ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሰኔ ዘጠኝ በሚባል ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አብዮት ቅርስ ተምረዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቁት በቅርስ አስተዳደር ትምህርት ነው፡፡
በቢዝነስ ሥራ አመራርና በዓለም አቀፍ ግንኙነት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ተከታትለዋል፡፡ ደቡብ ክልል ውስጥ ደራዊት በምትባል የገጠር አካባቢ የተወለዱት የዛሬው እንግዳችን ለቤተሰባቸው አራተኛ እና መንታ ሆነው ቤተሰቡን ከተቀላቀሉት አንዱ ናቸው፡፡ መንታ ወንድማቸው ሀገርን በህግ ሙያ በኃላፊነት ሲያገለግሉ እርሳቸው ባለሙያዎችን እያፈራ ያለውን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ተቋምን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡
«ድርና ማግ›› በሚል ርዕስ በ2011 ዓ.ም ያሳተሙት እና ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርስ በሚያስተሳስሩ የጋራ እሴቶች ዙሪያ የሚያጠነጥነው እና በ2008 ዓ.ም የታተመውን በአረቡ ዓለም የተከሰተውን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚቃኘውን ‹‹የአረቦችን ጸደይ›› መጽሐፎችን ለአንባብያን አበርክተዋል፡፡ የዛሬው እንግዳችን ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ከእንግዳው ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው ተጠናክሮ ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን:- ቴክኒክና ሙያ ትምህርት በኢትዮጵያ ያለው ታሪክ ምን ይመስላል (አጀማመሩ፣ ሂደቱ አሁን እስከደረሰበት) ?
ብሩክ (ዶ/ር):– ቴክኒክና ሙያ ትምህርት በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ አለው። በተለይም ከዘመናዊ ኢትዮጵያ ምስረታ ጀምሮ ከወሰድን ዘርፉ የመንግሥት ትኩረት መሆን የጀመረው ዘመናዊ ትምህርት መምጣትን ተከትሎ በ1905 ዓ.ም በወጣው አዋጅ ነው። ይህ አዋጅ ልጆች የአንድ ሙያ ባለቤት ሆነው መውጣት አለባቸው የሚል ድንጋጌን አውጇል። መደበኛ ትምህርት ከታወጀ በኋላ በብዛት የምናገኘው እንደመደበኛ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ከወሰድነው የአሰለጣጠን ሥርዓት የጀመረው ከሚሽነሪዎች መምጣት ጋር ተያይዞ ነው። ሚሽነሪዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሙያ ማሰልጠኛ ማእከላት ለመገንባት ጥረት አድርገዋል። ከእዛ በኋላ በነበረውም የጣሊያን የአምስት ዓመታት ጊዜ አንዳንድ የቴክኒክ ስልጠናዎችን የሚሰጡ ተቋማትን እዛም እዚህም ለመገንባት ጥረት ተደርጓል። ከእነርሱ መውጣት ከ1930ዎቹና 40ዎቹ በኋላ በርካታ ተቋማት ለመመስረት ጥረት ተደርጓል።
የቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ መንግሥት የቴክኒክ እና ሙያን ጉዳይ ጉዳይ ብሎ የያዘበት ወቅት ከተግባረ ዕድ መመስረት ጋር ይያያዛል። ተግባረዕድ 1942 ዓ.ም ሙያን ቴክኒክን ለማሰልጠን በሚል ዓላማ የተቋቋመ ነው። በወቅቱም የአስመራ ቴክኒክ ትምህርት ቤት የሚባልም ነበር። ወደ 1950ዎቹ ስንመጣም የተወሰኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን እዛም እዚህም ለማቋቋም ጥረት ተደርጓል።
በ1970ዎቹ ስንመለከትም ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በሀገር በቀር ማህበረሰብ ተኮር የስልጠና ተኮር መስኮች ላይ በማተኮር የቴክኒክ ትምህርቶች ይሰጡ ነበር። በኋላ ግን በፖሊሲ መልክ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በፖሊሲ ግልጽ አቅጣጫ ተቀምጦለት 1986 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ባግባቡ ትርጉም ሰጥቶታል። ከዛም በኋላ እ.አ.አ 2001 ቴክኒክና ሙያን የሚያስተባብር የሚኒስቴር መስሪያ ቤት በዴኤታ ደረጃ ተሰይሟል። ከእዛ በፊት በፕሮግራሞች፣ በዳይሬክቶሬትና መሰል የነበረው በዴኤታ ደረጃ ጭምር እውቅና ተሰጥቶታል።
በመቀጠልም የቴክኒክና ሙያ አዋጅ፣ ህጎች፣ ፖሊሲ የበለጠ እየተብራራ የወጣበት ሁኔታ ይታያል። የቲቬት ካውንስል የመመስረት ሥራ፣ የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ በሂደትም 2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ እየተመራችበት ያለው የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ ጸድቆ ሥራ ላይ ውሏል። ይህንን ተከትሎም የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተደርጓል። ላለፉት 100 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶት ጉዳዩን ከያዘው በኋላ ያለው እድገት እስካሁን እስከደረስንበት እነዚህን ደረጃዎች ያለፈ ነው፡፡
አዲስ ዘመን :- በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ተሰጥቶት የነበረው ትኩረት እንዴት ይገለጻል?
ብሩክ (ዶ/ር):- በተለያዩ የመንግሥታት ሥርዓት ወቅቶች ለቴክኒክና ሙያ ዘርፎች የተለያየ ትኩረት ሲሰጥ ቆይቷል። በየጊዜው በነበሩ የመንግሥት እይታዎች ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተለያየ የትኩረት ደረጃ ነበረው። ትምህርት ቤቶቹን የመክፈት፣ ስልጠናዎችን የመስጠት ቀደም ሲልም ሙከራዎች ነበሩ። ነገር ግን ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው በተለይም ከአምስት ዓመታት ወዲህ ባለው ጊዜ ነው። አሁን ያለው የለውጥ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያን ዘርፍ ጎላ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ ትልቅ እንቅስቃሴ አድርጓል። ለዚህ ማሳያዎች አሉ። አንዱ ማሳያ ቴክኒክና ሙያን የሚያስተባብር ራሱን የቻለ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተቋቁሟል። የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን እንደሚኒስትሪ ማቋቋም መቻሉ የሚያሳየው ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ነው።
በተለያዩ የመንግሥታት ሥርዓቶች ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እንደተጠበቀ ሆኖ ያመጣቸው ለውጦችም እንዳሉ ሆነው ግን በተለይም አሁን ያለው የለውጥ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያን የድህነት መውጫ መንገድ ነው የሚለውን አደረጃጀት ከመፍጠር ጀምሮ የቅርብ ክትትል፣ ድጋፍ እስከ ማድረግ ድረስ ትኩረት እያገኘ ያለ ዘርፍ ነው።
አዲስ ዘመን:- ሙያና ሙያተኞች ሀገራዊና ሕዝባዊ ፋይዳቸው እንዴት ይገለጻል፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮውስ ምን ይመስላል ?
ብሩክ (ዶ/ር):– የቴክኒክ እና ሙያ ጉዳይን አጥብቀው በያዙ ሀገራት የቴክኖሎጂ ልማት ሥራ ስኬታማ ነው። የድህነት እና የሥራ አጥ ምጣኔ ዝቅተኛ ነው። በዚህ ምክንያትም የዳበረ ኢኮኖሚ ለመገንባት የቻሉ ሀገራት ተፈጥረዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰደው የጀርመን ነው።
የጀርመን ቴክኒክና ሙያ ረጅም ጊዜ የዳበረ ልምድ ያለው ነው። ዛሬ ላይ ጀርመን ከአምስት በመቶ ያላለፈ ምጣኔ ነው ያላት። ምክንያቱ ደግሞ ቴክኒክና ሙያን ሙጥኝ ብላ በመያዟ ነው። የቴክኒክና ሙያ ሥርዓታቸውም ባለሁለት ሥርዓት በመባል የሚታወቅ ነው። የገነቡት ሥርዓት አንድ ሰው ወደቴክኒክና ሙያ ሲገባ መጀመሪያ የአንድ ኩባንያ ተቀጣሪ ሆኖ የተወሰነ ጊዜውን ደግሞ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያሳልፍበት ነው።
በመሆኑም ኢንዱስትሪዎቻቸው፣ የማሰልጠኛ ተቋማት፣ የመንግሥት ሚና አላቸው። እንደጀርመን ባሉ ሀገራት ሁሉም ተባብረው አንድን ዜጋ ለመቅረጽ ይረባረባሉ። ሲንጋፖርን በአብነት ብናነሳ ቴክኒክና ሙያን በመጠቀሟ ምክንያት የክህሎት ሥራ ላይ በማተኮሯ ምክንያት ባለፉ 40 ዓመታት ከነበረችበት የከፋ ድህነት ወጥታ ምሳሌ መሆን ችላለች። በወቅቱ ሲንጋፖርን ይመራ የነበረው የሲንጋፖር አባት በመባል የሚታወቀው ሊኩዋን የሚባል መሪያቸው ያለን ሀብት የተፈጥሮ ሀብት አይደለም፣ ውሃ ከማሌዥያ በፓይፕ እየቀዳን ነው፣ ሀብታችን የሰው ልጅ ነው ብለው ሰው ላይ በመስራታቸው በቁጥር አምስት ስድስት ሚሊዮን አካባቢ የሚገመት ሕዝብ ከሀገሩ በላይ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ የሌሎች ሀገራት ሕዝቦችን አቅፎ የዓለም አራተኛ ሀብታም ሀገር መገንባት የቻሉት ቴክኒክና ሙያ ላይ ስለሰሩ ነው።
ሌላው ዓለም ላይ ያለው የቴክኒክና ሙያ ልምድ ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት፣ የቴክኖሎጂ ሥራን ለመሥራትና የበለጸገ ኢኮኖሚ ለመገንባት አቅም መፍጠር የሚችል ዘርፍ ሆኖ አገልግሏል፤ በማገልገልም ላይ ነው።
አዲስ ዘመን:- እንደ ሀገር ስንከተለው በነበረው የትምህርት ፖሊሲ ምክንያት ወደቴክኒክና ሙያ ትምህርት የሚገቡ ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል ወደ መሰናዶ ማለፍ ያልቻሉ ነበሩ። ይህ የፈጠረው አሉታዊ ገጽታ አለ ። ይሄንን ገጽታ ለመቀየር የተሄደበት ርቀት ምን ይመስላል?
ብሩክ (ዶ/ር):- የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አንዱ ፈተና የተሳሳተ ምስል በማህበረሰቡ ውስጥ መዳበሩ ነው። ማህበረሰቡ ቴክኒክና ሙያን እንደሁለተኛ አማራጭ ነው የሚያየው። የወደቀ ሰው መሰባሰቢያ አድርጎ ነው የሚመለከተው። ነገር ግን ቴክኒክና ሙያ የዜጎች ሕይወት የሚቀየርበት፣ እጃቸው የሚፍታታበት፣ በቀላሉ ባገኙት ስልጠና ተመስርተው ወደኢኮኖሚ ገብተው ሕይወታቸውን የሚያሻሽሉበት መስክ ነው። መደበኛው ትምህርት የማሰላሰል አቅም ሊጨምር ይችላል፤ ንድፈሃሳባዊ አቅም ሊጨምር ይችላል፤ ያስፈልጋልም።
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ክህሎት አግኝተው ወደሚፈለገው የሙያ መስኮች እንዲሰማሩ ማድረግ ያስችላል። ነገር ግን ይህንን መገንዘብ ላይ ገና ባለመሰራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሙያ፣ ለቴክኒክ ጉዳይ ያለን ምስል በጣም የተዛባ ነው። በዚህ ምክንያት የአንድን ሙያ ባለቤት ያከበረ እሳቤ አልዳበረም። የብረት ሰራተኛን ቀጥቃጭ ብለን ነው የኖርነው፣ ለሸክላ ሥራ ባለሙያን ስም ሰጥተን ስናንጓጥጥ ከርመናል፣ ማህበረሰባችን አንጥረኛ ቀጥቃጭ ሲል ነው የከረመው።
የእንጨት ሙያን ሰርቶ በእንጨት ጥበብ ሕይወቱን የሚያሻሽልን ሰው ማህበረሰቡ ክብር አይሰጠውም። በሥራ መስክ የተሰማራ አድርጎ አያስበውም። በዚህ ምክንያት ለእነዚህ ሙያዎች የምንሰጠው ምስል የተሳሳተ ነው። ነገር ግን በሌላው ዓለም አንድ አናጺ፣ የኤሌክትሪክ፣ የብረት ባለሙያ የሚያገኘው ከበሬታ ከፍተኛ ነው። የጠነከረ ማህበራዊ ግንኙነት አለው፣ በትዳር ግንኙነትም ተፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን:- አሁን በተሻሻለው የሀገሪቷ ፖሊሲም ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችለውን የመቁረጫ ነጥብ ያላሟሉ ተማሪዎች ናቸው ወደ ዘርፉ እየገቡ ያሉት። ይሄስ ምን ያህል ከቀደመው አካሄድ ተላቋል ማለት ይቻላል?
ብሩክ (ዶ/ር):- ከቀደመው አሰራር በተለይ የአሁኑ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ክፍት ያደረጋቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ቴክኒክና ሙያ ራሱ እስከ ከፍተኛ የአሰለጣጠን ደረጃ እንዲያድግ በሩን ክፍት አድርጎታል። በዚህ መሰረት አሁን ያለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እስከ ስምንት ደረጃ ድረስ አድጓል። ይህ ማለት ዜጎች እስከ ደረጃ አምስት አድቫንስድ ዲፕሎማ ከደረሱ በኋላ ቀደም ሲል ዝግ ነበር። ዝግ የነበረውን ደረጃ የአሁኑ ፖሊሲ ክፍት አድርጎታል። ደረጃ ስድስት በሌላ አጠራር የዲግሪ፣ ደረጃ ሰባት በሌላ አጠራር የማስተርስ ዲግሪ፣ ደረጃ ስምንት ወደ ተርሚናል ወይም የፒኤችዲ ዲግሪ ሆኖ እንዲቀረጽ ተደርጓል። እስከ ከፍተኛው የአሰለጣጠን ደረጃ መድረስ ይቻላል።
ለምሳሌ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ከተሰጡት ስራዎች መካከል አንዱ ከደረጃ ስድስት በላይ የሰለጠኑትን እና ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡትን ያሰለጥናል። የወደቁ ናቸው የሚባለውም ቢሆን 12ኛ ክፍል አጠናቅቀው ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ዜጎች በቀጥታ ይህንን ተቋም መቀላቀል ይችላሉ። እንደውም አንድ ዙር አስመርቀናል። በአሁኑ የገቡም 300 ሰልጣኞች አሉ። እነርሱን ለኢንደስትሪው እያዘጋጀናቸው ነው።
የወደቀ ነው የሚሰባሰብበት የሚባለው ነገር እየተቀረፈ፣ እየተስተካከለ በሩ ዝግ የነበረው ማደጊያ መሰላሉ ክፍት እየሆነ መጥቷል። አምና የዩኒቨርሲቲ የማለፍ ምጣኔ ሶስት በመቶ ገደማ ነበር። በተቃራኒው ግን ቴክኒክና ሙያ ላይ ከሶስት ሚሊዮን ዜጎች በላይ እየተማሩ ይገኛሉ።
እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ በዲግሪ ደረጃ ማስተማር ተጀምሯል። በሁለተኛ ዲግሪም እያስተማርን እንገኛለን። በቀጣይ የፒኤችዲ (የሶስተኛ ዲግሪ) መርሀ ግብር ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል። ሰልጣኞች ከሁሉም ክልሎች ተመልምለው ሰልጥነው ይወጣሉ። በተቋማችን ተምረው የሚወጡ ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ መምህራን ይሆናሉ፤ የቴክኒክና ሙያ አመራር ትምህርት ክፍል የተማሩት ደግሞ መሪዎች ይሆናሉ፣ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑትም ቴክኒሽያኖች ይሆናሉ። በኢትዮጵያ በሚገኙ 15 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ማለትም ባህር ዳር ፖሊቴክኒክ፣ ተግባረዕድ፣ ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ ጅግጅጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ኢትዮ ኢጣሊያ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ድሬዳዋ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ አሰላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ ሆለታ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ ውቅሮ፣ አዲግራት፣ ማይጨውና በመሳሰሉት ኮሌጆች እየተተገበረ የሚገኝ ነው።
አዲስ ዘመን :- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ከገበያ ፍላጎት ጋር የሚለዋወጥ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር ስልጠናዎቻችሁ ምን ያህል ገበያ ተኮር ናቸው ?
ብሩክ (ዶ/ር) :- የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ገበያ መር እና ገበያ ላይ መሰረት ያደረገ የአሰለጣጠን ሥርዓትን መከተል አለበት። ይሄ በመደበኛም በአጫጭር ስልጠናም ነው የሚተገበረው። በመደበኛ ስልጠና እስካሁን የቀረጽናቸው መርሀ ግብሮች የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ በየጊዜው ይደረጋል።
አዳዲስ መርሀ ግብሮች ሲከፈቱ በቅርብ ምሳሌ ባነሳልህ ፋሽን ቴክኖሎጂ አዳጊ ዘርፍ ነው። ገበያው ይህንን ዘርፍ ስለሚፈልገው በተቋማችን ከፍተናል። ወደፊት የምንከፍታቸው ዘርፎች አሉ። ገበያውን መሰረት በማድረግ በመደበኛም በአጫጭር የሥልጠና መስኮች ላይም አዳዲስ መርሀ ግብሮች መክፈት ተግባራዊ እየተደረገ ነው። 22 መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ 19 መስኮች ደግሞ በማስተርስ ዲግሪ ይሰጣሉ።
ገበያን መሰረት ባደረገ መንገድ የስልጠና መስኮች ላይ ጥናት ይደረጋል፣ ሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ይደረጋል፣ የተከፈቱ አሉ፣ የሚከፈቱም የትምህርት ክፍሎች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን:- ቀጣሪ ተቋማትና ባለ ሀብቶች ከዚህ ዘርፍ የሚወጡ ሰልጣኞችን ተቀብሎ የመቅጠርና የማሰራት ፍላጎ ታቸውና ዝግጁነታቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ይታወቃል። ይሄንን በአሰራር ለመፍታት የሄዳችሁበት ርቀት ካለ ቢገለጽ?
ብሩክ (ዶ/ር) :– በተወሰነ መልኩ እውነትነት አለው። በሀገራችን የግሉ ዘርፍ አጭር ዕድሜ ያለው ነው። ከቴክኒክና ሙያ የሚወጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ፣ በተግባር አሰልጥኖ መቅጠር ላይ ልምምዱ መጠንከር አለበት። ነገር ግን የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ቀጣሪ ነው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ብዙ ተማሪዎችን ከቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ ይቀበላሉ። አንዳንድ መስኮች ለምሳሌ የቱሪዝም ዘርፍ በምረቃ ቀናቸው አብዛኞቹ ተማሪዎች ተቀጥረዋል። አንዳንድ ዘርፍ ደግሞ ከኩባንያዎቹ ጋር ተቀራርበን በመስራት ያሉትን ችግሮች መቅረፍ ይጠበቅብናል፡፡
ሆኖም ኢንዱስትሪው ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚወጡትን መቀበል ላይ በየጊዜው መሻሻሎች አሉት። ከተቋማቱ የሚወጡትን ባለሙያዎችን አምኖ ማሽን እንዲያንቀሳቅሱ በማድረግ በቂ አመኔታ ያለመፍጠርም ችግር አለ። ከቦታ ቦታ ልዩነት ስላለው የኩባንያ ባለቤቶች ብቁ ባለሙያዎችን እንዲያፈሩ በማድረግ ረገድ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- የስልጠና ተቋማቱ (ኮሌጆቹ) ምን ያህል በግብአት እና በቴክኖሎጂ የተጠናከሩና ተወዳዳሪ ናቸው ?
ብሩክ (ዶ/ር) :– የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የሚጠይቅ ዘርፍ ነው። ብዙ ማሽነሪዎች፣ ማሰልጠኛ መሳሪያዎች፣ የአሰልጣኝ አቅምም ይጠይቃል። በዚህ ምክንያት ቴክኒክና ሙያን በገንዘብ የመደገፍ እስትራቴጂ /ቲቬት ፋይናንሲንግ/ የተባለ አምስት አምዶች ያሉት ራሱን የቻለ ፕሮግራም አለ። መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ሚና ስለሚጫወት መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ ቴክኒክና ሙያን በገንዘብ መደገፍ አለበት የሚለው ቀዳሚው ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ፒፒፒ የሚባለው የፐብሊክ ፕራይቬት ሞዴል ነው፤ የግሉ እና የመንግሥት ዘርፉ ተቀናጅተው ቴክኒክና ሙያን ይደግፉ የሚለው ሲሆን እየተሰራበት ነው። ቲቬት ፈንድ የሚባል ፈንድም ሶስተኛው ነው። በቅርብ አዋጅ ወጥቶለታል።
በተለያየ አግባብ የሚመጡ፣ ዘርፉን ለመደገፍ የሚደረጉ የፋይናንስ ሥርዓቶችን ወደ አንድ መስመር የሚያመጣ ሥርዓት ነው። ሰልጣኙ ራሱ እንዲጋራ ድርሻ እንዲኖረው የሚደረገው በአራተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው።ራሳቸው ቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ ገቢ የሚያመነጩበት እሳቤ ነው፤ የሰው ኃይል አላቸው፣ ማሽን አላቸው ለዚህም ኢንተርፕራይዝ እንዲያቋቁሞ የሚደግፍ ነው። ማሰልጠኛ ተቋማቱ የውስጥ አቅማቸውን አጠናክረው ገቢ ፈጥረው ራሳቸውን መልሰው እንዲደጉሙ ኢንተርፕራይዝ በብዛት ወደመመስረት እየገቡ ነው። ለምሳሌ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ቴክኖ ቢዝ የተሰኘ ትልቅ ኢንተርፕራይዝ አቋቁሟል። አላማው ኢንስቲትዩቱ በተወሰኑ ዓመታት ከመንግሥት በጀት ነጻ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ብዙ ተቋማት በዚህ ተግባር ላይ ናቸው። አሰላ ፖሊ ቴክኒክን ብትመለከት የውስጥ ገቢ አቅሙን ነው፤ አዲስ አበባ እንደ ተግባረዕድ፣ ዊንጌት ያሉ ተቋማት ጥሩ ልምድ አላቸው። ከመንግሥት በጀት በሂደት ነጻ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት ነው ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ያለው። ከማሽነሪ፣ ከውስጥ ግብአት አቅም ያነሳኸው በአምስቱ አንኳር እሳቤዎች የሚመራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን:- በቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፉ ምን አስገኘ ?
ብሩክ (ዶ/ር) :- ቴክኒክና ሙያ ተቋማት አስደናቂ ከሚያደርጋቸው መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ ማሻሻል፣ ፈጠራና ማሸጋገር ላይ ሚና ያላቸው መሆናቸው ነው። ሙከራዎች አሉ። በየተቋማቱ ያሉ መምህራንና ተማሪዎች ለኮርስ ማሟያነት የሚጠቀሟቸው ቴክኖሎጂዎች፣ ማሻሻዎች ፈጠራዎች አሉ። እዛም እዚህም የሚደረጉ ሙከራዎች ግን በሀገር ደረጃ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ መሆን አለባቸው፡፡
ለምሳሌ በፌዴራል ደረጃ አንዱ የተደረገው አዲስ እሳቤ ተቋማቱ የቴክኖሎጂ አምራች ማዕከል መሆን አለባቸው በሚል እሳቤ ከሀገር አቀፍ የተውጣጡ ቴክኖሎጂስቶችን ወደ አንድ የማሰባሰብ ሥራ ተሰርቷል። በየጊዜው በሚደረጉ የክህሎት ውድድር የሚያሸንፉ ፈጣሪዎችን ከየኮሌጆቹና በየግላቸው የሚንቀሳቀሱትን በአንድ ማዕቀፍ የማደራጀት ሥርዓት ተዘርግቷል። ለምሳሌ በዚህ ተቋም ከክረምት ጀምሮ 400 በሀገር አቀፍ የተመረጡ፣ያሸነፉና ውድድር ላይ የመጨረሻ የደረሱ የፈጠራ ባለሙያዎችን አሰባስበናል። የቢዝነስ አዘገጃጀት፣ ዲዛይን ማሻሻል፣ የእርስ በእርስ ተግባቦት ስልጠና፣ የቢዝነስ ሃሳብ ፈጠራ ወደተቀራራቢ ሁኔታ ለማምጣት ተሰርቷል።
72 የሚሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን በ11 ክፍል ማለትም፤ በቱሪዝም፣ በኮንስትራክሽን፣ በማዕድን፣ በግብርና፣ በኢነርጂና በመሰል መስኮችን ኩባንያ ሆነው መውጣት የሚያስችል ስራ ተሰርቷል። በአጭር ጊዜ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሉ። ለምሳሌ ግብርና ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ አነስተኛ በእጅ የሚገፉ ትራክተሮች፣ መስኖ ሥራን የሚያሻሽሉ ሥራዎች የተሠሩ አሉ። በኢነርጂም ዘርፉን የበለጠ ሊያሻሽሉ የሚችሉ እንደባትሪ ምርት የማሻሻል ስራ መመልከት ይቻላል። ማዕድን ላይም የወርቅ ስራ ላይ ድንጋይ የሚፈልጥና ማንጠሪያ ተሰርቷል። የቱሪዝም ዘርፍ ቴክኖሎጂም መንገድ ላይ የሚገፉ የምግብ መሸጫ ጋሪ ተሰርቷል። በአይሲቲ ዘርፍ አይነስውራንን የሚመራ እንጨት፣ የድሮውን ቴክኖሎጂ ያሻሻሉ አሉ። በህክምና ዘርፍም በዘርፉ ማሻሻያ የሰሩ እናገኛለን።
የጎማ ተረፈ ምርትን በመቀየር ታይልስ ማምረት የሚቻልበት አሰራርንም የፈጠሩትን መመልከት ይቻላል። ባለሙያዎቹን ለመደገፍ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፈጠራውን ጎብኝተዋል። ዋና ችግር የሆነባቸውን የፋይናንስ ችግር ለመደገፍ ከኢትዮጵያ ልማት ጋር በመሆን በተደረገው ስር 72ቱን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለመደገፍ ፕሬዚዳንቱ ሁሉንም ፕሮጀክቶች ጎብኝተው 72 ኩባንያዎች ሆነው እንዲወጡ እናደርጋለን ብለው ቃል ገብተው እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን:- ለስልጠናው ጥራት አንዱ ግብአት የአሰልጣኞች ብቃት ወሳኝ እንደመሆኑ አቅማቸውን ለማሳደግ ምን ታከናውናላችሁ ?
ብሩክ (ዶ/ር) :- የአሰልጣኞች አቅም ለማሻሻል ዋና ዋና ስራዎችን እየሰራን ነው። ግብአትን፤ ሂደቱንና ውጤቱን ለማሻሻል ታቅዶ እየተሰራ ነው። የመጀመሪያው ፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የአሰልጣኞች ማሰልጠኛ ተቋም ነው። ከዚህ የሚወጣ ሰው በመላው ሀገሪቱ ተዟዙሮ አሰልጣኝ ይሆናል። እዚህ ተቋም ውስጥ የምንፈጥረውና የምናፈራው አሰልጣኞችን ነው። ከዚህ የሚወጡ ሰዎች በተለያዩ ሙያ ተቋማት፣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ውስጥ አሰልጣኝ ይሆናሉ።
ጥራት ያለው ስልጠና እንዲሰጥ የስልጠና ጥራት ሶስት ጉዳዮችን ታሳቢ ማድረግ አለበት፤ ግብአት፣ ሂደት እና የሚወጣው የሰው ኃይል ናቸው። ለዚህም ሲባል ግብአት ማሻሻል ላይ እያተኮርን ነው።
የማሰልጠኛ ግብአቶች በመንግሥት፣ በአጋር አካላት አቅም እያሟላን ነው። በተመረጡ የሥልጠና መስኮች ዘንድሮ እንኳን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ጥራት ያለው ስልጠና እንዲያገኙ የሚያደርግ ሰርቶ ማሳያዎችን አደራጅተናል። በአራተኛ ትውልድ በሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በተሻለ ደረጃ ሶስተኛ ዲግሪ የያዙ ለመቅጠር ጥረት ተደርጓል። ቴክኖሎጂን ለመማርና ለመቅዳት የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን በመቅጠር ጥረት ተደርጓል። በዚህ ምክንያት የአሰልጣኞች ስልጠና ጥሩ ግብአት እንዲያገኝ፣ ሂደቱም ዲጂታላይዜሽንን እንዲያካትት ተሞክሯል። ከሌሎች ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመፈራረም አሰልጣኞች ተጨማሪ እውቀት እንዲገበዩ ፣ የውጭ ልምድ በማካተት በሀገራዊ ቅኝት እንዲለውጡ ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን:- ከለውጥ በኋላ ዘርፉን ሪፎርም በማድረግ ምን ውጤት ተገኝቷል ?
ብሩክ (ዶ/ር):- ዘርፉ ራሱን ችሎ እንዲመራ መደረጉ አንዱ ከለውጡ በኋላ የመጣ ውጤት ነው። ቴክኒክና ሙያን በአዲስ እሳቤ ለመምራት ታስቦ እየተሰራ ነው። ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከያዛቸው የለውጥ እሳቤዎች መካከል ስልጠና መስጫ ተቋማት አላማቸው ከስልጠና በላይ ይሁን በሚል ‹‹ከስልጠና በላይ›› የሚባል እሳቤ መጥቷል፡፡
የማሰልጠኛ ተቋማቱ ማሰልጠኛ ብቻ ሆነው እንዳይቀሩ መደረግ አለበት፤ የሰዎችን ህይወት የሚቀይሩ ፈጠራዎች መታየት አለባቸው፡፡ ከተቋማቱ፣ የሚወጡ ዜጎችም ኢንተርፕረነር እንዲሆኑ ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ነው። ኩባንያን መፈልፈያ ለማድረግ አጫጭር ስልጠናዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡
ጸጋን መሰረት ባደረገ መንገድ የማደራጀት ስራ አዲሱ የለውጥ እሳቤ ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከ100 በላይ ፖሊ ቴክኒክ ተቋማት አሉ። እስከ 90 የሚደርሱት ጸጋን መሰረት ባደረገ መንገድ ይደራጁ ተብሎ የስልጠና መስክ ሲከፍቱ የተደረገው ጥናትን መሰረት ባደረገ መንገድ ነው። በጋራ ተቋማቱን የሚያሰባስብ የማሰባሰቢያ ካውንስል መመሰረታቸው አንዱ የለውጡ እሳቤ ነው። ዘንድሮ በቂ ልምድ ያላቸው ዜጎች የተሰባሰቡበት የቴክኒክና ሙያ ቲንክ ታንክ ግሩፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን:- የህግ ማእቀፎቹ ምን ይመስላሉ? ዘርፉን በመደገፍ በኩል አስተጽኦአቸው ምን ይመስላል ?
ብሩክ (ዶ/ር) :– በቅርብ ዓመታት ከወጡ የህግ ማዕቀፎች ውስጥ አንዱና ዋነኛ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ነው። ፖሊሲው ብዙ ሃሳቦችን አጭቆ ይዟል። ብዙ የዘርፉን ጥያቄዎችንም መልሷል። ሁለተኛው እየተጠናቀቀ የሚገኘው የስትራቴጂ ዝግጅት ነው። በፖሊሲ የተመላከቱ ነገሮች እንዲብራሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ እገዛ አለው። ከዘርፉ በርካታ ተዋናዮች መካከል ኩባንያዎችም አሉ። የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ከፍተኛ ተቋማትና ኢንዱስትሪው የሚመሩበት አዋጅ ወጥቷል። መካከለኛና የአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትን በተመለከተ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ደጋፊ ፖሊሲው ስራ ላይ ውሏል። እነዚን የህግ ማዕቀፎች ስትመለከታቸው ዘርፉን ለማሻሻል ፋይዳ እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን:- የዛሬ 10 አመትስ ዘርፉን የት እንጠብቀው ?
ብሩክ (ዶ/ር) :- ኢትዮጵያ ግልጽ የሆነ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ አላት። የብልጽግና ፍኖተ ካርታው የስ ሃይል ልማቱ ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶታል። የዛሬ 10 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በኢኮኖሚ አፍሪካ ውስጥ ሊጠቀሱ ከሚችሉ አገራት መካከል እንሆናለን። ኢኮኖሚያችን ያድጋል፣ ብዙ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከድህነት ይወጣሉ፡፡
ኢንዱስትሪን የማስፋፋት፣ ይበልጥ ኃይል የመጠቀም አቅም ያድጋል፣ ግብርና መር የሆነው ኢኮኖሚ ወደኢንዱስትሪው እየተሸጋገረ የሚሄድበት፣ የአገልግሎት ዘርፉ የድርሻውን የሚያበረክትበት ሁኔታ ይኖረዋል። የተረጋጋ፣ ምሳሌ የምትሆን ሀገር፤ በአፍሪካ በኢኮኖሚያቸው ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ ሀገራት መካከል እንሰለፋለን ተብሎ እየተሰራ ነው።
በፍኖተ ካርታው ላይ ትልቅ ሚና ያለው የሰው ሀብት ልማት ነው። የተገለጹት ሁሉ የሚሳኩት ሰው ላይ በሚደረግ የማልማት ስራ ነው። እንደኛ ነዳጅ የሌለው ሀገር አቅሙ ሰው ነው። ሰው ራሱ ነዳጅ ነው፣ የኢኮኖሚ አቅም ነው። ዘርፉም ይህንን ለማሳካት ትልቅ አቅም አለው።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ጥሩ ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
ብሩክ (ዶ/ር):- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም