የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለውጡን ተከትሎ በአዲስ መልክ ከተደራጁ ክልሎች አንዱ ነው፡፡ በአዲስ መልክ ከተደራጀ ዓመት ያልሞላው ክልል ቢሆንም ክልሉ ላይ የሚስተዋለው አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴና የሰላም ሁኔታ ግን ልብን የሚሞላ ነው፡፡
አዲስ ዘመንም በዛሬው ወቅታዊ እትሙ በክልሉ እየተከናወኑ ስላሉ የሰላም፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንዲሁም እንደሀገር ለውጡን ተከትሎ በተገኙ ስኬቶች፣ ፈተናዎችና የታለፈባቸው መንገዶች ዙሪያ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በክልሉ ለተገኙት የጋዜጠኞች ቡድን የሰጡትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት የለውጥ አመራሩ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ሥራዎችና የነበረው ቁርጠኝነት ምን ይመስላል?
አቶ እንዳሻው፡- የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተመሠረተው ነሐሴ 12 እና 13 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ነው:: ነሐሴ 12 ቀን ክልሉ ተመስርቶ ነሐሴ 13 ደግሞ ልዩ ልዩ አዋጆች ለሥራ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ከጸደቁ በኋላ ወደ ሥራ ገብተናል:: የክልሉ በአዲስ መልክ መደራጀት የለውጡ ቱርፋቶች መካከል አንዱ ነው::
ባለፈው ስድስት ዓመት የነበረው ለውጥ የተመራበት መንገድ የሚባለው ፣‹ሪፎርም› ነው:: ሁለት ዓይነት የሚታወቁ ለውጦች አሉ:: አንዱ ‹ሪፎርም› ሲሆን፣ ሁለተኛው ‹ሪቮሉሽን› ነው:: ‹ሪቮሉሽን› አንድ መንግሥት ተቀይሮ ሌላ መንግሥት ሲመጣ አጠቃላይ ያለፈው መንግሥት ሲሠራባቸው የነበሩ የፀጥታ ፣ የፋይናንስ፣ የደህንነትና የመከላከያ መዋቅሮች እና ሌሎችም መንግሥታዊ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሁሉንም አፍርሶ በአዲስ ማደራጀት ነው::
የእኛ መንግሥት የተከተለው ሪፎርም ነው:: በሪፎርም ሂደት ከነበሩት ነገሮች የተሻለ ነገር ካለ ይወሰዳል:: ለዘመኑ የሚሆኑ አዳዲስ ሃሳቦች እንዲገቡ ይደረጋል:: ወደፊት ደግሞ ሊያሻግሩ የሚችሉ ስትራቴጂክ የሆኑ ነገሮች ይታከላሉ:: ከነበረን ነገር ይወስድና ራሱ ጨምሮ ለወደፊት ደግሞ የሚሄድበትን ነገር አይቶ የሚሠራ የለውጥ ዓይነት ነው:: ስለዚህ መንግሥት አጠቃላይ የተከተለው የለውጥ ሂደት ሪፎርም ነው::
በዚህ ሂደት ያለፉትን አምስትና አራት ዓመታት ያሳለፍነው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር ነው:: ከዛ በኋላ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል ለሁለት ተከፍሏል:: በዚያን ወቅት በጋራ የተጀመረውን ሥራ ማእከላዊ ኢትዮጵያ ከሆነ በኋላ አንዳንዶችን ሥራዎች በላቀ ሁኔታ አንዳንዶችን ሥራዎች ደግሞ ከተጀመሩበት ባሕሪና ይዘት አንጻር እያየን የማስቀጠል ሥራ ሠርተናል:: ሪፎርም በባህሪው ከባድ ነው:: ብዙ የነበሩ ነገሮችን በጥቅሉ ይዞ ስለሚሄድ አመለካከቶችን ለማጥራት ሥራ የሚሠራው በአስተሳሰብ ነው፤ እሱን አጥርተን ተገቢው ደረጃ ላይ ማድረስ ይኖርብናል:: በርካታ ያላለቀላቸው ጉዳዮች ደግሞ በየጊዜው ይነሳሉ:: ለእነሱ በቂ ምላሽ መስጠት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ሕብረተሰቡ የደረሰበት ደረጃ አዳዲስ ጥያቄዎች የሚያነሳበት ጊዜ ነበረ:: እነርሱ ላይ በደንብ አስቦ ለጥያቄዎች መልስ መስጠት የመሳሰሉት ጉዳዮች በለውጡ ሂደት ውስጥ በደንብ ታስበው የተሠሩ ናቸው:: ክልላችንን ጨምሮ ሌሎች አዳዲሶቹ ክልሎች የዚህ ለውጥ ቱርፋቶች ናቸው ብለን መውሰድ እንችላለን::
የክልሎቹ በአዲስ መልክ መደራጀት ዋንኛ ዓላማዎች ለሕዝቡ አገልግሎትን በቅርበት መስጠት፣ ተመሳሳይ ሥነልቦና ያላቸው አካላት በጋራ ሆነው ክልል መመስረት፣ በቅርበት ተገቢውን ክትትል አድርጎ ዜጎችን ወደ ልማት ለማስገባትና ሰላም ማስፈን ተግባራትንም በአግባቡ ለማከናወን ነው::
ሌላኛው ለውጡ ካስገኛቸው ቱርፋቶች አንዱ ተሳትፎን ማሳደግ ነው:: በአንድ ሀገር ግንባታ ውስጥ ሁሉም ዜጎች በተለይ እድሜያቸው 18 እና ከ 18 ዓመት በላይ የሆናቸው በሙሉ በራሳቸው ማሰብ ይችላሉ ተብሎ ስለሚታሰብ የእነርሱን ተሳትፎ በሁሉም መስክ ማጠናከር ያስፈልጋል:: ሀገራችን ያለፈችባቸው ሁለትና ሦስት ዓመታት ምንም እንኳን ከውስጥም ከውጭም የተለያዩ ችግሮች ያጋጠሙን ቢሆንም እነርሱንም እየመከትን ግን ደግሞ የተሳትፎ መጠንን ማሳደግ እጅግ በጣም ያስፈልግ ነበር:: በዚህ የሴቶች፣ የወጣቶችና የአረጋውያን ተሳትፎና የመሳሰሉት ጉዳዮች ተጠናክረው እየሄዱ እናያለን:: በተጨማሪም ተሳትፎ የወለደው ሀገራዊ ምክክር በየቦታው እየተከናወነ ነው ያለው:: እኛም እንደ አንድ ፓርቲ መንግሥት በሚወክለን ቦታ ላይ እየተሳተፍን እነዚህ ጉዳዮች ቢነሱ ብለን ሃሳብ እናቀርባለን:: መጨረሻ ላይ ተሰብስቦ የኢትዮጵያ አጀንዳ የሆኑ ጉዳዮች ይወሰዳሉ ብለን እናስባለን:: ይህ ተሳትፎ ያመጣው ውጤት ነው::
በለውጡ ሂደት ላይ በጣም ፈተና የነበረው ሁላችሁም እንደምታስታውሱት ከሰሜኑ ወንድሞቻችን ጋር ወደከፍተኛ ግጭት ገብተን ነበር:: ይህ ግጭት በርካታ የሰው ሕይወት ቀጥፏል:: በርካታ ንብረቶችን አውድሟል:: ኢኮኖሚያችንም እዛ ላይ እንዲውል ተደርጓል:: በአንድ በኩል ይህ እየተመራ በሌላ በኩል ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ የተጀመሩ ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሳይቋረጡ እንዲሠሩ ማድረግ ተችሏል:: ስለዚህ ጦርነትና ሌሎችም ችግሮች ውስጥ ባንሆን በለውጡ የተጀመሩ ሥራዎች የት ይደርሳሉ ብሎ ማሰብ ይቻላል::
ለውጡ በጣም የተደራጀ የአመራር አንድነትን ይፈልጋል:: ሪፎርም በደንብ ጠርቶ የሆነ ደረጃ እስኪደርስ በሕዝቡ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአመራሩ ውስጥም ብዙ ውዥንብር ይፈጠራል:: የሚጻፉ በርካታ ነገሮች አሉ:: ማህበራዊ ሚዲያ እንደምታውቁት ዛሬ የትኛውም ኮርነር ላይ የኢንተርኔት ግንኙነት ያለውና እጁ ላይ ላፕቶፕ ወይም ሌላ አይነት መሣሪያ ያለው ሰው የፈለገውን ነገር ጽፎ በቀላሉ ማስተላለፍ ይችላል:: እነዚህ ሁሉ የሚፈጥሩትን ጫና ተቋቁሞ የአመራርን አንድነት ጠብቆ ሁሉም በብልጽግናዊ አስተሳሰብ ውስጥ ገብቶ ቅድሚያ ለሕዝብና ለሥራ ሰጥቶ የመንቀሳቀስ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል::
በአመራሩ መካከል ልዩነት ያለ በማስመሰል ሲነዙ የነበሩ ውዥንብሮችን ወደጎን ትቶ አመራሩ ጥሩ ቁመና ላይ ደርሶ በየቀኑ ስለሚሠራው ሥራ እያሰበ ነው:: በብልጽግና የተቀመጡ ፕሮግራሞች አሉ:: ማኒፌስቶው አለ:: እሱን መሠረት አድርጎ መንግሥት ደግሞ ከማንፌስቶው የቀረጻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አሉ:: እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግ የአመራር ቁመናን ማስተካከል በጣም ፈታኝ የነበረ ቢሆንም ተሻግረነዋል:: የለውጡ ሂደት ተሳትፎና አመራርን በጣም አመጣጥኖ መሄድ እጅግ በጣም ያስፈልግ ነበር::
ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለውጡ እንዲመጣ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ ነው:: ሰዎች በአንድ ሀገር ላይ በጋራ ሲኖሩ በሁሉም መስክ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጥን መሄድ አለብን:: አንዱ ቦታ በተለየ ሁኔታ ለምቶ አንዱ ቦታ ደግሞ የልማት ጉድለት ከታዬ መተማመን አይኖርም:: ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የጋራ ጎጆ ነች:: ሁሉም ሰው የጋራ ተሣትፎ ኖሮት የሚሠራ ሆኖ ኢትዮጵያ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ ደግሞ የሁሉንም አካባቢ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሄድ ያስፈልጋል::
በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና ግብዓት፣ በመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በኤሌክትሪክ፣ በስልክና በመሳሰሉት ነገሮች ሕዝቡን እያስተሳሰሩ መሄድ ያስፈልጋል:: ያልገባባቸው ቦታዎች ካሉ ማሳተፍ ያስፈልጋል:: ፍትሐዊነት በዚህ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ከመምራት አንጻር ተሳትፎ ባልነው ላይ ማንሳትም ይቻላል፤ ነገር ግን በዋናነት የሚያተኩረው ፍትሐዊነት ወደሚለው ነው::
የብልጽግና ፓርቲ ከተመሠረተ ጀምሮ ወይም ከመመሥረቱ ዋዜማ ጀምሮ በፕሮግራሞቹ ውስጥ ከያዛቸው ነገሮች አንዱ ግማሹ በደንብ በፓርቲ ውስጥ የሚሳተፍ ግማሹ ደግሞ ውጪ ሆኖ የሚመለከት እንዳይሆን አድርጎ ነው:: ዋና እና አጋር የሚባል የለም፤ ሁሉም ለኢትዮጵያ ዋና ነው በሚል አስተሳሰብና ፕሮግራም መሠረት ከተቀረጸ በኋላ በሁሉም ክልል ያሉ አመራሮች ክልላቸውን እየመሩ በፌዴራል መንግሥቱ ላይም በቂ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ተደርጓል:: አሁን ሁሉም ለሀገሩ እኩል ይንቀሳቀሳል:: በዚህም የሥልጣን ፍትሐዊ ክፍፍሉ ላይ በብልጽግና ዘመን ብዙ ነገር ተሻሽሏል::
እነዚህንና ሌሎችንም ጉዳዮች በሪፎርም ውስጥ አሳክቶ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር ልማቶችን ማከናወን ከባድ ነበረ፤ ቢሆንም ባለፍንባቸው ዓመታት ምንም እንኳን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ብንሆንም ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል:: እድገቱን እኛ ብቻ ሳንሆን የኢኮኖሚ እድገት የሚመዝኑ ሀገራት መዝነው ያረጋገጡት በጦርነት ውስጥም ሆነን ከስድስት ነጥብ አምስት እስከ ሰባት ነጥብ አምስት እያስመዘገብን መሆኑን ነው:: ይህ የአመራሩ መግባባትና ውህደት የፈጠረው ነው:: ለወደፊትም ይህችን ሀገር ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል:: አሁን የምንሰጠው አመራር ብቻ በቂ አይደለም:: አዳዲስ ሃሳቦችን ማምጣትና ማፍለቅ፣ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በየጊዜው ማሳደግና የጎደሉ ነገሮችን ቆጥረን መሙላት አለብን:: ይህን ማድረግ የምንችል ከሆነ የሕዝባችንን ኑሮ ለመቀየርና ብልጽግናን በኢትዮጵያ ለማረጋገጥ የጀመርነው ሥራ የሚሳካበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብዬ አስባለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተተገበሩ ካሉ ኢንሼቲቮችና የልማት ፕሮግራሞች አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርግብር ነው:: በክልሉ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር አተገባበር ምን መልክ አለው? ምን አይነት ውጤቶችስ ተመዘገቡ?
አቶ እንዳሻው፡- የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራን ስናከናውን የሚጠቀሰው ያከናወነውን ሀገር ብቻ አይደለም:: ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ደን ያለባቸው እንደ አማዞን ያሉ አካባቢዎች አሉ:: አማዞን በደንብ በመጠበቁ የሚጠቀሙት ደቡብ አሜሪካ ወይም ሰሜን አሜሪከ አካባቢ ያሉ ሰዎች ብቻ አይደሉም:: የአማዞን አካባቢ አየር ሲስተካከል የእነሱ አየር መስተካከል ቱርፋቱ ለእኛም ይጠቅመናል::
ሩቅ መሄድ አያስፈልግም:: ከአዲስ አበባ 550 ወይም 600 ኪሎ ሜትር ስንጓዝ ኢሉአባቦር መቱን እንዳለፍን የጎሬ ደን የሚባል አለ:: እሱን ይዘን ወደታች ወደ ደቡብ ምዕራብ ስንገባ ማሻ የሚባል አካባቢ አለ:: በጣም ግዙፍ ደን ነው:: ይህ ደን ለአርባ ለሃምሳ ዓመት ተጠብቆ የቆየ ነው:: ይህ ደን እዛ አካባቢ መኖሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ ዝናብ በማምጣት የአየር ሁኔታውን በማስተካከል ሌሎች አካባቢዎች ድርቅና ረሀብ ሲከሰት እዛ አካባቢ እንዳይከሰት የሚያደርግ ነው::
የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም እጅግ በጣም አስፈላጊ ፕሮግራም ነው:: አረንጓዴ ልማት እየተሠራ ያለው በእቅድ ነው:: በየዓመቱ በዚህ ክልል ከመከፈሉ በፊት መረጃ አለ:: ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እየተዘጋጁ ይተከላሉ:: የችግኖቹ አይነት አንዳንዱ የአየር ጸባዩን ለመጠበቅ በኋላም ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ ተቆርጠው ለጣውላ የሚሆኑ የመሳሰሉት ችግኞች ይተከላሉ:: በተጨማሪም ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችም በግለሰብ ጊቢ ውስጥ እንዲሁም ማሳ ላይ እንደማንጎ እና አቮካዶ የመሳሰሉት የፍራፍሬ ተክሎች እየተተከሉ ነው:: ችግኞችን መትከል ብቻ አይደለም:: ዋናው ጉዳይ ከተተከለ በኋላ እንክብካቤ ይፈልጋል፤ ከእንክብካቤ በኋላ የመጽደቅ መጠኑ በየዓመቱ እያረጋገጡ መሄድ ያስፈልጋል::
አሁን ባለንበት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰባት ዞኖች፣ ሦስት ልዩ ወረዳዎች አሉ:: ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ሁሉም ዘንድ ተግባራዊ እየተደረገ ነው:: ለምሳሌ የያዝነውን የ2016 ዓ.ም ብናነሳ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደዚህ ፕሮግራም እንሻገራለን:: ለተከላ የሚሆን ወደ 350 ሚሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል:: ችግኙ የሚዘጋጀው በሁለት አካላት ነው:: አንደኛው በክልሉ ግብርና ቢሮ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አማካኝነት ነው::
በክልሉ ከአንድ ሺህ 800 በላይ ችግኝ ማፍያ ቦታዎች አሉ:: በእነዚህ ቦታዎች ላይ ችግኖችን የማዘጋጀት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል:: በተለይ ችግኝ ከሆኑ በኋላ ምን አይነት ችግኝ ነው መተከል ያለበት በሚለው ላይ በቂ ሥራ እየተሠራ ነው:: ያደገ ችግኝ የሆነ ቦታ ላይ ሲተከል ወዲያው ሊጸድቅ የሚችል መሆን አለበት:: አንዳንድ ችግኞች በጣም አነስተኛ ሆነው ስንተክላቸው የማይጸድቁ ሊሆኑ ይችላሉ:: ይሄ ጥንቃቄ ተደርጎበት እየተሠራ ነው:: ለምግብነት በሚውሉ ችግኞች ላይም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እተሠራ ነው:: ይህ ሥራ አየሩ እንዲስተካከል፣ ዝናብ እንዲፈጠር በማድረግ ሂደትም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል:: ከውበት ባሻገር ተፈጥሮን፣ አካባቢን በመጠበቅ ትልቅ ሥራ አላቸውና ይህን ሥራ እያስፋፋን መሄዳችን የህልውና ጉዳይ ነው::
ከዚህ በፊት ነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከ23 በመቶ በላይ እንደነበር ይገለጻል:: አረንጓዴ ዐሻራን በደንብ ለመሥራት ሲታሰብ የኢትዮጵያ የደን መጠን ከሦስት በመቶ በታች ወርዶ ነበር:: ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ውስጥ በየአስር ዓመቱ የሚከሰት ድርቅ ነበር:: አንዳንዶችም ወደ ረሃብ ተቀይረዋል:: የዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም በደንብ መስፋፋት ከጀመረ በኋላ ድርቅ የሚከሰትባቸው አካባቢዎች በደንብ እየቀነሱ፣ በረሃማነት ባለባቸው ቦታዎች ጭምር ውሃዎችን ጠልፎ በመውሰድ የአረንጓዴ ልማት በማልማት ለውጥ ለማምጣት ተሞክሯል::
የእኛ አካባቢ በተፈጥሮው ሲታይ ሦስት አይነት የአየር ንብረት አለው:: ይኸውም የደጋ፣ ወይና ደጋ እና ቆላማ ነው:: አብዛኛውን ቦታ የሚይዘው ደጋና ወይና ደጋ ነው:: ከመጀመሪያውም ጀምሮ ዛፎች ነበሩት፤ ተክሎች ነበሩት ማለት ይቻላል:: ግን የተወሰኑ ቦታዎች ደግሞ ወደ በረሃማነት እየተለወጡ ነበር:: ስለሆነም ቶሎ ከስር ከስር መትከል ጥቅም ስለነበረው ይህ ፕሮግራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይፈለጋል:: በመሆኑም በጠንካራ ክትትልና በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተተገበረ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በለውጥ አመራሩ በትኩረት እየተሠራባቸው ከሚገኙ ሥራዎች አንዱ የሌማት ቱርፋት ይጠቀሳል:: በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያለው አተገባበርና እየተመራበት ያለው መንገድ ምን ይመስላል?
አቶ እንዳሻው፡– የልማት ቱርፋት ዋና ዓላማው በገጠርና በከተማ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው:: አሁን ባለንበት ደረጃ ከተረጅነት አልወጣንም:: ኢትዮጵያ ብዙ የሰው ኃይል ያላት፣ አፈሯ በጣም ለም የሆነ፣ ብዙ ወንዞች ከዳር እስከዳር የሚፈሱባትና ብዙ ጉልበት ያላት ሀገር ናት፤ ነገር ግን ተረጅነት ውስጥ ያለች ሀገር ናት:: ተረጅነት ደግሞ በጣም አንገት የሚያስደፋ ተግባር ነው::
አንገት ማስደፋት ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ክብር አሳልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲፈጠርም ያደርጋል:: የሚረዱ ሀገሮች ርዳታ ሲሰጡ ዝም ብለው ርዳታ አይሰጡም:: ርዳታ ሲሰጡ ይህን አድርጊ ያንን አድርጉ ብለው ነው:: አንዳንድ የሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ፖሊሲ እስከማስቀየር የሚደርሱ ናቸው:: በዚህ መልኩ ነው መቀጠል ያለብን ወይስ ያለንን ሀብት በማወቅ ሀብታችንን በአግባቡ በማስተዳደር የሕብረተሰቡን ኑሮ መቀየር አለብን ተብሎ ምርጫ ሲቀመጥ ሁለተኛውን ምርጫ ነው የወሰድነው:: ሀብት አለን፤ ሀብታችንን በአግባቡ መለየትና በአግባቡ ማስተዳደር አለብን የሚል ቁርጠኛ አቋም ነው ያለው መንግሥት:: በዚህ መሠረት በትኩረት እየተተገበሩ ከሚገኙ የልማት ፕሮግራሞች አንዱ የሌማት ቱርፋት ነው::
የሌማት ቱርፋት ቀለል ባለ መንገድ ለመግለጽ አንድ የከተማም ሆነ የገጠር አባወራ ዶሮ ቢኖረው እንቁላል ያገኛል:: ላም ቢኖረው ወተት ያገኛል:: ድንች፣ ስኳር፣ ድንች የመሳሰሉ ሥራ ሥሮችን ቢተክል ሌላ ተጨማሪ ምግብ ያገኛል:: ጓሮው ላይ ቀፎ ቢሰቅል ማር ማግኘት ያስችለዋል:: እነዚህ ወደሌማት ሲመጡ አንድ ላይ ተጠራቅመው የሌማት ቱርፋት ይባላሉ:: የየቀኑን የምግብ ፍጆታ ይችላል ማለት ነው:: የቀን የምግብ ፍጆታ መቻል ብቻ ሳይሆን የተረፈውን ነገር ደግሞ ወደ ገበያ ያወጣል::
ከዚህ አንጻር እንደ ክልል እየተተገበሩ ያሉ ሁለት ኢንሼቲቮች አሉ:: የመጀመሪያው ሰላሳ፣ አርባ፣ ሰላሳ ይባላል:: ይህም ማለት አንድ አርሶ አደር በመጀመሪያው ዓመት ሰላሳ የፍራፍሬ ዛፎችን ይተክላል:: በሁለተኛው ዓመት አርባ ይተክላል:: በሦስተኛው ዓመት ሰላሳ ዛፎችን ይተክልና በሦስት ዓመት አንድ መቶ የፍራፍሬ ዛፎች ይኖሩታል ማለት ነው:: ከመቶው ውስጥ ግማሹ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያና ሌሎችንም የፍራፍሬ ተክሎች የሚያካትት ነው:: እነዚህ ዛፎች ምርት መስጠት ሲጀምሩ የቤተሰቡን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን ወደ ገበያ የሚወጣም ይኖራል::
ሁለተኛውና ከዶሮ ጋር የተያያዘው ኢንሼቲቭ ደግሞ አምስት፣ አስር፣ ሃያ አምስት ይባላል:: አንድ አርሶ አደር በመጀመሪያው ዓመት አምስት በሁለተኛው ዓመት አስር እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት ሃያ አምስት ዶሮዎች እየጨመረ ይሄዳል:: አምስት ዶሮዎች ያለው ሰው በቀን አምስት እንቁላል ይኖረዋል:: ይህን እንቁላል ለቤተሰቡ ምግብነት ቢያውለው አልያም ወደ ገበያ አውጥቶ ቢሸጠው ትልቅ ጥቅም ያስገኝለታል:: በዚህ መልኩ ሌማት ቱርፋትን በሰፊው ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል:: ከተማ ላይ ብዙ መሬቶች ባዶ ናቸው:: ይህን ቦታ ቆፍሮ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ድንች፣ ቲማቲምና ሌሎችንም የጓሮ አትክልቶች ማምረት ይቻላል:: በዚህም ሌማታችንን ሙሉ ማድረግ እንችላልን:: እንደ ክልል በዚህ ላይ በጣም የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ ነው::
አንዳንድ ቦታ በደንብ የገባቸው ሰዎች ፕሮግራሙን በአግባቡ ተረድተውና የሚደረግላቸውን ድጋፍ በአግባቡ ተጠቅመው ትልልቅ ውጤት እያስመዘገቡ ነው:: አንዳንድ ቦታ በአግባቡ ያልገባቸውና ተጨማሪ ሥራዎችን የሚፈልጉትን በአግባቡ የማንቃት ግንዛቤ በመፍጠር ወደዚህ ሥራ ለማስገባት እየሠራን እንገኛለን::
በአጠቃላይ ሲመዘን በጥሩ መልኩ እየተገበረ ያለና ከተረጅነት አንዱ የመውጫ መንገዳችን ሊሆን የሚችል ነው:: በቀጣይነትም ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- እንደ ክልል ከተሞችን ለኑሮና ለሥራ ምቹ ከማድረግ አንጻር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችስ ምን ይመስላሉ?
አቶ እንዳሻው፡– የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወደ 126 ሺህ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ አለው:: ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ አራት ሺህ 900 የሚደርስ አመራር አለ:: እነዚህን አመራሮች በማደራጀት በገጠርም በከተማም የሚከናወኑ ተግባራትን በተገቢው መንገድ ለማከናወን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ:: ከተሞችን ምቹ ለማድረግ መሠረታዊ ተብለው ከሚሠሩ ሥራዎች አንዱ አረንጓዴ ማድረግ ነው:: ሁለተኛው የከተሞችን የመጸዳጃ ቦታዎችን መሥራት፣ ከተሞችን ጽዱ ማድረግ እንዲሁም ከተሞች በማስተር ፕላን እንዲመሩ ማድረግን ያጠቃልላል::
ክልሉ በአዲስ መልክ ከተመሠረተ በኋላ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ከተሞች ማስተር ፕላናቸው እየተሠራ ነው:: የትኞቹ ከተሞች ስማርት መሆን አለባቸው ተብሎ ተለይቶ ለምሳሌ ቡታጅራና ሆሳዕና ከተሞች የስማርት ከተማ ባህሪ እንዲኖራቸው ለማድረግ ዲዛይን ተሠርቶ አልቋል::
ሌላው ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ጊዜ የተወሰደው ልምድ የኮሪደር ልማት በሦስት ከተሞች ይጀመራል:: ሆሳዕና፣ ቡታጅራና ወራቤ ከተሞች ላይ:: ሆሳዕና ላይ ጊዜውን አልጠበቅንም፤ አሁን ላይ ተጀምሯል:: በከተማዋ ከሚሠሩ መንገዶች ላይ አያይዘን ሥራው እንዲጀመር ተደርጓል::
ከተሞችን ምቹ ማድረግ ለከተሞች ገቢ ጥቅም አለው:: ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ተመራጭ እንዲሆኑም ስለሚያደርግ ከተሞች ላይ በደንብ አቅደን እየሠራን ነው:: በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰባት መቀመጫ ከተሞች አሉ:: ሆሳዕና የአስተዳደርና ፖለቲካ መቀመጫ፣ ቡታጅራ የኢኮኖሚ ክላስተር፣ ወራቤ ማህበራዊ ክላስተር፣ ወልቂጤ የመሠረተ ልማት እና የምክር ቤት መቀመጫ ናቸው::
በተጨማሪም ዱራሜ የግብርና ክላስተር መቀመጫ፣ ሳጃ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የባህልና ቱሪዝም መቀመጫ ሆነው ያገለግላሉ:: እነዚህ ከተሞች የሚያድጉት ተያይዘው ነው:: ሆሳዕና ላይ የሚታሰብ ነገር ካለ ቡታጅራ ላይም ይታሰባል:: ቢሮ ግንባታ ከታሰበ ሁሉም ዘንድ ይታሰባል፤ ልዩ ልዩ ከተማን ሊያሳድጉ ሊያዘምኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች የምንጠቀም ከሆነ ሰባቱም ከተሞች ላይ እንጠቀማለን:: ይህን እየሠራን ሌሎች ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት፣ ደረጃ ሦስትና ደረጃ አራት ያሉ ከተሞች ላይ ደግሞ የተለያዩ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ:: በጥቅሉ ከተሞችን ማዘመን፣ ማሳደግና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ ትኩረት ከሰጠናቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ለሁሉም ሥራዎች መሠረቱ ሰላም ነውና የክልሉን ሰላም አስጠብቆ ለመቀጠል የተከናወኑ ተግባራትና የምትከተሉት ስትራቴጂ ምን ይመስላል? በቀጣይነትስ ይህን ሰላም አጽንቶ ለመቀጠል ምን ታስቧል?
አቶ እንዳሻው፡– ክልሉ ሥራ ከጀመረ በኋላ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ብለን ሰባት ጉዳዮችን ለይተናል:: የመጀመሪያው ሥራ ሰላምና ፀጥታ፣ ሁለተኛው ግብርና፣ ሦስተኛው ገቢ፣ አራተኛው ትምህርት፣ አምስተኛው ጤና ሲሆን፣ ስድስተኛው አንድ ፓኬጅ አድርገን ንግድ ኢንቨስትመንትና የሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ሰባተኛው የትኩረት መስክ መሠረተ ልማት ነው:: እነዚህ ሰባቱ ጉዳዮች በየዕለቱ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የልዩ ወረዳዎችና የወረዳ አስተዳዳሪዎችን ትኩረት የሚፈልጉ ሥራዎች ተብለው ተለይተው በየቀኑ ተገናኝተን የምንፈትሻቸው ሥራዎች ናቸው::
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው:: ለታቀዱት ሥራዎች ተግባራዊነት ሰላም በጣም አስፈላጊ ነው:: ስለዚህ እኛ እንደመጣን መጀመሪያ ያደረግነው ክልሉ ላይ ችግር ያለባቸውን ቦታዎች መለየት፣ የችግሩን መጠን መረዳት፣ ችግሩን ለመቀልበስ ምን መሥራት አለብን በሚለው ላይ በደንብ መወያየትና ለዚህ የሚመጥን እቅድ ማውጣት እንዲሁም የሥራ ስምሪት መስጠት ነበር::
ክልሉ ላይ ሰላምን ለማስጠበቅ የምጠቀምባቸው መንገዶች ሦስት ናቸው:: ማስተማር፣ ማወያየትት እና ሕግ ማስከበር ናቸው:: በዚህ መሠረት የማስተማር ሥራው በትምህርት ቤትና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል አደረጃጀቶች ይሰጣል:: ማወያየቱ ደግሞ እድሮች፣ የሽማግሌ ህብረቶች፣ የሸማች ማህበራት የመሳሰሉትን በማወያየት ይተገበራል:: ከዚህ ከፍ ያሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ደግሞ ሕግ እናስከብራለን:: ወንጀለኞች ተጠርጣሪዎች ይያዛሉ:: በሕጉ መሠረትም ይቀጣሉ::
የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ለምሳሌ ወደ አዲስ አበባ መሄጃ መንገዶች ከቡታጅራ ወደ ሌመን ስንወጣ የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ:: በቱሉ ቦሎ በወሊሶ ወደ ወልቂጤ ስንመጣም እንዲሁ ችግር ነበር:: በባቱ አቋርጦ ወደ ቡታጅራ የሚመጣ አንድ መንገድ አለ:: እሱም ላይ የተወሰነ ችግር ነበር:: ይህ ችግር ከሸኔ እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዝ ነበር:: የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ፖሊስና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ በጋራ በመሆን መንገዶችን ነጻ ለማድረግ ተሞክሯል:: አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ነገሮች አሉ:: አሁን ያለበት ደረጃ ግን አስተማማኝ፣ የመኪናዎች ዝውውር እንደልብ የሆነበት እና ቁሳቁስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚሄድበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ይሄ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር የምንገናኝበት መንገድ ነው::
አጠቃላይ በውስጣችን አጀንዳቸው የተለያዩ የሆኑ ጉዳዮች ይነሱ ነበር:: አንዳንዱ የመዋቅር ጥያቄ፣ የወረዳ መዋቅር ጥያቄ፣ አንዳንዱ የማንነት ጥያቄ እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ:: በውይይት ሁሉም ቦታ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ተሞክሯል:: ሌላው እንደማንኛውም አካባቢ ስርቆትን የመሰሉ ደረቅ ወንጀሎች አሉ:: እነዚህን ከሕብረተሰቡ ጋር በደንብ በመወያየት በየከተማው በየገጠሩ ችግር የሚፈጥሩ ሰዎችን በመምከርና በማስተካከል በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ አላስፈላጊ ዘመቻ የሚዘምቱ ሰዎችን በመለየትና በማጥናት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለን ምርመራ እያከናወን ነው:: በወንጀላቸው መጠን ይቀጣሉ ማለት ነው::
ስለዚህ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ለሰላም ቁርጠኛ አቋም አለው:: ምክንያቱም ሰላምን ባላረጋገጥንበት ሁኔታ የግብርና፣ የትምህርት፣ የጤና ሥራዎችን መሥራትና ሌሎችንም ተግባራት ማከናወን አንችልም:: በመሆኑመ ሰላም ማረጋገጥ ላይ ቁርጠኛ አቋም ይዘን ነው እየሠራን ያለነው::
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለምንም ችግር በነጻነት መንቀሳቀስ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: አሁን ያለው ሁኔታ ግን ለነገ ዋስትና አይሆንም:: ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው በሁለት መንገድ ነው:: የመጀመሪያው ሰላምን በመጠበቅ በማስተዳደር ነው:: ሁለተኛ ተጨማሪ ልማት በመሥራት ነው:: ብዙ ጊዜ ችግር ውስጥ ገብተው የምናያቸው በእድሜ ትንሽ የሆኑ ልጆች ናቸው:: ስለሆነም ለእነዚህ ልጆች ተከታታይ ሆነ የሥራ እድል ፈጠራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል::
ሰው ሥራ ከያዘ፣ ራሱን ማስተዳደር ከጀመረና ቤተሰብ ከመሠረተ በኋላ ብዙ ጊዜ ወደ ችግር አይገባም:: ስለዚህ የሥራ እድል ፈጠራ በጣም በተፋዘዘባቸው አካባቢዎች ችግሮች ይጨምራሉ:: የሥራ እድል ፈጠራ በደንብ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ደግሞ ችግሮች ይቀንሳሉ:: የሥራ እድል ፈጠራን በደንብ በማጠናከር የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ ከቴክኒክ ሙያ የተመረቁ ልጆችን በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ እቅዶችን ይዘን እየሠራን ነው::
በአንድ በኩል ያለውን ሰላም በደንብ ማስተዳደር በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ ልማት መሥራት የሚሉትን አንድ ላይ ደምረን በመሥራት የክልሉን ሰላም ለማጽናት እየሠራን ነው:: ሰላምን ካላጸናነው ችግር አለበት:: የሆነ ጊዜ አንድ አካባቢ ሰላም አለ ብለን ልናወራ እንችላለን:: ያ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው በተከታታይ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ:: እነዛን ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይነት እስከሁን በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ከመቀጠልና የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ምን ታቅዷል?
አቶ እንዳሻው፡- የተጀመሩ በርካታ ሥራዎች አሉ:: ሥራዎቹ ከበድ ከበድ ያሉ ናቸው:: ከበድ እንዲሉ ያደረጋቸው ዋናው ጉዳይ የህብረተሰብ ፍላጎት ጨምሯል:: የህብረተሰብ ፍላጎት ከመጨመሩ ባሻገር የእኛ ውድድር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አይደለም::
አሁን ያለንበት ዘመን የግሎባላይዜሽን ዘመን በመሆኑ ዓለም ወደ አንድ መንደር መጥታለች:: ይህም ውድድራችን ከብዙ ሀገራት ጋር እንዲሆን ያደርገዋል:: ስለዚህ የመጀመሪያው ጉዳይ የሚሆነው ይህን ውድድር በአግባቡ መረዳት ነው:: ሌላው ኢትዮጵያ ካለችበት ቦታ አንጻርና ከምናስተዳድራቸው ውሃዎች አንጻር አካባቢው የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆን አድርጎታል:: ይህን አካባቢ የማይፈልገው ኃይል የለም::
ብዙ ሀገሮችም ወደ አፍሪካ ለመግባት ሲያስቡ መግባት የሚፈልጉት ኢትዮጵያን አቋርጠው ነው:: ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ህብረትና የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ብዙ ሀገሮች ኢትዮጵያን የሚመለከቱበትን መንገድ በደንብ መረዳት ያስፈልጋል:: እኛ እንዴት ነው እምናያቸው ብቻ ሳይሆን እነሱ እንዴት ነው የሚያዩን የሚለውን ሁልጊዜ መተንተን ያስፈልጋል:: የውስጣችንን ነገር መተንተን የውጭውንም ነገር መተንተን ያስፈልጋል::
ሀገራችን ውስጥ ባለፉት ሦስት አራት ዓመታት የነበሩ ጦርነቶች ሲተነተኑ ኢትዮጵያውያን ፈልገው ያደረጉት ጦርነት ሳይሆን ሁሉም የውክልና ጦርነቶች ናቸው:: እነዚህን በደንብ ከተረዳን በኋላ ለውጡ እየተሻሻለ እንዲሄድ የአመራር ቁርጠኝነት መኖር አለበት:: ህብረተሰቡን አስተባብሮ ማሠራት፣ በየጊዜው በሚገኙ ድሎች አለመርካት ከዛ ይልቅ አዳዲስ ነገሮችን ለመሥራት መጣጣር ያስፈልጋል::
የህብረተሰብ ተሳትፎም በየጊዜው እያሳደገ መምጣት አለበት:: አሁን የደረሰበት ደረጃ በቂ አይደለም፤ ማደግ አለበት:: ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚነሱ የልማት፣ የማህበራዊና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ መሳተፍ አለበት:: የፍትሐዊነትን ጥያቄ እያረጋገጡ መሄድም ሌላኛው የቤት ሥራችን መሆን አለበት::
ሌላውና ወሳኙ ጉዳይ የኢትዮጵያን ትርክት እያስተካከልን መሄድ ነው:: በተሳሳተ መልኩ እየቀረቡ ያሉ ትርክቶችን እያስተካከልን ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችለውን መካከለኛውን መንገድ ይዘን መሄድ አለብን:: እነዚህንና ሌሎችንም አስፈላጊ ተግባራት የምናከናውን ከሆነ ለውጡ በታለመለት መንገድ ይሄዳል:: በተባለበት ጊዜም የኢትዮጵያ ብልጽግና ይረጋገጣል:: ለዚህ ደግሞ አመራሩና መላው የሀገሪቱ ሕዝብ እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ይገባዋል እላለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን::
አቶ እንዳሻው፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም