ሩሲያ 36 የዩክሬን ድሮኖችን መትቼ ጣልኩ አለች

የሩሲያ አየር መከላከያ ሥርዓት ዩክሬን ወደ በበርካታ የሩሲያ ግዛቶች ያበረረቻቸውን 36 ድሮኖች መትታ መጣሏን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡

15ቱ ድሮኖች ከዩክሬን ጋር በምትዋሰነው የኩርስክ ግዛት ተመትተው የወደቁ ሲሆን ዘጠኙ ደግሞ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቀው በደቡባዊ ሞስኮ ሌፕሴክ ግዛት መመታታቸውን ሚኒስቴሩ በቴሌግራም ገጹ ገልጿል።

እያንዳንዳቸው አራት ድሮኖች ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ በሚገኙት ቮሮኖዝ እና ብሪያንስክ ግዛቶች ተመትተው ሲወድቁ በቅርብ ባሉት ኦርዮል እና ቤልጎሮድ ግዛቶች ደግሞ በእያንዳንዳቸው ሁለት ድሮኖች ወድመዋል፡፡

የሊፕሴክ እና ብሪያንስክ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን በቴሌግራም ገጻቸው አስፍረዋል።

የሩሲያ ባለሥልጣናት በዩክሬን ጥቃት የሚደርሰውን ጉዳት ብዙውን ጊዜ ሙሉ በሙሉ ይፋ አያደርጉም። ኪቭ በሩሲያ ትራንስፖርት፣ ወታደራዊ እና የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እያደረሰች ያለችው፣ ሞስኮ በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ጀምሮ በዩክሬን ግዛት ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ነው።

ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” አሁንም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው። ሩሲያ ከወራት በፊት በምስራቅ ዩክሬን በዶኔስክ ግዛት ወሳኝ የተባለችውን አቭዲቪካ ከተማን እና በርካታ መንደሮችን መቆጣጠር መቻሏ ይታወሳል።

ዩክሬን እነዚህን ቦታዎች ለቃ የወጣችው የምዕራባውያን ወታደራዊ ርዳታዎች በወቅቱ ባለመድረሳቸው ነው የሚል ምክንያት ሰጥታ ነበር።

ሩሲያ፣ ዩክሬን በተከታታይ የከባድ መሣሪያ እና የድሮን ጥቃት የምትሰነዝርባትን በድንበር አካባቢ የምትገኘውን ቤልጎሮድን ለመከላከል በዩክሬኗ ካርኪቭ ግዛት በቅርቡ ያልተጠበቀ ጥቃት ፈጽማለች።

በዚህ ጥቃት ሩሲያ በካርኪብ ግዛት ያሉ በርካታ መንደሮችን ተቆጣጥራለች። ይህን ተከትሎ ምዕራባውያን ሀገራት ዩክሬን በለገሷት መሣሪያዎች ሩሲያ ውስጥ ያለ ኢላማ እንድትመታ ፈቅደውላታል። ሩሲያ ይህን የምዕራባውያንን ውሳኔ “በእሳት መጫወት” ነው ስትል መግለጿ ይታወሳል ሲል የዘገበው አል ዓይን ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You