“ችግኝ ተክሎ አለመንከባከብ ልጅ ወልዶ እንደመጣል የሚቆጠር ነው” -ፕሮፌሰር ተሾመ ሶሮምሳ (ዶ/ር) በአ.አ.ዩ መምህር እና ተመራማሪ

የትውልድ ሥፍራቸው ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ድሬ እንጪኒ ወረዳ በሚገኝ ቀበሌ ነው። ፊደል የቆጠሩትና እስከ ስድስተኛ ክፍልም የተማሩት እዛው በትውልድ ቀዬያቸው በጠቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተማሩበት ደግሞ እንጪኒ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመባል ይታወቃል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመማር ከአካባቢያቸው ወጣ ማለት የግድ ብሏቸው ነበርና የተማሩትም ወደ አምቦ አቅንተው ነው – የዛሬው የዘመን እንግዳችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ እና ቀመር ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ተሾመ ሶሮምሳ (ዶ/ር)።

ፕሮፌሰር ተሾመ፣ ልክ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የከፍተኛ ትምህርታቸውን የተቀላቀሉት አሁን በማስተማር ላይ በሚገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ እና ቀመር ኮሌጅን ነው። የመጀመሪያውን ብቻ ሳይሆን ሁለተኛውንም ዲግሪያቸውን የተማሩት በዚያው ኮሌጅ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሥነ-ምህዳር (Ecologi) ላይ ሠርተዋል። እንግዳችን የፕሮፌሰርነትን ማዕረግ ያገኙት ደግሞ በአካባቢ (Environment) ዘርፍ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በኮሌጁ በማስተማር ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር ተሾመ፣ የሚያስተምሩበት የትምህርት ክፍል የአካባቢያዊ ሳይንስ ማዕከል ሲሆን፣ ከማስተማርና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ከማማከር ጎን ለጎን ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በአካባቢ ጥበቃ ባለሙያነታቸው ነው።

ፕሮፌሰሩ፣ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በመገንዘብና በመንከባከብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ኢትዮጵያዊ የአካባቢ ሳይንስ ምሁር ናቸው። ለአካባቢ ጥበቃ እና ኢትዮጵያ ያላትን ሥነ-ምህዳር ትውልድ እንዲያውቀውና እንዲጠብቀው ከማድረግ አኳያ የማይናወጥ ቁርጠኝነትም ያላቸው ምሁር ናቸው።

ፕሮፌሰር ተሾመ፣ የሚያከናውኗቸው በርከት ያሉ ሥራዎችን ነው። ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን በአካባቢ (Environment) ላይ በማተኮር በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ አካባቢን መልሶ የማልማት (Rehabilitation) ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ለአብነት ያህል እንደ ኪሎሌ አይነት ሐይቅ ላይ ሥራ ሠርተው መልሶ እንዲያገግም ጥረት አድርገዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ሸዋ አካባቢም በመሥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ እንዲህ አይነቱን ሥራ ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን የሚሠሩት መሆኑን አጫውተውናል።

እርሳቸው ከማስተማር፣ ከማማከር እና የአካባቢ ጥበቃ ላይ አበክሮ ከመሥራት በተጨማሪ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሲሆን፣ ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት እንደ ትልቅ ፕሮጀክት ይዘው እየተገበሩ ያሉት ቋንቋን መተርጎም ነው። ይህንንም ተግባር ለማከናወን አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋም (ኤን.ጂ.ኦ) የኢትዮጵያ ቋንቋን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እርሳቸው እንዳሉን ከሆነም የኢትዮጵያን አምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፍ ሱማሌ እና አፋርኛ ) ዲጂታይዝ በማድረግ ላይ ናቸው።

እንደሚታቀው ዓለም ዲጂታይዝ እየሆነች ባለችበት በዚህ ዘመን፤ ሁሉም ነገር ዲጂታዜሽን ውስጥ እየገባ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችም ዲጂታይዝ የመሆናቸው ጉዳይ ትልቅ ነገር መሆኑን እንግዳችን አውግተውናል። ከዚህ የተነሳም ቋንቋዎቹን ወደ እዛ ፕላትፎርም ማምጣት ትልቅ ነገር ነውና እርሳቸው በዚህ ዘርፍ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች በማስተባበር በማሠራት ላይ ይገኛሉ።

ጉምቱው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፣ በዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ በርካታ ጽሑፎችን ማሳተም ችለዋል። በጉግል ስኮላር ላይ ወደ 190 አካባቢ ጽሑፎች ያሏቸው ቢሆንም፤ እርሳቸው የጻፏቸውና በተለያዩ ሳይንቲፊክ ጆርናሎች ላይ ያሳተሟቸው ግን ከ200 በላይ እንደሆኑም አውግተውናል። ከዚህ ውጭ በሰነድ መልክ የጻፏቸው በርካታ ሲሆኑ፣ ያላሳተሟቸው ጽሑፎች ከሁለት ሺህ በላይ እንደሚሆኑም አጫውተውናል። የጽሁፎች ዋና ትኩረት ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ሥራዎች ሁሉ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የተሠሩ ናቸው።

አዲስ ዘመንም እኚህን በአካባቢ ጥበቃ ተመራማሪነታቸውና ተሟጋችነታቸው የሚታወቁትን አንጋፋ ምሁር የዛሬው እንግዳ አድርጎ እንደሚከተለው አቅርቦታል።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በሙያዎ ሰፊ ሥራ የሠሩበት ዘርፍ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ ያለው እንደመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት ማድረግ ያለበት ምን ላይ ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡- የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ለረጅም ዓመታት ስንጮህ ቆይተናል። አፈር አይሸርሸር በሚል ብዙ ጊዜ ተናግረናል። በእርግጥ ቀደም ሲል የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ችግኝ ሲተክሉም ሲያስተክሉም እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን እንደአሁኑ ሕዝብን በስፋት በማንቀሳቀስ አልነበረም። ይህ የሆነው ችግሩ ገዝፎ ሲመጣ ነው።

እኔ እኤአ በ2007 ላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አሰማርቼ ሰበታ አካባቢ ከኦሮሚያ ደንና ዱር ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር አንድን ጉብታ ችግኝ ከተተከልን በኋላ ከታች እስከ ላይ በአጥር ዘጋን። ጉብታው 17 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደን መሆን ችሏል። እንዲያውም በጣም ትልልቅ የሚባሉ ዛፎችን መፍጠር ባይቻል እንኳን ወደ ደንነት መመለስ ችሏል፡፡

አንድ አካባቢ በዚህ መልኩ የሚሠራበት ከሆነ ወደ ደንነት ለመመለስ የሚፈጀው ጊዜ 10 ዓመት ብቻ ነው። በእነዚህ ዓመታት ቢያንስ ባዮ ማስን መመለስ ይቻላል። ከተማሪዎቹና ከቢሮው ጋር በመተባበር የተከልነው ጉብታ በአሁኑ ወቅት 97 በመቶ ማገገም ችሏል። ለዚህ ውጤት ዋናው ነገር ችግኞችን ጉብታው ላይ ተክለን ትተን አለመምጣታችን ነው። ችግኙ እንክብካቤ ይደረግለት ስለነበር ውጤታማ መሆን የቻለ ሥራ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቦታ የተራቆተው ከፍ ያለ ቦታ (ጉብታው) ነው። ወደ ሰሜኑና ማዕከላዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከታየ ጉብታዎቹ የተራቆቱ ናቸው። እነዚያ ጉብታዎች የተራቆቱበት ምክንያት በመታረሳቸውም ጭምር ነው፤ ነገር ግን ጉብታዎቹ ደናቸው ተመንጥሮ ቢበዛ ለሶስትና ለአራት ዓመታት ያህል ማረስ ያስችሉን ይሆናል፤ ከዚያ በላይ ግን ያለው እድል በጎርፍ እየታጠበ ዜሮ የመሆን ነው። ስለዚህም ጉብታዎቻችን መታረስ የለባቸውም፤ ጉብታዎችን መሸፈን ያለብን በደን ነው።

ብዙውን ጊዜ እኛ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችም የምንመክረው ጉብታዎችን በሽቦ እንዲያጥሯቸው ነው። ከአስር ዓመት በኋላ ደኑ መመለስ ይችላል። ዋናው ነገር ባሉን ጉብታዎች ላይ ችግኝ መትከልና መከለል ሲሆን፣ ከንኪኪ ነጻ ማድረጉ የነበረው ነገር እንዲመለስ ምክንያት ይሆናል።

ደን መልሶ ሲያገግም ደግሞ ብዙ ነገር አብሮ ይመለሳል። ለአብነት ያህል ከንጹሕ ውሃ ጀምሮ እስከ ንጹሕ አየር ድረስ አብሮ ይመለሳል። ከዚህ ጎን ለጎን ዝናብ በቀላሉ ማግኘት እንችላለን። ዝናብ አለ ማለት ደግሞ ሳር ይኖራሉ፤ ሳሩን ተከትሎ ከብቶችም እርሻም ይኖራል። ባዮማስ (ብስባሽም) ስለሚኖር ለዚያ አካባቢ እርሻ መልካም ይሆናል። ባዮማሱ መሬቱን በደንብ ስለሚዘጋው አፈር የመሸርሸር እድል እንዳይኖረው ያደርጋል። ደን ሕይወት ነው የሚባለውም ለዚህ ነው። ደን ከሌለ የሰው ልጅ ሕይወት ችግር ውስጥ ይገባል። አንድ መንግሥት ድህነትን እቀንሳለሁ ብሎ ካቀደ የሚቀንሰው በምን መልኩ ነው? ወደሚለው ሲመጣ በርካታ ነገሩ ከደን ጋር የተያያዘ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ሕዝብን በማንቀሳቀስ የችግኝ ተከላው በሰፊው ሲሠራበት ቆይቷል፤ በእናንተ በኩል የተደረገ ጥናት ካለ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ተግባር የሚገለጸው እንዴት ነው?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡– አረንጓዴ ዐሻራ ያመጣውን ለውጥ በተመለከተ አንድ ሥራ እንድንሠራ ወደእኛ ትምህርት ክፍል መጥቶ ነበር። አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብርን መተግበር ከጀመርን እኤአ 2019 በመሆኑ አምስተኛ ዓመታችንን ይዘናል። ያንን መርሃግብር በመከተል ዘንድሮም የምንተክል ይሆናል።

ባለፉት ዓምስት ዓመታት የተተከለው ችግኝ ዛሬ ላይ ደን ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። የሚጠበቀው ግን የመሬት ሽፋን በምን ያህል መጠን ጨምሯል? የሚለው ነው። አንዳንድ ግምት እንደሚያሳየው ሽፋኑ ከነበረበት ወደ 18 በመቶ ከፍ ማለቱን ነው። እዚህ ላይ ግን ሁለት ነገር ልብ ማለት ይገባል። አንዱ የተፈጥሮ ደን ሲሆን፣ እሱ አሁንም ችግር ላይ የሚገኝ ነው። ምክንያቱም ሰውም እየጨፈጨፈው ነው። ይሁንና የኢትዮጵያ የመሬት ሽፋን ጨምሯል ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የጨመረው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው? ቀደም ሲል የነበረውስ ምን ያህል ነበር?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡– በእርግጥ ሽፋኑ ቀደም ሲል እስከ 40 በመቶ ይደርስ እንደነበር ይታወሳል። እሱ ቀስ በቀስ እየተመናመነ አኃዙ እስከ ሶስት በመቶ ከዚያም ዝቅ ሲል በ1980ዎቹ ውስጥ ሁለት ነጥብ ሶስት በመቶ ሁሉ ደርሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይህ የመሬት ሽፋን በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ይገኛል። ይህ ደግሞ መልካም የሚባል ነው። የተያዘውን ምርጥ ተሞክሮን ግን ማስቀጠል የግድ ነው።

እንዴት ይቀጥላል ለሚለው በባለሙያ የታገዘ ሥራ በመሥራት ነው። ባለሙያ ሲባል ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ጉብታዎች ላይ የትኛውን የደን ዘር መተከል አለበት የሚለውን የሚያውቀው ባለሙያው ነው። አሁን በመተግበር ላይ ያለው አረንጓዴ ዐሻራው ጥሩ ነገር ነው። ይህንንም ባህል አድርገን ልናስቀጥለው ይገባል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እኤአ 2011 ላይ ቦን ቻሌንጅ (Bonn Challenge) የሚባል ኢኒሼቲቭ ነበር። ይህ ኢኒሼቲቭ 350 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ያለመ ነው። ይህ ኢኒሼቲቭ የተፈረመው ጀርመን ላይ ሲሆን፣ ሀገራቱ ቁርጠኛ ለመሆን ቃል የገቡበት ነው፤ ቻሌንጁ እኤአ በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ 350 ሚሊዮን ሔክታር የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲያገግም እናደርጋለን በሚል ስምምነት ላይ የተደረሰበት ሲሆን፣ ስምምነት ላይ ከደረሱ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡

ኢትዮጵያ፣ እኤአ በ2030 ላይ 15 ሚሊዮን ሔክታር የተራቆተ መሬትን መልሶ እንዲያገግም አደርጋለሁ በሚል፤ ቃል መግባቷ የሚታወስ ነው። ይህንን ከአረንጓዴ ዐሻራ ሌጋሲ ጋር አይይዘን ካየነው በእስካሁኑ ጉዟችን ግማሹን ማሳካት ችለናል። በዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብራችን ሳናቋርጥ የምንጓዝ ከሆነ በእቅድ የያዝነውን ግብ ማሳካት እንችላለን። በተለይ ደግሞ ዋናው ቁም ነገር ያለው ጉብታዎችን በመሸፈኑ ላይ ነው። ጉብታዎችን ስንሸፍን ታች ያለው መሬት በቂ እርጥበት ማግኘት ያስችለዋል።

በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር እኛ ሪፖርት እያደረግን ነው። የተገነዘብነው ነገር ቢኖር የተያዘውን እቅድ ስኬታማ ለማድረግ የአሁኑ ፍጥነት ጥሩ አመላካች መሆኑን ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ወቅቱ የችግኝ ተከላ ነው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ችግኝ በሚተከልበት ሰዓትና ከተተከለ በኋላ መደረግ ያለበት ሒደት ዛሬም የተፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰምና መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡- የመጀመሪያው ሥራ ምን አይነት ችግኞች ናቸው የሚተከሉት የሚለውን መለየትና ማዘጋጀት ነው። በተለይ ከተማ ውስጥ ደግሞ የፍራፍሬ አትክልት ላይ ትኩረት ቢደረግ ሁልጊዜ ጠቃሚ ነው እንላለን። ሌላው ቀርቶ የምንችል ሁሉ በየቤታችን የፍራፍሬ ዛፍ ብንተክል ውጤታማ መሆን ይቻላል፤ በእርግጥ ይህ እየተዘጋጀ እንደነበር አውቃለሁ።

በተከላ ወቅት ደግሞ ማድረግ ያለብን ሒደቱ በባለሙያ የታገዘ ዘመቻ መሆን ያለበት እንዲሆን ነው። እናም ዘንድሮ በተከላው ለመሳተፍ በዝጅት ላይ ነን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከ40 ሺ በላይ የሚገመት ቁጥር አለው። ስታፉ ሲታከልበት ደግሞ የሰው ኃይሉ ወደ 50 ሺ የሚጠጋ ነው። ይህ የሰው ኃይል ወደተግባር ሲሰማራ በርካታ ነገር መሥራት ይችላል። ስለዚህ ይህን ኃይል ለመጠቀም በጉዳዩ ላይ እየመከርንበት እንገኛለን።

ችግኝ መትከል ብቻ በራሱ ስኬት አይደለም፤ ችግኝ ተክሎ አለመንከባከብ ልጅ ወልዶ እንደመጣል የሚቆጠር ነው። ተክለን ትተን መሄድ የለብንም። ኃላፊነት መውሰድ የሚኖርበት ማን ነው የሚለውን መለየትና የተጣለብንን ኃላፊነት መወጣት ይኖርብናል። ስለዚህም ችግኙ እስኪጸድቅ ድረስ መንከባከብ የግድ መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ወደ ጎረቤት ሀገራት ችግኝ በመጋራት ላይ ትገኛለችና ይህ እንደምን ይታያል?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡- በነገራችን ላይ አካባቢ ጥበቃ ድንበር የለውም። “ይህ የእኔ፤ ያኛው ደግሞ ያንተ ነው” በሚል መስመሩን ያሰመረው የሰው ልጅ ነው። የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣ የሱዳን ዳር ድንበር እያልን ያበጀነው እኛው የሰው ልጆች ነን እንጂ አፍሪካ በራሱ አንድ ነው። ከሰው ልጆች ውጭ እንስሳቱን ብንወስድ ድንበር ስለሌላቸው ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ይንቀሳቀሳሉ። ስለዚህ ድንበር ተሻጋሪ ሥራን መሥራት ትልቅ ነገር ነው።

በአንድ ወቅት ሳሕል ቤልትን አረንጓዴ እናደርጋለን በሚል የሴኔጋል መንግሥት ተነሳሽነትን ወስዶ ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ሊቀጥል አልቻለም። ይሁንና እንዲህ አይነቱ ተነሳሽነት በጣም ጥሩ የሚባል ጅማሮ ነበር። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ መርሃግብር ሥራዋ በአሁኑ ወቅት ከራሷ አልፎ ለሌሎች ጎረቤት ሀገሮች መትረፍ እየቻለች ነው፤ ችግኝ በመስጠት ላይም ትገኛለች፤ ይህ ደግሞ ጥሩ አሠራር ነው።

ጎረቤቶቻችን ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ በመራቆት ላይ እንዳሉ አካባቢዎች የሚታዩ ናቸው። ስለዚህም ለጎረቤቶቻችን ችግኝ ሰጠን ማለት በተዘዋዋሪ በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ እየሠራን ነው ማለት ያስደፍራል። መርሃ ግብሩን ባሰፋን ቁጥር የሥራ እድሉን መጨመር እንችላለን። ብሎም በምግብ ራስን መቻልንም እናፋጥናለን።

ያደጉ ሀገሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ የእኛም ኢኮኖሚ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። ይህ ሲሆን፣ አንዱ ወደሌላው አይሰደድም፤ ባለበት ሆኖ ሕይወቱን በአግባቡ መምራት ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- እርሶዎ እየተሳተፉባቸው ከሚገኙ ዘርፎች አንዱ የወንዝ ዳር ፕሮጀክት ነው። ስለፕሮጀክቱ ቢያብራሩልን ?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡– የወንዝ ዳር ፕሮጀክቱን የጀመርነው እኤአ በ2016 ነው። በጉዳዩ ዙሪያ በርከት ያሉ ሕትመቶች ታትመዋል። ለአብነት ያህል ላንድስኬፕ ዲዛይን ተጠቃሽ ሲሆን፣ በስሪ ጂ ድረስ ሰርተን አስረክበናል። ወደተግባር ከመግባታችን አስቀድሞ የመጀመሪያ ምርጫ ያደረግነው አዲስ አበባ ወንዞች እና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰነዱን ያሳተምነው እኤአ በ2017 ላይ ነው። ጥናቱ ግን የጀመረው አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት እኤአ በ2016 ላይ ነው።

ጥናቱን አጥኑ ብሎ ኃላፊነቱን የሰጠን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሆን፣ ለጥናቱ የተመረጡት 411 ኤክስፐርቶች ናቸው። ይህ ባለሙያ ደግሞ የተውጣጣው ከዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን ከሌላው ሴክተር ጭምር ነው። የጥናቱ አካል በአምስት ፈርጅ የተሳለጠ ነው፡፡

የጥናት ቡድኑ ያደረገው የመጀመሪያው ነገር መልማት ያለበት የትኛው ነው? የሚለውን መለየት ነበር። አንዱ የከተማ ማዕከል ላይ ትኩረት እናድርግ የሚለው ነው። የአዲስ አበባ ወንዞች 76 ናቸው። እነዚህ ወንዞች ወደ እንጦጦ አካባቢ በርከት ይላሉ። ወንዞቹ ሁሉ ተሰብስበው አቃቂ ሲደርሱ አንድ ይሆኑና ወደአባ ሳሙኤል ይገባል። 76ቱን ወንዞች መቀጠል ቢቻል 607 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ናቸው፤ እሱ ማለት ደግሞ ከአዲስ አበባ መቱ እንደማለት ነው። ይህን ያህል ርዝመት ያለውን ወንዝ ማልማት በጣም ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ መወሰን የሚገባው አንደኛው ከገንዘብ አኳያ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከጊዜ አኳያ ነበር። ከዚህ አንጻር ምን ማድረግ አለብን? በሚለው ዙሪያ ከመከርን በኋላ ማዕከላዊ ከተማ ላይ ለመሥራት ተስማማን። እሱም ማለት የወዳጅነት ፓርክን ጨምሮ ሸራተን አካባቢን ይዞ እስከ አፍንጮ በር ድረስ እንዲሁም ቀበናን የተወሰነ ክፍል በተጨማሪም ከአምባሳደር ወደ ጨው በረንዳ የሚሄድ ቁርጡሚ የሚባል ወንዝ አለና እነዚያ ላይ ትኩረት እናድርግ ተባባልን።

ለዚህ ምክንያታችን ደግሞ የመረጥናቸው አካባቢዎች የሀገሪቱ ማዕከላዊ ቦታዎች ናቸው። አካባቢው ደግሞ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚበዙበት ሲሆን፣ እንግዶችም አለፍ ገደም የሚሉበት አካባቢ ነው። ስለዚህም አካባቢውን እናስውብ በሚል ወደተግባር ለመግባት ተዘጋጀን። በዚህ ጊዜ የተለያዩ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች “እኔ ካላለማሁ፤ እኔ ካላለማሁ” ማለት ጀመሩ። ከመካከላቸው አንደኛው ሥራውን ጀመረ። በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ ሲስተዋል አካባቢው ከመልማቱ የተነሳ በሚገባ መዋብ ችሏል። እሪ በከንቱ ቀደም ሲል ማለፍ የማያስችል ቦታ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ሰው ወደሥፍራው ሲቃረብ የተሽከርካሪውን መስኮት ዝቅ አድርጎ ንጹህ አየር እየማገ መሄድ ጀምሯል። ሥራው በዚህ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን በቀጣይም ለሌላው ይቀጥላል።

እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ወንዞች ለአትክልትም ሆነ ለምንም አይነት ተግባር መጠቀም የሚያስችሉ አልነበሩም። በመሆኑም ወንዞቹ በሙሉ በተጀመረው አይነት ሥራ መልማት አለባቸው በሚል ታሳቢነት እየተሠራ ነው። ሥራውን ስንጀምር ማዕከላዊ የሆኑ ቦታዎችን እንዳስቀደምን ሁሉ ቀጥሎ ደግሞ ትልልቅ ወንዞች ላይ እንሥራ የሚል እንቅስቃሴ አለ፡፡

ወንዞቸቻችን ቆሻሻነታቸውን አስወግደው ኩልል ያለ ውሃ እስከሚኖራቸው ድረስ እንሠራለን የሚል ተነሳሽነት አለ። ምክንያቱም ወንዞቹን ካላጸዳን ከተማውን ማጽዳት አንችልም። ቆሻሻ መጣያ እና መጸዳጃ ሆነው የቆዩትን ወንዞቻችንን በመጀመሪያ ማጽዳት ይጠበቅብናል። እሱ ላይ ጠንክረን ከሠራን ብዙ ነገር አቃለልን እንደማለት ነው፡፡

ያደጉ ሀገራት ለምሳሌ ከጀርመን ተነስቶ ጥቁር ባሕር የሚገባ አንድ ወንዝ አለ፤ ይህ ወንዝ የሚሄደው በርካታ ሀገራትን አቋርጦ ነው። ጀርመን ወንዙ ከእርሷ ቅጥር ወጥቶ ወደ ኦስትሪያ ሀገር ሲሄድ የምታሳልፈው በአግባቡ ከብክልት ጠብቃ ነው። ለወንዞች የሚሰጡ ደረጃዎች አሉ፤ የምትሠራው ያንን ጠብቃ ነው። ወንዙ ኦስትሪያ ከተማ ሲደርስ ንጹህ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች ይዋኙበታል፤ ይዝናኑበታልም። አንድ ሀገር በሀገሩ ውስጥ አገልግሎት መስጠት የተገባውን ወንዝ መበከል ይቅርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ወደሌላው ሀገር በክሎ እና አቆሽሾ ማሳለፍ አይፈቀድለትም። ጀርመንም የጠበቀችው ያንን ሕግ ነው። የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ትርጉም ይህ ነው። እኛ ከዚህ አንጻር ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። የወንዝ ዳርቻዎቻችን ማልማት ለትውልዱ ሳምባ እንደመስጠት ነው፡፡

እሪ በከንቱ የነበረውን ቆሻሻ እና መጥፎ ሽታ አጽድተን ንጹህ የሆነ አካባቢ መፍጠር ችለናል። ይህንን ሌላ ቦታ ማስፋፋት አለብን። እንደ እነ ጅማ ያሉ ከተማዎች ሥራውን ጀምረዋል። ሌሎቹም በዚህ መልኩ መቀጠል አለባቸው ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑን በአጭር ጊዜ ተሠርቶ ለእይታ ግልጽ የሆነ የኮሪደር ልማቱን በተመለከተ ያልዎት አመለካከት ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡- እንደሚታወቀው የኮሪደር ልማቱ በሚያስደንቅ ፍጥነት ከመሠራቱ በተጨመማሪ ውበቱን በመመልከት ላይ ነን። የአራት ኪሎን አቅጣጫ ተከትል በምንንቀሳቀስበት ወቅት የምናጤነው ነገር ቢኖር ውበቱን ነው። በዚህ አካባቢ ያለው የእግረኛ መንገድ በእግር ለመንቀሳቀስ ምቹ ሆኖ ተሠርቷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከተሞች አብዛኞቹ በወታደራዊ የጦር ኃይል የተፈጠሩ ናቸው፤ በአካባቢው የወታደር ካምፕ ሲሠራ ያንኑ ተከትለው የሚሰፍሩ በመሆናቸው ከተሞቹ ፕላን ያላቸው አይደሉም። አንድ የአስፓልት መንገድ በየከተማው ካለ በእርሱ ላይ መኪናው፣ ሰው እና እንስሳው ይሄዳል። ይህ ማለት የሰው እንቅስቃሴ ታገተ እንደ ማለት ነውና ኮሪደር ያስፈልገናል። ለምሳሌ የኪጋሌን ከተማ ላስተዋለ በጣም ጽዱ ከተማ መሆኗን ይረዳል።

ፕሬዚዳንቱ ከሠሯቸው ነገሮች አንዱ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ተጠቃሽ ነው። ወደ ኪጋሌ ያቀና የትኛውም ሰው ከአየር ማረፊያው ሲደርስ ከመውረዱ አስቀድሞ የፕላስቲክ ከረጢት አለመያዙን ደጋግሞ ማጤን ይጠብቅበታል። ሰነድ የተያዘበት የፕላስቲክ ከረጢት እንኳ ቢሆን ይዞ ወደከተማው መግባት አይቻልም። የዚያን ያህል ለአካባቢ ጥበቃ ጥብቅ ናቸው። የአካባቢ ጥበቃ ላይ መሠራት ያለበት እነደዚህ ነው።

በዚህ አግባብ በአሁኑ ወቅት በእኛ ሀገር እየተከናወነ ያለው የዘመነ የኮሪደር ልማት ነው፤ እርሱም ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ያለ ነው፡፡

ከዚህ ለልማት ጋር ተያይዞ ከተማው ውስጥ እየተሠራ ካለው ልማት የሀገር በቀል ዛፎችን ያለመትከል ነገር ይታያል። ሁሌም ቢሆን ባለሙያ ያስፈልጋል። ሀገር በቀል ዛፎች ላይ ትኩረት ብናደርግ ተመራጭ ነው። ሀገር በቀል ዛፍ ቅጠለ ሰፋፊ በመሆኑም የሚስበው ብዙ ካርበንን ነው። ከእድሜ አንጻር እንኳ ሲታይ ሀገር በቀል ያልሆኑ ዛፎች ብዙ አይቆዩም፤ ይወድቃሉ። ተፈጥሯቸው ተስማሚ የሚሆነው ለተወለዱበት አካባቢ ነው።

ለምሳሌ መናገገሻ ሱባ ውስጥ ያለውን የእኛን ጥድ ብንወስድ እስከ 500 ዓመት መቆየት የሚችል ነው። ይህ የእድሜውን መርዘም ብቻ ለመግለጽ ሳይሆን ብዙ ዓመት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም ለመጥቀስ ጭምር ነው። የሚቆመው ዛፉ ብቻ ሳይሆን ከዛፉ ጋር ብቻ ግንኙነት ያላቸው እንስሳት አሉ። ከዚህ አንጻር ትርጉሙ ብዙ ስለሆነ የኮሪደር ልማታችን በጣም ደረጃውን የጠበቀ ነው።

አንዱ የአካባቢ ደህንነት ሕግ የሚለው ነገር ቢኖር ዜጎች ንጹህ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው ነው። ስለዚህ ለዜጎች ንጹህ አካባቢን መፍጠር የግድ ነው። አሁን አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው ይህ በጎ ተግባር በሌሎቹም ከተሞች ላይ ተጠናክሮ መሠራት ያለበት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሀገሪቱ ቆሻሻ አወጋገድ ምን ይመስላል? ከዚህ አንጻር ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡- በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው ጥሩ የሚባል ሥራ እየሠራ ነው፤ የቆሻሻ አወጋገድ ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ነው። ቆሻሻ ገና ከቤት ሳይወጣ እንደየባህሪው ልየታን ማካሄድ ያስፈልጋል። ሕያው (Organic) ቆሻሻ ለብቻ፣ ብርጭቆ ለብቻ እንዲሁም ላስቲኩንም ለብቻ እዛው ቤት ውስጥ መለየት መቻል አለበት፡፡

እንደየወገኑ ሲሆን፣ ቆሻሻነቱ ቀርቶ ለተለያየ ጥቅም መዋል ይችላል። ሕያው (Organic) የሆነው ቆሻሻ ደግሞ የዶሮ እና የእንስሳት ምግብ ይሆናል። ቆሻሻ ጥቅም ላይ ሲውል የሚበከል አካባቢ አይኖረንም። አሁን አሁን ደግሞ ከቆሻሻ ነዳጅ አሊያም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተጀምሯል። ስለዚህ ቆሻሻ ሀብት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከሙያዎ ጎን ለጎን በዋናነት የሚሠሩት ቋንቋን በጉግል የመተርጎሙን ሥራ እንደሆነ ጠቅሰዋል፤ ይህ ጉዳይ እንደ ሀገር አቀፍም ሆነ እንደዓለም አቀፍ ጅማሮውን ያደረገው መቼ ነው?

ፕሮፌሰር ተሾመ፡– በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጀመረው እኤአ በ2006 ነው። ያደጉ ሀገራት ቋንቋዎች፤ እንግሊዝኛ፣ ስፓንሽ፣ አረብኛና ሌሎችም ቋንቋዎች ዲጂታይዝድ የሆኑት በዚሁ በጅማሬው ወቅት ነው። ወደ እኛ ስንመጣ ግን የተጀመረው በቅርቡ ነው። እንዲያውም በሀገራችን ከሚነገሩ ቋንቋዎች ፈጠን ካሉት መካከል አንዱ አፍ ሱማሌ ነው። አፍ ሱማሌ ቋንቋው ዲጂታይዝድ የሆነው እኤአ በ2013 ሲሆን፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጎረቤታችን ሱማሊያ ቋንቋዋን ዲጂታይዝድ በማድረጓ ምቹ ሁኔታ ስለተፈጠረለት ነው። በተመሳሳይ ትግርኛ ቋንቋም እንዲሁ ሲሆን፣ ኤርትራም ቋንቋዋን ቀድማ ዲጂታይዝድ በማድረጓ ትግርኛ ቋንቋ በቀላሉ አገልግሎቱን ማግኘት ቻለ።

ይሁንና በኢትዮጵያ የታሰበው ግብ ጋ ለመድረስ አሁንም ቢሆን በስፋት መሥራት የግድ ይላል። አንድ ቋንቋ ትክክለኛ ትርጉም ላይ ደርሷል የሚባለው ለምሳሌ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አንድ አምስት ሚሊዮን ያህል የሚሆኑ ቃላትን ማስገባት ከተቻለ ማሽኑ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ መሥራት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት አንድ ሰነድ ለአማርኛ ቋንቋ ቢቀርብ ማሽኑ የሚሰጠው የትርጉም አገልግሎት የተንበዛበዘ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አስፈላጊውን መረጃ አለመስጠታችን ነው። ሙሉ ለሙሉ ዳታው አልገባለትም ማለት ነው። ስለዚህ ዳታውን አስገብተን ስናጠናቅቅ የተጣራ መረጃ የሚሰጠን ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ዲጂታላይዝድ የሆኑ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ እና አፍ ሱማሌ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቋንቋን ዲጂታይዝ ማድረግ ፋይዳው ምንድን ነው? ሁሉን ለማሽን መስጠቱ የሰውን ልጅ በማሰቡ ረገድ ማዳከም አይሆንም?

ፕሮፌሰር ተሾመ፡- ቋንቋን ዲጂታይዝ ማድረግ ሊሞት የተቃረበን ቋንቋ ጭምር ሕይወት መዝራት የሚያስችል ነው። መረጃውን ማሽን ላይ ካስቀመጥን አንድ ለመሞት የተቃረበን ቋንቋ መታደግ እንችላለን። ቋንቋን ዲጂታይዝ ካደረግን በኋላ ለተለያዩ ተግባራት ይውላል። ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 133 የሚሆኑ ቋንቋዎች ዲጂታላይዝድ ሆነዋል። ይህ ማለት ደግሞ አንድን ቋንቋ ወደ 132ቱ ቋንቋዎች መተርጎም ይቻላል እንደማለት ነው።

በእርግጥ የሰው ልጅ ያለማሽን መንቀሳቀስ እንዳይችል ከማድረግ አኳያ ተጽዕኖው ግልጽ ነው። በአሁኑ ወቅት ማሽን ላይ ተደግፈናል ማለት ይቻላል። ሌላው ቢቀር የስልክ ቁጥር ማስታወስ ጭምር ትተናል። ሁሉ ነገራችን በተንቀሳቃሽ ስልካችን ላይ ሆኗል። ሰዎች አዕምሯቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ከመሥራት ይልቅ ማሽን ላይ እንዲደገፉ እያደረጋቸው ነው።

ይሁንና በአንድ በኩል ነገሩ ሕይወትን ቀለል እያደረገ ነው። ድሮ በብዙ ድካምና ልፋት የሚሠራ ሥራ እና ሥራው የሚወስደው ረጅም ጊዜ ብዙ ጉልበት ሳናወጣና በሰከንዶች ውስጥ መሥራት ወደሚያስችል መምጣት አስችሏል። እየሠራንበተት ያለው ማሕበር ስም “አፋን አፍሪካ አሶሴሽን” (Afan Africa Association – 3A) ይባላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ፕሮፌሰር ተሾመ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You