ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ላለፉት ስድስት ዓመታት የሰላምን በረከት እያጣጣመ የሚገኘው የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ የዘመናት የልማት ቁጭቱን ለመወጣት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረለት በሁሉም ዘርፍ የተሠሩት የልማት ሥራዎቹ ማሳያዎች ናቸው:: ክልሉ በግብርና ዘርፍ በተለይም የመስኖ ልማትን አዲስ የሥራ ባህሉ አድርጎት ይታያል:: በመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ ያሳየው እምርታም ተስፋ ሰጭ ነው::
በክልሉ ፈጣን ለውጥ ከታየባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ነው:: ክልሉ ያገኘውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው በስደት ይኖሩ የነበሩ የአካባቢው ተወላጆች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መዋለ ንዋያቸውን በክልሉ የልማት ሥራዎች ላይ እያዋሉ ይገኛሉ::
እነዚህ የክልሉ ተወላጆች በግብርናና በትምህርት ዘርፎች እንዲሁም በሆቴሎች፣ በትምህርት ዘርፍና በፋብሪካዎች ግንባታ ብርቱ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ:: በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ከተከናወኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መካከል በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎች ይጠቀሳሉ::
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማነቃቃት አስችሏል፤ ኢንቨስትመንቶቹ ኢኮኖሚውን በማንቀሳቀስም የአካባቢውን ገጽታ በመቀየር እና ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል በመፍጠር አስተዋጽኦ እያበረከቱም ይገኛሉ::
በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከለውጡ በፊት የነበሩት አጠቃላይ የፋብሪካዎች ብዛት (ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ) ከ85 አይበልጥም ነበር፤ ከለውጡ ወዲህ ግን 230 የሚሆኑ አዳዲስና ግዙፍ ፋብሪካዎች መገንባታቸውን ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ቃለ ምልልስ ባደረግንበት ወቅት አረጋግጠውልናል::
በስራ ላይ ከሚገኙ ፋሪካዎች መካከል ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበትና ለክልሉ እና ለሀገር አለኝታ የሆነው ‹‹ሱዌይስ ሞተርስ ኩባንያ›› (Suweys Motors Company) አንዱ ነው:: ኩባንያው በጂግጂጋ ከተማ የሚገኝ ሲሆን፣ ‹‹ጄቱር›› እና ‹‹ሱዙኪ›› ዲዛየር መኪኖችን እየገጣጠመ ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል::
ይህ ለግንባታው ብቻ 250 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገበት ፋብሪካ የሚገጣጠሙ የመኪና አካላትን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትም እንዲሁ ከፍተኛ ካፒታል ያንቀሳቅሳል::
የሱዌስ ሞተር ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲ ኢብራሂም እንዳሉት፤ ፋብሪካው በቀን አምስት መኪኖችን እየገጣጠመ ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል:: ሥራ በጀመረ በአንድ ወር ቆይታውም፣ በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ 40 ጄቱር እና 12 ሱዙኪ ዲዛየር መኪኖችን ገጣጥሞ ለገበያ በማቅረብ ሸጧል::
ከፍተኛ የግዢ ፍላጎት እንዳለ የተናገሩት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ ቅድመ ክፍያ ፈጽመው ለመግዛት ወረፋ የያዙ በርካታ ሰዎች ስለመኖራቸውም አስታውቀዋል:: ኩባንያው የሀገር ውስጥ የመኪና አቅርቦት ፍላጎትን ማሟላት ብቻ ሳይሆን መኪኖችን ወደ ጎረቤት ሀገራት የመላክም ራዕይን ይዞ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ፋብሪካው ስራ በጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ ብቻ ለሦስት መቶ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠሩን የተናገሩት አቶ አብዲ፣ ኩባንያው ወደፊት የማስፋፊያ ስራ ሲያካሂድና የንግድ ሰንሰለቱን ሲያረዝም ለሌሎች በርካታ ዜጎችም የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል::
‹‹ሳሂድ ሜታል ኢንዱስትሪ ኢንጂነሪንግ›› ሌላው በጂግጂጋ ከተማ የሚገኝ የከባድ መኪኖች አካላት ማምረቻ እና መገጣጠሚያ ግዙፍ ኩባንያ ነው። የኩባንያው የገበያ ክፍል ኃላፊ አቶ ነስር
ያሲን እንደሚሉት፤ ኩባንያው በራሱ ቅርጽ ማውጫ ማሽኖች ተጠቅሞ የከባድ መኪኖችን አካላት፣ ቦቴና የነዳጅ ማደያ ታንከሮችን ያመርታል። ሞተር እና ጋቢና ብቻ ያላቸውን ከባድ የጭነት መኪኖች ከውጭ እያስገባ የቀረውን አካላቸውን በፋብሪካው ውስጥ ሰርቶና ገጣጥሞ ተሽከርካሪዎቹን ሙሉ እያደረገ ለገበያ ያቀርባል ሲሉም ያብራራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኩባንያው ለ270 ሰዎች የሥራ እድል ፈጥሯል። በኩባንያው ውስጥ ከምንም ተነስተው ሥራ የጀመሩ ሠራተኞች ዛሬ ሙያ አካብተው ከፍተኛ ተከፋይ እስከመሆንም ደርሰዋል።
በክልሉ ከጂግጂጋ ቀጥሎ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ያሉባት የክልሉ ሲቲ ዞን ዋና ከተማ ሺኒሌ ነች:: ሺኒሌ በኢትዮ-ጂቡቲ አውራ መንገድ ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ የውጪና ገቢ ንግዱን ከማሳለጥ አንጻር የራሷን አስተዋጽኦ የምታበረክት የኢኮኖሚ ኮሪደር ስትሆን፣ ለኢንቨስትመንትም ምቹ ከሚባሉ የሀገራችን ከተሞች ትመደባለች:: በዚህም ምክንያት ምርቶቻቸውን ወደ ሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እና ወደ ውጭ ሀገር የሚያሰራጩ ፋብሪካዎች ተገንብተውባታል::
የሽኒሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሮብሊ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ በሽኒሌ ወረዳ በተለይም በሽኒሌ ከተማ የቶኔ እና የመርማርሳ ቀበሌዎች የኢንዱስትሪ መንደር ተብለው ተለይተዋል:: ለኢንዱስትሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት የአካባቢው ሰላም መሆን አስተዋጽኦ አበርክተዋል::
ፋብሪካዎቹ ከግንባታ ጊዜያቸው ጀምሮ ወደ ስራ እስከገቡበት ጊዜ ድረስ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል እየፈጠሩ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል:: በርካታ የአካባቢው ተወላጆችና ከሌላ አካባቢ የመጡ ዜጎችም ጭምር በፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል:: የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በዞኑ መኖራቸውን ጠቅሰው፣ የግራናይትና ማርብል ፋብሪካው በተለይ በድሬዳዋና በአካባቢው ቤት ለሚገነቡ ሁሉ ጥሩ አድል ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል::
በተጨማሪም ከ10 ሺ እስከ 25 ሺ ሊትር ውሃ መያዝ የሚችሉ ሮቶዎችን፣ የስፖንጅ ፍራሽ፣ የቆርቆሮ፣ የሳሙና እና የመጠጥ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካዎች እንዳሉም አብራርተዋል::
ወረዳው የገቢ ወጪ ንግድ የሚተላለፍበት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም በኢንቨስትመንት መስኮች ለተሰማሩ ባለሀብቶች አመቺ እንደሆነ አስታውቀዋል:: ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግም ባለሃብቶች እየመጡ በተለያዩ ሥራዎች እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል::
በተለይም በሪልስቴትና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች 125 ሄክታር መሬት ዝግጁ መደረጉንም ጠቁመዋል:: የውሃና የመብራት መሰረተ ልማት ዝግጁ በማድረግና ቀልጣፋ መስተንግዶ ለመስጠት ተዘጋጅቶ አልሚዎችን እየጠበቀ መሆኑንም አስታወቀዋል::
ከሽኒሌ-ድሬዳዋ እየተገነባ ያለው አዲስ የአስፋልት መንገድም በከተማዋ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተው፣ ለአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴም ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል::
የወረዳው የኢንቨስትመንት ቢሮ የሚመራው በክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር እንደሆነ ጠቁመዋል:: የአካባቢው ጸጥታና ሰላም አስተማማኝ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ባለሃብቶች ወደ አካባቢው በመምጣት በልማቱ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል::
በሽኒሌ ከተማ ከተገነቡት ግዙፍ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ‹‹ኢፎፒክ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ›› አንዱ ነው:: የኩባንያው የፕሮዳክሽን ማናጀር አቶ ሙአዝ ብርሃኑ ኩባንያው ሮቶ፣ የፕላቲክ ቱቦችን፣ ወንበሮችን እና የስፖንጅ ፍራሾችን ያመርታል ይላሉ::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ፋብሪካው ሥራ ከጀመረ አምስት ዓመቱ ነው:: እስከ 600 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወጪ ተደርጎበት የተቋቋመ ነው:: ከ500 እስከ 10 ሺህ ሊትር መያዝ የሚችሉ የተለያየ መጠን ያላቸውን ከ25 እስከ 30 የሚደርሱ ሮቶዎች በቀን ማምረት ይችላል::
እስካሁን እየሰራ የሚገኘው በአንድ ፈረቃ ቢቻ ሲሆን፣ ለ150 ሰዎችም የሥራ እድል ፈጥሯል:: 24 ሰዓት መስራት ሲጀምር የሰራተኞቹን ቁጥር በሶስት እጥፍ በማሳደግ ለ450 ዜጎች የስራ እድል የመፍጠር አቅም ይኖረዋል:: የፕላስቲክ ምርቶቹን ከሀገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ እንደ ጂቡቲና ሶማሌላንድ ለመሳሰሉ ሀገራትም ተደራሽ ያደርጋል::
በዚያው ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የስፖንጅ ፋብሪካም በቀን (በስምንት ሰዓት ውስጥ) እስከ አምስት ሺህ የተለያየ መጠን ያላቸው ፍራሾችን ያመርታል:: ምርቱ ሙሉ ለሙሉ ለሀገር ውስጥ ገበያ በተለይም ለምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ እንደሚቀርብ የተናገሩት አቶ ሙዓዝ፣ የገበያው ውስንነት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት ተግዳሮት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል::
ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ከውጭ ሀገራት እንደሚያስገቡ የተናገሩት ማናጀሩ፣ ሽኒሌ ለጂቡቲ ወደብ ቅርብ መሆኗ ግብዓት ለማቅረብና ምርቱን ወደ ውጭ ለመላክም አመቺ እንደሆነች ገልጸዋል::
ከውጭ የሚመጡ ግብአቶችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት በስራቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑንም ማናጀሩ ጠቅሰዋል:: በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተሟላ ግብዓት ማቅረብ አለመቻሉን አስታውቀው፣ በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ ፋብሪካው አንዳንድ ጊዜ ለመቆም እንደሚገደድም ተናግረዋል::
ሌላው በሽኒሌ ወረዳ በኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማሩት የ‹‹ዋቢ ግሩፕ ማርብል እና ግራናይት ፋብሪካ›› ባለቤት አቶ ጣሂር አብዲ ናቸው:: መንግስት ባለሃብቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው በልማት ሥራ እንዲሳተፉ ያስተላላፈው ጥሪ እና የሚያደርገው እገዛ እንዲሁም በክልሉ የተገኘው ሰላም ከሚኖሩበት የስደት ሕይወት ወደ ሀገራቸው ገብተው በልማት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስታውቀዋል::
እርሳቸውና መሰል ጓደኞቻቸው በአክሲዮን ተደራጅተው በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ‹‹ዋቢ ግሩፕ ማርብል እና ግራናይት ፋብሪካ››ን ማቋቋማቸውን ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው ግንባታው ተጠናቆ ወደ ማምረት ስራ ለመግባት እየተዘጋጀ ይገኛል:: ለሕንጻ ቤቶች ንጣፍ የሚሆኑ የተለያየ ቅርጽ ያላቸውን ምርቶች ከድንጋይ እና እምነበረድ በማምረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የማሟላትና ከውጪ የሚገቡ መሰል ምርቶች የመተካት፤ ምርቱን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ራዕይም አለው:: ለፋብሪካው ግብዓት የሚውሉና በአካባቢው የሚገኙ ግብአቶችን ወደ ፋብሪካው እያስገባም ይገኛል::
በስራ እድል ፈጠራ በኩልም በፋብሪካው ተከላ ሂደት ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩን ገልጸው፣ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ደግሞ በሶስት ፈረቃ በሚከናወነው ሥራ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል::
አቶ ጣሂር፤ ፋብሪካው በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ጠቅሰው፤ አሁን የሚስተዋለው የመብራት መቆራረጥ የሚቀጥል ከሆነ የማምረቱን ስራ እንደሚጎዳው ተናግረዋል:: የመብራት መቆራረጡ ጉዳይ ከወዲሁ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም