ስፖርትና ሠራዊት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው›› – ኢንጂነር አይሻ መሐመድ  የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር

ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርት ጋር እኩያ ሊባሉ ከሚችሉ ክለቦች መካከል መቻል ተጠቃሽ ነው። የሀሃገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባለፈ በዓለም አቀፍ አደባባይ የስኬት ታሪክን የሚጋራው ጦሩ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት በመትጋት ላይ ይገኛል። በ1936 ዓም ምሥረታውን ያደረገው አንጋፋው መቻል የ80ኛ ዓመት በዓሉን ‹‹መቻል ለኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበረ መሆኑ ይታወቃል።

በርካታ ሁነቶችን ባቀፈው ክብረ በዓል አንጋፋ የክለቡን ሙያተኞች ያሳተፈና፤ መቻልን በምን መልኩ ወደ ስመጥር ክለብነት ማድረስ ይችላል በሚለው ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክም ተከናውኗል። መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ ስፖርትና ሠራዊት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ወታደራዊ ቁመናው የተስተካከለ አካላዊና አዕምሯዊ ጥንካሬ ያለው መሆን የወታደር መለያ ነው። ለዚህም ሁነኛ መሣሪያ ስፖርት ሲሆን፤ ችግሮችን ተቋቁሞ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ ያስችለዋል።

በመሆኑም ሠራዊቱ የእርስ በእርስ ውድድር ከማድረግ አልፎ በሀገር አቀፍ፣ በአሕጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የበኩሉን አስተዋፅዖ እያበረከተ የሚገኝ የስፖርት ክለብ ነው። መቻል ከምሥረታው ጀምሮ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራ አንጋፋ ክለብ ሲሆን፤ የሥራ አመራር ቦርዱ ሊያሳካ ለያዛቸው እቅዶች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ዋጋ ሰጥቶ እንደሚሠራባቸውም ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት።

የአንጋፋው ክለብ ታሪካዊ ዳራ የሚያሳይ ዳሰሳም በመድረኩ የቀረበ ሲሆን መቻል ለኢትዮጵያ ስፖርት የነበረው አስተዋፅዖም ተጠቁሟል። በጥቅሉ ‹‹ጦሩ›› የሚል ቅጽል የሚታወቀው ክለቡ እንደየወቅቱ ጠቅል፣ መቻል፣ ፋና፣ ፀሐይ ግባት፣ መከላከያ፣ ማዕከላዊ ዕዝ፣ ጦር ሠራዊት፣ ምድር ጦር፣ አየር ኃይል፣ ባሕር ኃይል፣ …የሚሉ መጠሪያዎችም ነበሩት። ከምሥረታው ጥቂት ዓመታት በኋላ ከ1948 አንስቶ በተለያዩ ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች በመሳተፍም ራሱን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ያስጠራና አሁንም በዚያው ሁኔታ ለመቀጠል በጥረት ላይ ያለ ክለብ ነው።

በተለይ በአትሌቲክስ እና እግር ኳስ ስፖርቶች ዘመናትን የተሻገረ ዝናን የገነባ ቢሆንም፤ መረብ ኳስ፣ ቦክስ፣ ብስክሌት፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ውሃ ዋና፣ ጠረዼዛ ቴኒስ እና ክብደት ማንሳት ስፖርቶችም በውድድሮች ላይ ይካፈል ነበር። ከሜልቦርን ኦሊምፒክ አንስቶ ኢትዮጵያን በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ያስጠራው ሻምበል አበበ ቢቂላን ጨምሮ፤ ባሻዬ ፈለቀ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ እሸቱ ቱራ፣ ቶሎሳ ቆቱ፣ መሐመድ ከድር እና ሐዲስ አበበን የመሳሰሉ አትሌቶች የውትድርናው ዓለም ለኢትዮጵያ ያበረከታቸው ቀደምት ዕንቁዎች ናቸው። አሁንም አትሌት ኢማና መርጋ፣ አሊ አብዶሽ፣ ሱሌ ኡቱራ፣ ደረሰ መኮንን፣ ድሪባ ጋሪ፣ አልማዝ አያና፣ ሙክታር እድሪስ፣ ፀጋዬ ከበደ፣ ቲኪ ገላና፣ ኢብራሂም ጄይላን፣ ጌታነህ ሞላ እና ሐዊ ፈይሳን የመሳሰሉ አትሌቶች ባለቤት ነው ክለቡ።

ይሁንና ከ1983 ዓም ጀምሮ አብዛኛዎቹ የጦሩ ክለቦች ፈርሰው፣ መጠሪያውም መከላከያ ወደሚል ተቀይሮ የቀድሞ ድምቀቱ ደብዝዞ፤ ትኩረቱን በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ እና መረብ ኳስ ስፖርቶች ላይ ብቻ አድርጎ መቆየቱ ይታወቃል። የተቋሙን ሪፎርም ተከትሎም ክለቦ በቀድሞ ስሙ መቻል እየተባለ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የውጤታማነት መንገድ ጀምሯል። በባለሙያ፣ በካምፕ፣ ሙዚየም እና ጂምናዚየሞች ላይም ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፤ በቀጣይ ላቀደው ስኬታማነትም ሊሠሩ ይገባሉ በሚል በባለሙያ ምክረሃሳብ ቀርቧል። ይህንንም ተከትሎ በመድረኩ ከተገኙ አንጋፋ የክለቡ ስፖርተኞች አስተያየት ተሰጥቷል።

ውይይቱን የመሩት የመቻል ስፖርት ክለብ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን፤ መቻል ትልቅ ታሪክ ያለው፣ እንደ ሀገርም ያበረከተው አስተዋፅዖና ያሳረፈው ዐሻራ የማይረሳ በመሆኑ የሚታወቅበትን ታላቅነት ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል። በመድረኩ የተነሱ ሃሳቦችንም በግብዓትነት የሚወሰዱ መሆኑን ጠቁመዋል። ከተነሱ ሃሳቦች መካከልም የክለብ መስፈርት ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የስታዲየም ግንባታ አንዱ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአየር ኃይል የተገነባውና ለብሔራዊ ቡድኑ የኦሊምፒክ ዝግጅት እየዋለ የሚገኘው መም የሚበረታታ መሆኑ ተነስቷል። በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎና ውድድሮችን በማዘጋጀት ገቢ መሰብሰብ እንዲሁም ስፖንሰር ማፈላለግም ተገቢ ነው። በተጨማሪም ከመቻል ባለፈ እንደ አየር ኃይል እና ባሕር ኃይልን የመሰሉ የቀድሞዎቹ የተቋሙ ክለቦች ዳግም መቋቋም እንደሚገባቸውም ተመላክቷል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You