እንደ ሀገር የጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ትግል በሁለንተናዊ መልኩ በጠንካራ የሕግ እና የሞራል መሠረት ላይ ካልተዋቀረ፣ ውጤቱ የተጠበቀውን ያህል መላው ሕዝባችንንን ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሁም እንደ ሕዝብ ተስፋ የምናደርጋቸውን ነገዎች ተጨባጭ ያደርጋቸዋል ተብሎ አይታሰብም።
በተለይ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (መኒ ላውንደሪንግ)፣ ሙስና፣ ኮንትሮባንድ፣ የታክስ ስወራ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ጥቁር ገበያ …ወዘተ አሁን ላይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን በአግባቡ መከላከል ካልቻልን ድህነትን ለማሸነፍ የጀመርነው ትግል ትርጉም ሊያጣ ይችላል ።
በአቋራጭ ከፍተኛ ሀብት ለማፍራት የሚፈፀሙት እነዚህ ወንጀሎች፣ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የከፋ አደጋ ከማስከተላቸውም በላይ የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍጠር፣ መንግሥታዊ ሥርዓትን በመፈታተን የሕግ የበላይነትን ስጋት ውስጥ በመክተት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ሊያቀጭጩ የሚችሉ ናቸው።
በተለይም እንደኛ ባሉ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ባሉባቸው ሀገራት፣ እነዚህ ወንጀሎችና በወንጀሎቹ የሚገኙ ሀብቶች የፍላጎት ተቃርኖዎችን በመፍጠርና በማስፋት እና የግጭትና የሁከት ምንጭ በመሆን ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሀገራዊ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉም ይታመናል።
በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብና ንብረት የሽብር ወንጀል ማስፈጸሚያ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው። እንደ የሽብር ቡድኑ አደረጃጀት፣ ዓላማና ሁኔታ ይለያይ እንጂ አብዛኞቹ የሽብር ወንጀሎች የሚፈጸሙት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ገንዘብና ንብረትን በመጠቀም ነው። ይህም ለዓለም አቀፍ ሠላም እና ደኅንነት ስጋት እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል።
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የኢኮኖሚ ደኅንነት ስጋት ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጸኝነት ያለውና ጤናማ እንዳይሆን በማድረግ የፋይናንስ ሥርዓቱን የሚያናጋ ወንጀል ነው፡፡
መንግሥት የዋጋ ንረትን በቀላሉ እንዳይቆጣጠርና በኢኮኖሚ ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ እየተዘዋወረ እንደሚገኝ የተጣራ መረጃ እንዳይኖረው በማድረግ፣ የገንዘብ አቅርቦት እና ዝውውርን የሚቆጣጠርበትን አቅም ይፈታተናል፤ መሰብሰብ ያለበትን ግብር እንዳይሰበስብ ያደርገዋል፡፡ በዚህም አጠቃላይ በሆነው የልማት እንቅስቃሴ ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ የከፋ ነው።
ከዚህም ባለፈ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት መልካም ስም እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በተዓማኒነት እንዳይሠሩ ያደርጋል፡፡ የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት በማዛባት የኢኮኖሚና የፖለቲካ አለመረጋጋትን በመፍጠር ለሀገራዊ ልማት እንቅፋት ይሆናል፡፡
ሀገራት ይህንን በሁለንተናዊ መንገድ አደጋ የሆነ ወንጀልን ለመከላከል የተለያዩ ሕጎችን በማውጣት ተፈጻሚ ያደርጋሉ። ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕቀፎችን በመተግበርም በጋራ ይንቀሳቀሳሉ። ሀገራችንም የወንጀሎቹን አደገኝነት በማጤን የሽብር ወንጀሎችንና ተዛማጅ የፋይናንስ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ሕግ፣ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 ተግባራዊ አድርጋ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡
ሀገራችን አሁን ላይ ካለችበት ተጨባጭ እውነታ እና ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕቀፎችን ታሳቢ ያደረገ፣ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳትን ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሰፋፊ ሥራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ አሠራሩን መደገፍ የሚያስችሉ ተጨማሪ የሕግ ድንጋጌዎችንም ማውጣት ይኖርባታል።
ከዚህ በፊት በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ጉዳዮችን ይዞ ሲሠራበት የቆየ ቢሆንም፣ በሚፈለገው ደረጃ ሥራውን ውጤታማ አድርጎ ለመምራት የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈልጎታል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግም በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት መንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ረቂቅ አዋጁን ለተወካዮች ምክር ቤት መርቷል ።
ረቂቅ አዋጁ ዓለማቀፍ ስጋት የሆነውን ወንጀል በተሻለ መንገድ ለመከላከል የሚያስችል፣ እንደ ሀገር የጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ትግል በሁለንተናዊ መልኩ በጠንካራ የሕግ እና የሞራል መሠረት ላይ እንዲዋቀር ስትራቴጂክ አቅም በመሆን፣ ሕዝባችን ተስፋ ከሚያደርገው ልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል የሕግ አግባብ ነው።
በተለይ ከሀገራዊ ልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚ ለመሆን ባላቸው አቅም የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን በተሻለ መልኩ የሚያበረታታ፣ ለልማት የሚሆን የተሻለ ሀገራዊ ምኅዳር መፍጠር የሚያስችል፣ ለሀገራዊ ሠላም እና መረጋጋት ተጨማሪ ጉልበት የሚሆን ነው። ሀገር እና ሕዝብን በሚጎዱ የተለያዩ ወንጀሎች እየተሳተፉ ያሉ ዜጎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲመጡ ተገቢውን ማስጠንቀቂያ ማስተላለፍ የሚያስችልም ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም