ልማቱ የሚፈልገውን የግብር ገቢ ለመሰብሰብ!

የአንድ ሀገር መንግሥት የልማት ፋይናንስ ምንጮች ከሆኑት መካከል ግብር/ ታክስ/ እና ባንኮች ከዜጎች ቁጠባ የሚሰበስቡት ሀብት ይጠቀሳሉ፡፡ የውጭ ብድርና ርዳታም በእዚህ በኩል አስተዋጽኦ እንዳለው ቢታመንም፣ ይህ ሀብት ግን ለተለያዩ ተጽዕኖዎች የተጋለጠ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አስተማማኝ ምንጭ ተደርጎ አይወሰድም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም የሚያካሂዳቸውን የልማት እቅዶች ለማሳካት የሚያስፈልገውን የሀብት ምንጭ በወሳኝነት ከግብር/ታክስ/ በሚገኝ ገቢና ከዜጎች በሚሰበሰብ ቁጠባ ላይ አድርጎ ይሰራል፡፡ ለዚህም ከግብር የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ በግብር ገቢ ላይ ለውጦችን ማሳየትም ተችሏል፡፡

ገቢው በየዓመቱ እያደገ ስለመሆኑም ሁሌም ይገለጻል፤ በዚያው ልክም የሚሰበሰበው ገቢ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ሲባል ነው የኖረው፤ ከፍተኛ ገቢ መሰብሰቡ በተጠቆመበት በአሁኑ ወቅትም ይሄው ጉዳይ ተነስቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ከትናንት በስቲያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳስገነዘቡት፤ በዚህ በጀት ዓመት መንግሥት 529 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ባለፉት አስራ አንድ ወራት /የዚህ ወር አልተጠቃለለም/ 466 ቢሊዮን ብር ወይም 96 በመቶ ገቢ ሰብስቧል፡፡ ይሄም ከአምናው ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ መሻሻል ያለው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንዳንድ አፍሪካ ሀገሮችን የገቢ ግብር አሰባሰብ በመጥቀስ ኢትዮጵያ ያለችበትን የግብር ገቢ አሰባሰብን አቅምንም አሳይተዋል፡፡ ሞሮኮ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷ /ጂዲፒዋ/ 32 በመቶ፣ ደቡብ አፍሪካ 24 በመቶ ፣ ኬንያም 15 ነጥብ 9 በመቶ በየዓመቱ እንደሚሰበስቡ ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከኬንያ በግማሽ ያነሰ፤ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷ /ጂዲፒዋ/ ሰባት በመቶ ገደማ ብቻ ግብር እንደምትሰበስብ ጠቅሰው፣ ሰባት በመቶውን ወደ 10 በመቶ ማድረስ ብትችል የልማት ጥያቄዎቿን በስፋት ለመመለስ እንደሚያግዛት አመልክተዋል።

በግብር ገቢው የሚሰበሰበው ሀብት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል እንዳይሆን አድርገዋል ከሚባሉት ምክንያቶች መካከል የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ፣ ገቢ መሰወር፣ ህገወጥ ንግድ የሚሉት ሁሌም ይጠቀሳሉ፤ ዘንድሮም ተጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የገቢ ሰብሳቢ ተቋሙን በማዘመንና በመሳሰሉት ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዘርፉ ለውጦች እየታዩ ያሉትም ይህንኑ ተከትሎ ነው፡፡ በግብር ገቢ አሰባሰቡ ላይ አሁንም የተጠናከረ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በግብር አሰባሰብ ላይ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ሥራ ላይ ውለው ውጤታማ ማድረግ ያስቻሉትን አሰራሮች ማስቀጠል፣ የማኅበረሰቡን የግብር ግንዛቤ ማስፋት፣ ዜጎች በፈቃደኝነት ግብር መክፈል ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ላይም መስራት ሁሌም ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባሮች ናቸው፡፡ በሕገወጦች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ባለበት ሁኔታ ችግሩ እንዴት ሊቀጥል እንደቻለ በጥናት በመለየት ሌሎች መፍትሔዎችን ማመላከትም ይገባል፡፡

ለሀቀኛ ግብር ከፋዮችና የግብር ሰብሳቢ ሠራተኞች የሚሰጠውን እውቅና ማስፋት፣ ለአጠቃላይ ግብር ከፋዩ የሚያበረታታ ሥርዓት በስፋት መዘርጋት፣ እንደ ጎዳና ነጋዴዎች ያሉት በሕጋዊ መንገድ ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ በስፋት መፍጠር፣ ወደ ግብር መረብ መግባት ባለባቸው ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ በትኩረት መሥራት የግብር ገቢውን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡

በተለይ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከሀገር ውስጥም አልፎ ከውጭ ድርጅቶች ጋር መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ያሉት ዜጎች ግብር እንዲከፍሉ እንዲሁም ዘመኑን የሚመጥን ግብር አሰባሰብ እንዲኖር ለማድረግ የውጪ ተሞክሮን መቃኘትም ያስፈልጋል፡፡

የገቢ ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣት፣ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ተገቢውን ግብር መሰብሰብ የሚገባ መሆኑ እንዲሁም የአፍሪካ ሀገሮች ተሞክሮ ሲታይ በገቢ አሰባሰብ ላይ ከቀደሙት መንገዶችም በላይ አዳዲስ የገቢ አሰባሰብ መንገዶችን መማተርን የግድ እንደሚል አውቆ መሥራት ቀጣዩ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡

የልማት ፍላጎቱ፣ ለልማቱ የሚያስፈልገው ሀብት ከፍተኛ እየሆነ በመጣበት በዚህ ዘመን እነዚህን ሁሉ የሚመጥን ርምጃ መውሰድ የግድ ይሆናል፡፡ ለዚህም በግብር አሰባሰባቸው ውጤታማ የሆኑ እንደ ሞሮኮ ያሉ ሀገሮችን ተሞክሮ ጠጋ ብሎ መመልከትና ለሀገር የሚጠቅሙ አሠራሮችን በመቅሰም ፈጥኖ መተግበር ወሳኝ ነው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You