የነብስ አድን ክትባት ዘመቻ

አንዳንድ ጊዜ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የጤና አገልግሎቶች ሊቋረጡ ይችላሉ:: ይህንኑ ተከትሎ በተለይ ሴቶችና ህፃናት ተጎጂ ይሆናሉ:: በኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት ወድመዋል:: በዚህም በርካቶች ከጤና አገልግሎት ውጪ ሆነዋል:: በተመሳሳይ በሀገሪቱ በኦሮሚያና አማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ድርቅ በመከሰቱ ብዙዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ከጤና አገልግሎቶች ለመራቅ ተገደዋል:: በጦርነቱና በድርቅ ምክንያት ህፃናት ቀደም ሲል የጀመሩትን ክትባት አቋርጠዋል:: ሌሎቹ ደግሞ በጭራሽ ክትባት አልጀመሩም:: በዚህ መነሻነት ነው እንግዲህ ክትባት ጀምረው ያቆረጡና ያልጀመሩ ህፃናትን እንዲከተቡ ጤና ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት መጨረሻ የክትባት ዘመቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስጀመረው::

የጤና ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደሚናገሩት፤ በጤና ፖሊሲ ውስጥ ከፖሊሲ የሚመነጩ የተለያዩ ስትራቴጂዎች አሉ:: ከነዚህ ውስጥ የአምስትና የሶስት አመት እቅድ ውስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የጤና አገልግሎቶች ውስጥ የእናቶችና የህፃናት ጤና አንዱ መሆኑ ይታወቃል:: ባለፉት አመታት መንግሥት፣ አጋር ድርጅቶችና ማህበረሰቡ በጋራ በሰሩት ስራ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል:: ኢትዮጵያም በተለይ የእናቶችና ህፃናትን ሞትና ህመም በመቀነስ ጥሩ ስም ያላት ሀገር ለመሆን በቅታለች::

የክትባት አገልግሎት ደግሞ የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው:: በኢትዮጵያ ባለፉት አራት አስርት አመታት የክትባት መርሃ ግብር በርካታ ህፃናትን ተጠቃሚ አድርጓል:: በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን ከሞት ታድጓል:: ዘርፉን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በክትባት ላይ የሚደረገው የአንድ ዶላር ኢንቨስትመንት ምላሹ ከሀምሳ ዶላር በላይ ነው:: ይህም ክትባት ምን ያህል ክፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያመለክታል:: ክትባት የጤና ጥቅም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑ ይነገራል::

ኢትዮጵያ ከአርባ አመት በፊት ከስደስት በማይበልጡ የክትባት አይነቶች የጀመረችው ክትባት በአሁኑ ውቅት ከአስራ አራት በላይ የሚሆኑ የክትባት አይነቶች ለህፃናት፣ ለልጃገረዶችና ለአዋቂዎች እየጠሰጡ ይገኛሉ:: እነዚህ ክትባቶች በሽታን የመከላከል ስትራቴጂን መሰረት አድርገው የሚሰራባቸው ናቸው:: ከዚህ በፊት ክትባቶች ከውጪ የሚመጡ ቢሆንም አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ክትባት የማምረት ጅምር አለ:: ይህን በማጠናከር ኢትዮጵያ ራሷን ችላ በሀገር ውስጥ ክትባቶችን አምርታ ህፃናት በሚያስፈልገው የጥራት ልክ በክትባት ተደራሽ የሚሆኑበት ግዜም ሩቅ አይደለም::

ሚኒስትር ዲኤታው እንደሚገልፁት፤ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ሰው ሰራሽና የጠፈጥሮ አደጋ ምንም አይነት ክትባት ያላገኙና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ በርካታ ህፃናት አሉ:: ህፃናቱ ሀሉንም ክትባቶች ወስደው ሲያጠናቅቁ ነው ተከትበዋል ሊባሉ የሚችሉት:: እነዚህ ህፃናት በአብዛኛው የሚገኙት በግጭትና ድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች፣ ራቅ ያሉ ቦታዎችና የአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ሲሆን በከተሞች አካባቢዎችም ያልተከተቡ በርካታ ህፃናት እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ::

ህፃናቱ ክትባት ሳያገኙ ወይም ክትባቱን ጀምረው ለማቋጣቸው በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ:: በዋናነት ግን በሀገሪቱ የነበሩ የተለያዩ ግጭቶችና የድርቅ አደጋዎች ህፃናቱ ክትባት እንዳያገኙና የጀመሩትን ክትባት እንዳያጠናቁ ምክንያት ሆነዋል:: በእያንዳዱ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ምን ያህል ህፃናት ክትባት እንዳላገኙና አግኝተው ያቋጡት ምን ያህል እንደሆኑ ጥናት ተሰርቷል:: እነዚህን ህፃናት በክትባት ተጠቃሚ ለማድረግ የማካካሻ ክትባት መርሃ ግብር/big catch policy/ ከሶስት ወራት በፊት ተዘጋጅቷል:: እስካሁን ድረስ በመደበኛው ክትባት ክትባት ጀምረው ያቋረጡና ያልጀመሩ ህፃናትን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል:: በዚህም በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ህፃናት ሙሉ በሙሉ ክትባት እንዲያገኙ ተደርጓል:: በዚህ ብቻ ግን የሚያበቃ መሆኑን በማየት ለአስር ቀን የሚቆይ የክትባት ዘመቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማድረግ ተወስኗል:: የክትባት ዘመቻውም ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በይፋ ተጀምሯል::

የክትባት ዘመቻው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከናወን ሲሆን ትኩረት የሚደረግባቸው የተወሱ አካባቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ:: በዚህ ዘመቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህፃናት ይከተባሉ:: የሚከተቡት ህፃናት እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑና ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ክትባት ያልወሰዱ ወይም ደግሞ ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ናቸው:: በዚህ የክትባት ዘመቻ ትኩረት የሚሹና ቅድሚያ የሚሰጣቸው በተለይም በግጭትና በድርቅ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉና ወደቀያቸው እየጠመለሱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ::

በሌላ በኩል የተለያዩ ወረርሽኞች ያሉባቸው አካባቢዎች በክትባት ዘመቻው ቅድሚያ ይሰጣቸዋል:: ተለይ ኮሌራ፣ ኩፍኝ ወይም የወባ ወረርሽኝ ያለባቸው አካባቢዎች በክትባት ዘመቻው ቅድሚያ ይሰጣቸዋል:: በፀጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች የነበሩበት ቦታ ላይ ቅድሚያ ይሰጣል:: ምክንያቱም የበለጠ ብዙ ህፃናት ክትባት ያለወሰዱበት ቦታ እንርሱ ስለሆኑ ለእነርሱም ተጨማሪ ቅድሚያ ይሰጣል:: ራቅ ያሉ ወረዳዎች፣ በጤና ሴክተር ዝቅተኛ አፈፃፀም ባላቸው አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጓል::

ስለዚህ ከ1 ሺ በላይ የሚሆኑ ወረዳዎችን በመለየት ለየትኞቹ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ታውቋል:: ለእያንዳንዱ ወረዳ ምን ያህል የህክምና ግብአት እንደሚደርስ ተረጋግጧል:: ለክትባት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ተሟልተዋል:: የጤና ባለሞያዎች ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል:: የክትባት መስጫ ተቋማትም ዝግጁ ሆነዋል::

በዘመቻው ሁሉም የጤና ባለሞያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ:: በተለይ ከ38 ሺ በላይ የሚጠጉት የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ሙሉ በሙሉ በክትባት ዘመቻው ይሳተፋሉ:: በጤና ጣቢያ ያሉትም እንዲሁ ጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን ወርደው በመርዳት ሰፊ ስራ ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል:: ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችም ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሞያዎች ወርደው ድጋፍ ያደርጋሉ:: ክትባቱንም በጤና ተቋማት ውስጥ ይሰጣሉ:: ከዛም ውጪ ያሉ ተንቀሳቃሽ ቡድኖችም ራቅ ባሉና ጤና ተቋማት በቀላሉ በማይገኙ ቦታዎች ላይ አስፈላጊውን ክትባቱን ይዘው ይቀርባሉ::

ዘመቻው ሀገር አቀፍ እንደመሆኑ በተለይ ለመግባት ቀላል ባልሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች የሁሉም ጤና ባለሞያዎች ድጋፍ ያስፈልጋል:: በዚህ ክትባት ሙሉ በሙሉ ክትባት ያልጀመሩና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል:: ከዛ በኋላ የክትባት ስረአቱን በማጠናከር ክትባት ያልወሰዱ ወይም ያልጀመሩ ህፃናት በማይኖሩበት መንገድ መስራት ያስፈልጋል::

በግጭት በተጎዱ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ላይ መድረስ እንደሚቻል ከክልሎች ጋር ንግግር ተደርጓል:: የተወሰኑ ቦታዎች ግን ተጨማሪ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል:: ከዚህ አንፃር ከፀጥታ አካላት፣ ከልማትና አጋር ድርጅቶች፣ በአካባቢው ካሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆንና ማህበረሰቡን በማስተባበር በእነዚህ ቦታዎች ላይ ተደራሽ ለመሆን ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ:: በተለይ ግብአት ለማድረስ ሊከብድ ስለሚችል የአለም ጤና ድርጅትን የመሰሉ አጋር ድርጅቶችን በመጠቀም በቦታዎቹ ላይ ለመግባት ጥረት ይደረጋል::

በክትባት ዘመቻው እድሚያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናት ሁሉንም የክትባት አይነቶች ያገኛሉ:: ትልቅ ትኩረት የሚደረግባቸው አምስት የክትባት አይነቶች ግን አሉ:: በተለይ ፀረ አምስት/ፔንታ/፣ የሳምባ ምች፣ የኩፍኝ፣ የአንጀት ህመምና የፖሊዮ ክትባቶች በዚህ ክትባት ዘመቻ ህፃናት የሚከተቧው የክትባት አይነቶች ናቸው:: ነገር ግን ደግሞ የህፃናቱ እድሜ ታይቶ ማንኛውም የክትባት አይነት የሚሰጥበት ሁኔታ ይኖራል::

ሚንስትር ዲኤታው እንደሚሉት ይህን ክትባት ማካካሻ መርሃ ግብር ተፈፃሚ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል:: በተለይ የጤና ባለሞያዎችና አመራሮች ለክትባት ዘመቻው እውን መሆን ኃላፊነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ መወጣት ይጠበቅባቸዋል:: ግን ደግሞ የክትባት ዘመቻው የጤናው ዘርፍ ስራ ብቻ ባለመሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ የመንግሥት አመራሮችም ለክትባት ዘመቻው መሳካት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል:: ሌሎች አጋር ድርጅቶችና ማህበረሰቡም በክትባት ዘመቻው ንቁ ተሳታፊና አጋዥ መሆን አለባቸው::

በተለይ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑና ምንም አይነት ክትባት ያላገኙ ወይም ደግሞ ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት ጤና ባለሞያዎች በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ለይተዋቸው ዝግጁ ማድረግ ይኖርባቸዋል:: ጤና ተቋማትም ለዚህ ዝግጁ መሆን አለባቸው:: ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ የክትባት ዘመቻው መሆን አለበት:: ከክልሎች ጋርም በተግባቦት እየተሰራ ይገኛል:: በቀጠሮ ያሉትን ህፃናትንም ደግሞ ፈልጎ ማግኘት፤ ተፈናቃይ ከሆኑ የት እንደሄዱ፣ ወደ ቀያቸው ከተመለሱም በአግባቡ ፈልጎ ማግኘትን ጭምር የሚሰራ ሥራ ነው::

ከዚሁ የክትባት ዘመቻ ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ ሌሎች ስራዎችም ይኖራሉ:: በተለይ የወባ ወረርሽኝ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኝ በክትባት ዘመቻው ቤት ለቤት ሲኬድ አብሮ የሚታይ ይሆናል:: ይህ ብቻ ሳሆን ከሥርአተ ምግብ ጋር በተያያዘ በተለይ የምግብ እጥረት ያጋጣማቸውን ህፃናት የመለየት፣ ህክምና የመስጠትና ወደ ህክምና ተቋማት መላክና ሌሎችም ተጓዳኝ ስራዎች የሚከናወኑ ይሆናል::

ይህ የክትባት ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆንና ልጆች የዚህ ክትባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወላጆችና አሳዳጊዎችም ልጆቻቸውን ወደ ህክምና ተቋም በመውሰድ ማስከተብ ይጠበቅባቸዋል:: ነገር ግን ክትባቱ በጤና ተቋማት ብቻ የሚሰጥ ባለመሆኑ በግዚያዊነት በውሎ ገብ በተንቀሳቃሽ ቡድን በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚሰጥ በመሆኑ ወላጆች እነዚህን ሁሉ አማራጮች በመጠቀም ልጆቻቸውን ማስከተብ ይኖርባቸዋል:: በተመሳሳይ የመገናኛ ብዙሃንም ይህን የነብስ አድን ክትባት ዘመቻ አስፈላጊነት በማጉላትና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል::

በተከታታይ አስር ቀናት የሚከናወነው የነብስ አድን ክትባት ዘመቻ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጣ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግና የህፃናትን ሞት በእጅጉ እንዲቀንስ የራሱን አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You