ወጣትና አንጋፋ አትሌቶች የተፋለሙበት ‹‹አበበ ቢቂላ›› ማራቶን

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንጋፋው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን አንዱ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለ40ኛ ጊዜ በሃዋሳ ከተማ ባለፈው እሁድ ተካሂዷል፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቶችም ውድድሩን በበላይነት አጠናቀዋል። በሁለት ዙሮች 42 ኪሎ ሜትር ርቀት በሸፈነው ውድድር በወንዶች ጎሳ አምበሉ፤ በሴቶች ደግሞ ኩረኒ ጀሊላ አሸናፊዎች ሆነዋል።

ከክልል፣ ከከተማ አስተዳደር እና ከክለቦች የተውጣጡ አትሌቶች የተሳተፉበት ይህ ውድድር ከፍተኛ ፉክክርን ያስተናገደም ነበር። በሁለቱም ጾታዎች ነባርና ልምድ ያላቸው አትሌቶች የተፎካከሩ ሲሆን፤ በእለቱ የነበረው የአየር ሁኔታም አስተዋጽኦ ነበረው። በወንድ አትሌቶች መካከል እስከ መጨረሻው በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ እስከ 37ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ አሸናፊውን ለመለየት አዳጋች ነበር፡፡

አንገት ለአንገት የነበረው ብርቱ ፉክክር በስተመጨረሻም በኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቱ ጎሳ አምበሉ አሸናፊነት ተደምድሟል። አትሌቱ ቀሪውን 5 ኪሎ ሜትር በአስደናቂ አሯሯጥና አጨራረስ በመሸፈን የወርቅ ሜዳሊያውን ሊያጠልቅ ችሏል። በውድድሩ ከፍተኛ ፉክክርን በማሳየት ከጎሳ ጋር እስከ መጨረሻዉ ትግል ያደረገው የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አትሌት ጊዜው አበጀ በሁለተኝነት በመግባት የብር ሜዳሊያውን ሲወስድ፤ የኦሜድላው ሳህለስላሴ ንጉሤ ደግሞ በሶስተኛነት የነሃስ ተሸላሚ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

በሴቶችም አስገራሚ የፉክክርና የአሸናፊነት ትግል የታየ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቷ ኮረኒ ጀሊላ በአስገራሚ ብቃት አሸንፋ የወርቅ ሜዳሊያውን የግሏ ማድረግ ችላለች። በአሸናፊነት እልህ እስከ መጨረሻው የተናነቀችው የኦሜድላዋ ሙሉሀብት ጸጋ ሁለተኛ፤ ሌላኛዋ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌት ያደኔ አለማየሁ ደግሞ ሶስተኛ በመውጣት የብርና የነሃስ ሜዳሊያቸውን አጥልቀዋል። አትሌቶቹ በአንጋፋው የማራቶን ውድድር ያልተጠበቀ ውጤትን በማስመዝገብም የታሪካዊው ድል ባለቤት ሆነዋል።

የወንዶች ውድድድር አሸናፊው አትሌት ጎሳ አምበሉ፤ በታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላ በተሰየመው የማራቶን ውድድር በማሸነፉ ትልቅ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል። በአትሌቶች መካከል የነበረው ፉክክር ጥሩ እንደነበረና እስከ 20ኛ ኪሎ ሜትር ድረስ ከብዶት የነበረና 25ኛ ኪሎ ሜትር ሲደርስ ግን እየቀለለዉ መምጣቱን አክሏል። ውድድሩ 32 ኪሎ ሜትር ላይ ሲደርስ በ200 ሜትር ርቀት ሲመራ የነበረውን የክለቡ አትሌት ላይ ለመድረስ አስቦ ወደ ፊት መውጣቱ ሳያስበው ለአሸናፊነት አብቅቶታል።

37 ኪሎ ሜትር አካባቢ አትሌቱን ካለፈው በኋላ ሞራል እንደተሰማውና በዛው ፍጥነት ሮጦ ያሸነፈ ሲሆን፤ የአየር ሁኔታው እንደተፈራው አለመሆኑ አግዞታል። ወደ ፊት ለሚጠብቁት ዓለም አቀፍ ውድድሮች እረፍት ከወሰደ በኋላ ከአሠልጣኙ ጋር ጠንክሮ በመሥራት ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠራም በአስተያየቱ ጠቁሟል።

በሴቶች ድል ያደረገችው አትሌት ኩረኒ ጀሊላ በበኩሏ ውድድሩን በማሸነፏ ትልቅ ክብር እንደተሰማት ጠቁማለች። በውድድሩ ትልልቅና ብቃት ያላቸው አትሌቶች በመሳተፋቸው ጠንካራ ፉክክር ተስተናግዷል። ከክለቧ አትሌቶች ጋር በቡድን ሥራና በመተጋገዝ መጫረሻ አካባቢ ፉክክሩ በአስር አትሌቶች መካከል በነበረበት ወቅት ደረጃ ይዛ ለማጠናቀቅ አስባ ወደፊት በመውጣቷ ልታሸንፍ ችላለች። በማራቶን ጥሩ ሰዓት ቢኖራትም በወሊድና በጉዳት ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከውድድር ርቃ ከተመለሰች በኋላ በማሸነፏ መደሰቷንም አስረድታለች።

የፌዴሬሽኑ የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተሩ አቶ አስፋው ዳኜ፤ ከኢትዮጵያ ቻምፒዮና ቀጥሎ አንጋፋ የሆነውን የሻምበል አበበ ማራቶን በሃዋሳ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል። በርካታ አትሌቶች የተሳተፉበትና ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ውድድር ከዚህ ቀደም ውጤታማ የነበሩ እንደነ ኦሜድላ ያሉ ክለቦች ወደ ውጤት መመለሳቸው ትልቅ ስኬት ነው። አንጋፋ አትሌቶችም ላለባቸው ዓለም አቀፍ ውድድር እራሳቸውን እንዲገመግሙ እንደሚረዳቸውም አክለዋል።

በቡድን ሴቶች ኦሮሚያ ፖሊስ በ17 እና በወንዶች ኦሜድላ በ35 ነጥቦች አንደኛ ሆነው በማጠናቀቅ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችለዋል። በሴቶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ39 እና ፌዴራል ማረሚያ በ53 ነጥቦች ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ በወንዶች መቻልና ኦሮሚያ ፖሊስ በ52 እና 61 ነጥቦች ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ውድድራቸውን ፈጽመዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 /2016 ዓ.ም

Recommended For You