ሥልጣኔ የማይኮርጁ ዲያስፖራዎችና ምሁራኖቻችን

ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ናቸው አሉ፤ እነ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን እና ሌሎች የዘመኑ ሰዎችን ለትምህርት ወደ አውሮፓ ለመላክ የሽኝት መርሀ ግብር እንዲዘጋጅ ያደረጉት። በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት ንጉሡ ለትምህርት ወደ አውሮፓ ለሚሄዱት እንዲህ አሉ።

‹‹… ስትመጡ ስለአውሮፓ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እና ሰፋፊ አስፋልቶች እንድትነግሩን አይደለም። ይዛችሁ መምጣት ያለባችሁ ሀገራችንን የምንገነባበትን ብልሃትና ሥልጣኔ ነው …››

እነሆ ከዚያን ዘመን ጀምሮ በርካታ ምሁራን ለትምህርት ወደ አውሮፓ ሀገራት ይሄዳሉ። የብዙዎች የትምህርትና የሥራ መረጃ (CV) ሲታይ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወይም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሆነች አውሮፓዊት ሀገር ወይም በሌላ የሰለጠነች ሀገር የሠሩ ናቸው። እነሆ ከዚያን ዘመን ጀምሮ የአውሮፓን ሰማይ ጠቀስ ፎቆችና ሰፋፊ አስፋልቶች መናገር እንጂ እንዴት እንደሰለጠኑ ግን መኮረጅ አልተቻለም። ሲቆጩበት እንኳን የምናየው በጣም ጥቂቶች ናቸው።

የዲያስፖራዎችን ደግሞ እናስተውል። ሲመጡ የሚተርኩልን የአሜሪካ ወይም አውሮፓን ጽዳት ብቻ ነው። እዚህ ለማጽዳት ዘመቻ ሲያስጀምሩና ሲያነቁ አይታዩም። እንዲያውም አንዳንዶቹ የሚጠቀሙት ለጉራ ጭምር ነው። ‹‹እዚህ ስቴት እያለሁ፣ ከዚህ ወደዚህ ስሄድ…›› አይነት የግል ገጠመኞቻቸውን ማስቀናት በሚመስል ድምጸት ይናገሩታል። አንዳንዶቹም በገቡበት ካፌ ወይም መገልገያ ቦታ ‹‹እንዴት እንደዚህ ታደርጋላችሁ? አውሮፓ ውስጥ እኮ እንደዚህ አይደረግም! ምንትስ ስቴት እኮ እንደዚህ አይደረግም!…›› እያሉ ይገረማሉ። ከሁለትና ሦስት ዓመት በፊት ጥለውት የሄዱት ሀገር በአንድ ጊዜ አውሮፓ ሆኖ ወይም የሆነች የአሜሪካ ግዛት (ስቴት) ሆኖ የሚጠብቃቸው ነው የሚመስላቸው።

አዎ! አውሮፓ የሰለጠነ መሆኑን እናውቃለን። የአሜሪካ ስቴቶች የሰለጠኑ መሆናቸውን እናውቃለን። ዜጎቻቸው የነቁ መሆናቸውን እናውቃለን። አሠራሮቻቸው ሁሉ ቀልጣፋና ዘመናዊ መሆናቸውን እናውቃለን። ችግሩ ግን እንዴት ያንን እዚህ አምጥተን በሀገራችን እንዘርጋው የሚለው ነው። ዝም ብሎ በወቀሳ እና በስድብ ብቻ ሊስተካከል አይችልም። ቁጭት እና ቆራጥ ውሳኔን ይጠይቃል። ሀገራቸው እንደ አውሮፓ አለመሆኗ የሚቆጫቸው እዚያ ያዩትን እዚህ ለመተግበርና ለማስተግበር መሥራት አለባቸው። እነዚያ የሰለጠኑ ሀገራት እንዴት እንደሰለጠኑ ታሪካቸውን ጠይቀው መምጣት አለባቸው።

ዛሬ የሥልጣኔ ማማ ላይ ያሉ ሀገራት እጅግ ኋላ ቀር ከሆነ ልማድ እና እጅግ አስከፊ ከሆነ ድህነት የወጡ ናቸው። እንዴት ወጡ? ከተባለ፤ በጥቂት ምሁራን እና በዲያስፖራዎቻቸው ቁጭት እና ቆራጥ ውሳኔ ነው። ጃፓንም ይሁን ሲንጋፖር፣ ላስቬጋስም ሆነች ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነቡም። ወይም የሀገሪቱ ሕዝብ በሙሉ አንድ ጊዜ ነቅቶ እና ሠልጥኖ አይደለም። በተደጋጋሚ እንደሚባለው ጃፓን የሰለጠነችው በጥቂት ቆራጦች ነው። ወዲያኑ ግን የመላው የጃፓን ሕዝብ ልማድ ሆነ። ዛሬ ሁሉም በአንድ ሳንባ የሚተነፍሱ እስከሚመስል ድረስ የጋራ ሥነልቦና ፈጥረዋል።

የኢትዮጵያ ምሁራን ግን በሠለጠኑ ሀገራት መማራቸውን የሚናገሩት መድረክ ላይ እና በሕይወት ታሪካቸው ውስጥ ነው። ዲያስፖራዎችም ከአንድ ካፌ በረንዳ ላይ እግራቸውን ሰቅለው ጥቁር መነጽር ገድግደው የአውሮፓ ቆይታቸውን የሚናገሩት ወግ ለማሳመር ነው። ‹‹ምን መሰለህ….›› እያሉ እኔ ልዩ ነኝ የሚል ስሜታቸውን ለመግጽ ነው። ከዚያም አንድ ስህተት ሲያዩ ‹‹እንዴት እንደዚህ ይደረጋል!›› በማለት የእንግሊዘኛ ቃላት የበዛበት ንዴታቸውን ይገልጻሉ።

ቁጭት እንደዚያ አይደለም። በግለሰቦች ብቻ የሚሆንም አይደለም። ተቋማዊ የሆነ እና ንቅናቄን የሚፈጥር አንዳች መላ መፈጠር አለበት። አለበለዚያ በመጣችሁ ቁጥር የምታገኙት ከዓመታት በፊት ትታችሁት የሄዳችሁትን ልማድ ነው። ዘመዶቻችሁ የሚኖሩት ያንኑ የምታውቁትን ሕይወት ነው። ልክ እንደነ ጃፓን ቆራጥ ውሳኔ ይጠይቃል። ጃፓን ዛሬ ያለችበት ደረጃ ላይ የደረሰችው ከአውሮፓ ኮርጃ ነው። ስትኮርጅ ደግሞ በግለሰቦች ደረጃ ሳይሆን ተቋማዊ አሰራር በማድረግ ነው። ይህ የሆነው ከ100 ምናምን ዓመታት በፊት ነው። እኛ ግን እነሆ ዛሬም እዚያ ቁጭት ላይ አልደረስንም።

‹‹ድህነታችን በምርጫ የተቀበልነው ነው›› ይላሉ የደን ሥነምህዳር ተመራማሪው ዶክተር አለማየሁ ዋሴ። ምክንያታቸውን ሲናገሩም፤ የቁጭት መነሳሳት ላይ አይደለንም። ምሁራን አልቆጫቸውም። ሀገር የምትለወጠው ደግሞ በምሁራን ቁጭት ነው። ምክንያቱም የብዙ ሀገራት ተሞክሮ አላቸው፤ ብዙ ነገር ያውቃሉ። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ልካ ያስተማረቻቸው ከሌላ ማህበረሰብ በተሻለ የሥልጣኔና ዕድገት ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ነው። ይህ ካልሆነ ድህነትንና ኋላቀርነትን መርጠነዋል ማለት ነው፤ አልቆጨንም ማለት ነው።

በነገራችን ላይ ይህን አስተያየት የሰጡት ዶክተር አለማየሁ ዋሴ በብዙ መድረኮች የሚናገሩት ይህንኑ ነው። የማንቃት ጥረት ላይ ናቸው። በጻፏቸው መጻሕፍት ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና ሀብቶችን ካስተዋወቁ በኋላ በታተሙት መጽሐፎቻቸው ደግሞ የሰለጠኑ ሀገራት ተሞክሮና ገጠመኞቻቸውን አካፍለዋል። የሠለጠኑ ሀገራትን ያስተዋሉ ሁሉም ምሁራን የዚህ አይነት ቁጭት ቢያድርባቸው አጀንዳው የበለጠ ይሰፋ ነበር፤ ቁጭት ይፈጥር ነበር።

ያም ሆኖ ግን በአጀንዳ ብቻም ለውጥ አይመጣም። በምሁራን እና በዲያስፖራዎች ጩኸት ብቻ አውሮፓን አንሆንም፤ ችግሩ ግን ምሁራን እና ዲያስፖራዎቻችንም የማነቃቃት ጥረት ላይ አለመሆናቸው ነው።

እዚህ ላይ ግን የመንግሥትና የፖለቲከኞች ሚና መዘንጋት የለበትም። አብዛኛው የመንግሥት ባለሥልጣናት የሰለጠኑ ሀገራትን ያስተዋሉ ናቸው። ፖለቲከኞች በየመድረኩ የሚተነትኑት የውጭ ሀገራትን ተሞክሮ በመጥቀስ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት በብዙ ሰበብ አስባቦች ወደ ሰለጠኑ ሀገራት ይሄዳሉ። ዳሩ ግን ቁጭት ፈጥሮባቸው እነዚያን ያስተዋሉዋቸውን ሀገራት ለመሆን አይጥሩም።

ባለሥልጣናትም ሆኑ ተቃዋሚዎቻቸው እንደዚያ የሰለጠነ ሀገር አይተው መጥተው፤ እዚህ ግን የውስጥ ሽኩቻ ላይ ይራኮታሉ። የሰለጠኑ ሀገራት ድንበራቸው የት ጋ እንደሆነ እንኳን እንደማያስታውቅ አይተው መጥተው፤ እዚህ ግን በአንድ ሀገር ውስጥ በክልልና በክልል፣ በዞንና በወረዳ መካከል የሚፈጠር የወሰን ግጭት አይቆጫቸውም፤ ‹‹ለምንድነው እንዲህ የሆንነው?›› የሚለው ቆራጥ ውሳኔ ሲወሰድበት አይታይም። እንዲያውም ይባስ ብሎ አንዳንዶቹ የእርስ በርስ ግጭት አቀጣጣዮችም ናቸው።

ሀገር የሚለወጠው በምሁራን፣ በፖለቲከኞች እና የሰለጠኑ ሀገራትን ተሞክሮ ባስተዋሉ (ዲያስፖራዎች) ንቃት ነው። የሀገር ፍቅር ማለት ዝም ብሎ ባንዲራ መልበስ ብቻ አይደለም። ወይም ስለኢትዮጵያ በተዘፈኑ ዘፈኖች መመሰጥ ብቻ አይደለም። የምናምን ሺህ ዘመን ታሪክ ያለን ነን እያሉ መፎከር አይደለም። የሀገር ፍቅር ማለት ከግል ጥቅም በላይ ለትውልድ ሲሉ ዋጋ መክፈል ማለት ነው። የዛሬዋን ጃፓን ለዚህ ያበቋት አሁን በሕይወት የሉም፤ ዳሩ ግን የጃፓን ዜጋ ሲኮራባቸው ይኖራል። ስለዚህ የሀገር ፍቅር ማለት ለትውልድ መሥራት ነውና ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና ዲያስፖራዎች የሰለጠኑ ሀገራት እንዴት እንደሰለጠኑ ብልሃቱን ይኮርጁ! (እዚህ ላይ ዲያስፖራው ስንል በጅምላ እንዳልሆነ እንዲታወቅልን ያስፈልጋል። ፖለቲካን ከሀገርና ሕዝብ የሚለዩ እንዳሉ፤ የሕዝብና ሀገርን ዘላቂነት፣ የፖለቲካን ወቅታዊ/ጊዜያዊነትን የተረዱ መኖራቸው ልብ ማለት ተገቢ ነው።)

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You