ታላቁን የእግር ኳስ ሰው ለመዘከር

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ታላቅ ክብርና ዝናን ማትረፍ ከቻሉ የቀድሞ ተጫዋቾች መካከል ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 102 ጊዜ ተሰልፎ 68 ግቦችን ያስቆጠረው ተጫዋቹ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ በመድረኩ በኮኮብ ግብ አግቢነት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ በመሆንም እስካሁን ተጋሪ ያላገኘ ታሪክን አስመዝግቧል። በተጫዋችነትና አሠልጣኝነት ሀገሩን ማገልገል የቻለው ይህ ታላቅ የእግር ኳስ ሰው ካረፈ 14 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ታሪኩ ግን በትውልዱ ዘንድ እምብዛም አይታወቅም ማለት ይቻላል።

በመሆኑም ታሪካዊውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋች ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁን የሚዘክር የመታሰቢያ መርሃ ግብር ለማካሄድ ታቅዷል። ይህንን ሀገር አቀፍ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ለማዘጋጀትም አንጋፋ የእግር ኳስ ባለሙያዎችን ያቀፈ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፤ ስራዎቹን የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም፣ ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር፣ በተመረጡ ስታዲየሞች የመቀመጫ ስያሜ እና የመሳሰሉትን ተግባራት ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩንም በልጁ ዳዊት መንግሥቱ የሚመራው ኮሚቴ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

በመግለጫው ላይ የተገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው መርሃ ግብሩ ‹‹የመንግሥቱ ወርቁ ታሪካዊ ትንሳኤ›› በሚል ገልጸውታል። መንግሥቱን ከ1950ዎቹ አጋማሽ አንስቶ የሚያውቁት ሲሆን፤ ሲጫወት ከመመልከት ባለፈ የአሠልጣኝነት ሥልጠናም እንደሰጣቸው ያስታውሳሉ። ኢትዮጵያን በስፖርቱ ያስተዋወቀው ኢንስትራክተር መንግሥቱ በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ የተመሰከረለትና የተመሰገነ የእግር ኳስ ሥልጠና ባለሙያ እንደነበረም ያረጋግጣሉ።

በሌሎች ሀገራት በስፖርቱ ትልቅ ሥራ ያከናወኑ ሰዎች ማስታወሻ የሚደረግላቸው ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አባት የሆነውን ሰው ታሪክ ግን መርሳት አግባብ አይደለም። ምክንያቱም ያኔ መንግሥቱን እየተመለከቱ ያደጉ ወጣቶች ዛሬ ላይ እግርኳሱ ላይ እየሠሩ ይገኛሉ። ስለዚህም ለሌሎች ምሳሌና አርዓያ የሆነው የእግር ኳስ ሕይወቱን ለማስታወስና ለመዘከር የሚያስችለው የማስታወሻ መርሃ ግብር ዓመታዊና ቀጣይነት ያለው መሆን እንዳለበት አንጋፋው አሠልጣኝ አሳስበዋል።

የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ሰለሞን በቀለም ‹‹የኳስ ዶክተር፣ የኳስ ፊት አውራሪ፣ የኳስ ንጉሥ›› እየተባለ ይጠራ የነበረው መንግሥቱ ወርቁ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በርካታ ታሪኮችን እንዳስመዘገበ ይጠቁማሉ። ከ2ኛው እስከ 7ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ ለኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ የተጫወተ፣ በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ዋንጫውን እንድታነሳ ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረገና በመድረኩም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪም ነበር። ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ለተከታታይ ዓመታት የኢትዮጵያ ቻምፒዮና እንዲሁም የጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን እንዲሆን አስችሏል። ከዚህም ባለፈ በአሠልጣኝነት(በክለብ እና በአሠልጣኝነት ሥልጠና) ምርጥ የእግር ኳስ ባለሙያዎችን ያፈራ እንዲሁም በማማከርም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ ሚና እንደተወጣም ያስታውሳሉ።

ይሁንና ይህ ታሪኩ ተነግሮ ለሌሎች ማስተማሪያነት አልዋለም። በመሆኑም መንግሥቱን ለመዘከር ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። እነርሱም ለብሶት ይጫወት የነበረውን 8 ቁጥር ማሊያ ላይ የመሥራት፣ የእግር ኳስ ታሪኩ ለማስተማሪያነት እንዲሆን የሚያስችል ዶክመንተሪ በመሥራት፣ በተመረጡ ስታዲየሞች ቋሚ መጠሪያ እንዲያገኝ የማድረግ፣ በስሙ የሚጠራ ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር ማዘጋጀት እንዲሁም ቋሚ መታወሻ እንዲኖረው ለማድረግ ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ለመሥራት ታቅዷል። የዚህ ሃሳብ መነሻ ቤተሰቦቹ ቢሆኑም ዓላማውን በመረዳትና የተለያዩ የእግር ኳስ ባለሙያዎችን በኮሚቴነት በማቀፍ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስረድተዋል።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም

Recommended For You