ከምርቃት በፊትና በኋላ

በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማእከል ተፀንሶና ተወልዶ፤ ወደ መሬትም ወርዶ እነሆ በብዙዎች ልብ ውስጥ ታትሞ ይገኛል። ″ይገኛል″ ብቻ አይገልፀውም፤ ወደ ፊትም ይህ ታትሞ የመኖሩ ነገር በትውልዳዊ ሰንሰለት ተሳስሮ ይቀጥላል። ዩኒቨርሲቲው ቢተወው እንኳን የሕዝብ ″ሆኗል″ና በሌሎቹ አስመራቂ ተቋማት በተመራቂና ቤተሰቦቻቸውን ልብ ያስቴፈስህ ዘንድ መዜሙ የሚቀር አይሆንም- የ″እንኳን ደስ አላችሁ›› መዝሙር፡፡

ልክ እንደ ″እንኳን ደስ አላችሁ!!!″ ሁሉ ከወራትም ሰኔ ከትምህርት እና መመረቅ (ምሩቃን) ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው ሲሆን፤ ዛሬ ዛሬ የአስመራቂና ተመራቂዎች ብዛት እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት እስከ ነሐሴ ዘለቀ እንጂ አስቀድሞ ሰኔ የትምህርት ቤቶች መዝጊያ ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርሲቲዎችም ማስመረቂያ ነበር። በመሆኑም፣ ሰኔ ግም ሲል የ″እንኳን ደስ አላችሁ″ ዜማ (ሕብረ ዝማሬ) በጆሯችን ላይ ማቃጨሉን ይጀምራል ማለት ነው። የ2018 ምረቃ በአልን አስመልክቶ ቢቢሲ ስፍራው ተገኝቶ እንዳሰፈረው ከሆነ ለአንዳንዱ ምሩቅ ስሜቱ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ፀጉር ድረስ የሚነዝር ነው። ለአንዳንዱ ወደ ኋላ የሚመልስ። ለበርካቶች ደግሞ የተማሪነት ሕይወት የሚያበቃበት ደወል ነው።

እለቱንም በተመለከተ ″የምርቃት ቀን ልዩ ናት። የበርካታ ዓመታት ጥረት ዕውቅና የሚሰጥበት ዕለት! ከዚህም በላይ ደግሞ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ሌላኛው የሕይወት ምዕራፍ የሚሸጋገሩበት ቀን ነው። ማንም የማይክደው ሀቅ ደግሞ ለስራ ዝግጁ የመሆን የመጀመሪያው ደወል ነው።″ ሲል ነበር ዘገባው ያሰፈረው።

ከእንኳን ደስ አላችሁ ጋር በተያያዘ ″ግራጁዌሽን ፓርቲ″፣ የተመራቂዎችን መጽሔት እና ሌሎችንም የምረቃ ወቅት ግርግሮች በማንሳት ፈገግ ማለት የሚቻል ሲሆን፤ ለጊዜው ከጊዜ አኳያ ወደዛ አንገባም።

ለመግቢያ ያህል ስለ ″እንኳን ደስ አላችሁ!!!″ም ሆነ ተመራቂ፣ አስመራቂዎችና ሰኔ ይህንን ያህል ካልን (ስለ ″እንኳን ደስ አላችሁ″ ካነሳን አይቀር በየዓመቱ ወደ መድረክ የሚመጡ ሕፃናትን ድምፅ አይለወጤነትና ሕፃናቱን መልምሎ በማዘጋጀት ወደ መድረክ የሚያመጣውን አካል ሳያመሰግኑ፤ እንዲሁም፣ ሕብረ ዝማሬው ሲሰማ በትምህርት ዓለም ለቆየ የሚፈጥረውን ልዩ ስሜት ሳይጠቅሱ ማለፍ አይገባም)፤ ከዛ በፊት ግን፣ ባለፈው ዓመት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በርእሰ አንቀጹ ″ተገቢውን መንገድ አልፎ መመረቅ ያኮራል!″ እንዳለው፣ ይህ ″እንኳን ደስ አላችሁ!!!″ ጽሑፍም በአግባቡ ለፍተው፣ ጥረውና ግረው የተመረቁትን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።)

የትምህርት እድል ማግኘት ችግር በነበረበት ድሮ እዛ ላይ፣ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ብቻ ተሰቅሎ የነበረው መመረቅ፤ የስራ እድል ማግኘት ችግር በነበረበት ዛሬ እዛ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከትንሹ ኬጂ (መዋዕለ ሕፃናት) ጀምሮ በየደረጃው ሞቅ፣ ደመቅ ባለ ክብረ በአል መከበር ከጀመረ ቆየ። ″ይህ ሁሉ የምን አትርሱኝ ነው?″ ቢባልም፣ ጉዳዩ ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ ሆነና ከነፉክክሩ ድግሱና አጃቢዎቹ እንደ ቀጠሉ ናቸው። ከዓመት ዓመትም እየገዘፈና እየተስፋፋ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ለአንዳንድ የኬጂ ምሩቃን የምረቃ ስነስርአትም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እስከ መደረግ እየተደረሰ መሆኑ ሰኔ በመጣ ቁጥር እንደ አዲስ እየተነገረ ይገኛል። ትኩረታችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምረቃ ስነስርአት በመሆኑ ″ኬጂ″ንና ሌሎችን እንለፋቸው።

ከ″እንኳን ደስ አላችሁ″ በፊት

″ሠላማዊ የዩኒቨርሲቲ ድባብ ለመፍጠር የሚያግዝ ሰነድ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ በሆኑት አቶ ታምሩ ደለለኝ የቀረበ ሲሆን፤ የሰነዱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በመቀነስ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለዚህም የተማሪዎችን አእምሮዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ስነ-ምግባራዊ ስብዕናን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቁሟል።″ የሚል ዜና በፈረንጆቹ ኖቬምበር 2020 ከወደ ባህር ዳር ተሰምቶ እንደ ነበር ይታወሳል።

በየዓመቱ በርካታ ወጣቶችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (በተለይም ከኮሌጆችና ከዩኒቨርሲቲዎች) ከምታስመርቀው ኢትዮጵያ፤ ተመራቂ ተማሪዎች ይዘው ሊወጡ የሚገባቸውን አጠቃላይ ስብእና በተመለከተም፣ ″ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚሰጣቸው መደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በግቢ ውስጥና ከግቢ ውጭ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት፣ በትምህርታዊ ክለባት: በፈጠራና ስፖርታዊ ውድድር፣ በሙዚቃ፣ ድራማና ተዛማጅ የጥበብ ስራዎች፤ እንዲሁም ትምህርታዊ ውይይትና ክርክር ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማገዝ ተማሪዎች ይዘውት ከመጡት ነጠላዊ ማንነት (mono/singular identity) ባሻገር ሌሎች ማንነቶችን እንዲያዳብሩ″ መደረግ ያለበት መሆኑ ከዚሁ፣ ከጠቀስነው መረጃ ጋር ተያይዞ ለንባብ በቅቶ ተመልክተናል።

ይህ የሚያመለክተው ተማሪዎች የበርካታ እውቀቶችና ክሂሎች ድምር ውጤት እንጂ የአንድ ነጠላ ተግባር (እውቀት) ውጤቶች አለመሆናቸውን ነውና ጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው ሁሉ ቢመለከቱት መልካም ይሆናል። በተለይ የአሁኑ ዘመን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚታሙባቸው አንዱ ይኸው በመሆኑ ከወቀሳና ሀሜታው ነፃ ይወጡ ዘንድ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተደረገውን ሊደግሙት ይገባል።

በእለቱ እንደተገለፀው ዶ/ር ታደሰ አክሎግ የተባሉ የዩኒቨርሲቲው ባልደረባ ‘Building a healthy institu­tional Ethos’ በሚል ርዕስ የጥናት ወረቀት ያቀረቡ ሲሆን፣ በጥናታቸውም የተማሪዎችን ሁለንተናዊ ስብዕና ለመገንባት ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የጋራ እሴት (shared institutional ethos) ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል። በዚህ ዙሪያ የተሻለ ተሞክሮ ያለውን የጅዋራላል ዩኒቨርሲቲ (’Jawaralal Nehru University’ (JNU)ን ልምድም አጋርተዋል።

ከላይኛው ሀሳብ መረዳት እንደሚቻለው፣ ከመመረቅ በፊት ከነ ሙሉ ስብእና ለመመረቅ በርካታ ጉዳዮች መሟላት ያለባቸው ሲሆን፤ ከላይ ከተጠቀስናቸው በተጨማሪ የሚከተሉትም ምሩቃኑ ከመመረቃቸው በፊት ሊያዳብሯቸው የሚገቡ መሰረታውያን ናቸው።

″ለ2014 ዓ·ም ተመራቂ ተማሪዎች የተቀጣሪነት ክሂሎት ሥልጠና ተሰጠ″ ከሚለው ቀጥሎ፣ ″የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል በኢንፎማይንድ ሶሉሽንስ ንዑስ የቢዝነስ ዩኒት ከሆነው ደረጃ ዶትኮም ኃ.የተ.የግ. ድርጅት (Dereja.Com) ጋር በመተባበር በተለያዩ የትምህርት መስኮች በ2014 ዓ·ም ለሚመረቁ ተማሪዎች የተቀጣሪነት ክሂሎት ሥልጠና″ መስጠቱ ተነግሯል። ይህንኑ ተከትሎም፣ ″ሥልጠናው ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ‹‹Soft Skill›› የሚባሉትን ራስን መግለጽ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ በራስ የመተማመንና ሌሎች ክሂሎቶች ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ቀጣሪው ድርጀት በሚፈልገው ልክ ብቁ ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ″ እንደ ሆነም ከደረጃ ዶትኮም ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈራረም በየዓመቱ የተቀጣሪነት ክሂሎት ሥልጠናን በሚሰጠው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ተብራርቷል።

እንግዲህ ጊዜው ይህንን ሁሉ ግድ ይላልና በአሁኑ ዘመን መመረቅ በራሱ የመጨረሻው ግብ አለመሆኑን ተመራቂዎቻችን ልብ ሊሉትና ጊዜና ዘመኑ የሚፈልገውን ከወዲሁ ሊያስቡበት እንደሚገባ፤ አስበውም መከወን ያለባቸው መሆኑን ከስሩ አስምረንበት ማለፍ እንፈልጋለን። ተመራቂዎች በሥራ ዓለም ሊያጋጥሟቸው የሚችሉና ቀጣሪው ድርጅት ከእነሱ የሚፈልጋቸውን የጊዜ አጠቃቀም፣ ራስን የመግለጽ፣ በራስ የመተማመን እና ሌሎች በአካዳሚክ ዕውቀት የማይገኙ ክሂሎቶች ላይ ሥልጠና የሚሰጠው፤ እንዲሁም ከተመረጡ ድርጅቶች ጋር በማገናኘትም የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የሚያደርገው፤ ለአዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጠው Dereja.Com አይነት ተቋማትም ለአገራችን የሚኖራቸው ፋይዳ ቀላል አይደለምና፤ ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሁሉ የእነዚህም ቁጥር ሊበራከት ይገባል።

ከ″እንኳን ደስ አላችሁ″ በኋላ

ከላይ በጠቀስነው ዘገባ ውስጥ የተጠቀሱት ባለሙያ እንደሚሉት ከሆነ መመረቅ ጥሩ ሆኖ ከምረቃ በኋላ ያለው መንገድ ቁልቁለት አይደለም። እንደ እኝሁ ምሁር አስተያየት ከምረቃ በኋላ ስራ ማግኘት፣ በተለይ በታዳጊ አገራት እራሱን የቻለ ፈተና ነው።

በአንድ ወቅት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት፣ በሕንድ አገር የፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ተማሪ እና በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የማሕበራዊ ስነ-አዕምሮ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ዋቅቶላ ደምሰው አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች የሚገጥማቸውን ፈተና እንዴት መወጣት እንዳለባቸው ያስረዳሉ።

አቶ ዋቅቶላ እንደሚሉት ከሆነ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች በሚኖሩባት አገር ለአዲስ ተመራቂዎች ስራ በቀላሉ ያገኛሉ ማለት ይከብዳል። እንደ ቅድመ ዝግጅት ግን ቀጣዩቹ 5 ነጥቦች ወሳኝ ናቸው ይላሉ፡፡

የትምህርት እና የስራ ልምድ ማስረጃ ማደራጀት

የአዲስ ተመራቂ ተማሪዎች የመጀመሪያው የቤት ሥራ የሚሆነው የትምህርት እና ክሂሎት፤ እንዲሁም የሥራ ልምድ ካላቸው በተሟላ መልኩ በሲቪያቸው (CV) ላይ መጥቀስ ነው። ምሩቃን ለሥራ ቅጥር ለጽሑፍ ፈተናም ይሁን ለቃለ መጠይቅ ከመቅረባቸው በፊት የትምህርት እና የሥራ ማስረጃቸውን መጠየቃቸው አይቀሬ ነው።

ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት

መንግሥት ተመራቂዎችን በሙሉ ሊቀጥር የሚችል አቅም የለውም። ወይም ምሩቁ(ቋ) የተመኘ(ች)ውን የሥራ ዓይነት ማግኘት ቀላል አይሆንም። ስለዚህም ያለውን ውስን እድል ለመጠቀም ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል።

አቶ ዋቅቶላ ሲያስረዱ የቅጥር ማመልከቻ ከማቅረባችን በፊት ሥራው ምን አይነት ክሂሎቶችን ይፈልጋል ብለን መጠየቅ፤ ባገኘነው መረጃ መሰረትም መዘጋጀት አለብን።

መረጃ ማሰባሰብ

ተመርቀው ስራ ፈላጊ የሆኑ የስራ አዳኞች የሥራ ቅጥር መረጃዎችን፣ ስለ ቀጣሪው ማንነት እና የሚያመለክቱበት የስራ መደብ ስለሚፈልገው እውቀት እና ክሂሎት በቂ መረጃ ሊኖራቸው የግድ ነው።

ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ተለይቶ መገኘት

ከትምህርት ማስረጃችን በተጨማሪ ያመለከትንበት የሥራ ዘርፍ፣ ቀጣሪው ድርጅት የሚፈልገውን ክሂሎት ማወቅ እና ይህንንም ለቀጣሪው ድርጅት በማሳየት የቅጥር እድላችንን ማስፋት እንችላለን።

የአዕምሮ ዝግጅት ማድረግ

በተማሪነት ዘመናችን ያሰብናቸውን እና ያለምነውን ማሳካት ላይሆንልን ይችል ይሆናል። ለዚህም የአዕምሮ ዝግጅት ማድረግ ጠቃሚ ነው። ያ ያለምነው፣ ያሰብነው – – – ለምን አልሆነም ብለን መጨነቅ የለብንም።

በመጨረሻም

ቀደም ሲል የጠቀስነው ድርጅት (Dereja.Com) ዓላማው በሀገራችን የሚታየውን የተማረ ሥራ-አጥ ቁጥር መቀነስና አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች እኩል ችሎታ እንዳላቸው ማሳየት ነው።

ድርጅቱ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ያንግ አፍሪካን ወርክስ (Master Card Foundation Young African Works) ከሚባል ድርጅት ጋር ስምምነት በማድረግ እ.ኤ.አ እስከ 2020 ድረስ ከ65ሺህ በላይ የሚሆኑ አዲስ ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ካምፓኒዎች ጋር ማገናኘት መቻሉ በሪጂናል ማኔጀርና አሠልጣኝ በእምነት ለጥይበሉ በኩል ተነግሮለታል።

ስልጠናውን በተመለከተ ከተሰበሰቡት አስተያየቶች መካከልም ″ብዙ ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች ካስመረቁ በኋላ ተማሪዎቻቸው የደረሱበትን አይከታተሉም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገሪቱ በምን መስክ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን እንደምትፈልግ ለይተው ማስተማር አለባቸው″ የሚለው ሚዛን ደፍቶ እንደ ተገኘም ተነግሯል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባካሄደው ጥናት፣ የተቋሙ መምህርና የጥናት አቅራቢ አቶ ፍሬው አበበ እንደገለፁት በዘርፋ የሰለጠነው የሰው ኃይል 47 በመቶ ሲሆን አቅርቦትና ፍላጎትም ያልተጣጣመ መሆኑና በዘርፋ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚፈልጉት አግባብ የሰለጠ የሰው ኃይል ለማግኘት አልቻሉም። በመሆኑም፣ ″በሆቴልና አስጎብኚ ድርጅቶች ውስጥ 80 በመቶ፤ በሬስቶራንቶች 74 በመቶ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የባለሙያ ክፍተት ይታያል።″

ይህ የሚያሳየው ቀጣሪና ተቀጣሪ አለመናበባቸውን እንጂ በሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያ ወይም ምሩቃን ጠፍተው አይደለም። ለዚህ አባባላችን ደግሞ ዋቢያችን አክሱም ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ (ቱሪዝም) ያስመረቃቸው ምሩቃን ያለ ስራ ተቀምጠው የስራ መደቦቹ የተያዙት በሙያው ባልተመረቁ ሰዎች መሆኑን በጥናቴ ደርሼበታለሁና ሊታረም ይገባል ማለቱ ነው።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በባዮቴክኖሎጂ ተማሪዎችን ያስመርቃል፤ አገሪቷ የባዮቴክኖሎጂ ባለሙያ እንደሌላትና የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የእነዚህ ባለሙያዎች አስፈላጊነት ይነገራል። ነገር ግን፣ ከጠቀስነው ዩኒቨርሲቲ የወጡ ምሩቃን ስራ አጣን በማለት ባልሰለጠኑበት መስክ ተሰማርተው ነው የሚገኙት። ሌሎችንም በዚሁ መልኩ ማየት ይቻላል።

እየተበራከቱ በመጡት ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት በአገሪቱ የሚገኙ የሥራ ዕድሎች ዝቅተኛ የመሆናቸው ጉዳይ ለውይይት የሚበቃ አይሆንም። ምንም ይሁን ምን ግን፣ ችግሩ የራሳችን በመሆኑ እራሳችን ላይ ማዘናችን አይቀርም። በራሳችን ላይ ማዘናችን ግን ምናልባት ወደ ፊት እንዳይደገም ያደርግ እንደ ሆነ እንጂ አሁን ላይ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት እንዲህ በቀላሉ እንዲያገግም የሚያደርግ አይደለም። በደረሰው ጉዳትና ቀውስ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንደ ተነሱትና የመማር እድላቸውን (ሰብአዊ መብታቸውን) እንዳጡት ሁሉ በስራ እድሉ ዘርፍም በርካታ ምሩቃን የስራ እድሎችን አጥተዋል። በመሆኑም፣ በማያዳግምና በማይደገም መልኩ ችግሩ ይወገድ ዘንድ ሁሉም ሊረባረብረብ፤ ምሩቃኑም በሰለጠኑበት ሙያ ወደ ስራ ሊሰማሩና ራሳቸውንና አገራችቸውን ሊጠቅሙ ይገባል፡፡

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You