በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በርካታ የቦክስ ክለቦች የሚገኙበት እንደመሆኑ ብሔራዊ ቡድንን በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወክሉ ቦክሰኞችን በማፍራት ረገድ ግንባር ቀደም ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ከተማው ሀገርን መወከል የቻሉና እየወከሉ የሚገኙ ቦክሰኞችን ቢያፈራም ከፍተኛ ፍልሚያን የሚያስተናግዱት ውድድሮች ከተቋረጡ ሰነባብተዋል፡፡ ይሁንና ከዚህ ቀደም ተወዳጅነትና ተዘውታሪነትን ያገኘው ይህ ስፖርት እንዲነቃቃ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽንን በኃላፊነት እንድትመራ መመረጧ፤ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፖርቱ በዓለም አቀፍ ውድድሮች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ስፖርቱን ወደ ነበረበት እንዲመለስ እገዛ አድርጓል፡፡ ስፖርቱን የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ ቦክስ ፌዴሬሽን በብሔራዊ ቡድንና በሌሎች ውድድሮች ምክንያት በዚህ ዓመት የራሱን የቦክስ ውድድሮች ማዘጋጀት ባይችልም፤ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር የምሽት የቦክስ ፍልሚያ እያካሄደ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በስካይላይት ሆቴል የተዘጋጀው ውድድር ከብሔራዊ ቡድን እና ከአዲስ አበባ ክለቦች የተወጣጡ ቦክሰኞችን በማፋለም ለአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡
የዚህ ፍልሚያ ሁለተኛ ምዕራፍ የሆነና ትልቅ ሽልማትን የሚያስገኘው ከተማ አቀፍ የአሸናፊዎች ምሽት (Night of the Champions) የተሰኘ የቦክስ ውድድርን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ውድድሩ ነገ ምሽት ከ12፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ፤ 1 ሚሊዮን ብር እንደሚያሸልምም ተነግሯል፡፡ ውድድሩ የሚዘጋጀው ሜላ ኢቨንትስ ከተሰኘ ሁነት አዘጋጅ ጋር በመተባበር ሲሆን፤ በከባድ ሚዛን የ92 ኪሎ ግራም ፍልሚያ ይደረጋል፡፡ በዚህም ቦክሰኞቹ ሙሉቀን መልኬ (ኮንሶ) እና ዳንኤል ታደለ 1 ሚሊዮን ብሩን የግላቸው ለማድረግ ይቧቀሳሉ፡፡ ሁለቱም በቦክስ ስፖርት የብዙ ዓመታት ልምድን ያካበቱ ጠንካራ ቡጢኞች በመሆናቸው የሚያደርጉት ፍልሚያ እጅግ ተጠባቂ ነው፡፡ ተጋጣሚዎቹ ውድድሩን ለማሸነፍ ሰፊና ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነና ለማሸነፍ እንደሚፋለሙም ተናግረዋል፡፡
በርካታ የቦክስ ታዳሚዎች ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ መድረክ የስድስት ወራት ዝግጅት እንደተደረገም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቁሟል፡፡ ውድድሩ 5 ዙሮች ያሉት ሰሚ ፕሮፌሽናል የቦክስ ፍልሚያ ነው፡፡
በተጨማሪም ውድድሩ በአራት ቀላል እና መካከለኛ ኪሎዎች ይካሄዳል፡፡ መታደም ለሚፈልጉ የቦክስ አፍቃሪያን ደግሞ የመግቢያ ትኬቶች የተዘጋጁ ሲሆን፤ መደበኛ 2ሺህ ብር፣ ቪአይፒ 5ሺህ ብር እንዲሁም ቪአይፒ 10ሺህ ብር እንደሆነም ይፋ ተደርጓል፡፡
ይኸውም ስፖርቱን ከማነቃቃትና ቦክሰኞችም ያላቸውን አቅም እንዲያወጡ ከማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት እርግጥ ነው፡፡ ከሀገር አልፎ በውጪ ሃገራት በሚካሄዱ መሰል ውድድሮች ላይ የመካፈል ፍላጎት ከማሳደር አልፎ የሽልማት ገንዘቡ ሌሎች ፕሮፌሽናል ቦክሰኞችንም ሊስብ የሚችል ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በቀጣይም ታዳሚዎችን የሚያሳትፉና ቦክሰኞችንም በገንዘብ መደገፍ የሚችሉ ፍልሚያዎችን ለማካሄድም አቅዶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አስቻለው ኃይለማርያም፤ በቀጣይ ዓመት የሚወጡ መርሃግብሮችን መሠረት በማድረግ ትልልቅ ውድድሮችን ለማዘጋጀት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ በየወሩ አንድ አንድ ውድድሮችን በማካሄድ በዓመት አስር ውድድሮችን ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በመሆኑም የቦክስ ስፖርትን የሚያሠለጥኑ የታዳጊ ፕሮጀክቶች እና ክለቦች እንዲዘጋጁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በተጨማሪም፣ አሁን እየተካሄዱ እንዳሉት ዓይነት የቦክስ ፍልሚያዎችንም በዓመት ሁለት ጊዜ ለማዘጋጀት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ውድድሩን ለማዘጋጀት የስድስት ወር ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤ ዋናውን ፍልሚያ ጨምሮ 5 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡ ስፖርቱን የሚያሳድግና ቦክሰኞችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መሰል፣ ዳጎስ ያሉ ሽልማቶችን የሚያስገኙ ውድድሮችንም በዓመት ሁለቴ ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም