ቴክኒክና ሙያ በፋሽን ኢንዱስትሪው

ባሳለፍነው ሳምንት 14ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሮ አልፏል። በዚህ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የተውጣጡ ተማሪዎች እና አሰልጣኞች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን አሳይተዋል። በተለይም የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች በስፋት የቀረቡ ሲሆን፤ የፋሽን ሾው ውድድርም ተካሂዷል። እኛም የፋሽን ውድድሩን በመታደም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አቶ ሰለሞን እሸቱ በኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ውስጥ የፋሽን ዲዛይን አሰልጣኝና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ነው። በ14ተኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ‹‹ሙያ እና ክህሎት ለልማት በሚል መሪ ቃል›› በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ በኮሌጁ የሚገኙ የትምህርት ክፍሉ አሰልጣኞች እና የፋሽንና ዲዛይን ተማሪዎች የየራሳቸውን ሥራ ይዘው ቀርበዋል።

በቴክኒክና ሙያ ሳምንቱ የኮሌጁ የፋሽንና ዲዛይን ትምህርት ክፍል ይዘው የቀረቡትንም ሥራ ‹‹ውብ ሀገር ክታቴ›› የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ክታቴ የሚለው ቃል ትርጓሜውም ተዘርቶ የነበረን እህል ወይንም ተበታትኖ የነበረን ሰው መሰብሰብ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት እየተደረገ የሚገኘውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማሳያም ነው። የፋሽን ዲዛይን ስራዎቻቸው እንዲሁ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን በመጠቀም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ አልባሳትን በመድረኩ ይዘው ቀርበዋል።

የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የተለያዩ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን፤ የፋሽን ዲዛይን ትምህርትንም ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ድረስ ስልጠናውን ይሰጣል። በትምህርቱ ወቅት ከስዕል እና ንድፍ ከማውጣት ጀምሮ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን በመጠቀም ስፌት ወይም የተለያዩ ልብሶችን በመስራት የራሳቸውን ዲዛይን እንዲፈጥሩ በማድረግ ተማሪዎችን የማብቃት ስራን ይሰራል።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሁን አሁን እየተስፋፉ የመጡት የፋሽን ትምህርት ቤቶች ሳይፈጠሩ ቀደም ሲልም ነበሩ። በዘርፉም በፋሽን ኢንዱስትሪው ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች የሚሰለጥኑበት ነው። የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ የተለያዩ ሙያዎችን ለማሰልጠን የተዘጋጁ እንደመሆናቸው በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ።

የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅም ወደዚህ የትምህርት ክፍል መቀላቀል ለሚፈልጉ ተማሪዎች በሩን ክፍት ከማድረግ ባሻገር በተለያየ መንገድ መረጃው ማህበረሰቡ ጋር እንዲደርስ ያደርጋል። የቴክኒክና ሙያ ሳምንትን የመሳሰሉ እና ሌሎች የፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ያተኮሩ ዝግጅቶች ላይም የራሱን ስራ ይዞ ይቀርባል።

በ14ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ላይ የራሳቸውን ስራዎች ይዘው የቀረቡ ሲሆን፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የባህል አልባሳት ታሪክን የሚገልጹ የልብስ ዲዛይኖችን ይዘው ቀርበዋል። ‹‹የተነሳንበት ሃሳብ ውብ ሀገር ነው። ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ናት በዚህ መድረክ ግን የተወሰኑትን መርጠን የተለያዩ የባህል አልባሳትን ይዘን ቀርበናል›› የሚለው አሰልጣኙ፤ እንደዚህ አይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው ዘርፉን ከማሳደግ አንጻር ኮሌጁ የሚኖረውን ተደራሽነት ያሰፋል። ከዚህም ባለፈ እየሰራ ያለው ስራ እንዲታወቅ ያስችለዋል ያለው አሰልጣኙ፤ የፋሽን እና ዲዛይን ዘርፍ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ መሰጠቱ ያለውን ፋይዳ ሲያስረዳም ‹‹ሀገራችን በሽመና እና በተለያዩ በሽመና ፈትል ፣ ጥልፍ የታወቀች ሀገር ናት፤ ምናልባት ዘመናዊ እና ወቅቱን የጠበቀ በማድረግ ክፍተቶች ይኖራሉ። የኛም ልብስ የሚያተኩረው ዘመናዊ በሆነ መንገድ ሲሆን፤ የሀገር ልብሶችን በመስራት በየዕለቱ መለበስ የሚችል እንዲሆን ማድረግ ነው።›› በዚህም ተቋሙ በሚሰጣቸው ስልጠናዎች ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ማፍራት መቻሉን አስረድቷል።

ወደ ማሰልጠኛ ተቋሙ መጥተው ስልጠናውን የሚወስዱ የፋሽን እና ዲዛይን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲጨርሱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የመስራት አልያም ደግሞ የራሳቸውን ድርጅት በመክፈት ወደ ስራ ላይ ይሰማራሉ። በየአመቱ ከፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ በተጨማሪ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ስልጠናቸውን ወስደው ይመረቃሉ ወደ ስራም ይሰማራሉ። ነገር ግን የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በሀገራችን የሰሩትን ያክል የተመሰገኑ አይደሉም። ሲል አሰልጣኙ ያነሳል። ‹‹የተለያዩ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ ውስጥ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ገብተው ስልጠና ቢወስዱ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መትረፍ ይችላሉ። እንዲሁም በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ በግላቸው የተሰማሩ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ መድረኮችን የሚያዘጋጁ ሲሆን፤ ኢንዱስትሪው ላይ ያተኮሩ እነዚህን የመሳሰሉ መድረኮች በተደጋጋሚ ቢዘጋጁ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ይረዳል››ሲል ይናገራል።

በ14ተኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ስራዎችን ይዘው የቀረቡት የደረጃ ሶስት እና አራት ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ኮሌጁ ስልጠናውን በሚሰጥበት ወቅት በሀገራቸው ውስጥ የሚገኙ ሀብቶችን ተጠቅመው እንዲሰሩ ያበረታታል። በማለት ትምህርታቸውን ሲጨርሱ እንደቴክኒክና ሙያ ተቋም የትብብር ስልጠና በሚለው መርሀ ግብር ወደ ውጭ ወጥተው ከገበያው ጋር እንዲተዋወቁ ይደረጋልም ብለዋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You