የአፍሪካ ቀንድን ከትርምስ ወደ ትብብር የመለወጥ የኢትዮጵያ ውጤታማ መንገድ

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካለበት የጂኦ-ፖለቲካ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አኳያ፤ የበርካታ ኃይሎች ዓይን ማረፊያ ነው። በተለይ ቀጣናው ከቀይ ባሕር ጋር ካለው ቁርኝት፤ ብሎም በአካባቢው እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ከፍ ያለ የታሪክም፣ የፖለቲካና ሀገረ መንግሥት ውቅር ያላቸው ሀገራት ያሉበት መሆኑ ደግሞ፤ እነዚህ ኃይሎች በቀጣናው የራሳቸው ፍላጎት ለማስፈጸም ሲጥሩ እንዲኖሩ አድርጓል።

በዚህ ምክንያት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ መረጋጋት ርቆት የጦርነት ቀጣና ሆኖ ዘልቋል። ትናንት እነ ሶማሊያ ሠላም ርቋቸው፤ ጠንካራ ሥርዓተ መንግሥት አጥተው ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የመዝለቃቸው፤ ዛሬም እንደ ሱዳን ያሉ ሀገራት በሁለት ጎራ በተከፈለ የኃይል አሰላለፍ ውስጥ ገብተው በፈጠሩት ጦርነት ዜጎች ለስደትና ረሃብ፣ ብሎም ለከፋ እልቂት መዳረጋቸው፤ በጎረቤት ሀገራት መካከል ከመተባበር ይልቅ መጠራጠርን፣ ከመተባበር ይልቅ መገፋፋትን እንዲያስቀድሙ ሆነው እንዲሳሉ ያደረጋቸውም ይሄው ፍላጎት የወለደው የቀጥታም፣ የእጅ አዙር ተፅዕኖ ስለመሆኑ ብዙ ማረጋገጫ አለ።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም ከትናንት ጀምሮ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍላለች። አሁንም ድረስ እየከፈለች ትገኛለች። ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ነፃ እና ቅኝ እንዳልተገዛች ሉዓላዊት ሀገር በችግር ውስጥ ከመዳከር ይልቅ፤ ለራሷም፣ ለቀጣናውም የተሻለ ነገርን ከማሰብና ያሰበችውን ከመተግበር ወደኋላ ብላ አታውቅም። እናም ቀጣናውን ከመነጣጠል ወደ መተባበር፤ ከመጋጨት ወደ መወያየትና መደራደር፤ በድህነት ውስጥ ከመዳከር የጋራ አቅምን አሰባስቦ በጋራ ሠርቶ ወደ መበልጸግ ለማሸጋገር ከፍ ያለ ሥራን እያከናወነች ትገኛለች።

ይሄ ተግባሯ ደግሞ የቀጣናውን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኅብረት በ2063 አሳካዋለሁ ብሎ ያስቀመጠውን ግብ እውን እንዲያደርግ የሚያስችለው ነው። ለምሳሌ፣ ሠላምና ፀጥታ አንዱ የኅብረቱም፣ የኢትዮጵያም ትኩረት ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የራሷን ሠላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ ባሻገር፤ የጎረቤት ሀገራትን ሠላምና ደህንነት የሚያስጠብቁ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች፤ እያከናወነችም ትገኛለች።

ለአብነትም፣ ትናንት በሶማሊያ እና ሱዳን ያለውን የሠላም ችግር ለማቃለል ሠራዊቷን በየአካባቢዎቹ አሰማርታ ለሠላማቸው ተግታለች፤ ዛሬም በዛው ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ከመፍታት አኳያም ቀደም ሲል አደራድራ ሠላምን አውርዳለች፤ ዛሬም ያለውን ጦርነት ከማስቆም አኳያ በገለልተኝነት እየሠራች ትገኛለች።

ከልማትና አብሮ ከመበልጸግ አኳያም፣ ቀጣናውን በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር ዓላማን ወጥና ከፍ ባለ ቁርጠኝነት እየተገበረች ትገኛለች። ከጎረቤት ሀገራት ጋር በየብስም በአየርም መሠረተ ልማት ተሳስራለች። በዚህም፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳንና ሌሎችም ጋር በተሽከርካሪም፣ በባቡርም፣ በአየርም የተሳሰረችባቸውን ሁነቶች መመልከት ይቻላል።

ከዚህ ባሻገር በንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፤ በኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር እና ሌሎችም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ፤ የቀጣናውን አብሮነትና ትብብር በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ አተኩራ እየሠራች ትገኛለች። በቅርቡም የባሕር በር የማግኘት እና ቀጣናው ያለውን አቅም አዋጥቶ በጋራ መልማትና መበልፀግ የሚችልበትን አግባብ ነድፋ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደረገችበት ጉዳይም የዚሁ አንድ አካል ነው።

ከሰሞኑ የተሰማው፣ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለውን ትብብር ከፍ የሚያደርግ የመንገድ መሠረተ ልማት ትግበራን እውን የማድረግ አጀንዳም፤ የዚሁ ቀጣናውን የማስተባበር እና ከችግሩ የተሻገረ እሳቤና አቅም የማላበስ መንገዷ ማሳያ ነው። ይሄ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኝ የ220 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታን የሚመለከት ሲሆን፤ ይሄንን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በሁለቱ ሀገራት መካከል እ.አ.አ. ግንቦት 2023፣ የ738 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈጽሞ ነበር። ከሰሞኑም፣ የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ሕግ አውጪ ምክር ቤት የዚህን ድንበር ተሻጋሪ መንገድ ግንባታ የገንዘብ ስምምነት አፅድቆታል።

ይሄን መሰሉ ርምጃ ደግሞ፣ የሁለቱ ሀገራት ትብብርና አብሮ የመልማት ፍላጎት መገለጫ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው እውን እንዲሆን የምትሻው የተባበረ እና በመተማመን ላይ የተመሠረተ የጋራ ብልጽፅግና እውን የመሆን መልካም ጅማሮ ነው።

ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በሰው ኃይል አቅም እና በወታደራዊ ቁመና ግንባታ፣ በመሠረተ ልማት ትስስር፣ በሠላምና ደኅንነት እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ አቅምን ደምሮ ቀጣናውን ከትርምስና ድኅነት ይልቅ፤ ወደ ትብብር፣ ሠላምና ብልጽግና የማሸጋገር መልካም እሳቤ ፍሬ እያፈራ ስለመሆኑ አመላካች ነው። ለአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ መሳካትም መሠረት ነው!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You