የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሊጀመር ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። በታላቁ መድረክ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀትና የማራቶን ውድድሮች የዓለም ከዋክብት አትሌቶችን አሰልፋ ውጤታማ ትሆናለች ተብላ የምትጠበቀው ኢትዮጵያ ግን ውጤታማ ለመሆን ከምታደርገው ዝግጅት ይልቅ ስፖርቱን በሚመሩ ተቋማትና አመራሮች የሚፈጥሩት ውዝግብ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል። በዚህም ኢትዮጵያ ስሟና ባንዲራዋ ከፍ ብሎ በሚጠራበት ዓለም አቀፍ መድረክ የተለመደ ድል እንዳታስመዘግብ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ስጋት አድራል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሕግና ደንብ ውጪ ካደረገው የፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ የጀመረው ውዝግብ ቀጥሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየጊዜው ከሚቀያይረው መርህ አልባ የአትሌቶች ምርጫ እንዲሁም የሀገሪቱን ስፖርት በበላይነት ከሚመራው ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር የተፈጠረ አለመግባባት ድረስ ስፖርቱ እየታመሰ ነው። ይህም በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ ያስነሳና አትሌቶች እንዲበደሉ ማድረጉ ለማንም የተሸሸገ አይደለም። በዚህ ውዝግብ መካከል ሁሉም አካላት በመግለጫ ጋጋታ ድንጋይ ከመወራወር ባለፈ ስለ ሀገር ቆም ብለው እያሰቡ እንዳልሆኑ በግልፅ ታይቷል።
እነዚሁ አካላትም በተለያዩ ጊዜት በግል እንዲሁም እንደ ተቋም ጋዜጣዊ መግለጫ በመጥራትም ችግሩን ከማረጋጋት ይልቅ እያባባሱት ይገኛሉ። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም ሕዝብ ዘንድ ከፍ ብላ የምትታይበትን የእንቁ አትሌቶች የኦሊምፒክ ዝግጅት በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል።
በኦሊምፒኩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች፣ አሠልጣኞችና ክለቦች አሁንም ድረስ ከምርጫና ከሌሎች አሠራሮች ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን በማንሳት ላይ ይገኛሉ። ባለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የታየው የውጤት ድርቅ በፓሪስም እንዳይደገም ልዩነቶችን በመግታት ትኩረቱን በአትሌቶችና በውድድሩ ላይ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ከሚያመላክቱ አካላት መካከልም የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር አንዱ ነው።
በቶኪዮ ከተከሰተው የውጤት መጥፋት ትምህርት በመውሰድና አብሮ በመሥራት በኦሪጎኑ የዓለም ቻምፒዮና አንጸባራቂ ድል መመዝገቡን የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነቴ ያስታውሳል። ነገር ግን በዚህ ኦሊምፒክ ችግሩ ዳግም አገርሽቶ ብሄራዊ ቡድኑን በአንድነት ማሠልጠን እንኳን እንዳልተቻለ ይናገራል። አትሌቶች ዝግጅታቸውን በየፊናቸው እያደረጉ መሆኑንም ማሳያ አድርጎ ያስቀምጣል። ‹‹ለአንድ ሀገር በአንድ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ተለያይተዋል›› ሲልም ስጋቱን አጋርቷል።
ይህንን ተከትሎም ማህበሩ ለሚመለከተው አካል አካሄዱ ትክክል አለመሆኑን ቢያስታውቅም መፍትሄ ማግኘት ግን አልተቻለም። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የታየው አሳፋሪ ክስተት መፍትሄ አለማግኘቱም እየተንከባለለ መጥቶ አሁንም በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ እየታየ እንደሚገኝ ኮሚሽነር ማርቆስ ተናግሯል። ‹‹ስለ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሚጨነቅ አካል በቀረው ጥቂት ሳምንት መፍትሄ መፈለግ አለባቸው። አትሌቶችም በትክክል መሳተፍ በሚገባቸው ርቀቶች ካልተሳተፉ የሚጠበቀው ውጤት ላይመጣ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ ወቅት አትሌቶች ዝግጅታቸውን አጠናቀው ትኩረታቸውን በውድድሩ ላይ የሚያደርጉበት እንጂ ስለምርጫ የሚታሰብበት መሆን አልነበረበትም፡፡›› በማለት ኮሚሽነር ማርቆስ ያስረዳል።
እንደ ኮሚሽነር ማርቆስ አስተያየት፣ የአትሌቶች ምርጫ አሠልጣኞች በሚመለከቱት ወቅታዊ አቋም ላይ የተመሠረተ እንጂ በፌዴሬሽኑ የሚደረግ መሆን የለበትም። እስካሁን በትክክል የትኛው አትሌት በየትኛው ርቀት ይሳተፋል የሚለውን መለየት አልቻሉም፤ ምክንያቱም አትሌቶች እየተመረጡ ያሉት በግለሰቦች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው። ይህም የአትሌቶች ትኩረታቸውን ዝግጅታቸው ላይ እንዳያደርጉ አእምሯዊ ሰላም የሚነሳና ሥነልቦናቸውን የሚጎዳ ነው። ማህበሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚመለከታቸው አካላት ያለውን ስጋት አስታውቋል፣ ነገር ግን ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ ማዘኑን ኮሚሽነር ማርቆስ ይናገራል።
በሌላ በኩል ከኮሚቴው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ጋር በተያያዘም በድብቅ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነም ነው ፕሬዚዳንቱ የጠቆመው። ‹‹የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ በግልጽና አባል ማህበራትን ባሳተፈ መልኩ መሆን ነበረበት። ምርጫው ተደርጓል መባሉን ተከትሎም አትሌቶችን በመወከል ሥራ አስፈጻሚውን እንዲቀላቀሉ የተደረጉት አትሌቶች በማህበሩ የተወከሉ አይደሉም። ልክ እንዳለፈው ዓመት በድብቅና ከሕግ ውጪ በሆነ ሁኔታ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውጪ በአመራርነት ለመቆየት ሲባል መደረጉ በእርግጥም ስፖርቱን ይጎዳዋል፡፡›› ሲልም አስረድቷል፡፡
ኮሚሽነር ማርቆስ ኮሚቴው ሀገርን ከሚያስጠራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በአትሌቶች ላይ አተኩሮ መሥራት ሲገባው ኦሊምፒክ ሲደርስ ብቻ ጠብቆ ውዝግቦች እንዲነሱ ምክንያት እንደሆነ ያምናል። የኮሚቴው ሃላፊነት የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ቡድንን መምራት ብቻ ቢሆንም ቴክኒካዊ ሥራዎች ላይ ጭምር ጣልቃ እንደሚገባም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚና የቴክኒክ ኮሚቴ አባል የሆነው አንጋፋው አትሌት ማርቆስ ይናገራል። በዚህም ምክንያት የአትሌቶችን ስሜት በእጅጉ እየጎዳ ይገኛል ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም