ዜጎች በአንድም በሌላም ምክንያት ይመራናል ብለው ለመረጡት መንግሥት ጥያቄ ያቀርባሉ። ጥያቄ የቀረበለት መንግሥትም የሕዝቡን ጥያቄዎች በልካቸው መዝኖ እንደየፈርጃቸው ምላሽ ይሰጣል። ሆኖም እነዚህ ጥያቄዎችን የመመለስ ሂደቱ እንደ ጥያቄዎቹ ሁኔታ በአጭር ወይም በመካከለኛ፣ ካልሆነም በረዥም ጊዜ ተግባራት ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉ ናቸው።
ይሄ ሲሆን ደግሞ ሕዝቦች ጉዳዩን በልኩ ተገንዝበው የጥያቄዎቻቸውን መመለስ መጠባበቅ ይኖርባቸዋል። ይሄው ሲደረግም ኖሯል። ይሁን እንጂ እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ተገን በማድረግ፣ ለሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ እንታገላለን፤ ለሕዝባችን ነፃነትን እናጎናጽፋለን፤ በሂደቱ አቅም ካገኘን መንግሥትን በነፍጥ እንጥላለን፤… በሚል የተሳሳተ እሳቤ ያልተገባ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ቡድኖችና ኃይሎች ሲፈጠሩ ይታያል።
እኒህን መሰል ኃይሎች ታዲያ አካሄድና ፍላጎታቸው ሊለያይ ቢችልም ትናንትም የነበሩ፤ ዛሬም ያሉ፤ ነገም ሊኖሩ የሚችሉ ናቸው። ኢትዮጵያም በዚህ መልኩ በበዙ ነፃ አውጪዎች ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች፤ ሕዝቦቿም ጥያቄዎቻቸው እየተጠለፉባቸው በእነዚህ መሰል ኃይሎች ዘመናትን ዋጋ እየከፈሉ ኖረዋል፤ ዛሬም እየከፈሉ ይገኛሉ።
ዛሬም ላይ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ የቡድኖች የኃይል እንቅስቃሴዎች መሠረታቸው ይሄው የሕዝብን ጥያቄ ተገን አድርጎ የቡድኖችን ፍላጎት ለማሳካት የሚደረግ ጥረት ውጤት ነው። ባይሆንማ ጥያቄዎች በኃይል ሳይሆን በመነጋገር፤ በመወያየትና በመመካከር ላይ ተመሥርተው በሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ነበር ዋጋ የሚከፈለው።
አሁን እየታየ ያለው ግን ስለ ሕዝብ እንታገላለን እያሉ ሕዝብን ማሰቃየት፤ ማፈናቀል፣ መዝረፍና መግደል ነው። ሆኖም የሕዝብን መከራና እንግልት ማብዛት፤ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶችንና ተቋማትን ማውደምን የመሳሰሉ ተግባራት ደግሞ የሕዝብን ጥያቄ ይዤ እየሠራሁ ነው ከሚል ኃይል የሚጠበቁ አይደሉም። በመሆኑም ለሕዝብ ሠላምና ደኅንነት፤ ልማትና ብልጽግና የሚሠራ ማንኛውም ኃይል ሁሌም ሠላማዊ መንገድና ምክክርን ማስቀደም መገለጫው ሊሆን ይገባል።
ከሰሞኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች፣ በተለይም በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የሠላም ኮንፍረንስ ደግሞ፣ እንደ ሀገር ዋጋ እያስከፈለ ያለውን ግጭት፤ እንደ ክልልም መከራ ያበዛውን አለመረጋጋት መቋጨት የሚያስችል የውይይትና ምክክር ዓውድ በመፍጠር ዘላቂ ሠላምን ለማምጣት አቅም እንደሚሆን ይታመናል። ይሄ እንዲሆንም በመንግሥት በኩል ከነበረው ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪ ባሻገር፤ ስለ ሠላም ግድ ይለናል የሚሉ አካላትም የሠላም ጥሪዎችን እያስተላለፉ ይገኛሉ።
እነዚህ ተደጋጋሚ እና በተለያዩ ባለድርሻዎች የሚደረጉ የሠላም ጥሪዎች ታዲያ ማዕከል ያደረጉን የሕዝቦችን ሠላምና ደኅንነት እውን ማድረግ የሚያስችል ዘላቂ ሠላምን መፍጠር ነው። ሆኖም ዘላቂ ሠላም ሊመጣ የሚችለው፣ በአንድ ወገን (በመንግሥት) ጥረትና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በተለያየ መልኩ ኃይልን አማራጭ አድርገው የተሠማሩ ኃይሎችም ለዚህ ራሳቸውን ማስገዛት ሲችሉ ነው።
ምክንያቱም እነዚህ ኃይሎች ማዕከል አድርገው የሚታገሉት የሕዝብን ጥያቄ ስለመሆኑ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣል። በአንጻሩ ሕዝብ ጠይቆ ምላሽ ያገኘባቸውን የልማትና ሠላም ጉዳዮች በማበላሸት ወደተራዘመ ጥያቄ እንዲገቡ ሲያደርጉ ይታያል። በዚህም ሕዝቡ የመልማት ዕድሉን እያቀጨጩበት፤ ወጥቶ የመግባት፣ ሠርቶ የመብላት፣ ወልዶ የመሳም፣ ብሎም በሕይወት የመኖር ሕልውናውን ጭምር ጥያቄ ውስጥ ከትተው ለመከራ ዳርገውታል።
ይሄን መሰሉ ችግር መቋጫ እንዲያገኝ እና እነዚህ ኃይሎች በትክክልም የሕዝቡን ልማትና ሠላም እውን የማድረግ፤ ደኅንነቱ ተጠብቆም እንዲኖር የሚሹ ከሆነ፤ ከመንግሥትም ሆነ ስለ ሕዝብ ሠላምና ደኅንነት ግድ ይለናል ከሚሉ አካላት የሚስተጋቡ የሠላም ጥሪዎችን ማድመጥ የተገባ ነው። ምክንያቱም ስለ ሕዝብ የሚታገል ሕዝብን አያጎሳቁልም፤ ሕዝብን አይቀማም፤ ሕዝብን አይገድልም፤ ሕዝብ ከመከራ እንዳይወጣ በሚያደርግ ተግባር ላይም የሙጥኝ ብሎ አይቆይም።
ይልቁንም የሕዝቡን ልማትና ሠላም በሚያመጡ አማራጮች ላይ ያተኩራል። ለመመካከር፣ ለመወያየትና ለመነጋገር ራሱን በማዘጋጀት ሕዝቡን ከችግር እንዲወጣ ያደርጋል። በዚህ ረገድ አሁን ላይ እየተደረጉ ላሉ የሠላም ኮንፍረንሶች መሳካት አቅም መሆን፤ ለሚሰሙ ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎችም ጆሮ መስጠት ከእነዚህ ኃይሎች ይጠበቃል። ምክንያቱም ስለ ሕዝብ የሚታገል ማንኛውም ኃይል ሕዝብን ለሚጠቅሙ እና ደኅንነቱን ለሚያስጠብቁ ጉዳዮች ሁሉ ቅድሚያ ይሰጣልና!
አዲስ ዘመን ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም