ከንቲባ አዳነች አቤቤ የብሔራዊ ቡድን የበላይ ጠባቂ ሆነው ተሰየሙ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን የበላይ ጠባቂ ሆነው ተሰየሙ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከንቲባዋ ለስፖርቱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የዕውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብርም አካሂዷል።

በዕውቅና እና የሽልማት መርሃግብሩም ከንቲባዋ ኢትዮጵያን በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ የሚወክለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ መሰየማቸውን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል። ብሔራዊ ቡድኑ በሚያደርጋቸው የትኛውም እንቅስቃሴም ከፌዴሬሽኑ ባለፈ ክትትል የሚያደርግለት የበላይ ጠባቂ አግኝቷል። ፌዴሬሽኑ ይህንን ይፋ ያደረገውም ከትናንት በስቲያ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ፤ ቡድኑ ለማድረግ ባቀደው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እንዲረዳው ከንቲባዋን በበላይ ጠባቂነት መምረጡን አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸውም ‹‹ሀገራችን የካፍ መስራች ናት። በዚህ ደረጃ ላይ ያለች ሀገር ባይተዋር ሆና ቆይታ በሰው ሀገር ሜዳ እየለመንን መጫወታችን ቁጭት ውስጥ የሚከት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትራችን በ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያለንን ፍላጎት በቅርቡ ይፋ አድርገዋል። ከዚህ ጎን ለጎን አንገት የሚያስደፋ ብሄራዊ ቡድን ሊኖር አይገባም በሚል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ክብርት ከንቲባችንን የበላይ ጠባቂ አድርገን መርጠናል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ወክዬ የምሰጠው ይህ የበላይ ጠባቂነት ሥልጣን የሕዝብ አደራን መስጠት ነው። ብሄራዊ ቡድኖቻችንን በበላይነት የሚከታተል የመንግሥት አካል በማግኘታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለማሳደግ እንዲሁም ብሄራዊ ቡድኑን በማበረታታት አንጻር ለነበራቸው ከፍተኛ ሚናም ለከንቲባዋ ዕውቅና ሰጥቷል። መርሃ ግብሩ ድርብ እውቅና መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ከ2010 ዓ.ም በፊት በከተማዋ የነበሩት የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ቁጥር 495 ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የእግር ኳስ ሜዳዎች 166 እንደነበሩ አብራርተዋል። ከዚያ በኋላ በተሠሩ ሥራዎች ግን በከተማዋ የሚገኙት ሜዳዎች ቁጥር 1 ሺ199 ደርሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ 351ዱ ሜዳዎች የእግር ኳስ ናቸው። ለዚህም ሥራ እውቅና መስጠት ያስፈልጋል በማለት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በመወሰን የዕውቅና መርሃ ግብሩ ሊሰናዳ ችሏል። ኳስ ሜዳ መሥራት ዜጋ ላይ መሥራት በመሆኑ፤ በከተማዋ ካለው ኮሪደር ልማት ጎን ለጎን ስፖርቱ የሚስፋፋበት ጊዜው ሩቅ እንደማይሆንም ተስፋቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በተለያየ ጊዜ ብሄራዊ ቡድኑ በውድድሮች ላይ ተካፍሎ ሲመለስ ከንቲባዋ የሚያደርጉት ማበረታቻም የእውቅናው አካል እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በሴካፋ 3ኛ ደረጃ ይዞ ሲመለስ በራሳቸው ተነሳሽነት ሽልማት አበርክተዋል። ብሄራዊ ቡድኑ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍም በተመሳሳይ ከንቲባዋ የሽልማት መርሃ ግብር ማከናወናቸውንም አስታውሰዋል። በዚህም ከንቲባ አዳነች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የበላይ ጠባቂ ሆነው መሰየማቸውን በማስመልከት ማስታወሻ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማሊያ እንደተበረከተላቸው የኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ከንቲባዋ ባደረጉት ንግግር ‹‹ፌዴሬሽኑ ይህን ጥቂት እንቅስቃሴ ትርጉም አለው ብሎ እውቅና ሲሰጥ፤ ከሁሉ በላይ ሽልማቱ ለተገኘነው ውጤት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ኃላፊነት መውሰድ ነው። የእግር ኳስ ጥማት ያለበትን ማህበረሰብ ከዚህ በላይ እንድንሠራ የሚያነሳሳም ነው። በቀጣይ ቡድናችን ውጤታማ ማድረግ የምንችልበት፣ የቀደመ የብሄራዊ ቡድኑን ክብር መመለስ እንድንችል፣ አዲሱም ትውልድ በእግር ኳሱ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንዲሆን መሥራት ይኖርብናል። አደይ አበባ እና አቃቂ ቃሊቲ ስታዲየሞችንም በፍጥነት በመሥራት ለማጠናቀቅ እንጥራለን›› በማለት ሹመቱን በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ፣ የቀድሞ እና የአሁኑ የኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል።

ብርሃን ፈይሳ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2016

 

Recommended For You