ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብቷ ሊረጋገጥላት ይገባል !

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባሕርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች:: 1 ሺህ 800 ኪሎሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባሕር ይዞታ የነበራትና ለወጭና ገቢ እቃዎች ሁለት ወደቦች የምታስተዳድር ሀገር ነበረች:: ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ውጪ ቀይ ባሕርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ ከባድ ነው::

ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትወገድ ተደርጓል:: ለዘመናትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ምንም ድርሻ እንዳልነበራት ሆን ተብሎ በተሰራጨው ትርክት እና በተሠራው ሴራ ኢትዮጵያና ቀይ ባሕር ተቆራርጠው ኖረዋል:: ከ60 ኪሎ ሜትር የባሕር ርቀት ላይ እየተገኙ ኢትዮጵያውያን ወደብ እና የባሕር በር እንዳይኖራቸው ተፈርዶባቸው ቆይተዋል::

የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከሥነልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል:: የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል::

ለበርካታ መሠረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል:: ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል:: በዲፕሎማሲ እና በተፅዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የባሕር በር አለመኖር የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው::

በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሠራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባሕር በር ጥያቄ ነው:: መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል:: የባሕር በር ማጣት ስብራትን በማከም አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የባሕር በር የምታገኝበት አማራጮችን በማፈላለግ ላይ ይገኛል ::

ሠላማዊ አማራጭን ሲከተል የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊ ላንድ ጋር የባሕር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) በመፈራረም ተዘግቶ የነበረውን የኢትዮጵያውያንን የባሕር በር ጥያቄ ዳግም ወደ መድረክ አምጥቶታል:: በዚህ ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ ደስታ ስሜት ተሰምቷቸዋል::

መንግሥት የጀመራቸው ጥረቶች አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ በር የሚከፍት ነው:: ቀጣናዊ ሠላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆንም በር ይከፍታል::

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል:: በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባሕር በር ከሌላቸው ሁሉም ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል::

ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም:: ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በባሕር በር የተከበበች ሀገር ናት:: በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር አፈጣጠሯ ከቀይ ባሕር የሚነጠል ሊሆን አይችልም:: በሌላም በኩል በታሪክ ረገድም በቀይ ባሕር ላይ ለዘመናት የበላይ ሆና መቆየቷን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ያሏት ሀገር ናት::

ስለዚህም ኢትዮጵያ በሴራ ከባሕር በር ይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጪ ባለቤትነቷን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም:: ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባሕር የተደረገበት አካሄድ ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነውና::

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትወገድና ወደብ አልባ እንድትሆን የተደረገው በ1900፤ 1902 እና 1908 ከቅኝ ገዢዎች በተደረጉ ውሎች አማካኝነት ነው:: እነዚህ ውሎች ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት መመሥረቻ ቻርተር ሕጋዊነታቸውን አጥተዋል::

ስለዚህም ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት እንዳትሆን የሚያግዳት አንዳችም ማስረጃ የለም:: በመሆኑም አማራጭ የወደብና የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያውን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብና ለዚህም የተለያዩ የሠላም አማራጮችን በመጠቀም የሀገሪቱን እና የሕዝቧን ዘላቂ ጥቅም ማረጋገጥ የግድ ይሆናል!

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You