በአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት ተስፋ የታየበት የአፍሪካ ሻምፒዮና

በካሜሮን፣ ዱዋላ ሲካሄድ በቆየው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዕውቅና መርሐ ግብር ዛሬ ይደረጋል። ትናንት ምሽት ወደ ሃገሩ የገባው ብሔራዊ ቡድኑ 4ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ የሚታወቅ ነው። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በውድድር መድረኩ ሃገራቸውን ለወከሉ አትሌቶች ረፋድ ላይ ዕውቅና የሚሰጥ ይሆናል።

በሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ ስፖርቶች ሃገራትን የሚያፎካክረው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዘንድሮ በካሜሮን አዘጋጅነት ላለፉት ስድስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል። ከአህጉሪቷ 27 ሀገራት የተውጣጡና ከ2ሺህ 500 በላይ አትሌቶች የተሳተፉበት ውድድሩ በደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል። ሃገሪቷ 20 ሜዳሊያዎችን መሰብሰቧ ቀዳሚ ያደረጋት ሲሆን፤ ኬንያ በ19፣ ናይጄሪያ ደግሞ በ15 ሜዳሊያዎች ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል። አራተኛዋ ሃገር ኢትዮጵያም 5 የወርቅ፣ 4 የብር እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችላለች።

እነዚህ ሜዳሊያዎች የተገኙትም ባሳተፈቻቸው 32 ሴት እና በ36 ወንድ፤ በድምሩ 68 አትሌቶች ነው። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በሩጫና በሜዳ ተግባራት የተሳተፈች ቢሆንም ውጤት የተገኘው ግን በተለመዱት ርቀቶች እና በእርምጃ ብቻ ነው። በዚህም በ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ርቀቶች የተወዳደረው አትሌት ንብረት መላክ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ቀዳሚው ሆኗል። ልምድ ካላቸው አትሌቶች መካከል የሚመደበው ንብረት ከ5ሺህ እስከ ግማሽ ማራቶን በመሮጥ ይታወቃል። ከወራት በፊት በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይም በ10ሺህ ሜትር ለሃገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበ ሲሆን፤ ያለፈው ዓመት የሊዝበን ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊም ነው።

በወንዶች ምድብ ሁለተኛው የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ በአትሌት ምስጋናው ዋቁማ የተገኘ ነው። ተጨማሪዎቹ የወርቅ ሜዳሊያዎችም በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር በአትሌት ሳሮን በርሄ፣ በ5ሺህ ሜትር ፈንታዬ በላይነህ፤ እንዲሁም በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ስንታየሁ ማስሬ ተመዝግበዋል። የብር ሜዳሊያዎቹም በ5ሺህ ሜትር በአትሌት ውብርስት አስቻል እና በ3ሺህ ሜትር በአለምናት ዋሌ፤ እንዲሁም በወንዶች 10ሺህ ሜትር በአትሌት ድሪባ ገመቹ በብቸኝነት ተመዝግቧል። ኬንያዎች የበላይነቱን በያዙበት የሴቶች 10ሺህ ሜትር ደግሞ አትሌት ገላ ሃምቢሴ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ብቸኛውን የነሐስ ሜዳሊያ ለሃገሯ አስገኝታለች።

በዚህ ውድድር ከተሳተፉት አብዛኛዎች አትሌቶች ወጣቶች ሲሆኑ፣ በዓለምና አሕጉር አቀፍ ውድድሮች ልምድ በመቅሰም ላይ የሚገኙና በቀጣይም ታላላቅ የውድድር መድረኮች ላይ ሃገራቸውን ይወክላሉ በሚል ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው። በተወሰኑ ርቀቶች ውጤት ማስመዝገብ ባይቻልም ኢትዮጵያ በታወቀችባቸው የረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ግን እንደተለመደው ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። በሌሎች የውድድር ዓይነቶች ደግሞ በርካታ ዲፕሎማዎች የተመዘገቡ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ዲፕሎማዎች የተገኙባቸውና ማጣሪያውን አልፈው የፍጻሜ ፉክክር ውስጥ መግባት የተቻለባቸው ውድድሮችም ኢትዮጵያ እምብዛም የማትታወቅባቸው የአጭር ርቀት አትሌቲክስ፤ እንዲሁም የሜዳ ተግባራት ናቸው። ይኸውም በስፖርቱ ወደ ስኬት የመጠጋት ተስፋን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ በምን መልኩ ሊሠራበት ይገባል የሚለውን ለፌዴሬሽኑም ሆነ ለስፖርቱ ባለሙያዎች አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው። የኢትዮጵያ የዘንድሮው የሻምፒዮናው ተሳትፎዋ በበርካታ ስፖርቶች መሆኑ በአጭር ርቀት ሩጫ፣ ዝላይ፣ ውርወራ እና እርምጃ የሚሳተፉ አትሌቶች ዓለም አቀፍ የውድድር ልምድ የሚያገኙበትን ዕድል የፈጠረላቸው ከመሆኑ ባለፈ ያሉበትንም ደረጃ የሚገመግሙበት ነው። በመሆኑም ተሳትፎው በተለያየ አቅጣጫ ስፖርቱን የሚጠቅምና ለወደፊትም መሰል ውድድሮች ላይ በስፋት መካፈል ያለውን ጠቀሜታ ያመላከተ ነው ሊባል ይችላል።

የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እአአ ከ1979 አንስቶ በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ውድድር ነው። በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የሚመራው ይህ ውድድር በየመሐሉ ወቅቱን ሳይጠብቅ የሚካሄድ ቢሆንም ዘንድሮ 23ኛው ላይ ደርሷል። እአአ በ2008 ሻምፒዮናውን የማስተናገድ ዕድል ገጠሟት የነበረችው ኢትዮጵያም ከመድረኩ በሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች በሜዳሊያ ዘንጠረዡ 6ኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ ችላለች። ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ እና ሞሮኮም ከአንድ እስከ አምስት ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You