አካታች በሆነ የብዙሃነት መንፈስ ካልተቀየረ ስጋቶቻችን አይለቁንም። ዘረኝነትን ለብሰን ስለራሳችን ብቻ ምንታትረው የራስወዳድነት ውርስ ካለቀቀን አብሮነትን ማቀንቀን አንችልም።
ኢትዮጵያ ፍሬ እንድታፈራ እኛ ልጆቿ በሃሳባችን፣ በአብሮነታችን ፍሬ ልናፈራ ይገባል፡። የእኛ ፍሬ ነው ሀገራችን ላይ የሚታየው። የእኛ ፍሬ ነው ትውልዱ ላይ የሚገለጠው። አበባዎቻችን በእርስ በርስ ሙግት እንዳይደርቁ፣ ቁንጉሎቻችን በዘረኝነት ያለጊዜአቸው እንዳይመክኑ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚል መርህ ያስፈልገናል። ያለምንም ደም፣ ያለምንም ጦርነት፣ ያለምንም ግፊያ ኢትዮጵያ እንድትቀድም ሃሳባችን ዋጋ አለው።
ከመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከጆርጅ ዋሽንግተን ጀምሮ እስካሁኑ ጆባይደን ድረስ በአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ወለም ዘለም የማይል አንድ መመሪያ አለ እርሱም ‹ቅድሚያ ለአሜሪካ› የሚል ነው። በግራ ዘመሙም ሆነ በቀኝ ዘመሙ፣ በሪፐብሊካንም ሆነ በዲሞክራቶች ዘንድ ‹ቅድሚያ ለአሜሪካ› የሚል መተዳደሪያ መፈክር አለ። በብዙ ተለያይተው መስማሚያቸው ሀገራቸውና ሕዝባቸው ነው።
በአንዳንድ ሀገራት ይሄ እውነታ መልኩን ስቶ ሀገርና ሕዝብ መታረቂያ ከመሆን ይልቅ የግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ እየሆነ ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የእኛ ፖለቲካና ሕዝብ እናገለግላለን የሚሉ ፖለቲከኞቻችን ናቸው። በእኛ ሀገር የፖለቲካ ታሪክ ፖለቲካውም ፖለቲከኞቻችን ሕዝብ እያገለገሉ አይደለም። በሕዝብ ስም የራሳቸውን ፍላጎት እያራመዱ እንጂ።
ወደ ሕዝብ ማየት እስካልጀመርን ድረስ ስጋቶቻችን ያይላሉ እንጂ አይረግቡም። ሌሎቹ ሀገራት በብዙ ሃሳብ ተለያይተው መድረሻቸው ግን ሀገራቸው እና ሕዝባቸው ናቸው። እኛ ግን በብዙ ሃሳብ ተለያይተን መነሻና መድረሻችን ብሄርተኝነት ነው። ወደሕዝብ፣ ወደትውልዱ፣ ወደአብሮነታችን ማየት እስካልቻልን ድረስ በብቻ እና በግል ፍላጎት የብዙሃኑን ጥያቄ መመለስ አንችልም። ይሄ ብቻ አይደለም ሃሳቦቻችን ውሃ እንዳያነሱ፣ ተነጋግረን እንዳንግባባ እክል እየፈጠርን ነው።
ሀገር ያልቀደመችበት ሃሳብ፣ ትውልድ ያልተከተለበት ፖለቲካ መርዛም ነው። ፖለቲካችን ባሳደገንና የልጅነታችን ጥበብ በሆነው ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› በሚለው እውነታ በኩል ወደሕዝብ ይንጸባረቅ። ትስስሩ ‹መንግሥት ማለት ሕዝብ፣ ሕዝብ ማለት መንግሥት› የሆነ እውነታ ወደአንድ ወገን ሲያጋድል ሀገር ይዞ ነው የሚወድቀው።
በብሄር እና በዘረኝነት ልንወድቅ ወደአንድ ወገን አጋድለናል ቀና የሚያደርገን ደግሞ ከብዙሃነት ውስጥ የተማጠ ኢትዮጵያዊነት ነው። በብሄራዊ ምክክር ስም እንነጋገር ብለን መድረክ ስናዘጋጅ በትርክት ሊበጠስ የሰለለውን ውል ለማጠንከር ነው። ብዙሃነትን ወደአንድነት አንድነትን ወደብዙሃነት ለመመለስ ነው። ሀገር የማዳን ተልእኮ በትዕቢትና በማንአለብኝነት አይሆንም ።
ሀገር ትሁት ልብ፣ ታጋሽ አእምሮ ትፈልጋለች። ሀገር ቅን ፖለቲካ እና ቅድሚያ ለሀገሬ የሚል ፖለቲከኛ ትሻለች። ከሥርዓትና ጨዋነት፣ ከኢትዮጵያ ሥነምግባር ያልወጣ ሥርዓት መልኳ ነው። ከትናንት ወደዛሬ ስንመጣ፣ በዓለም አደባባይ ስንታወቅ በእንዲህ አይነቱ ስም በኩል ነው። በጥላቻ ውስጥ የአብሮነት መንፈስ የለም። እየቀጡ እና እየተቃወሙ ተግባቦት የለም። እየገደሉ እርቅ የማይታሰብ ነው። ከሁሉ በፊት ራሳችንን እንጠይቅ..ሰላም ወደሚሰጠንና ሰላም ወዳለበት ወደእርሱ መልህቃችንን እንጣል።
ኢትዮጵያ በብዙ መለያየት ውስጥ የጋራ ብለን የምንጠራት ሀገራችን ናት። በብዙሃነት ውስጥ አንድነትን ያገኘንባት፣ የክብራችንና የማንነታችን ዋርካ ናት። በፍቅር ከሆነ ጥላዋ ሰፊ ነው። በአብሮነት ከሆነ እቅፏ ለምለም ነው። ለሁሉም የሚበቃ የእናትነት እልፍኝ አላት። በዝተንና ሰፍተን መቶ ሰላሳ ሚሊዮን ብንደርስም በፍቅር ከሆነ አትጠበንም። እያበበችን እያነሰችን ያለው የብኩርና ግፊያ ስለያዝን ነው። ፍቅር ያለበት ሁሉ በረከተ ሰፊ ነው። ፍቅር አጥተን፣ አንድነት ርቆን ጠየምን እንጂ ዓለምን ያፈገግን የብርሃን በትሮች ነበርን።
ኢትዮጵያ በሚለው ስም በኩል ሙሉና ምልኡ ነን። ከዚህ ስምና ከዚህ ወኔ ሌላ በብዙሃነት ውስጥ አንድነትን፣ በአንድነት ውስጥ ብዙሃነትን የምናስቀጥልበት ሌላ መተማመኛ ስም የለንም። በዚህ ስም በኩል ዘመን ተሻጋሪ የጋራ ድሎችን ተቀዳጅተናል። ድሎቻችን በነጠላ ትርከት ያልተፈጠሩ፣ በፊትና ኋላ ስም ያልሰመሩ ከእኛው በእኛው የሆኑ የውህድ ውጤቶች ናቸው። ተደባልቀን በአንድነት የቆምነው፣ በብዙሃነት ውስጥ በኢትዮጵያዊነት የጸናነው በእንዲህ መሳዩ አመክንዮ ነው። አሁን ላይ በያዝንው የአብሮነት ምክክር የጋራ ትርክቶች ያስፈልጉናል።
እንደሀገር ስንቆምና እንደማህበረሰብ ስንጠራ መነሻ ያደረግንው ከአብሮነት ውስጥ የተወለደን ታሪክና ሥርዓት፣ ባህልና ወግ፣ ክብርና ሉዓላዊነት ነው። እነዚህ የህብረብሄራዊነት ጌጦች እንደክታብ አንገታችን ላይ ተንጠልጥለው የመቻቻልና የመከባበር ስሞቻችን ሆነዋል። ከእኛ አልፈው መላውን ዓለም ነጻ ያወጡ የሰላምና የፍቅር ምልክት ሆነው የክብር ስምን አሰጥተውናል። እነዚህን ማስቀጠል እንጂ ማበላሸት ለማንም ክብር አይጨምርም። ስለሰላም የሆነ የምናወራው፣ ስለአንድነት ከሆነ የምንመክረው ብዙሃነት የታከለበት የጋራ ትርክት ነጻ አውጪያችን ነው።
ከእኛነት ውስጥ ፈልቅቀን ባወጣነው የአብሮነት መርህ ካልተመራን፣ ከብዙሃነት ውስጥ በተወለደ የእድልና ድል ሕግ ከልተገዛን ተነጋግረን መግባባት ይቸግረናል። አስታራቂና አዋሃጅ በሆኑ ሃሳቦች ስር ካላረፍን፣ ትናንትን በይቅርታ ዛሬን በእርቅ ነገን በተስፋ ለመቀበል በተሰናዳ ሥነልቦና ካልጸናን ከስጋት አንድንም። ኢትዮጵያን ባለና ባስቀደመ ፖለቲካ ስር ካላረፍን፣ ዘረኝነትን በሚሽር እና አብሮነትን በሚያስቀጥል ምክክር ሃሳብ ካልተለዋወጥን አንግባባም።
በኢትዮጵያዊነት ብዙ እና አንድ መልክ ነን። ተደባልቀን ቅይጦች ሆነናል። ከዚህ ትስስር ውስጥ አንድ መምዘዝ መላውን ማውደም ነው የሚሆነው። ልክ እንደ ደም ስር ማንነታችን በአንድ ቋጠሮ ስር ነን። ልዩነቶቻችን ትንሽ አንድነታችን ግዙፍ ሆኖ ታሪክ የሠራን፣ ሥርዓት ያጸናን የወንድማማችነት ተምሳሌቶች ነን። የነበረውን ከማስቀጠል ውጪ የምንፈጥረው አንዳች ነገር የለንም።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም