ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በድጋሚ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን አነሳ

ጠንካራና ተፎካካሪ ክለቦች መኖራቸው ውጤታማ ብሄራዊ ቡድንን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አያጠያይቅም። እንደ የስፖርቱ ሁኔታ ክለቦች የሚወዳደሩበትን ሊጎች እና ቻምፒዮናዎች ማጠናከር ስፖርቱን ከማሳደግ አልፎ ሀገርን ማስጠራት እንደሚያስችል በተግባር ምስክር ከሆኑት መካከል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ተጠቃሽ ነው። በቅርቡ ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የዞን 5 የወጣቶች እጅ ኳስ ቻምፒዮና ብሄራዊ ቡድኑ የዋንጫና የደረጃ ባለቤት ሆኖ ውድድሩን መፈጸሙ ደግሞ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀዛቅዞ የቆየውን ስፖርት እንዲነቃቃ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ ፕሪምየር ሊግ ማስጀመሩ ክለቦችን ከማጠናከር አልፎ ተፎካካሪ ቡድንን መገንባት ተችሏል። በዚህም ኢትዮጵያ የወጣቶች ቻምፒዮና ባካሄደችበት ማግስት የአፍሪካ እጅ ኳስ ቻምፒዮናን ለማዘጋጀት በድጋሚ እድሉን እንድታገኝ፤ ከሊጉ ጠንካራ ክለቦች የሚመረጡ ተጫዋቾችም ዓለም አቀፍ የውደድር ልምድ እንዲያገኙ ያደርጋል። ለምርጥ ብሄራዊ ቡድን መሰረት የሆነውና ዓመቱን ሙሉ በከፍተኛ ፉክክር ሲካሄድ የቆየው ፕሪምየር ሊጉ ከሰሞኑ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማም በድጋሚ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል። በሶስት የተለያዩ ከተሞች ሲደረግ ቆይቶ ፍጻሜውን ያገኘው ውድድር አስር ክለቦችን አፋልሟል።

ሊጉ 8 ዓመታትን ሲያስቆጥር የተሻሉ እንቅስቃሴዎችንና ጠንካራ ፉክክሮችን በማስተናገድ እየተጠናከረ መሆኑ እርግጥ ነው። በሀዋሳ እና ድሬዳዋ ከተሞች ውድድሮችን በማካሄድ በአዲስ አበባ አሸናፊው ክለብ ተለይቷል። በ18 ሳምንታት 90 ጨዋታዎችን በማድረግ ማራኪና የተመልካችን ቀልብ በሳበው ፉክክር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በበላይነት ሊጉን በተከታታይ ዓመታት በማንሳት ታሪክ መጻፉን ቀጥሏል። ከስምንቱ ዓመት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎች አምስቱን በማንሳት ጠንካራና ተፎካካሪ ክለብ እንደሆነም አስመስክሯል።

ክፍለ ከተማው በድጋሚ ባለድል የሆነው ከተፎካካሪዎቹ መቐለ 70 እንደርታ እና ኦሜድላ ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር በማድረግም ነው። በሊጉ ባከናወናቸው ጨዋታዎች 32 ነጥቦችን በመሰብሰብ ዋንጫውን ሲወስድ፣ መቐለ 70 እንደርታ 29 ነጥብ፤ ኦሜድላ ደግሞ በ28 ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች በመያዝ አጠናቀዋል። የሊጉን መጠናቀቅ ተከትሎ ተሳታፊ ክለቦች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁት ደግሞ እንደየ ደረጃቸው ሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፕሪምየር ሊጉን በማሸነፉ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ባህርዳር ከነማ የጸባይ ዋንጫውን ወስዷል።

ሊጉ በርካታ ክለቦች የሚካፈሉበትና በድምቀት የሚካሄድ ቢሆንም ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮች ግን መስተዋላቸው አልቀረም። ፌዴሬሽኑም ይሄንኑ በማመን ችግሩ በስፋትና በተደጋጋሚ የሚከሰት በመሆኑ ለማረም ቅጣቶችን እያስተላለፈ ቢሆንም ለውጥ አልታየም። በቀጣይም የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለትን የሚያሳዩ አሰልጣኞችና ተጫዋቾችን መምከር እና አስተማሪ እርምጃን መውሰድ ላይ መሰራት እንዳለበት ገልጿል። ኢትዮጵያ አህጉር አቀፉን ውድድር በድጋሚ የማስተናገድ እድል ከማግኘቷ ጋር ተያይዞ የምትገነባው ጠንካራ ቡድን በስፖርታዊነት ጨዋነት የታነጸ ሊሆንና ይህም ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ ግልጽ ነው።

ቻምፒዮናው በቀጣይ ዓመት (2017 ዓ·ም) ጥቅምት ወር የሚካሄድ ሲሆን፤ እንደቀደሙት ውድድሮች ውጤታማ ለመሆን ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት እንደሚደረግ በፌዴሬሽኑ ተጠቁሟል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ፍትህ ወልደሰንበት (ዶክተር) ኢትዮጵያ ከፕሪምየር ሊግ ካገኘችው ሰፊ ልምድ በመነሳት በብሔራዊ ቡድን የተመዘገበው ውጤት እንዳስደሰታቸው ይጠቅሳሉ። ውጤቱ በትንሽ ድጋፍ የተገኘ በመሆኑ ለቀጣዩ ውድድር ጠንካራና ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን ለማዘጋጀት ድጋፍ መደረግ አለበት። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቻምፒዮናን ለማስተናግድ በድጋሚ እድል ያገኘችው በወጣቶች ውድድር ባሳየችው ጥሩ መስተንግዶ ነው።

በሊጉ መዝጊያ ላይ በመገኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትም ይሄንኑ የሚያጠናክር ሃሳብን አንጸባርቀዋል። የእጅ ኳስ ስፖርት ከዚህ ቀደም የሚወደድ እና የሚዘወተር ቢሆንም በነበሩት ሁኔታዎች ማደግ አልቻለም። ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን እያነቃቃና ለውጦችን እያመጣ ሲሆን፤ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖር በጋራ መስራት ያስፈልጋል። ሥራዎችን በተገቢው መልኩ እያከናወነ ሕጋዊ ፍቃድ ለማግኘት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ፌዴሬሽን በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው።

ፌዴሬሽኑ የዞን 5 የእጅ ኳስ ቻምፒዮና በማዘጋጀት፣ የሀገርን ገጽታ በመገንባትና ተወዳድሮ ውጤታማ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚያበረታታም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል። ባሳየው የአዘጋጅነትና በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት በመተማመን የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ለሰጠው የማዘጋጀት እድል ተገቢውን ድጋፍ በማድረግና በስኬታማነቱ ላይም በጋራ ይሰራል። ለዚህም ቀድሞ እቅድ በመያዝና ጠንካራ ብሔራዊ ቡድንን በማዘጋጅት ውጤት ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

 

Recommended For You