የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነትና መልካም ፈቃድ ለኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በማሳተፍ ነፃ አገልግሎት የሚያበረክቱበት ተግባር ነው::
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም አይነት ክፍያ የማያገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የህሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራሱ ተነሳሽነት የሚፈፅመው ተግባር ነው:: ይህ ተግባር ሰዎች ዘር፤ ቀለም ብሄርና ኃይማኖት ሳይለያቸው የሚሳተፉበት በጎ ተግባር ነው::
ሆኖም በገቢር እንደሚታየው የበጎ ፈቃድ በተነሳ ቁጥር ሁልጊዜ ግንባር ቀደም ሆነው የሚገኙት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የመንግሥት አካላት ብቻ ናቸው:: ለቁጥር የሚያዳግቱት አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በጎ ፈቃድ ሥራ ሲመጣ የት እንደሚገቡ አይታወቅም::
የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረት ዋነኛ ጉዳይ የሀገር ልማት እና እድገት እስከሆነ ድረስ አብዛኞቹ ፓርቲዎች በበጎ ፈቃድ ለመሳተፍ ዳተኛ የሆኑበት ምክንያት እንቆቅልሽ ነው:: የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምስረታቸው ጀምሮ እስከ ሥልጣን ድረስ ያሰቡትን ዓላማ ማሳካት የሚችሉት ሀገር ስትለማ ነው:: ሀገር የምትለማው ደግሞ በፖለቲካ ዲስኩር ወይም በፖለቲካ ሽኩቻ አይደለም::
በሠለጠኑት አለማት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱና ዋነኛ መመዘኛ የበጎ ፈቃድ ሥራ ነው:: ተወዳድሮ ለማሸነፍና ሥልጣን ለመያዝ የመጀመርያው መመዘኛ ፓርቲው ወይም ግለሰቡ የሰራቸው በጎ ፈቃድ ሥራዎችና ያመጣው ውጤት ነው:: ያለበለዚያ በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብና የመንግሥትን ህጸጽ እየፈለጉ ብቻ በመውቀስ ሥልጣን ላይ ፊጥጥ ማለት አይታሰብም::
የእኛ ሀገር የፖለቲካ ፓርቲዎች እሳቤ የሚመነጨው በተገኘው አማራጭ ሁሉ ወደ ሥልጣን መምጣት እንጂ ባከላቸው ጊዜ ለሕዝብ እና ለሀገር በጎ ሥራ መስራት አይደለም :: ለማንም ክፍት የሆነውና ሁሉም በሠብዓዊነት የሚሳተፍበትን የበጎ ፈቃድ ሥራ ለፖለቲከኞቻችን የተከለከለ ይመስል በአጠገቡም ዝር አይሉም:: እነሱ ሥልጣን ካልያዙ በስተቀር ሀገር የሌለች ይመስል ከፖለቲካ ወቀሳና ማጣጣል በስተቀር አባሎቻቸውን አስተባብረው ይህ ነው የሚባል የበጎ ፈቃድ ሥራ ሲሠሩ አይታይም::
አሁን በእጃቸው ያለውን የበጎ ፈቃድ ሥራ ሳይሠሩ ነገ ሥልጣን ጨብጠው የሚሠሩትን ሥራ እና የሚለውጡትን ሀገር ያልማሉ:: ይህ ደግሞ ህልም እንጂ እውን ሊሆን አይችልም::
ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ ባህል ስናይ በጎ ሥራ ሠርቶ ሀገር እና ሕዝብን ከመጥቀም ይልቅ የራስን ጥቅም፤ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስን ስሜት፤ ከሀገር ህልውና የፓርቲ ህልውናና ማስቀደም ላይ ትኩረት የሚደረግበት ነው:: ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ላልተገባ እሰጥ እገባና ግጭት አልፎ ተርፎም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትዘልቅ አድርጓታል::
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጉድለት ፖለቲካን ከሸፍጥ ጋር መቆራኘቱ ነው:: ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ በጎ ሥራ መሥራት የተከለከለ ይመስላል:: ይልቁንም ሴራ መተንተንና መንግሥትን መውቀስ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጥንካሬ መለኪያ ተድርጎ እየተወሰደ ሀገር እና ሕዝብም ከፖለቲከኞች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እያጡ ነው፤ ይባሱንም ሀገርና ሕዝብን በማያራምድ አጀንዳ ሰቅዘው የኋሊት እንድንጓዝ እያደረጉን ነው::
የፖለቲካ ሥርዓታችን ለሀገር በጎ ማሰብና አለፍ ሲልም በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ውስጥ ተሳትፎ ሕዝብና ሀገርን ከመጥቀም ሀገር በትብብር እንዳትቆም የጥላቻ መርዝ መንዛት ነው:: ተባብሮ ተደጋገፎ ሀገርን ማቆም ፖለቲከኞቻችን በሩቁ የሚሸሹት ጸበል ነው::
ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው:: አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሠረት ሌሎችን አጥፍቶና አንቋሾ፤ ጥላቻ ዘርቶና አኮስምኖ የራሱን ሥብዕና ለመገንባት ሲሞክር ማየት የተለመደ ነው::
በጋራ ሠርቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ መልካም ሥራ ሊሠራ የተነሳን ወገን ማንቋሸሽና በሕዝብ ዘንድም በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ የኖርንበትና እየኖርንበት ያለ ሀቅ ነው:: በየጊዜው ጥላቻና ግጭትን መፈብረክ ሀገርን የኋሊት እንድትጓዝ ማድረግ አንዱ ፖለቲካ ታሪካችን ነው::
ሀገርን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀምና የአቅምን ያህል ሃሳብ ከማዋጣት ይልቅ ሀገርን በሚያፈርሱ አጀንዳዎች ውስጥ መጠመድ ፤ አለፍ ሲልም ሃሳብን በነፍጥ ለመጫን ማዳከር አንዱ የእኛነታችን መለያ ሆኖ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፤ ዛሬም የሚታየው ሀቅ ይኸው ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ማቀዷን ይፋ ሲያደርጉ ከልቡ የተቀበለው ጥቂቱ ነበር፤ ለመዘባበት የሚሞክሩም ብዙ ነበሩ:: ሆኖም በመጀመርያ ዓመት ብቻ ከ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል እንዲሁም በአንድ ጀንበር ደግሞ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በዘመቻ በመትከል ኢትዮጵያ ታሪክ ጻፈች::
በቅን አሳቢ ኢትዮጵያውያን በተደረጉ ጥረቶችም እስከ አምና ድረስ 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ማስተከል ችለዋል:: አምና በአንድ ጀንበር 569 ሚሊዮን ችግኝ በመትከልም ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረክ ፋና ወጊ መሆን ችለዋል::
ጉዳዩን በቅርብ የተረዱ ወገኖች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የሚካሄደውን፣ የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ ዘመቻን የሚደግፉ ሰዎች፣ የችግኝ ተከላው የሀገሪቱን የአረንጓዴ እጽዋት ሽፋንን እንዳሳደገ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እየተከላከለ እና የሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ቢናገሩም አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህ መልካም ሥራ ብዙም እውቅና ሰሲሰጡ አልታዩም።
እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተቋቋሙ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ስትጎዳ ተመልክተዋል:: ድርቅ በየአመቱ እየደጋገመ እየመጣ በርካቶችን ከአካባቢያቸው ሲያፈናቅል፤ ሲያሳደድና ሰዎች በርሃብ ሲሞቱ ተመልከተዋል:: ሆኖም የእኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሩን ቁጭ ብሎ ከመመልከት ወይንም ደግሞ ወቃሽ ከመሆን ድርቅን በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻልበትን አማራጭ ሲጠቁሙ አይታዩም::
አለፍ ሲልም ያላቸውን ዕውቀትና የአባላት ብዛት በመጠቀም አስተባብረው ችግኝ ሲተክሉ አይታዩም:: አረንጓዴ ዐሻራ መትከል በጎ ፍላጎትንና ቅን አሳቢነትን እንጂ ሥልጣንን ወይንም ገንዘብን አይጠይቅም:: ስሙ እንዲህ የሚባል ፓርቲ አባላቱን አስተባብሮ ይሄን የሚያክል ችግኝ ተከለ የሚባል ዜና የምንሰማው መቼ ይሆን?
በተመሳሰይም አንድ ፓርቲ አባላቱን አስተባብሮ የድሃ ቤት ማደስ ለሀገር ለወገን ማሰብን እንጂ የተለየ ጥበብን አይጠይቅም:: እንዲሁ ለአፍ እና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ለድሃው የቆምኩ ነኝ የሚለው ፕሮፓጋንዳ ትዝብትን ከማትረፍ ውጪ የሚያሰገኘው ፋይዳ የለም::
ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የተለበሱ ሕዝቦች ናቸው:: በርሃብም ሆነ በድርቅ፤ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል::
ኢትዮጵያውያን ዘር ፣ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፣ የተራበን ማብላት፣ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል:: እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባህር አቋርጦ፣ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው ፣ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው::
ይህ የመተሳሰብ ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና ድሃ ድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው::
በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅመ ደካማ ቤቶች እየታደሱ ከዝናብና ከጎርፍ ለመታደግ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው:: በዚህም በርካቶች ከስቃይና ከመከራ ተላቀው በጎ አድራጊዎችን ሲያመሰግኑና ሲመርቁ ተሰምተዋል::
በየዓመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅም ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው::
በዚህ በጎ ፈቃድ ሥራ ውስጥ በርካታ ወጣቶችና ሴቶች አለፍ ሲልም በጎ አድራጊ ባለሀብቶች ሲሳተፉ ቢታዩም ፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ግን ከሰልፉ ውስጥ አልታዩም:: በተለይም ተወዳድረን፤ ሥልጣን ይዘን ፤ ሀገር እንመራለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጎነታቸውንና ለሀገርና ለወገን ያላቸውን ተቆርቋሪነት ማሳያው ጊዜ አሁን ሊሆን በተገባ ነበር:: ግን በእድሉ ሲጠቀሙ አይታዩም::
በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማእድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው:: በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው:: እዚህስ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን የታሉ?
የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረትና ህልውና ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው:: ወጣቱን ያልያዘ የፖለቲካ ፓርቲ ቀጣይ ሕይወት አይኖረውም:: ሆኖም አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ወጣቱን በስሜት ከመቀስቀስና መንግሥት ላይ ከማነሳሳት በዘለለ ዘላቂ የሆነ መርሃ ግብር ቀርጸው የወጣቱን ሕይወት ለማሻሻል ሲጥሩ አይታዩም::
በአሁኑ ወቅትበ ወጣቱ በመጤ ባህሎችና በአጓጉል ሲሶች እየተጠቃ ይገኛል:: ይህ ደግሞ የነገ ሀገር ተረካቢ ብለን በየመድረኩ የምናነሳውን ወጣት ሕይወት በእጅጉ የሚጎዳና ጦሱም ለሁላችንም የሚተርፍ ነው::
ነገር ግን የወጣቱ በሱስ ውስጥ መዘፈቅና በመጤ ባህሎች መመረዝ አሳስቦት እንቅስቃሴ ያደረገ ፓርቲ አላጋጠመኝም:: ቢያንስ ወጣቱ ከአጓጉል ሱስ እንዲጠበቅ ግንዛቤ የሚፈጥሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ማዘጋጀትና ወጣቱ ላይ ንቃት መፍጠር የተለየ ክህሎት የሚጠይቅ አይደለም::
በተመሳሳይም ስለሚደፈሩ ሴቶች መከራከርና ጥብቅና መቆምም የእነዚሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ መለያ መሆን ነበረበት:: እዚህ ጉዳይም ላይ አልፎ አልፎ ከሚሰነዝሩት ትችት በስተቀር የሴቶችን መደፈርና ሠብዓዊ መብት መከበር በተመለከተ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥረት ሲያደርጉ አላየናቸውም::
የኑሮ ውድነቱን ከፖለቲካ ፍጆታ ነጥሎ በመመልከት አባላቱን አስተባብሮ የሰው ኑሮ የሚቀነስበትን መላ መዘየድ እና ተግባራዊ እቅስቃሴ ማድረግስ እንደ ኒዩክለር ሳይንስ የከበደው ለምንድን ነው ?
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም