የአንድ ሀገር ዓመታዊ በጀት ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ አድርጎ የሚሰላ ፤ ሀገራዊ አቅምን ፣ መሻቶችን እና እያደጉ የሚሄዱ ማኅበራዊ ፍላጎቶችን ከግምት የሚያስገባ ነው። ከዚህ የተነሳም የበጀት ጉዳይ ከቁጥር ባለፈ ብዙ ነገሮችን መናገር እንደሚያስችል ይታመናል።
በተለይም እንደኛ ባሉ በዕድገት እና በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኙ ሀገራት ለዓመታዊ የመንግሥት ሥራዎች የሚመድቡት በጀት/ ሀብት ፤ የኢኮኖሚያቸውን ግዝፈት ፤ የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ከማሳየት ባለፈ፤ ሀገራቱ ወዴት እየተጓዙ መሆኑን መጠቆም የሚያስችሉ ናቸው።
በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የፌዴራል መንግሥት በጀት ፤ አጠቃላይ ስለሆነው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ፣ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫም ሆነ ፤ እንደ ሀገር ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ አመላካች ነው።
የበጀት ረቂቁ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለማቃናት የሚረዳና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ፣ የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማፋጠን፣ ኢንቨስትመንትን፣ የወጪ ንግድን፣ የኢኮኖሚ አጋርነትን ማጠናከርን ታሳቢ ያደረገ ነው ፡፡
በረቂቅ ከተያዘው በጀት ውስጥ 451 ቢሊዮን 307 ሚሊዮን 221 ሺህ 52 ብር ለመደበኛ በጀት፤ 283 ቢሊዮን 199 ሚሊዮን 335 ሺህ 412 ብር ደግሞ ለካፒታል በጀት የሚውል ነው፡፡ ለክልሎች የሚከፋፈለው የድጎማ በጀት 222 ቢሊዮን 694 ሚሊዮን 109 ሺህ 445 ብር ፤ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያነት ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር መያዙም በረቂቁ በጀቱ ተመላክቷል፡፡
በጀቱ በመቶኛ ሲሰላ ካለፈው ዓመት ጋር የ21 ከመቶ ዕድገት ታይቶበታል ፤ ይህም አጠቃላይ የሆነውን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ፤ ከዚያም ባለፈ በቀጣይ መንግሥት የኢኮኖሚውን እድገት በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው።
በርግጥ መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ የሚያስችሉ ርምጃዎችን በመውሰድ ፤ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። የበጀቱ ዕድገትም የዚሁ በየዓመቱ እየተመዘገበ ያለው ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ድምር ውጤት እንደሆነ ለመገንዘብ የሚከብድ አይደለም።
የሀገሪቱ ዓመታዊ የመንግሥት በጀት አሁን የደረሰበት ደረጃ ፣ በአጋጣሚ ሳይሆን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በተገኘ ስኬት የተመዘገበ ነው። ብዙ ማሰብን ፣ ማቀድን እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም በቁርጠኝነት መንቀሳቀስን የጠየቀ ነው። በረቂቅ በጀቱ የተያዘውን ሀብት በተጨባጭ አግኝቶ ወደ ሥራ የመለወጡ ሂደትም የዚያኑ ያህል ማሰብንና ማቀድን የሚጠይቅ ነው።
ሀገር ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ፣ ወደ ተጨባጭ የልማት አቅም ሊለወጡ የሚችሉ አቅሞችን እና ዕድሎችን አሟጦ መጠቀምን የሚጠይቅ ነው። ለዚህ ሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን፣ በዲፕሎማሲው መስክ ያሉ አቅሞችን እና ዕድሎችን መጠቀም እንዲሁም ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል።
ይህ ትልቅ ሀገራዊ ሀብት ወደ ሥራ ሲገባ ፣ አሁን እንደሀገር ያለውን የዋጋ ግሽበት እንዳያባብሰው ከወዲሁ መዘጋጀትም ብልህነት ነው፣ በጀቱ ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ፤ ለዚህ የሚሆን ጠንካራ የክትትልና የድጋፍ እንዲሁም የተጠያቂነትን ሥርዓት ማስፈንም ተገቢ ነው፡፡
አሁን ላይ ከሚታየው የተቋማት የኦዲት ግኝት ክፍተት አኳያ፣ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በሚጠበቅባቸው ልክ ራሳቸውን ብቁ አድርገው የተመደበላቸውን የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት በጥንቃቄ በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ እንደ ሀገር ለጀመርነው ለውጥ ስኬት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥት ለጀመረው ልማት ስኬት ስትራቴጂክ አቅም ናቸው ብሎ በለያቸው የግብርና ፣ የማዕድን ፣ የቱሪዝም ፣ የኢንዱስትሪ እና የዲጂታላይዜሽን ዘርፎች ያሉ ባለበጀት ተቋማት የዘርፎቹን ስትራቴጅክ አቅም ታሳቢ ያደረጉ ስኬታማ ሥራዎችን ለመሥራት የተሻለ ዝግጁነት መፍጠር ይኖርባቸዋል።
መንግሥት ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት በራስ አቅም /በገቢ ሰብሳቢ ተቋማት በኩል ለመሰብሰብ ከያዘው እቅድ አኳያ ፣ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ግልጽ ቀልጣፋና ፈታኝ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ራሳቸውን በሁለንተናዊ መልኩ ለተሰጣቸው ትልቅ ኃላፊነት ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በጀቱ በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ሀገራዊ ሰላም የማስፈኑ ሂደት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝባችን በመሆኑ ፣ አሁን ላይ በብዙ ዋጋ የተገኘውን ሰላም ከመጠበቅ ጀምሮ ለሰላም ተገቢውን ዋጋ በመስጠት ፣ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን ሁሉም ዜጋ በሃላፊነት ሊንቀሳቀስ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም