ግንዛቤ የሱስ ሕመምን ለማከም

መክብብ ታገል (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ) በአሥራዎቹ መጨረሻ የእድሜ ክልል ነበር ከጓደኞቹ ጋር ለመዝናናት ብሎ ጫት መቃም የጀመረው። ታዲያ ጫት መቃም ላይ ብቻ አልቆመም። ጫት የመቃም ልምምዱ እያደገ መጥቶ ሌሎች ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮችን ወደ መጠቀም እንዲገባ ጋብዞታል።

ዛሬ መክብብ ጫት ቢቅም ባይቅም ለእርሱ ምንም የሚፈጥረው አዲስ ነገር የለም። ሌሎች መጠጦችም ለእርሱ ብርቅ አይደሉም። አንድ ነገር ካልቀመሰ ግን ‹‹ደም ሥሬ አይንቀሳቀስልኝም›› ይላል። እርሱም አረቄ ነው። አረቄ መጠጣት እንዴት እንደጀመረ በደምብ ያስታውሳል። ከጫት በኋላ በብዛት ቢራ ይጠጣ ነበር። ሳይሠሩ በየቀኑ መጠጣት እና መቃም ምን እንደሚመስል መክብብ በሚገባ ያውቀዋል። ‹‹አምጣ፤ አምጣ፡፡›› የሚለውን ስሜት ለማስተናገድ ሲል የብዙዎችን ፊት አይቷል። ‹‹እከልዬ ብር ሙላልኝ?›› ከሚለው የልመና ቃል ጀምሮ የእናቱን ጥሪት እየደበቀ እስከ መሸጥ ደርሷል። እናም የቢራው ዋጋ ለእርሱ የሚቀመስ አልሆነምና ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ አረቄ አዞረ፡፡

መክብብ በዘመድ አዝማድ አረቄ መጠጣቱን እንዲተው ብዙ ጊዜ ተመክሮ እንደሚተው ምሎ ቢገዘትም ወደ ተግባር መቀየር ግን አልቻለም። ከዚህ በፊት ወደ ሕክምና ተቋም በማምራት ክትትል ጀምሮ ከአረቄ እና ከጫት ጋር ለተወሰኑ ወራት ተለያይቶ ነበር። ‹‹ግን የምኖርበት ሠፈር አረቄ በስፋት እና በዓይነት የሚገኝበት በመሆኑ መቁረጥ ተሳነኝ፡፡›› በማለት በድጋሚ መጀመሩን ያስረዳል። ዛሬ በቤተሰቦቹ ርዳታ ከሱሱ እንዲላቀቅ ዳግም ክትትሉን ጀምሯል። እስካሁን በጥሩ መንገድ እየሄደ እንደሚገኝ በመግለጽ እስከመጨረሻው ወደ አረቄ ላለመመለስ ሰፈር መቀየሩንና ጓደኞቹን መሸሹን ይናገራል፡፡

ዶክተር አስራት ኃብተ ጊዮርጊስ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ናቸው። እርሳቸው ስለሱስ ሕመም ከመናገራቸው በፊት አሁን አሁን ህመምን እንደ ስያሜ የመቁጠር ነገር ይስተዋላልና ‹‹ሱሰኛ›› ፣‹‹ሱስ›› እና ‹‹ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች›› ለያይቶ ማየት አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ። በተቻለ መጠንም ‹‹ሱሰኛ›› የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ጥረት ቢደረግ መልካም እንደሆነም ይናገራሉ።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በእንግሊዝኛ ስያሜው ‹‹Substance Use Dis order›› በአማርኛ ‹‹የንጥረ ነገር አጠቃቀም ቀውስ› የሚለው ስያሜ ‹‹ሱስ ምንድ ነው?›› የሚለውን ነገር ለማብራራት ይረዳል። ሰዎች የተለያዩ ሱስ የሚያመጡ ንጥረ ነገሮችን በተለያዩ መንገዶች ሊጠቀሙ ይችላሉ። አንዳንዶች ለመዝናኛ እንዲሁም ብለው በማሕበራዊ መስተጋብሮች አማካኝነት አልፎ አልፎ በጥቂቱ ቢወሰድ ችግር የለውም ተብሎ የተጀመረ በኋላ ግን መቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ።

አንድ ሰው የንጥረ ነገር አጠቃቀም ቀውስ ወይም የሱስ ሕመም አለበት ለመባል የሚያሳያቸው የተለያዩ ምልክቶችን መጥቀስ ይቻላል። የአስተሳሰብ ባህሪ መቀየር እና አካላዊ ለውጦችን ማስተናገድ ከምልክቶቹ መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ከዚህ በተጨማሪም ሰዎች ድሮ ከሚያደርጓቸው ነገሮች በመነሳት ለውጥ ማምጣት ሲሆን ለአብነትም በማሕበራዊ ሕይወት ላይ ክፍተት መፍጠር፣ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን በሚገባ አለመወጣት ይጠቀሳል።

የጤና እና አካላዊ ጉዳት እያደረሰባቸው እንደሆነ እያወቁ እንኳን ንጥረ ነገሮችን መጠቀም መቀጠል ሌላኛው ምልክት ነው። ይህንን ሃሳብ ዶክተር አሥራት ሲያስረዱ ‹‹ለምሳሌ አንድ ሰው ሲጋራ በማጨሱ ምክንያት፤ የሳንባ ካንሰር፣ የከንፈር ካንሰር፣ የጉሮሮ ካንሰር አምጥቶብሃል ቢባል ‹‹አምጣ አምጣ›› የሚለው ስሜት በመኖሩ ማጨሱን ይቀጥላል፡፡›› በማለት ያስረዳሉ። ከጤና፣ ከማሕበራዊ ጉዳቱ በተጨማሪም በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ችግር እየታወቀ ራስን መቆጣጠር አለመቻልም አንድ ሰው በሱስ ሕመም እንደተያዘ አመላካች ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች ማቆም እየፈለጉ እና እየሞከሩ ግን ደግሞ ማቆም አይችሉም፡፡ይህም አንድ ሰው በሱስ ሕመም መያዙን የሚያሳይ ምልክት ነው የሚሉት ዶክተር  አሥራት፤ ሌላው አደገኛ የሆኑ ነገሮች ውስጥ እስከ መግባት እንደሚደርስም ይጠቅሳሉ። በተለይም ራስን ለአደጋ ባጋለጠ መልኩ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም ሲሆን፤ አልኮል ጠጥቶ እና እንደ ካናቢስ ያሉ እጾችን ወስዶ መኪና ማሽከርከርም ሆነ ሌላ ኃላፊነትን የሚጠይቁ ነገሮች ላይ በመገኘት ራስን ለአደጋ የማጋለጥ ዕድልን በሰፊው ይጨምራል።

በአብዛኛው ሰው በኩል ‹‹ሱስ›› ሲባል ከሲጋራ፣ ጫት እና መጠጥ የመስጠቱ ነገር በስፋት ይስተዋላል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሱስ የሚያመጡ ንጥረ ነገሮች ተብለው በዋናነት የሚጠቀሱት እና በእኛ ሀገር አንዳንዶች እየተጠቀሙት ካሉት መካከል የተለያዩ የመጠጥ አይነቶች ፣ ማሪዋና፣ ካናቢስ እና ሌሎችም ይገኙበታል። እንደ አነቃቂ ተብለው በመድሃኒትነት መልክ የሚሠጡም አሉ ያሉት ዶክተር አሥራት፤ በአጠቃላይ ጫት ኮኬይን፣ ለሕመም ማስታገሻነት የሚሰጡ መድኃኒቶች፣ ቡና፣ ሲጋራ ወይም የትምባሆ ውጤቶች ተጠቃሽ ናቸው። አወሳሰዳቸውም በመጠጣት፣ በማሽተት፣ በመዋጥ እና በመርፌ መልክ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡

የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር አሥራት እንደሚያስረዱት የሱስ ሕመም ዓይነቱ ብዙ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ንጥረ ነገር ያልሆኑ ግን በቀላሉ ሱስ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች አሉ። ይህ ዓይነቱ ሱስ ‹‹ባህሪያዊ ሱስ›› ተብሎ ይገለጻል። የቁማር ሱስ፣ የጌም፣ የኢንተርኔት፣ ማሕበራዊ ሚዲያን ከመጠን ባለፈ መጠቀም እና ሌሎች የባህሪ ሱሶች መኖራቸው ይታወቃል። ይህ ዓይነቱ ሱስም ልክ ንጥረ ነገሮች በመጠቀም የሚያመጡትን አእምሯዊ ወይም አካላዊ ለውጦችን በማምጣት ወደ ባህሪያዊ ሱስነት ይሸጋገራሉ፡፡

አንድን ሰው ወደ ሱስ ሕይወት እንዲገባ አጋላጭ የሚባሉ ምክንያቶች ብዙ ናቸው። ነገር ግን ይህ ከሰው ወደ ሰው የተለያየ ነው። በዋናነት አካላዊ (Phsical Fac­tors) ወይም ሥነ ሕይወታዊ (Biological Factors)፣ የዘረ መል ተጋላጭነት ወይም በቤተሰብ ውስጥ የሱስ ሕመም ያለበት ሰው ፤ ቤተሰቡ የሱስ ሕመም ከሌለበት ሰው ጋር ሲነጻር የመጋለጡ ዕድል ሰፊ ነው። ሌላው አካላዊ ሕመም ያላቸው አንዳንዶች ታማሚዎች ከሕመማቸው ፋታ ለማግኘት (ለማስታገስ) ሲሉ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን መጠቀማቸውም የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

አካባቢያዊ/ማሕበራዊ (Social Environment) ሁኔታ ለሱስ ሕመም ለመጋለጥም ሆነ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትልቅ ሚና አለው። ይህም ሲባል በአንድ አካባቢ ላይ የሚገኘው ንጥረ ነገር፤ በአካባቢው ያለው ተቀባይነት፣ የመገኘቱ ሁኔታ፣ ብቸኝት፣ ማሕበራዊ ድጋፍ የመኖርም እና ያለመኖር፣ ዕድሜ በተለይም ከ 18 እስከ 25 ያሉ ወጣቶች የበለጠ ተጋላጭች መሆናቸው ይገለጻል። ይሁን እንጂ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ያለ ሰው በሱስ ሕመም ሊያዝ ይቻላል፡፡

ጾታም ለሱስ ሕመም አጋላጭ ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከሴቶቸ ይልቅ ወንዶች የበለጠ ተጋላጭነታቸው ሊጨምር እንደሚችል ዶክተር አሥራት ይገልጻሉ፡፡

ሌሎች የጤና እክሎችም በሱስ ሕመም ለመያዝ አጋላጭነታቸው ሰፊ ነው። በተለይም የአእምሮ ህሙማን፣ እንደ ድብርት፣ ውጥረት፣ ጭንቀት፣ ከፍተኛ የአእምሮ መወቃስ ያለባቸው ታማሚዎች የበለጠ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ በሚገጥማቸው ነገር ችግሮቻቸውን ለመርሳት እንደ መፍትሄ ወይም መደበቂያነት ይጠቀሙባቸዋል። ታዲያ በሂደት ብዙ በመጠቀማቸው ወደ ሱስነት ደረጃ ሊሸጋገርባቸው ይችላል።

እንደ ዶክተር አሥራት ገለፃ፤ የሱስ ሕመም በማሕበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪም በጤና ላይ የሚደሰው ጉዳት ከፍተኛ የሚባል ነው። የሚያደርሰው ጉዳት እንደ ንጥረ ነገሩ አይነት የሚወሰን ሲሆን፤ ንጥረ ነገሩ የሚያልፍበት የሰውነት ክፍል ላይ ተመሥርቶ ከአእምሮ ጀምሮ ሁሉንም የአካል ክፍሎች ላይ ጉዳት የማድረስ አቅም አለው።

ንጥረ ነገሮቹ የአእምሮን አሠራር የመቀየር አቅም ያላቸው በመሆኑ አእምሮ ላይ ከሚያደርሱት ጉዳቶች መካከል የአእምሮ ህመም አንዱ ነው። ከሱስ ሕመም ባለፈም ድብርት፣ ጭንቀት፣ ሽቅለት (Bipolar)፣ የድብርት መፈራረቅ፣ ከፍተኛ የአእምሮ መቃወስ፣ የእንቅልፍ እጦት፣ የስብዕና ቀውሶች እና ሌሎች የአእምሮ ሕመሞች ሊያስከትል ይችላል። አካላዊ ሕመሞችም የሚያጋጥም ሲሆን፤ ሲጋራ ወይም አልኮም በመጠቀማቸው የሳንባ፣ የጉበት፣ የኩላሊ እንዲሁም አብዛኞችን የአካል ክፍሎችን ሊያጠቃ እንደሚችል እና እንደ ንጥረ ነገሩ አይነት የሰውነት ክፍል ላይ ጉዳት የማድረስ አቅም እንዳላቸው ዶክተር አሥራት ይናገራሉ፡፡

በሱስ ሕመም ምክንያት የሚመጡትን የተለያዩ ሕመሞችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል የሚናገሩት ዶክተር አሥራት፤ አዋጭ የሚሆነውም መከላከል ላይ ቢሠራ ነው ይላሉ። በዋናነትም ግንዛቤ ላይ መሥራት የሚገባ ሲሆን፤ በግለሰብ ፣በማሕበረሰብ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ እና ከዛ በሻገርም በፖሊሲ ደረጃ ከመቅረት በሻገር ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ለውጥ ለማምጣት ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪም ወጣቶች፣ አፍላ ወጣቶች እና ታዳጊ ልጆች ላይ ግልጽ የሆነ ንግግር በመፍጠር፣ በቤተሰብ መካከል ተግባቦት እና ቅርበት መፍጠር፣ ድጋፍ ማድረግ፣ ግለጸኝነትን እንዲለማመዱ ማድረግ ፤ ችግር ሲያጋጥማቸው በፍጥነት ለመፍታት እንዲሁም ኃላፊነት ለመውሰድ ዕድል እንዲኖራቸው በጋራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ይህ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያግዝ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አሥራት የመከላከያ መንገዶች ሳይተገበሩ ከቀሩ የሱስ ሕመም ልክ እንደሌሎች ሕመም መታከም የሚችል በመሆኑ ወደ ሕክምናው መሄድ ይመከራል። ሕክምናው በዋናነት የሚያተኩረው የሥነ ልቦና ሕክምና ወይም የንግግር ሕክምና ላይ ነው፡፡በሂደቱም ሰዎች በራሳቸው ሃሳብ (እይታ) ነገሮችን በደንብ መፈተሽ እንዲችሉ እና ውሳኔያቸውን በደንብ አሰላስለው ምክንያታዊ በመሆነ መልኩ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ በማገዝ ከሕመማቸው እንዲያገግሙ የሚረዳ ነው፡፡

የሱስ ሕመም ጥሩ እና መጥፎ ነገሮች አሉት። ጥሩው ነገር በሕክምና መዳን የሚችል ሲሆን፤ መልካም ያልሆነው ደግሞ ግርሻ /በድጋሚ/ የመከሰቱ ዕድል ሰፊ መሆኑ ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከጊዜያዊ መፍትሄ ይልቅ ረዘም ያለ እንዲሁም ግርሻን የመከላከል ሁኔታን ያካተተ ሕክምና መውሰድ ያስፈልጋል።

የሕክምና ተቋማቱ ከሚሰጡት ሕክምና ጎን ለጎን ከታማሚዎች የሚጠበቅ ነገር እንዳለ ያመላከቱት ዶክተር አሥራት፤ አንድ ታማሚ ራሱን ወደ ሕከምና እንዲሄድ ከማድረግ በሻገር ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ እና ለውሳኔ ዝግጁ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን ቁጥራዊ አሃዞችን ለመጠቀም በቂ መረጃዎች ባይገኙም አሁን አሁን የተለያዩ ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን በወጣቶች በኩል የመጠቀሙ ነገር በስፋት እየተስተዋለ እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል። ከዚህ ሃሳብ ጋር ተያይዞም ዶክተር አሥራት ውጤታማ እና ከሱስ ነጻ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር በትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። የወጡ ፖሊሲዎች በምን መልኩ እየተተገበሩ ይገኛሉ የሚለውን መፈተሽ እና ግንዛቤ ላይ መሥራት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You