የኬሮድ 15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በወልቂጤ ከተማ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓም የሚካሄድ ይሆናል:: በውድድሩ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ለአሸናፊዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱም ታውቋል::
በጉራጌ ዞን፣ ወልቂጤ ከተማ ላይ የሚደረገው ዓመታዊው ኬሮድ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ታስቦ የሚደረግ ሲሆን፤ ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ለማካሄድ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው::
ውድድሩ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም መነሻውን ወልቂጤ ዪኒቨርሲቲ፣ መድረሻውን ደግሞ ወልቂጤ ከተማ በማድረግ እንደሚካሄድ የሩጫው አዘጋጆች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል:: ከአዋቂዎች ውድድር በተጨማሪ የ1 ኪሎ ሜትር የዊልቸር ውድድር፤ እንዲሁም የሕጻናት ሩጫ ለማካሄድም ከዞኑ አስተዳደር ጋር ውይይት እየተደረገ ነው:: ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድና የፀጥታ ችግር እንዳይገጥምም ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል::
በውድድሩ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ምዝገባውም ከዛሬ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓም ጀምሮ እንደሚካሄድም ተነግሯል:: በርካታ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ በሚጠበቀው ሩጫ፤ ከ600 በላይ አትሌቶችን እና ከ10ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍልን ለማሳተፍ ታቅዷል:: ለውድድሩ ወደ ከተማዋ ለሚጓዙ አትሌቶችም ከወልቂጤ ዪኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የደርሶ መልስ መጓጓዣ፤ እንዲሁም ማረፊያ ተዘጋጅቷል:: የከተማዋ ነዋሪም በስፋት ወጥቶ በሩጫው እየተዝናና እንዲሳተፍም ከፍተኛ የቅስቀሳ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተገልጿል::
በውድድሩ ለሚያሸንፉ አትሌቶች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ክብረወሰን የሚያሻሽሉ አትሌቶች ደግሞ ተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል:: በሁለቱም ፆታዎች አንደኛ ደረጃን በመያዝ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች 100ሺህ ብር ሲሸለሙ፤ በወንዶች 43 እና በሴቶች 51 ደቂቃ የሆነውን የቦታውን ክብረወሰን የሚያሻሽሉ አትሌቶች ተጨማሪ ጉርሻ ያገኛሉ:: ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ለሚያጠናቅቁትም የገንዘብ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን እንደየደረጃው ከ50ሺህ ብር እስከ 5ሺ ብር ሽልማት ይበረከትላቸዋል::
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተሳተፈው አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ፤ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ተሳታፊ እንዲወዳደር ከዞኑ አስተዳደር ጋር እየሠሩ መሆኑን ጠቁሟል:: የውድድሩ ዓላማ ለታዳጊ አትሌቶች የውድድር ዕድልን መፍጠር ነው:: በከተማዋ የሚገኙ ታዳጊ አትሌቶች የውድድር ዕድልን በማግኘት የክለቦች ዓይን ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ዋንኛው ግቡ ነው:: ከውድድሩ በተጨማሪም በአራት ክልሎች የታዳጊ ፕሮጀክቶችን ለማቋቋምም ታስቧል:: የውድድሩን ደረጃ ከፍ ለማድረግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ እንደሆነም ገልጿል::
አትሌት ሰለሞን ባረጋ በበኩሉ ክረምት መሆኑ ለውድድር አመቺ ባይሆንም ከሌሎች ውድድሮች ጋር እንዳይጋጭ ታስቦ በዚህ ወቅት እንደሚካሄድ ጠቅሷል:: ለውድድር የሚያመቸውን ጊዜ ለመምረጥ ከአትሌቶች ጋር ውይይት መደረጉንና ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት እና ማጠናቀቂያ ላይ ለማካሄድ ታስቦ እየተሠራ መሆኑንም ገልጿል:: ከዚህ በፊት በተካሄዱ ሦስት ውድድሮች ጥሩ ምልክት የታየ ሲሆን፣ ዘንድሮም ውጤታማ አትሌቶችን ለማግኘት ዝግጅት ላይ ይገኛሉ::
ማኅበሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የክልል ከተሞች ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር የማድረግ ፍላጎት ቢኖረውም በፀጥታ ስጋት ምክንያት እንዳልተቻለ ተመላክቷል:: ውድድሩ እስከ አሁን በወልቂጤና ቡታጅራ እየተካሄደ ያለ ሲሆን በቀጣይ ወራቤ እና በሆሳዕና ከተሞች ለማካሄድ፤ ከዚያም በሁሉም ክልሎች ለማስፋፋት ታቅዶ ከፌዴሬሽኖች ጋር እየተሠራ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል::
ኬሮድ ሩጫ አዘጋጅ ማኅበር የተመሰረተው በታዋቂ አሰልጣኞችና አትሌቶች ሲሆን አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ ሙክታር እድሪስ፣ አየለ አብሽሮ፣ ጥላሁን ኃይሌ እና አሠልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ከመሥራቾቹ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው::
በመድረኩ የተሳተፉ አትሌቶች ከሽልማት በተጨማሪ የውጪ የውድድር ዕድሎችን በማግኘት ራሳቸውን ማሳየት እንደቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ ከ1-25 ባለው ደረጃ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች ውጪ ሄደው እንዲወዳደሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መፍቀዱንም በጋዜጣዊ መግለጫው ተብራርቷል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም