ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ መሪነት እየተመሠረተ ያለውን “የእስያ ኔቶ” በዋዛ አልመለከተውም አለች

ሰሜን ኮሪያ፤ አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር “የእስያ ኔቶ”ን የመሰለ ወታደራዊ ጥምረት እየመሠረተች ነው ስትል ወቀሰች።

ሶስቱ ሀገራት የጀመሩት ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ሀገራቱ ትብብራቸው እያደገ መሄዱን አመላካች መሆኑንም ነው የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘገበው።

አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ከሃሙስ ጀምሮ “የነጻነት ጥግ” የሚል ስያሜ የሰጡትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ ነው።

የአሜሪካን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ (ቲወዶር ሩዝቬልት)ን ጨምሮ የጦር አውሮፕላኖች እና መርከቦችን ያካተተው የጦር ልምምድ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፒዮንግያንግ ጉብኝት ባደረጉ ማግሥት ነው የተጀመረው።

ሶስቱ ሀገራት የሰሜን ኮሪያን የኒዩክሌር ፕሮግራምና የማያቋርጥ የሚሳኤል ሙከራ በጋራ ለማስቆም ባለፈው ዓመት በሜሪላንድ ካምፕ ዴቪድ ስምምነት ከደረሱ በኋላ ትብብራቸው ተጠናክሯል።

የሀገራቱን ወታደራዊ ልምምድ እንደ ጦርነት ዝግጅት የምትቆጥረው ፒዮንግያንግ አሜሪካ መራሹን የሶስትዮሽ ወታደራዊ ጥምረቱን በዋዛ እንደማትመለከተው ነው ያስታወቀችው።

ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ሬውተርስ እንዳስነበበው ሰሜን ኮሪያ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ያባብሳል ያለችውን የሶስትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ለመግታት “ከባድ ርምጃ” እወስዳለሁ ብላለች።

አሜሪካ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓንን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አካል የማስመሰል ሙከራዋንም ኮንናለች።

ለዚህም ለአብነት ያነሳችው ደቡብ ኮሪያ ወደ ዩክሬን የጦር መሣሪያዎችን እልካለሁ የማለቷን ጉዳይ ነው።

ሴኡል በቅርቡ ወደ ኬቭ የጦር መሣሪያዎችን እንደምትልክ የዛተችው የፒዮንግያንግና ሞስኮ “ጠላትሽ ጠላቴ ነው” ወታደራዊ ትብብር አሳስቦኛል በሚል ነበር።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የተፈራረሙትን የወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ በሴኡል የሚገኙትን የሩሲያ አምባሳደር መጥራቷ ይታወሳል።

ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ፒዮንግያንግ በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችን ለሩሲያ እንደምትልክ ይገልጻሉ።

ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ደጋግመው ውድቅ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You