ጦር አውርድ – ፈውስ አልባ ልክፍት

የሰው ልጅ አሁን ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ በበርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ኩነቶች ተፈትኗል፡፡ ከሰው ሰራሽ ፈተናዎች መካከል ጦርነት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ጦርነት ከሰው ልጅ ማህበረሰባዊ እድገት ጋር የተቆራኘ እና አብሮ የኖረ ስለመሆኑ የተለያዩ ተቋማቶች ያመላክታሉ፡፡

ጦርነት አጥፊ እና አሰቃቂ ውድመት የሚያስከትል ቢሆንም በአንጻሩ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጦርነት የገቡ ህዝቦች /ሀገራት ከጦርነቶች ብዙ ተምረው ዛሬ ላይ በብዙ መንገድ የተሻለ ሕይወት ለመምራት የቻሉበትን ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡

አውሮፓዊያን በ18 እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ካደረጓቸው ደም አፋሳሽ አብዮት ወለድ ጦርነቶች(የእርስ በርስ ጦርነት) በኋላ ኑሯቸውን ለማሸነፍ አዳዲስ አሰራሮችን እና መዋቅሮችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በዚህም ኢንዱስትሪ አብዮትን በማምጣት ኑሯቸውንም አዘምነዋል፡፡ አሁን ላይ በአውሮፓ የሚገኙ ሀገራት ብሔርን ወይም ደግሞ ሌላ መስፈርትን መሰረት አድርገው የእርስ በርስ ጦርነትን አያደርጉም፡፡ ለማድረግም ፈጽሞ አያስቡትም።

አሜሪካዊያንም ካደረጉት አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ከስህተታቸው ተምረው አዳዲስ አሰራሮችን ቀመሩ፡፡ ጦርነትን አብዝተው ተጠየፉ፡፡ በአንደኛው የአለም ጦርነት ሁኔታዎች አስገድደው የጦርነቱ ተጋባዥ ቢያደርጓቸውም እነሱ ግን ግብዣውን ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡ ሌሎች ዓለማት በጦርነቱ ኢኮኖሚያቸው አይሆኑ ሆኖ ሲደቅ አሜሪካ ግን የዓለማችን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሆና ብቅ አለች፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ከጦርነቶች መማር የሚባል ነገር ፈጽሞ አንፈልግም፡፡ የእርስ በርስ ጦርነቶችን በማቆም ችግሮቻችንን በሃሳብ ለመፍታት ፈጽሞ ዝግጁ አይደለንም፡፡ ስለእውነት ከእርስ በርስ ጦርነት ጋር የተገናኘ ፈውስ አልባ ደዌ የተጣባን ይመስላል፡፡ እንደሌሎች ሀገራት ከጦርነት ጥፋት መማር ራሳችንን ከጦርነት ማራቅ ተስኖን ዘመናት እየቆጠርን ነው።

ከግራ ከቀኝ፤ ከላይ ከታችም ካሉ ኢትዮጵያዊያን የበለጠ የጦርነትን አስከፊነት የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ዛሬም ችግሮችን በንግግር እና በምክክር ከመፍታት ይልቅ ሁሉን ነገር በጦርነት ለመፍታት ስንጥር እንታያለን፡፡ ‹‹አዞ በሞላበት ኩሬ ካልዋኘን›› ብለን ለያዥ ለገናዥ እናስቸግራለን፡፡

‹‹ጦር አውርድ!›› እንላለን፡፡ ‹‹መንገድ ሳለ በዱር በቅሎ ሳለ በግር›› እንዲሉ ሀገራችን ሁሉ ነገር ሞልቷት፤ ችግሮችን በንግግር መፍታት ሲቻል ሁልጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለመግባት እንሽቀዳደማለን፡፡ ሰለምን በርካታ አማራጮች እያሉ ጦርነትን የሁሉም አማራጭ እናደርገዋለን? እንዴት ‹‹መንገድ ሳለ በዱር በቅሎ ሳለ በግር›› እንመርጣለን? እስከመቼ ጦር አውርድ!? እስከመቼ ኢትዮጵያስ በልጆቿ ማስተዋል ማነስ ትጎሳቆል!?

‹‹ሞኝን ሁለት ጊዜ እባብ ነደፈው ፤ አንድም የእባብን ተናዳፊነት ሳያውቀው ነካክቶት ሁለትም ይህ ነው የነደፈኝ ብሎ ለሌሎች ሰዎች በእጁ ነክቶ ሲያሳይ›› አሉ፡፡ እኔ የምለው እስከመቼ ነው አንድ ጊዜ የነደፈንን እባብ ተናዳፊነት ለሰዎች ለማሳየት በእጃችን እየነካን የምናሳየው?

አሁን በሀገራችን በብዛት እየተስተዋለ ያለው ጦርነት ደግሞ ለውሽማ ሞት ፊት አይነጭለት አይነት ነው፡፡ የአንዱ ብሔር መሞት እና መጎሳቆል ለሌላው እንደምን ነው። ይባስኑ ሌሎች ብሔሮች ሌላ ጦር አውርድ የሚሉ ይመስላል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡

ጦር አውርድ የሚለውን ሃሳብ ሳነሳ አጼ ልብነ ድንግልን ያስታውሰኛል፡፡ አጼ ልብነ ድንግል በዘመነ መንግሥታቸው ጠንካራውን እና ታዋቂውን የአዳል ሱልጣን ማህፉዝ (ማኅፉድን) ገደሉ። የመንግሥታቸውን ጠንካራ ተቀናቃኝ የገደሉት ንጉሱ አስተማማኝ በሚባል ደረጃ መንበረ ስልጣናቸውን አጸኑ። በኢትዮጵያ አጼ ልብነ ድንግልን በኃይል የሚገዳደር ጠፋ። በኢትዮጵያም ሰላም፣ ጥጋብ እና ደስታ ሆነ፡፡

በዚህ ጊዜ የንጉሱ መኖሪያ ቦካን የሚባል ሀገር ነበር፡፡ ቀንን ቀን ሲወልደው አጼ ልብነ ድንግል ‹‹ጭር ሲል አልወድም፤ ጦር አውርድ!›› አሉ፡፡ በቦካን እያሉ ‹‹ጦር አውርድ›› እያሉ ከመኳንንቶቻቸው ጋር የፈርስ ጉግስ እያደረጉ የራሳቸውን መኖሪያ ግንብ በጦር ይወጉ ነበር። ከእለታት በአንድ ቀንም ችግር የበዛበት የንጉሱ መኖሪያ ግንብ ተደርምሶ በግንቡ ስር የነበሩ ነዳያኖችን ተጭኖ ገደለ፡፡ ግንቡን በጦር ሲወጉ የነበሩት ንጉሱ እና መኳንንቶቻው ‹‹ጦር አውርድ›› እያሉ መሬትንም በዱላ ይደበድቡ ነበር፡፡

ይህም አልበቃቸው ጦርነት ይመጣላቸው ዘንድ ለጣና ቂርቆስ እና ለደብረ ሊባኖስ ገዳማት አንድ አንድ ጫን (15 ማዳበሪያ) እጣን ላኩ። ለገዳማቱ አባቶችም ‹‹ጦርነት እንዲመጣ ጸሎት አድርጉልኝ›› አሉ። አባቶችም ንጉሱ የሚሰሩት ስራ ትክክል አለመሆኑን ነገሯቸው። ነገር ግን ሰሚ አልተገኘም፡፡

በመጨረሻም የለመኑትን የማይነሳ ፈጣሪ አህመድ ግራኝን አስነሳባቸው፡፡ አህመድ ግራኝ በተነሳ ጊዜ ለጦርነት ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ንጉሱ ሐረር ድረስ ሂደው ገጠሙ፡፡ ነገር ግን ተሸነፉ፡፡ ወደኋላም ሸሹ። ድል ፈጽሞ ራቃቸው ፡፡ አህመድ ግራኝ የማይቆረጠም የጠጠር ቆሎ ሆነባቸው፡፡ በሚሸሹበት ሁሉ እየተከታተለ አጠቃቸው፡፡

ከአጼ ገላውዴዎስ ቀጥሎ አጼ ሚናስ ተብሎ የነገሰውን ልጃቸውንም ማርኮ ቱርክ ሀገር ለባርነት ሸጠው፡፡ ‹‹ጦር አውርድ›› ብለው ፈጠሪን ሲለምኑ እና ሲያስለምኑ የነበሩት ንጉስ ልጆቻቸውን እንኳን ከባርነት መታደግ ሳይችሉቀሩ፡፡

ይህ ክፉ ልክፍት ተጣብቶ አለቅ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ካለፈው ጊዜ ሳይማሩ ቀርተው ዘመነ መሳፍንትን አመጡ፡፡ ከዘመነ መሳፍንት መማር የተሳናቸው ኢትዮጵያዊያን ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ዛሬ እርስ በርስ መዋጋትን ስራዬ ብለው የያዙት ይመስላሉ። አዞ በበዛበት ኩሬ መዋኘትን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡

‹‹ሀ ባሉ ተዝካር ይበሉ›› እንዲሉ ሁልጊዜም በእኛ ሀገር ጦርነት የሚነሳው ትንሽ ፊደል በጠነቆሉ ፖለቲከኛ ነን ባይ ፍርፋሪ ለቃሚዎች ነው፡፡ የጦርነት ሂደቱም ‹‹ሀብታም ለሀብታም ይጠቃቀሱ ፤ ድሃ ለድሃ ይለቃቀሱ›› እንደሚሉት ነው፡፡

በታሪክ ከዚህ የተለየ የጦርነት ሂደት አላየንም፡፡ ጦርነት ሲጀምር ከሀብታሞች ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ይሸመታል፡፡ ሲያልቅ ደግሞ ፖለቲከኛ ተጠቃቅሶ ይስማማል፤ይተቃቀፋል፡፡ ድሀ ግን ልጆቹን በጦርነት ተነጥቆ እንዲያለቀስ ይፈረድበታል፡፡ የጦርነት መጀመሪያው እና መጨረሻው ይኸው ነው፡፡

ይህ አካሄድ ፈጽሞ ትክክል አይደለም። የዴሞክራሲ ባህልን በመገንባት የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ፖለቲካችን ‹‹ከኔትወርኪንግ›› እና ከኢመደበኛ አደረጃጃት አውጥተን ተቋማዊ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ፖለቲካችን በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ ፖለቲካችን ማንኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ በጠረጴዛ ዙሪያ ላይ ተነጋግረን መፍታት እንችላለን ወደሚል መምጣት አለበት፡፡ ከመጠፋፋት እሳቤ መውጣት አለበት፡፡

የተለያየ ሃሳብ የያዙ አካላት ለአንድ ሀገር እንደሚሰሩ አምነው የተሻለ ሃሳብ ማምጣት እንጂ ፖለቲካን በብሔር እሳቤ መግዛት፣ የሀሰት ወሬ እና ትርክትን በመገንባት ወይም በአፈሙዝ የበላይነት ማመን ትክክል አይደለም፡፡

በሥራ አጋጣሚ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ክልሎችን አይቻለሁ፡፡ በሄድኩባቸው ክልሎች ሁሉ ከላይ እስከታች የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የሚያደርጉት እርብርብ፣ በከተማ እና የገጠር ቀበሌዎች እየተከናወኑ ያሉ የሌማት ቱርፋት ተግባራት እጅጉን የሚበረታቱ እና የበርካታ ወገኖችን ህይወት መቀየር የቻሉ ናቸው ፡፡

የሥራ አጥ ቁጥሩን ከመቀነስ ባሻገር የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት አንጻር ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማመን የሚከብድ ነው፡፡ ይህን እንዲሁ ለማለት ሳይሆን በተግባር ካየሁት ነው፡፡ እነዚህን ሥራዎች ክልሎች ሲያከናውኑ ብዙ የሀብት ወጪ አላደረጉም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ያልተነካ የምቅ ሀብት ባለቤቶች ናቸው ፡፡

አሁን ላይ በክልሎች የሚታዩት የልማት ስራዎች ኢትዮጵያዊያን ባላቸው እምቅ ሀብት ላይ ትንሽ እሴት መጨመር ከቻሉ ዓለምን ጉድ የሚያስብል ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ሁነኛ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ አሁን ላይ እኛ የምንፈልገው ባለን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ትንሽ እሴት ጨምሮ ችግርን የሚያጠፋ ለጨለማ ጊዜ መብራት መሆን የሚችሉ ለችግር ጊዜ ብልሃት የሚቀምሩ ፖለቲከኞችን ነው፡፡

እነዚህ ፖለቲከኞች በተግባር የታሪካዊ ቁስ አካል (historical materialism) ሳይንሳዊ ፍልስፍና በውል የተረዱ፣ ስለአንድ ህዝብ ማህበረሰባዊ አስተደዳግ ፣ ህግ እና ታሪካዊ አመጣጥ የተገነዘቡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ሁሌም ሰላም እንዲኖር ሁላችንም አበክረን መስራት ይኖርብናል፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ሰላም ለሁሉም ነገር ቅደመ ሁኔታ እንጂ ለሰላም ምንም ቅድመ ሁኔታ ማበጀት የለብንም፡፡ ከተጣባን ክፉ የጦር አውርድ ደዌ የሚፈውስ መድኃኒት ይስጠን! አሜን፡፡

አሸብር ኃይሉ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You