‹‹የጤና ኮሪደሩን በማዘመን የሜዲካል ቱሪዝሙን ለማሳደግ እየሠራን ነው›› አቶ ያሲን አብዱላሂ  የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ

የአንድ ማኅበረሰብ ጤና መጠበቅ ለአንድ ሀገር ሕዝብ ጤና መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። ይህን ታሳቢ በማድረግ የጤና ሚኒስቴር በሽታን መከላከል መሠረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ በመቅረጽ ወደ ሥራ ከገባ ሰንበትበት ብሏል። ታዲያ ይህ ፖሊሲው መሬት ይነካ ዘንድ ከክልልና በየደረጃው ካሉ የጤናው ዘርፍ ተቋማት ጋር ተናቦ መሥራትን የሚጠይቅ ነው።

በዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ከሀገራዊ የጤና ፖሊሲ አንጻር በክልሉ የተከናወኑ በሽታን የመከላከል ሥራዎች ምን እንደሚመስሉ፤ በክልሉ ተነሳሽነት እየተከናወኑ ያሉ የጤና ኮሪደር ልማት የሥራ ሂደት፤ ሐረርን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ከማድረግ አንጻር ምን እየተከናወነ እንደሆነ እና መሰል በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ዐቢይ ተግባራት ምን ይመስላሉ? ስንል ከክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ጋር ቆይታ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ክልል ጤና ቢሮ ባለፉት ወራት ምን ታቅዶ ምን ተሠራ?

አቶ ያሲን፡- የሀገራችን የጤና ፖሊሲ በሽታን መከላከል መሠረት ያደረገ እና አክሞ የማዳንን አቅጣጫዎችን የሚከተል ነው። በዚህ መሠረት በ2016 ዓ.ም የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም የጤና ዘርፉን ክፍተቶችና የሚፈለጉ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። በዚህ መሠረት በዋናነት ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለማከም የሚረዱ ሰፋፊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንገኛለን።

በተጨማሪም ቱሪዝም የክልሉ እምቅ ሀብት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በክልሉ የጤና ቱሪዝምን እውን ማድረግ እየሠራን ነው። ሐረርን በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ዜጎች ለጤና አገልግሎት የሚመጡባትና የሚጎበኝዋት ከተማ ለማድረግ እየሠራን ነው።

ይህንን ግብ ያማከለ ሥራ በዚህ በጀት ዓመት አቅደን እየሠራን ነው። ከዚህ አንጻርም ተላላፊ በሽታዎችን በገጠርም በከተማም የመከላከልና የማከም ሥራዎች ላይ እጅግ አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የእናቶች ጤና እንክብካቤ፤ የሕጻናት ጤና፤ እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ላይ አበረታች የሆኑ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለምሳሌ በሐረሪ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በወባ በሽታ የሞተ አንድም ሰው የለም። ከዚያም አልፎ የእናቶች የሚሰጠው ጤና አገልግሎት ከእቅድ አንጻር ከመቶ ፐርሰንት በላይ ማድረስ ተችሏል።

በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የቤተሰብ ምጣኔ ካለባቸው ክልሎች መካከል አፋር፤ ሱማሌ እና ሐረሪ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናቸው። በመሆኑም እንደክልል በቤተሰብ ምጣኔ ላይ በትረኩት እየሠራን ነው። ከባለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደር መሻሻል አሳይቷል። ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ወር ውስጥ የነበረው የቤተሰብ ምጣኔ ተጠቃሚ ቁጥር 56 በመቶ ነበር። በ2016 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወር ደግሞ 63 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል። ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከልና የመቆጣጠር በተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግበናል።

በዋነኛነት ባለፈው ዘጠኝ ወር ውስጥ ወረርሽኝን የመከላከልና የኅብረተሰብ የጤና ስጋቶች ላይ በሰፊው ሲሠራ ነበር። በተለይም የጤና ስጋትን በሆኑ ኩነቶች ላይ ፈጣንና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ቁመና ያለው ሥርዓት መገንባት ላይ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በምሥራቁ አካባቢ ባለፈው ዘጠኝ ወር ውስጥ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቀነስ መከላከል መሠረት ያደረገ ፖለሲን ተከትለን ስንሠራ ነበር። ከአጎራባች ክልሎች ወረርሽኙን ይዘው ወደ ክልላችን የሚመጡ ሰዎችን ያስተናገድንበት እና ወደክልላችን ማኅበረሰብ እንዳይዛመት ያደረግንበት እንቅስቃሴ ለጤና ስጋት በሚሆኑ ኩነቶች ላይ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጥሩ የሆነ ቁመና ያለው ሥርዓትን እየገነባን መሆኑን ተረድተናል። ይህን የበለጠ ማጠናከር ይገባል።

ባለፈው በዘጠኝ ወር ውስጥ በ600 የሚሆኑ የኮሌራ በሽታ ሕሙማን የነበሩ ሲሆን ከ99 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ሕሙማን ሕክምና ሰጥተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈውስ አግኝተው ወደ ቤታቸው የተመለሱበት ሁኔታ አለ።

ከምሥራቅ ሐረርጌ፤ ጨለንቆና መሰል ሩቅ ስፍራ የመጡ ታካሚዎች በሽታው ከ24 ሰዓታት በላይ ቢቆይባቸውም አክመን ማዳን ችለናል። ይህ በጤናው ዘርፍ አክሞ በማዳን ውስጥ መልካም የሆነ ልምድ እየተገነባ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።

በተጨማሪም ኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ተደራሽነት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሠርቷል። ለምሳሌ ባለፉት ሦስት ዓመታት በጤና መድኅን ሽፋን ክልሉ መቶ “ፐርሰንት” ላይ ይገኛል። ይህ ማለት በክልሉ መመዝገብ የነበረባቸውና ለጤና መድኅን ፕሮግራም የደረሱ ዜጎች በሙሉ ተመዝግበው አገልግሎት እያገኙ ነው። በዚህ ዓመት 46 ሺህ 196 የሚሆኑ አባወራዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል። በአጠቃላይ ከ200 ሺህ በላይ የሚሆን የኅብረተሰብ ክፍል የጤና መድኅን ተጠቃሚ ሆኗል።

አሁን ላይ ኅብረተሰቡ ሲታመም ኪሱ ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ አቅም ሳይመለከት መታወቂያውን ብቻ ይዞ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አገልግሎቱን እያገኘ ነው።

በክልሉ የጤና መድኅን ተጠቃሚው ቁጥር ማደጉ ማኅበረሰባችን የጤና አገልግሎት የመፈለግ ባሕሪው ከመሠረቱ እየተቀየረ እና የጤና አገልግሎትን የመጠቀም ባሕል እያዳበረ መሆኑን ሁነኛ አመላካች ነው።

አዲስ ዘመን፡- በጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚዎች እና ከኪሳቸው አውጥተው በሚታከሙ ሰዎች መካከል ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር አገልግሎት በመስጠት ጤናማ የሕክምና ሥርዓት እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ቢሮው ምን እየሠራ ነው?

አቶ ያሲን፡- ብዙ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ጤና መድኅን አገልግሎቱ ገብቶ ሲመጣ በወጉ ያልተደራጀና አቅሙ ያልጎለበተ የጤና ሥርዓት ላይ የራሱ የሆነ ጫና ይፈጥራል። ምክንያቱም ከፍሎ የሚታከምና በጤና መድኅን የሚታከም የማኅበረሰብ ክፍል የሚጠይቀው ፍላጎቱ የሚረካበት ሁኔታ ይለያያል። ስለዚህ ሁለቱም ያማከለ ሥራ በመሥራት ላይ እንገኛለን።

የጤና ሥርዓቱ የበለጠ አቅም እንዲኖረውና ይህን ግፊት መቋቋም የሚችልና ኅብረተሰቡን ሊያረካ የሚችል የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው በማመን ሰፋፊ ሥራዎችን ጀምረናል። ለምሳሌ የጤና መድኅን ተጠቃሚ የሆነ አንድ የማኅበረሰብ ክፍል የጤና ባለሙያው ወይም ደግሞ የጤና ዘርፉን ሠራተኛ መልካም ሥነምግባር ይፈልጋል። ከዚያም አልፎ አገልግሎቱ ላይ ፈጣን እና ሙሉ አገልግሎት ይፈልጋል። አምስት መድኃኒት ታዝዞለት አንድ መድኃኒት በተቋሙ የማይገኝ ከሆነና ሌላ ቦታ ሪፈር የሚሆን ከሆነ በአገልግሎቱ ያለው እርካታ ይወርዳል። ይህም በጤና ሥርዓቱ ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህንን እና መሰል ጫናዎችን ለመፍታት በየጤና ተቋሙ የቅሬታ ኮሚቴ በማደራጀት እየሠራ ነው። አገልግሎቱን ፈጣን በማድረግ ቅሬታ ካለም መፍታት እንዲቻል ለማድረግ ኮሚቴው የሚሠራ መመሪያ በማውጣት እና በማደራጀት ወደ ሥራ ገብተናል።

ቀደም ብሎ በነበሩት ዓመታት ከመድኃኒትና ሕክምና ወጭ ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች በስፋት ይነሱ ነበር። ይህን ችግር ለመቅረፍ ባለፈው ዓመት ብቻ በዘጠኝ ወረዳዎች ዘጠኝ የኮሚኒቲ ፋርማሲዎች ተከፍተዋል። እነዚህ ፋርማሲዎች የማኅበረሰባችንን ችግር ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባይችሉም እንኳን ማኅበረሰባችን መድኃኒቶችን በቅርበት እንዲያገኝ አስችለውታል።

በነገራችን ላይ ከሕክምና ግብዓቶች ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር የአቅርቦት እጥረት አለ። ይህም ከዓለማቀፋዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ሀገራችን በምግብ ራሷን ለመቻል እንደምታደርገው ጥረት ሁሉ መድኃኒት በማምረትም ራሳችንን ለመቻል መሥራት አለብን።

በጤና ሚኒስቴር ደረጃም እየተሠራበት ያለ ስትራቴጂ ሀገራዊ የመድኃኒት ፍላጎታችን ለማርካት የሚያስችሉ የሀገር ውስጥ ምርትን የማበረታታት፤ የማገዝ ጅምሮች ውጤማ እንዲሆኑ መመራት የሚችልበት የማስፋት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን በግዢ ከውጭ እንዲገቡ እየተደረገ ነው። ስለዚህ የአቅርቦቱ ችግር እንዳለ ሆኖ እያንዳንዱ የጤና አገልግሎት ላይ የራሱን ጫና ይፈጥራል። ስለሆነም ይህ ጫና እንዳይፈጠር ቢሮው በራሱ አቅም እስከ ወረዳ ድረስ የማኅበረሰብ ፋርማሲዎችን ከፍቶ ተደራሽ ለመሆን እየሠራ ነው።

ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ጋር ልዩ የሆነ ስምምነት በማድረግ በማንኛውም ሰዓት እነዚህ የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት የሚያገኙበት ዕድል ተፈጥሯል። አሁን ያለው መረጃ ቢታይ በክልሉ ውስጥ ባሉ የጤና ተቋማት ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦቱ ከ80 እስከ 90 በመቶ ነው። 90 በመቶ ከሆነበት የጤና ተቋም ላይ ከመቶ ታካሚ ውስጥ 10 የሚሆኑት ፍላጎታቸው አልተሟላም ማለት ነው። ይህ ጥሩ ሊባል ቢችልም አሁንም ጉድለቱ ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከሕክምና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚሠሩ ሥራዎች እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ ያሲን፡- እንደክልል የማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎት ፍላጎት ከፍተኛ ነው። አገልግሎት የሚሰጥበት አቅም ደግሞ ዝቅተኛ ነው። ይህ ደግሞ ከጤና ባለሙያዎች ከባሕሪ ጋር የሚያያዝ ነው። በክልሉ በርካታ የጤና ባለሙያዎች በጣም አገልጋይ፣

ሩህሩህ እና ቅን ቢሆኑም አልፎ አልፎ ግን አገልግሎት መስጠት ላይ የባሕሪ ክፍተት የሚታይባቸውም አሉ። እንደ ቢሮ ይህን በማረም ለኅብረተሰባችን ጤናማና መልካም አገልግሎት መስጠት ይቻል ዘንድ ለጤና ባለሙያዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ከትትል እና ድጋፍና የማድረግ ሥራዎችን በትኩረት እየሠራን ነው ።

አንድ ባለሙያ ሥልጠናና ተከታታይ የባሕሪ ማሻሻያ ድጋፍ ተደርጎለት ሙያው በሚፈቅደው ልክ መሥራት እና መለወጥ ካልቻለ በሕግ የሚጠየቅበት አግባብ አለ። ነገር ግን እስካሁን በዚህ ደረጃ የጎላ ችግር አልገጠመንም። ይሁን እንጂ አይገጥመንም ማለት ስላልሆነ አገልግሎቱን አሁን ካለበት ለማሻሻል የጤናው ዘርፍ ሠራተኞች ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን እንዲያከብሩ፣ ለሀገሪቱ ሕግችና መመሪያዎች ተገዢ እንዲሆኑ በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ነው። በዚህም ጥሩ የሚባሉ ውጤቶች ተገኝተዋል። ነገር ግን ከሕዝባችን ፍላጎት አንጻር አሁንም ገና ሰፊ ሥራዎች ይጠብቁናል።

በአጠቃላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በእቅዳችን መሠረት ስንመዝን የተሻለ አፈጻጸም ካስመዘገቡ ክልሎች ውስጥ እንገኛለን። ነገር ግን ያልታቀደ የሕዝብ ጥያቄም ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ተደራሽነትንና ጥራትን ማሻሻል ላይ በስፋት መሥራት እንደሚገባ በመገንዘብ እየሠራን ነው። ክልሉን የጤና ቱሪዝም ለማድረግ በክልሉ ድጋፍ እየሠራን ነው። ይህን የሚያስችሉ ብዙ የጤና ተቋማት በክልሉ ተገንብተዋል።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ምን ያህል የጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች አሉ? እንደክልል የታቀደውን የሜዲካል ቱሪዝም እውን ለማደረግ የሚኖራቸው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ያሲን፡– በክልሉ ዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ከአንድ ወረዳ በስተቀር በሁሉም በትንሹ አንድ ጤና ጣቢያ ይገኛል። ጤና ጣቢያ ለሌላው ወረዳም የሕክምና መስጫ ማዕከል ለመገንባት በሂደት ላይ እንገኛለን።

በክልላችን ሁለተኛ ትውልድ የሚባሉት ዘጠኝ ጤና ጣቢያዎች አሉን። እነሱም ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን አንድ ጤና ጣቢያ ደግሞ ግንባታው 90 በመቶ ተጠናቆ በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል። በጤና ኬላ ደረጃ ሲታይ እንደ ክልል 26 የሚሆኑ ጤና ኬላዎች አሉን።

ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ባለሃብቶች በጤናው ዘርፉ ተሠማርተው ይገኛሉ። በተለይም ከጤና ቱሪዝም ግብ አንጻር የግል ዘርፉ የድርሻውን እንዲወጣ የማበረታታት ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። በዚህ መሠረት በክልሉ በአንድ አካባቢ በርካታ የጤና ተቋማትን በመገንባት እና በአካባቢውን የኮሪደር ልማት በማካሄድ ልማቱንም የጤና ኮሪደር ብለን ሰይመነዋል። ይህም በሀገር ደረጃ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው። ዋና ዓላማውም በኮሪደሩ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው። በዚህም የጤና ኮሪደሩን በማዘመን የሜዲካል ቱሪዝምን ለማሳደግ እየሠራን ነው።

በሐረር ከተማ ለጤና አገልግሎት የሚመጣ ሰው ምንም ሳይንገላታ በኮሪደር ልማቱ በአንድ ሰፈር ውስጥ በተገነቡ የጤና ተቋማት ማንኛውንም አይነት አገልግሎት ማግኘት ይችላል። የግል የጤና ተቋማትም በኮሪደሩ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ፍቃዶችን እየሰጠን እንገኛለን። በዚህ ዓመት ብቻ ለሁለት የጤና ተቋማት ፈቃድ አግኝተው ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ይገኛሉ። ተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎት ተመሳሳይ እና ተደጋጋሚ እንዳይሆን እንደ አዲስ ለሚገነቡ የጤና ተቋማት ዘርፍ እየለየን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ እያደረግን ነው።

አሁን ላይ ሥራው ጅምር ነው። ራዕያችን ሁሉም አይነት አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። መንግሥታዊ እና የግል የጤና ተቋማት የሚገኙበት ስፍራ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የጤና ትምህርት ተቋማት ጭምር የሚገኙበት እንዲሆን ነው። የጤና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለጤና ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲሰጡ ማስቻል ራዕያችን ነው።

በክልል የሚገኙ የጤና ተቋማት ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሰባት መቶ ሺህ የሚሆን የማኅበረሰብ ክፍል አገልግሎት ሰጥተዋል። ይህ አኅዝ ከክልሉ ሕዝብ ቁጥር በላይ ነው። ይህ የሚያሳየው ከሌሎች ክልሎች በርካታ ታካሚዎች እንደሚመጡ ነው። ይህም እንደክልል የታቀደውን ጤና ቱሪዝም ያሳካ ነው ።

አዲስ ዘመን፡- ከክልላችሁ ባለፈ ለሌሎች ክልሎች አገልግሎት እየሰጣችሁ ነው። ለሌሎች ክልሎች አገልግሎት ከመስጠታችሁ በፊት የራሳችሁን ክልል ማኅበረሰብ የጤና አገልግሎት እርካታ ገምግማችኋል?

አቶ ያሲን ፡- የማኅበረሰብ እርካታንም ለመመዘን ሞክረናል። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እስካሁን ባለው ድረስ ከ80 እስከ 85 በመቶ ያለ እርካታ ተገኝቷል። ይህንንም ከፍ ማድረግ ይገባናል። በቲቢ በሽታ ሕክምና ዘርፍ ያለው የሥራ አፈጻጸማችን ከሀገሪቱ ሁለተኛ ደረጃ ይዘናል። በጤና መድኅን ሽፋን ከሁሉም የተሻለ ደረጃ ላይ ነን፤ በወባም በተመሳሳይ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል። ስለዚህ ቀጣይ አቅጣጫችን ጥራት እና አገልግሎት ማስፋት ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው።

ነገር ግን ከሀገራዊ የመድኃኒትና የሕክምና እቃዎች ጥረት ላይ የሚስተዋለው ማነቆ እኛንም እየፈተነን ይገኛል። በመሆኑም ያልዘመነ የአገልግሎት አሠራራችንና የሲቪል ሠራተኛው የአገልጋይነት ደረጃ ኅብረተሰቡ ከሚፈልገው እርካታ አንጻር ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በትኩረት የምንሠራ ይሆናል። ይህንን ማነቆ ለመፍታት የምንሠራው ሥራ እንዳለ ሆኖ የጤና ቱሪዝም ራዕይ ለማሳካት የምንሠራቸው ግቦች አሉ። በጤናው ዘርፍ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የማስቻል አገልግሎቱን የማስፋት ሥራዎች ላይ በትኩረት እንሠራለን።

የጤናው ዘርፍ የሚመራው በስትራቴጂ ነው። አሁን የምንመራበት ስትራቴጂ የአምስት ዓመት ነው። አራት ዓመት ላይ ያለ ስትራቴጂክ ፕላን ነው። ሁለት ዓመት ተኩል ላይ ክለሳ በማድረግ በቀሪው ሁለት ዓመት ተኩል በዋነኝነት አገልግሎትን የማስፋት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አቅደን ለመተግበር የዝግጅት ሥራዎችን እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- አገልግሎቱን የማስፋት ሥራው ዋና ዓላማውና ግቡ ምንድን ነው?

አቶ ያሲን፡– ዋናው ዓላማችን ጤና ቱሪዝም ራዕያችንን እውን ለማድረግ ነው። ጤና ቱሪዝም ራዕችንን እውን ለማድረግ ደግሞ እንደክልል ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ሕዝብ ማገልገል የሚችል የጤና ሥርዓት መገንባት ነው። ከአራት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለማገልገል ከፍተኛ የሆነ አቅም መገንባት ያስፈልጋል።

አሁን ያለንበት ክፍለ ዘመን ሕክምና በከፍተኛ ሁኔታ የሕክምና ግብዓት እና መሣሪያዎች ላይ ጥገኛ የሆነ ነው። እሱን ለማሟላት በስፋት ልንሠራበት ይገባል። የጤና ተቋሞቻችን በትንሹ ‹‹አልትራሳውንድ›› ሊኖር ግድ ነው። የሕክምና ግብዓቶች ለማሟላት በዘንድሮው ዓመት ብቻ ወደ 15 ሚሊዮን ብር የሚሆን የካፒታል በጀት በክልሉ መንግሥት ተመድቦ እና ውል ተገብቶ ለጤና ተቋማት በፍላጎታቸው መሠረት የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች እያሟላን ነው።

እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱ ጤና ጣቢያ “የሲቢሲና” አልትራሳውንድ ማሽን እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ ነው። ሆስፒታሎችም እንዲሁ የተለያዩ የሕክምና ግብዓቶችን እያሟሉ ይገኛሉ። እንደቢሮ እስካሁን የመደገፍ እና ሁሉም የመንግሥት ተቋም መሠረታዊ የሕክምና ግብዓት እንዲኖራቸው እየሠራን ነው። የግል ተቋማቱም በዚህ መልክ ዘመናዊ ግብዓቶችን አምጥተው እንዲሠሩ እያደረግን እንገኛለን።

እያንዳንዱ ሥራዎቻችን እሴት እየጨመሩ በታሰበው ልክ ወደ ራዕያችን ለመቅረብ ትኩረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን። ባጠቃላይ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታና አፈጻጸሙ ጥሩ መሆኑን ከሌሎች ያገኘነው ግብረ መልስ ይህንን ያሳያል።

አዲስ ዘመን፡- ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማን በተለይም አልጋ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሆስፒታሎች ችግር መሆኑ ይነሳል። በሐረሪ ክልል ደግሞ የተሻለ አልጋ ተደራሽነት መኖሩ ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው ?

አቶ ያሲን ፡- እንደ ክልል ለምሳሌ ሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው አዲሱ ሕንጻ አንድ ሺህ አልጋ የመያዝ አቅም ያለው ነው። ግን አሁን ላይ የአቅሙን ያህል እየሠራ አይደለም። እሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ ሥራ እንዲጀምር ለማድረግ ከሆስፒታሉ ጋር እየሠራን እንገኛለን። በክልላችን ሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተጨማሪ ሌሎች ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች አሉ።

እነዚህም ሰፊ አልጋ ያላቸው ናቸው። እንደክልል እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ በሚገኙ ተቋማት ተኝተው ለሚታከሙ ሰዎች ሁኔታዎችን እያመቻቸን እንገኛለን። ይህ ደግሞ በክልችን ጥሩ የሆነ የአልጋ ምጣኔ መኖሩን ያሳያል። አልጋ የሚታየው ከኅብረተሰቡ ምጣኔ አንጻር ነው። ከዚህ አንጻር ጥሩ ምጣኔ አለ። አሁንም ቢሆን ግን ክፍተቶች የሉም ማለት አይደለም። በቀጣይ ሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ ሥራ ሲገባ አንድ ሺ አልጋ ይኖረናል። ይህ ደግሞ በክልል የሚኖረውን የአልጋ ክፍተት የሚሞላ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሐረር ጥንታዊ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ጥንታዊ የሕክምና ማዕከልም ነበረች። በጤናው ዘርፍ የነበራትን ቀዳሚነት ለመመለስ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ያሲን፡– እንደሚታወቀው ሐረር ጥንታዊት ከተማ ነች። ጥንታዊነቷ ሕክምናንም ይጨምራል። በቀደመው ጊዜ ከዘመናዊ ሕክምና በተጨማሪ በባሕላዊ ሕክምናው ዘርፍም በጣም ታዋቂ ነበረች። አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በሁሉም ዘርፍ እንደገና ራሷን በማነቃቃት በቀጣይ በኢትዮጵያ ብልፅግና ውስጥ የራሷን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራን ነው። ከዚህ አንጻር ያሉንን ታሪካዊ ሀብቶች የማልማት ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። የጤና ቱሪዝም እቅዱም ከዚህ ጋር ተመጋጋቢ ነው።

ሰዎች ታሪካዊ ሁነቶችን ከመጎብኘት ባለፈ የጤና አገልግሎትም ለማግኘት ይመጣሉ። በታሪካዊ ሆስፒታሎችም ይታከማሉ። ሆስፒታሎችም ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው። ይህም ክልሉን ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት እየገነባ እንዲሄድ ያስችለዋል። ከዚህ አንጻር ክልሉ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በጥሩ ጅምር ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን ከዚህ በተሻለ ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል። እሱን ደግሞ አሁንም እየሠራን እንገኛለን።

እንደሚታወቀው የጀጎል ሆስፒታል በሀገራችን ከሚገኙ ሆስፒታሎች በእድሜ ጠገብነት የመጀመሪያው ነው። ይህን ሆስፒታል ወደክልላችን ለሚመጡ ቱሪስቶቸ የማሳወቅ እና የማልማት ሥራዎችን በመሥራት ጤና እና ቱሪዝምን እያስተሳሰርን ብልፅግናችንን እየገነባን እንገኛለን ።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት በነበሩ 30 ዓመታት የሐረር የታሪክ አሻራዎች አንዱ የሆነው ሕክምና አቧራ እንዲለብስ ተደርገዋል የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

አቶ ያሲን፡– እውነት ነው። ከለውጡ በፊት የሐረር ኣሻራዎች ተሸፍነው ነበር። አሁን ላይ እሱን የማስተካከል ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው።

ሐረር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠላም እና የመቻቻል ከተማ ተብላ ትታወቃለች። ማንም ሰው ስለሐረር ሕዝብ አብሮነት በተጨባጭ ይመሰክራል። ሐረር ጀጎልን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ያስመዘገበችው እና የዓለም ሕዝብ ሀብት ያደረገችው ቅርሷ ነው። በተጨማሪ ሸዋሊድን የመሰለ የማይዳሰስ ቅርስ ያላት ከተማ ናት።

ይህ ሁሉ የሐረር ሥልጣኔ ከሕክምና የተለየ አይደለም። ስለዚህ ጀጎልን የመሰለ ሥልጣኔ የነበረው ማኅበረሰብ ደግሞ በርግጠኛነት የሠለጠነ ሕክምና ባለቤት መሆኑ አይቀርም። ይህ ማለት ደግሞ ሐረር ከሁሉም የተሻለ የጤና አገልግሎት ነበራት ማለት ነው። አሁን የእኛ ትውልድ ደግሞ ያንን የሕክምና ከፍታዋን መልሶ ለማምጣት እየሠራን ነው ።

አሁን ላይ ከዘመናዊ ጤና ጣቢያዎች ጎን ለጎን በጥናት ላይ የተመሠረተ ባሕላዊ ሕክምናዎችን ለማስኬድ አቅደናል። በእርግጠኝነት ለመናገር ይህ አሠራር በሌሎች የጤና ቢሮዎች አታገኘውም። ይህ መደረጉ ሐረር በሕክምናው ዘርፍ ያላትን ታሪክ ለዚህ ትውልድም ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። የጤና ቱሪዝም ስንል ይህን ሁሉ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልሉ መንግሥት እና ከሌሎችም አካላት ጋር ተባብሮ እና ተናቦ ከመሥራት አንጻር ያላችሁ ተሞክሮ ምን ይመስላል?

አቶ ያሲን፡- የክልሉ መንግሥት የሥራው ባለቤት ነው። በማንኛውም አይነት የጤና ሥራ ላይ አቅጣጫ የሚሰጥ፣ የሚመራ የሚያስፈልገውን ሀብት የሚያቀርብ እና የሚደግፍ ነው። በነገራችን ላይ በጤናው ዘርፍ ላይ የሚታዩ እድገቶች የክልል መንግሥት “ኢንሸቲቭ” ነው።

ከጤና ሚኒስቴር ጋርም በጣም ጥሩ የሆነ ግንኙነት አለን። በአፈጻጸማችንም ጥሩ ስለሆን ጤና ሚኒስቴርም ለምንጠይቃቸው ነገሮች በሙሉ ቅድሚያ ይሰጠናል። በጥሩ ሁኔታ አብረን እና ተባብረን እየሠራን እንገኛለን።

እንደክልል የእኛ ትልቁ ችግር በጤና ዘርፉ ላይ የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች በብዛት ያለመኖር ነው። እንደሚታወቀው አጋር ድርጅቶች የጤና ዘርፉን በስፋት ያግዛሉ። የእኛ ሥራዎች ግን በአብዛኛው የሚደገፉት በመንግሥት ነው። በርግጥ አንዳንድ የሚያግዙን አካላት አሉ። ነገር ግን እንደሌሎች ክልሎች በቋሚነት አይታዩም። አጋር አካላት ከእኛ ጋር መሥራት ቢፈልጉ የበለጠ የሥራቸውን ውጤት ማየት እንዲችሉ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ገንብተናል። ስለሆነም ከእኛ ጋር መጥው እንዲሠሩ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ሐረር ለወደብ ቅርብ በሆነው በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል እንደመገኘቷ የኮንትሮባንድ መድኃኒቶች በክልሉ እንደሚዘዋወሩ ይነገራል። ከዚህ አንጻር ይህን ለመቆጣጠር ምን እየሠራችሁ ነው።

አቶ ያሲን፡– እኛ በሕግ ማስከበር ላይ በምንም መልኩ አንደራደርም። ምክንያቱም ሕዝባችን መጠቀም የሚችለው በሕጋዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ነው። በምሥራቁ ላይ ኮንትሮባንድ አለ ይባላል። ነገር ግን ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት የሚባለውን ያህል አይደለም። ድሮ ሐረር የኮንትሮባንድ ማዕከል ነበረች የሚባል ነገር አለ። አሁን እኔ ባለሁበት የአመራር ዘመን ያን ያህል አደጋ ወይም ችግራችን አይደለም።

አደጋ ወይም ችግራችን ባይሆንም ግን አልፎ አልፎ ይታያል። አልፎ አልፎ የሚታየውን ግን በመያዝ በሕግም ተጠያቂ እያደረግን እንገኛለን። ለዚህ ሥራ ብቁ የሆነ ሥርዓትም አለን። ለምሳሌ በዚህ ዓመት ሁለት “ኬዞች” ሪፖርት ተደርገው ነበር። ይህንም መመያዝ በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራዎችን ሠርተናል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ ያሲን፡- እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You