ፕሬዚደንት ባይደን የኔቶ አባል ሀገራትን ከጥቃት ለመመከት ቃል ገቡ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የኔቶ አባል ሀገራትን መሪዎች በዋሺንግተን ዲሲ ተቀብለው አስተናግደዋል።

ጠንከር ያለ ንግግር ያሰሙት ፕሬዚደንቱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራትን ከጥቃት ለመመከት እንዲሁም በሚመጣው ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ለመርታት ቃል ገብተዋል።

አጠር ያለ፤ ነገር ግን ጠንካራ የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት ባይደን የጦር ቃል-ኪዳኑ “ከመቼውም ጊዜ በላይ ጉልበት ያዳበረበት ወቅት ነው” ነው ካሉ በኋላ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ያለው ጦርነትን አውስተዋል።

“አምባገነኖች የዓለምን ሥርዓት እያዛቡ ነው” ሲሉ ያስጠነቀቁት ባይደን ለኪዬቭ ተጨማሪ እርዳታ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ከጆ ባይደን በተጨማሪ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ እና ሮሜኒያ ለዩክሬን ፓትሪዮት የተሰኘው ሚሳዔል ባትሪ ለመለገስ ቃል የገቡ ሲሆን ይህ ርዳታ ለዩክሬን የአየር ኃይል መጠናከር አስፈላጊ ነው ተብሏል።

“ጦርነቱ የሚያበቃው ዩክሬን ነፃና ራሷን የቻለች ሀገር ስትሆን ነው” ሲሉ ማክሰኞ ከሰዓት በነበረው  የኔቶ ስብሰባ ላይ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

“ሩሲያ ፀንታ አትቆይም። ዩክሬን ግን ትፀናለች።” ብለዋል ባይደን። ለ13 ደቂቃዎች ያክል በግልፅ በሚሰማ ቃል ንግግር ያደረጉት ባይደን ባለፈው ወር ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ክርክር ጊዜ ከነበራቸው አቋም ተለይተው ቀርበዋል።

በተያያዘ ዜና የኮንግረስ አባል የሆኑ ዴሞክራቶች ዝግ ስብሰባ አካሂደው ባይደን ፓርቲውን ወክለው ይወዳደሩ ወይ በሚለው ጉዳይ መክረዋል። በስብሰባ ላይ የነበረው ሁኔታ “አሳዛኝ” ነበር ሲሉ አንድ ሕግ አውጭ ለአሶሲዬትድ ፕረስ ተናግረዋል።

ያለፈው ማክሰኞ ዕለት የኒው ጀርዚ ግዛት የሕዝብ እንደራሴ የሆኑት ዴሞክራቱ ሚኪ ሼሪል የምናጣው ነገር “ብዙ ነው” በማለት በአደባባይ ባይደን በሚመጣው ምርጫ እንዳይሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለኔቶ ስብሰባ የመጡ ዲፕሎማቶች ስለባይደን መፃዒ ዕጣ ፈንታ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት አንፀባርቀዋል ይላሉ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች።

“ከክርክሩ በኋላ እንዴት አድርገው ስማቸውን መገንባት እንደሚችሉ አናውቅም” ሲሉ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአውሮፓ ዲፕሎማት ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል። “ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የዩኤስ እና የኔቶ አለቃ ሆነው መቀጠል ይችላሉ ብዬ አላምንም።”

የባይደን ቡድን የ81 ዓመቱ ዕጩ በሚቀጥለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ተወዳድረው ማሸነፍ እንደሚችሉ ለማሳየት የአቅማቸውን እያደረጉ ነው።

ዋይት ሐውስ እንደሚለው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ኔቶ በተለይ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ እንዲስፋፋ፤ ፊንላንድ እና ስዊድን እንዲቀላቀሉ ሚና የተጫወቱት ባይደን ናቸው።

32 የኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች እየመከሩ ባሉባት በአሜሪካዋ ዋና ከተማ ዋሺንግተን ዲሲ አዲሱ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ተገኝተዋል።

ወደ ዋሺንግተን ከማቅናታቸው በፊት ንግግር ያደረጉት ስታርመር ፓርቲያቸው ሌበር “ለኔቶ ያለውን የማይናወጥ ድጋፍ ላረጋግጥ እወዳለሁ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ረቡዕ ዕለት ባይደንን በግል እንደሚያገኟቸው ይጠበቃል። ዴሞክራት እና ሪፐብሊካን የኮንግረስ አባላትንም ያናግራሉ።

ስብሰባው ከአስርት ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ቃል-ኪዳኑ ስምምነት በተደረገበት አዳራሽ እየተካሄደ ሲሆን ባይደን በንግግራቸው ይህን አውስተዋል።

ባይደን በንግግራቸው ማገባደጃ ላይ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ጄኔራል ጄንስ ስቶልንበርግን ወደ መድረክ ጋብዘው በአሜሪካ ትልቁ የሆነውን ፕሬዚዳንታዊ የነፃነት ኒሻን ሸልመዋቸዋል።

ማክሰኞ ዕለት ፍሎሪዳ በሚገኘው ጎልፍ ክለባቸው ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያሰሙት የ78 ዓመቱ ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አባላትን ነቅፈዋል።

የኔቶ አባል የሆኑ ሀገራት ከአጠቃላይ ገቢያቸው 2 በመቶውን ማዋጣት አለባቸው ሚለውን ሕግ ተከትሎ ነው ትራምፕ ነቀፌታቸውን ያሰሙት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም

Recommended For You