የእናት ጡት ወተት ለጨቅላ ህፃናት ተኪ የለሽ ምግብ ከመሆኑ አኳያ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ እናቶች ልጆቻቸው ስድስት ወር እስኪሞላቸው ድረስ ጡት ማጥባት እንደሚገባቸው የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲያስገነዝቡ የሚደመጠውም ከዚሁ ፋይደው አኳያ በመነሳት ነው፡፡
የእናት ጡት ወተት ለጨቅላ ህፃናት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ ቢታወቅም፣ ሰው ሰራሽ የህፃናት ምግቦችና ወተቶችን ለማቅረብ በሚደረግ የማስታወቂያ ሥራ በሚስተዋል ፍትሐዊና ጤናማ ያልሆነ ውድድር ሳቢያ የእናት ጡት ወተት ትኩረት እንዳያገኝ እየተደረገ ነው፡፡
ሰው ሰራሽ የህፃናት ምግቦችና ወተቶች የሚያመርቱ እና ለገበያ የሚያቀርቡ አካላት ለገበያ ሲሉ በሚያሰራጩዋቸው ማስታወቂያዎች ምክንያት እናቶች ጡት ማጥባት ሲገባቸው እየተታለሉ እነዚህን ምግቦች በመግዛት ለልጆቻቸው ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ ህፃናትም የእናት ጡት ወተት ባለማግኘታቸው ለተለያዩ በሽታዎች፣ ለምግብ እጥረትና አልፎም ተርፎ ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት በኩልም የህፃናትን ጤንነት ለመጠበቅ በሚል እነዚህን ምግቦችና ወተቶችን ለማስተዋወቅ በሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ህግ ማውጣት እስከማስፈለግ ደርሷል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት አድን ድርጅት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ እ.ኤ.አ በ1979 የእናት ወተትን ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ የሚጠቅም ህግ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን፣ይህን ህግ ተከትሎም የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ1981 ዓለም አቀፍ የእናት ጡት ወተት ምትክ የሆኑ ምግቦች ግብይት ስነ ምግባር ደንብ /International Code of Marketing of Breast-milk Substitutes/ በሚል በማውጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆን አድርጓል፡፡
በወቅቱም 118 ሀገራት ህጉን በመደገፍ የሀገራቸው ህግ አካል በማድረግ ሊሰሩበት የሚገባም አንቀፅም በህጉ ተካቷል፡፡ ህጉም እ.ኤ.አ በ1984 የተከለሰ ሲሆን፣የጨቅላ ህፃናት ምግብ ደህንነትና ጥራት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ተጨማሪ አንቀፅ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
ይህ ህግ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በአዋጅ ደረጃ ያልተዘጋጀ ቢሆንም፣ በተወሰነ ደረጃ ወደ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ በመውሰድ የህፃናት ምግብ ማስተዋወቅ ቁጥጥር ረቂቅ መመሪያ በሚል እ.ኤ.አ ከየካቲት 2015 ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡ ፡መመሪያው እ.ኤ.አ በ2018 ዳግም ተከልሶ የህፃናት ምግብ ቁጥጥር መመሪያ በሚል እስካሁን ድረስ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ይሁንና በመመሪያው ዙሪያ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ለህብረተሰቡ እየተሰጠ ባለመሆኑ የእናት ጡት ወተት ተኪ የሌለው መሆኑን በመገንዘብ በተለይ እናቶች በሰው ሰራሽ የህፃናት ምግቦችና ወተቶች ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑ የሚደረጉ ጥረቶች አሁንም ዝቅተኛ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡
በምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብና ኒውትሪሽን አማካሪ አቶ ወንድአፍራሽ አበራ እንደሚሉት፤ የህጉ ትኩረት በዋናነት የእናት ጡት ወተትን ለመጠበቅና የበለጠ ለማስተዋወቅ ነው፡፡ በሰው ሰራሽ መንገድ የሚዘጋጁ የህፃናት ምግቦችና ወተቶች ከሚገባው በላይ በመተዋወቅ ለህብረተሰቡ በአነስተኛ ዋጋ፣ በተለያየ መልክና መጠን እየቀረቡ በመሆናቸው እናቶች በዚህ ሳይታለሉ ከማጥባት እንዳይቆጠቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት በርካታ እናቶች ምንም አይነት የጤና ችግር ሳይኖርባቸው ማጥባት እየቻሉ በሰው ሰራሽ መንገድ የተዘጋጁ የህፃናት ምግቦችንና ወተቶችን ለልጆቻቸው ይመግባሉ የሚሉት አቶ ወንድአፍራሽ፣እናቶች ይህን ማድረጋቸውን እንደ ስልጣኔ እንደሚቆጥሩትም ነው የሚገልጹት፡፡ የእናት ጡት ወተት በውስጡ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን መያዙን እንዲሁም በሽታን ከመከላከልና ሰውነትን ከመገንባት አኳያ የበለጠ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተው፣ ጥቅሙን ለማስጠበቅና ለማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ ህጉን ወደ ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታ በመውሰድና አስፈላጊ አንቀፆችን በማካተት ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ወንድአፍራሽ ማብራሪያ፤ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት እናቶች በሰው ሰራሽ መንገድ የሚዘጋጁ ምግቦችንና ወተቶችን ለልጆቻቸው ሲመግቡ በተፈለገው መጠን ወተቱን ላይበጠብጡት ስለሚችሉ ልጆቻቸው ላልተመጣጠነ የምግብ እጥረት ይዳረጋሉ፡፡ ምግብና ወተት በሚያዘገጁበት ጊዜ ተገቢውን ንፅህና ላይጠብቁ ስለሚችሉ ህፃናት ለከፍተኛ ተቅማጥና ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎች ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
አማካሪው የእናት ጡት ወተት የተሻለ ጠቀሜታ እንዳለው በመጠቆም፣ ማጥባት የምትችል እናት የግድ ጡት እንድታጠባ ይመከራል ይላሉ፡፡ ህጉ በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት እንዲወጣና ሀገራትም ወደራሳቸው ወስደው እንዲተገብሩት የሚደረገውም ወተትን የሚያስተዋወቁ አካላት ከልክ በላይ እያስተዋወቁ በመምጣታቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አማካሪው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ህጉን ወስዳ ሰው ሰራሽ የህፃናት ምግቦችንና ወተቶችን የማስተዋወቁ ተግባር ከሚገባው በላይ በጤና ተቋማትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች እንዳይተዋወቅ የሚያደርግ ድንጋጌ አካታበታለች፡፡አዲስ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ውስጥ የተካተተው ድንጋጌ የህጻናት ምግቦችና ወተቶች ደህንነታቸውና ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ነው ፡፡
አቶ ወንድአፍራሽ እንዳሉት፤በአዋጁ የህፃናት ወተት ምን ማለት እንደሆነ፣ በምን መልኩ መመረት እንዳለበት፣ ምን አይነት ደረጃዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅበት ተብራርቷል፡፡ሰው ሰራሽ የህጻናትን ምግቦች እና ወተቶችን የማስተዋወቅ ተግባር ሲከናወን በተለይ የጨቅላ ህፃናት ምግብና ወተት ማሸጊያዎች ላይ ገላጭ ፅሁፍ ከመለጠፍ በስተቀር በማንኛውም የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ ምርቶቹን ማስተዋወቅ የተከለከለ ነው፡፡ይህም በተለይ በአንቀፅ 58/4 ላይ ተጠቁሟል፡፡
ይህም የእናት ጡት ወተትን በማስጠበቅና በማስተዋወቅ ረገድ የድርሻውን አስተዋፅኦ ስለሚያበረክት መመሪያው በደምብ ሊተዋወቅ ይገባል ያሉት አስተባባሪው፣የጤና ተቋማት ባለሙያዎችም መመሪያውን አውቀውት ቢፈፅሙትና ወደ ትግበራ ቢገቡ ጡት ማጥባትን የበለጠ ማበረታታት ይቻላል ይላሉ፡፡ ህፃናትም አስፈላጊውን የእናት ጡት ወተት አግኝተው ጤናማ ሆነው ለማደግ እንደሚያስችላቸው ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ወንድአፍራሽ ማብራሪያ፤የጤና ባለሙያዎች ህጉን አውቀው ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ በጤና ተቋማት ደረጃ በሰፊው መሰራት ይኖርበታል ፡፡ በተለይ እናቶችና ህፃናት በብዛት የሚገኙት በጤና ተቋማት ከመሆኑ አኳያ ባለሙያዎቹ በሃገር አቀፍ ደረጃ የወጡትን ህጎችና መመሪያዎች ማወቅና መተግበር ይገባቸዋል፡፡ በሌላ በኩልም ጤና ተቋማት ለእናቶች ከሚሰጧቸው ሌሎች ትምህርቶች በተጓዳኝ ስለመመሪያውና ስለ ጡት ማጥባት ጥቅም ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡
በህጉ በርካታ ሀገራት ውጤታማ መሆን መቻላቸውን የሚገልፁት አማካሪው፤ ኢትዮጵያ ከህጉ ውስጥ የተወሰኑ አንቀፆችን በመውሰድ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች ይላሉ፡፡ ሌሎች ሃገራት ህጉን ሙሉ በሙሉ ወስደው ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የተወሰኑትን የህጉን አንቀፆች ብቻ ወስዳ እየሰራችበት ከመሆኑ አኳያ በቀጣይ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን ይጠይቃታል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ ህጉን ሙሉ በሙሉ ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል ከሆነም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤በአሁኑ ወቅትም በውጪ ተመርተው ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ወተቶችን የመመዝገብ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህም ያልተመዘገቡ የወተት ምርቶች ወደገበያ እንዳይወጡ ያስችላል፡፡ ከማስታወቂያ ጋር በተያያዘም የህፃናት ምስሎች በማሸጊያዎች ላይ ማድረግ ክልከላዎችም በተወሰነ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ጀምረዋል፡፡
በአንዳንድ የጤና ተቋማት ውስጥ በሰው ሰራሽ መንገድ የተዘጋጁ ምግቦችና የወተት ምርቶች ማስታወቂያዎች እንደሚታዩ አማካራው ጠቅሰው፣ይህም ህጉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኗል ለማለት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የጤና ተቆጣጣሪ አካላት በጤና ተቋማት ውስጥ ጠንካራ ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር በላይነሽ ይፍሩ መመሪያው የህፃናት አመጋገብ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም ህፃናት በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት ውስጥ ትክክለኛ አመጋገብ ካልተመገቡ የከፋ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ያመለክታሉ፡፡
እንደ ዶክተር በላይነሽ ገለጻ፤እነዚህን ችግሮች ለመከላከል በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት ላይ ከፍተኛ ሥራ መስራት ይገባል፡፡ ህፃናት የእናት ጡት ወተት እስከ ስድስት ወር ድረስ ጠብተው ማደግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሲባል ግን ሰው ሰራሽ ምግቦችንና ወተቶች አያስፈልጉም ማለት ሳይሆን ወተቶቹና ምግቦቹ ጥቅም ላይ መዋል የሚገባቸው አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር ነው፡፡ የእናት ጡት ወተት ግን መተኪያ የሌለው በመሆኑና በሽታንም ስለሚከላከል እናቶች ልጆቻቸውን አዘውትረው ማጥባት ይኖርባቸዋል፡፡
መመሪያው የህፃናት ወተትን ለማስተዋወቅ ያካተታቸው ነጥቦች እንዳሉም እሳቸውም ጠቅሰው፣ወተት አምራች ድርጅቶች ወይም አስተዋዋቂዎችና አስመጪዎች ከልክ ባለፈ መልኩ ምርቶቻቸውን እንዳያስተዋውቁ መመሪያው ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ በዚህም ጡት የማጥባትን ጥቅም በማስጠበቅና በማስተዋወቅ የህፃናትን ጤንነት መጠበቅ ይቻላል፡፡ የጤና ሚኒስቴር አንዱ ሥራው በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የእናት ጡት ወተት ለህፃናት ዋነኛ ምግብ መሆኑን ለእናቶች ማስገንዘብ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
መመሪያውን ለሁሉም ወገን በማስገንዘብ በኩል የመገናኛ ብዙሃን ለህብረተሰቡ መረጃ በማቀበል ሂደት ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አመልክተው፣ መመሪያው ተግባር ላይ ከዋለ ወዲህ አንዳንድ የህፃናት ወተት አስመጪዎችም መመሪያው የሚከለክላቸውን ነገሮች በመተው ላይ እንደሚገኙም ዶክተር በላይነሽ ይጠቅሳሉ፡፡ መመሪያው በቀጣይ በደምብ ተግባራዊ እንዲሆን አስፈፃሚ አካላት ማስተባበር ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ፣መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሃይለሚካኤል ካህሳይ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ መመሪያው በዋናነት የህፃናትን ምግብ ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅና ቁጥጥር ለማድረግ ያስችላል፡፡ በዚህም ባለስልጣኑ የህጉን አንቀፆች በመውሰድ የሚያስፈፅማቸው ሥራዎች አሉ፡፡ይህም የማስታወቂያና የማሸጊያ ገላጭ ፀሁፎችን ያጠቃልላል፡፡
ባለስልጣኑ በህጉ ውስጥ የተካተቱ መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣በተለይም በህፃናት ምግብ ቁጥጥር መመሪያና የምግብ ማስታወቂያ መመሪያዎች መሰረት ህጉን እያስፈጸመ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በዚህም መሰረት ሰው ሰራሽ የህጻናት ምግቦችና ወተቶች በምግብ ምዝገባ ሂደት ጥራታቸውና ደህንነታቸው ከሃገራዊ ደረጃ አንፃር ይታያል፡፡ በምግቦቹ ማሸጊያ ላይ ያለው ገላጭ ፅሁፍ የእናቶችና የህፃናት ምስል የያዘ አለመሆኑ ይረጋገጣል፡ ፡ እናቶችም በሰው ሰራሽ መንገድ የተዘጋጁ የህፃናት ምግቦችን እንዲጠቀሙ የሚገፋፉ ነገሮች እንዳይኖሩ የቁጥጥር ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ መመሪያው አስገዳጅ ከመሆኑ አኳያም በአሁኑ ወቅት በምግቦቹና በወተቶቹ ላይ የህፃናትና የእናቶች ምስሎች አይታዩም፡፡ ከተገኙም በህግ አግባብ አስፈላጊው ርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡
በሰው ሰራሽ መንገድ የሚዘጋጁ የህፃናት ምግቦችና ወተቶች የእናት ጡት ወተትን ሊተኩ እንደማይችሉ በእናቶች በኩል በቂ ግንዛቤ የለም የሚሉት ዳይሬክተሩ ፣በተለይ የእናቶች ጡት ወተትን ለማስጠበቅና ለማስተዋወቅ የወጣውን መመሪያ በየደረጃው ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ እሳቸውም ይገልጻሉ፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ታች ድረስ በመውረድ በጤና ተቋማት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በስልጠና ማብቃት ይጠበቅበታል፤የጤና ባለሙያዎችም የወሰዱትን ስልጠና መነሻ በማድረግ ከስራቸው ያሉ ሰራተኞችን ማብቃት ይኖርባቸዋል ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡ እናቶችም የጡት ማጥባትን ጠቀሜታና ተኪ የለሽነት በመረዳት ልጆቻቸውን ለስድስት ወራት ማጥባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2011
አስናቀ ፀጋዬ