“እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው”

ጽሑፋችንን በተጠቃሽ ብቻ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ፤ ዓለም አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሳል (ሁለንታዊ) በሆነ፤ አብዝቶም ታዋቂና እልፍ አእላፍ ጊዜ ተጠቃሽ በሆነ ጥቅስ (ኮቴብል ኮት) ስንጀምር ያለ አንዳች ምክንያት ሳይሆን፣ “ምናልባት” እንዲሉ፣ ምናልባት አንዳች የሚለው ነገር ካለ ይል ዘንድ በማሰብ ነው።

ይህ፣ ዛሬ ወደዚህ ገጽ ያመጣነው “እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው” ተጠቃሽ ጥቅስ አዲስ አይደለም (“አዲስ አይደለም” ማለት “ተረድተነዋል” ማለት ባይሆንም)። አዲስ ላለመሆኑ ማስረጃው ደግሞ ካልጠቀሱት የጠቀሱት ምሁራን፤ ካላካተቱት ያካተቱት ጥናቶች፤ በእለት ተእለት ሕይወታቸውና ሥራዎቻቸው ውስጥ ከማያዘወትሩት የሚያዘወትሩት ወዘተ መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን፤ በየትምህርት ተቋማት በሮችና ግድግዳዎች፣ በጋዜጦችና መጽሔቶች አናት ላይ በብዛት አለመታጣቱም ጭምር ነው።

“እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው” ለህሊና ማንቂያነት፤ ለአስተሳሰብ መግሪያነት፤ ለሃሳብ ማጠናከሪያነት፤ ለትሁት ባህርይ መገለጫነት፤ በአቋራጭ (በአጭሩ) ማስተማሪያነት፤ ለእውቀት ወርድ፣ ጥልቀት፣ ስፋት ማሳያነት፤ ከመታበይ መፈወሻነት፤ የ“ከእኔ በላይ ላሳር” ባዮች ማስታገሻነት፤ የሥነ ምግባር ማፅኛነት መድኃኒት በመሆን ሥራ ላይ ከዋለ ዘመኑ የሰነበተ ሲሆን፤ ለስንባቴውም ፈጣሪ ባለቤቱ የጥንት ግሪክ ፈላስፋ እና አስተማሪ፤ የዕውቀቱን ድንበር እና ልክ አሳምሮ የሚያውቀው፤ የሚያውቀውን ብቻ ሳይሆን አለማወቁንም የሚያስተምረው፤ እንዲሁም የምዕራቡ ዓለም ፍልስፍና መስራች (ሶቅራጥስ (470 ዓ.ዓ. — 399 ዓ.ዓ.)) መሆኑ ነው።

ወደ ርእሳችን እንምጣ። ያለ ምንም ፍርሀትም ሆነ ኩራት (ማን ነበር “ፍራትም የለች፤ ኩራትም የለች” ያለው?) አንድ መናገር የምንችለው እውነት ቢኖር በአሁኑ ሰአት ሀገራችን የሶቅራጥስ አይነት ሰው የሚያስፈልጋት መሆኑን ነው። የሶቅራጥስ አይነት ሰው እንኳን ባታገኝ እሱ ያለውን የሚረዳላት ሰው፤ እሱ ይሆን ዘንድ የተመኘውን የሚያደርግላት ሰው፤ “እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው” የሚል(ላት) ሰው የሚያስፈልጋት መሆኑን ነው። ይህንን ያለ ምንም ኩራትም ሆነ ፍርሀት መናገር ይቻላል።

እዚህ ላይ የዚህ ጽሑፍ አላማ በቀድሞው ዘመን በዚሁ ጸሐፊ የልጅነት እድሜ ወቅት “ሁሉ አውቃለሁ ባይ፤ ሁሉ ተቺ፤ ሁሉ • • •፤ ሁሉ • • •” የተባለውን፤ እውነትም ይሁን ሀሰት፤ ተክክልም ይሁን ኢ-ትክክል ወዘተ ለማስታወስ አለመሆኑን ከወዲሁ ማስታወስ ያስፈልጋል። ወቅቱ፣ ርእዮቱና ስርአቱ የተለያየ ነውና ያንን እዚህ ማምጣት ምናልባትም ነገር መደባለቅ ብቻ ሳይሆን መደበላለቅ ሊሆን ስለሚችል በ“እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው” ማለፉ የተሻለ ይሆናል።

ሰውየው አስቀድሞ እንዳለው፣ ተከታዮቹም ሆኑ ደቀ መዛሙርቱ እስከዛሬና እስከ ማእዜኑ እንዳስተጋቡለትና እንደሚያስተጋቡለት “ሁሉን አወቅ” ሰው የለም። ዛሬ ዛሬ ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን እንጂ ሁላችንም ኢትዮጵያን አናውቃትም። ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን እንጂ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ አናውቅም።

ሁላችንም የኢትዮጵያ ዜጎች እንሁን እንጂ ስለ ኢትዮጵያ ሲባል በአያት ቅድመ አያቶቻችን፤ እናት አባቶቻችን የተከፈለውን መስዋእትነት (የፈሰሰውን ደም እና የተከሰከሰውን አጥንት) አናውቅም። ምንም አይደለም፤ “ሁሉን አወቅ” አለመሆን አያስጠይቅም፣ አያስወቅስምና፤ “ሁሉን አወቅ” መሆን አይቻልም (ከእሱ፣ ከላይኛው በስተቀር) እና ከሳሽም ተከሳሽም የለም፤ ሊኖርም አይችልም።

ዛሬ ኢትዮጵያን ባለማወቃችን ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ እያደረስነው ያለው ጉዳት ጉዳቱ ከዛሬ ይበልጥ ነገ የሚሰማን ይመስላል። ከምናውቀው የማናውቀው እንደሚበልጥ ባለማወቃችን ምክንያት ለማወቅም ይሁን ለመተዋወቅ የምናደርገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ቀጫጫ ነው። ከብርሀኑ ይልቅ ጭለማውን አግዝፈን፤ ከፍቅሩ ይልቅ ጥላቻውን አፍቅረን አለማወቃችንን እያሳወቅን ሲሆን፤ ችግሩ አለማወቃችንን እራሳችን አለማወቃችን ነው።

ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከሚያዝወትሯቸው አገላለፆች መካከል አንዷ ድንቁርና እጅግ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን የሚገልፁባት መንገድ ነበረች። “ሌላው ሀገር ስልጣን ከእውቀት ይመነጫል፤ እኛ ሀገር እውቀት ከስልጣን ይመነጫል።” የምትል። ሰውየው ምን ለማለት እንደ ፈለጉ አንባቢ በየቤቱ እሚለውን ይል ዘንድ ትተንለት ወደ “እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው” እንመለስ። (ካስፈለገም፣ “እያወቁ በሄዱ መጠን አለማወቆትን ይረዳሉ” ያለውን ሰው ፈልጎ ለምን እንዳለው መጻፍ ይቻላል።)

እውነት፣ እውነት — አለማወቃችንን አለማወቃችን እንጂ ብናውቃት ኖሮ ኢትዮጵያ ምን አጥታ ነው ይሄ ሁሉ ጥል፤ ይሄ ሁሉ እሰጥ አገባ፤ ይሄ ሁሉ ረብሻ፤ ይሄ ሁሉ ንጥርቂያ፤ ይሄ ሁሉ መቧቋስ፤ ይሄ ሁሉ መካካድ፤ ከሁሉም በላይ ይሄ ሁሉ መገዳደል። ይሄ ሁሉስ የብሔር ከረጢት ለምን አስፈለገ? “እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው” ማለትን ፈርተን እንጂ አለማወቃችንን አውቀን ለማወቅና መተዋወቅ ብንጣጣር “ሁሉ በጃችን፤ ሁሉ በደጃችን” ሆኖ አናገኘውም ነበርን? ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ከአንድ የአፍሪካ ሀገር ስፋት በላይ የሆነ ታራሽ መሬት (ማእድኑን ዝም ነው) መኖሩን እናውቃለን፤ ካላወቅንስ አለማወቃችንን አውቀን ለማወቅ እንጥራለን?

በሀገራችን የመጀመሪያው የብሔረሰቦች እኩልነት አቀንቃኝ ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” በማለት ያሰፈረው ዘመን ተሻጋሪ ግጥም የገጣሚውን አለማወቁን አስቀድሞ ስለማወቁ የማይናገረው የለምና አለማወቅን ማወቅ የበርካታ ችግሮች መፍትሔ ማፈላለጊያ መንገዶች ስለመሆኑ ማሳያ ነው።

ከበቂ በላይ እንደ ተባለው፣ በብዙዎች ጥናትና ምርምር ስራዎች በደማቁ እንደ ተሰመረበት “እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው” የሚለው ፍልስፍናዊ አተያይ ለመጠየቅ (ለጥያቄ) ቀስቃሽ ነው። ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉትን የሚፈጥር ጓጓጭ ነው። አለማወቁን ከማያውቅ በተቃራኒ አለማወቁን የሚያውቅ ሰው ለማወቅ ይቆፍራል፤ ይጠይቃል፤ ያጠያይቃል።

አለማወቁን የሚያውቅ ከአለማወቁን ከማያውቀው በተቃራኒ እንደ በሬ ሽንት ወደ ኋላ ሳይሆን ጉዞው ወደ ፊት ነው፤ አለማወቁን ከማያውቀው ይልቅ ለሚያውቀው መጪው ዘመን ብሩህ ነው። አለማወቁን የሚያውቅ ሰው ለውይይት ክፍት ነው።

አለማወቅ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ችግር ሆኖ አያውቅም፤ ችግር ሆኖ የሚያውቀው አለማወቅን አለማወቁ ነው። በአሁኑ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ዘመን የጥፋት ሁሉ፤ የወንጀል ሁሉ፤ የግጭቶች ሁሉ ወዘተ አለማወቅ ሳይሆን አለማወቅን እራሱ አለማወቅ ነውና፤ አለማወቅን በማወቅ እስካልተካን ድረስ ኑሯችን በጭለማ ውስጥ ከመሆን አያመልጥም። አለማወቃችንን አውቀን ለመፍትሔ ካልተንደረደርን በስተቀር ጉዟችን የኋልዮሽ መሆኑ የማይቀር ነው። ዓለም አወቅ ዋጋ ማስከፈሉ የግድ ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You