በሀገር በቀል እውቀት ሰላሙን ያረጋገጠው ሸካ ዞን

‹‹ለሦስት ዓመታት በዘለቀው የሰላም እጦት ዘግናኝ ነገሮች ተፈጽመዋል። ብር ካላመጣህ ተብሎ ሰው ይገደል ነበር። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የኮሚቴ አባል ለመሆን ያስፈራም ነበር። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን ቴፒ ከተማና የኪ ወረዳ ውስጥ አጋጥሞ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታትና ሰላምን ለማስፈን በተዋቀረው ሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ውስጥ ሲሠሩ ከነበሩት መካከል አንዱ አቶ ታፈሰ ታደሰ ናቸው።

ሰው አላግባብ ከሚገደልና አካባቢውንም ለቅቆ ከሚሄድ እኔ ሞቼ ሌላው መትረፍ አለበት ብዬ አምኜበት ነው የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ሆኜ ወደ ሥራ የገባሁት የሚሉት አቶ ታፈሰ፤ ሌሎች የኮሚቴ አባላትም በተመሳሳይ ስሜት ነው የተቀበሉት ብለዋል።

አቶ ታፈሰ እንደገለጹት፤ የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ፤ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያየ ብሔር ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተካተቱበት ሲሆን፤ ኮሚቴው መሳሪያ ታጥቀው ጫካ የገቡ ኃይሎችን

አግባብቶ ወደ ሰላም ለመመለስ ትልቅ ዋጋ ከፍሏል። ድንጋይ ተሸክመው ጫካ ውስጥ ገብተው በመማፀን ጉልበት በመሳም ለሰላም ዝግጁ ማድረግ ችለዋል።

ጫካ የገባው ኃይል በቀድሞ ሥርዓት በደረሰበት የኢኮኖሚ ጫናና የፍትሕ መጓደል ብሶት የነበረውና ለውጥ የናፈቀ ስለነበር ለውጥም ቢመጣ የነበረውን ስሜት መቆጣጠር ያቃተው እንደነበር በውይይታቸው ወቅት መገንዘባቸውን ነው ያስረዱት።

ሰላምን ለማምጣት እርቅ መፍጠር አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ ጫካ የገባውንም የፖለቲካ አመራሩንም የማሳመን ሥራ ከኮሚቴው አባላት የሚጠበቅ ተግባር እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ታፈሰ፤ በዚህ መልኩ መግባባት ላይ ተደርሶ ለውጤት መብቃታቸውን ይገልጻሉ።

ሌላው የኮሚቴው አባል ሼህ አህመድ ሽበሺ፤ ኮሚቴ በማዋቀር የአካባቢ ሰላምን ለማረጋገጥ ለተሠራው ሥራ የዞኑ አመራር ቁርጠኝነት እንደነበረው አስታውሰዋል። የኮሚቴው አባላትም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ከዳር ሳያደርሱ ወደ ኋላ እንዳይሉ ቃለ መሀላ ፈጽመው ሥራ መጀመራቸውንም አስረድተዋል። የሁሉም እምነት ተከታዮች በየሁሉም ቤተእምነት በመሄድ ትምህርት በመስጠት ጭምር መንቀሳቀሳቸውን አመልክተዋል።

ኮሚቴው ጫካ የገቡትን ብቻ ሳይሆን በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙትም ምህረት ተደርጎላቸው ሰላም የማውረድ ሥራ መሥራቱን ነው የተናገሩት። የኮሚቴው አባላት የልፋት ዋጋ ፍሬ አፍርቶ ሰላም ርቆት በቆየው ቴፒ ከተማ ላይ የልማት ሥራ መጠናከሩን ጠቁመዋል። ይሄን ማየት መቻላቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከተለመደው የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ወጣ ባለ የሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም ችግሩን ለመሻገር ተችሏል። የክልል አመራሩ፣ በፌዴራል በኩልም የሚመለከተው አስፈጻሚ አካል ሚናውን ተወጥቷል።

ሀገር በቀል እውቀትን መጠቀም ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ በውጤቱ ማረጋገጥ መቻሉን የጠቆሙት አቶ አበበ፤ በአንድ በኩል መሣሪያ ታጥቆ ጫካ ገብቶ የአካባቢውን ሰላም ለማወክ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ኃይል በማግባባት ትጥቁን ፈትቶ ለሰላም ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፣ ከቤተሰብ አኳያም ‹‹የእኔ ልጅ ጫካ ውስጥ ሆኖ ሊሞት ይችላል ›› የሚል ስጋትን ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

በጥፋተኝነታቸው ፍርድ ተሰጥቷቸው በማረሚያ ቤት ውስጥ ከነበሩ ታራሚዎች ጋር በተመሳሳይ በተደረገ መግባባት ከእስር ተፈተው ከሕዝቡ ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉና ‹‹ልጄ፣ ወገኔ እስር ቤት ውስጥ ነው›› ብሎ ቅሬታ የሚያቀርብና የሚያዝን ቤተሰብ እንዳይኖር የተሠራው ሥራ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል። ወደ ሰላም የተመለሱትም የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው በተለያየ ሥራ ዘርፍ ተሰማርተዋል። አንዳንዶችም ለስኬት በቅተዋል ብለዋል።

አካባቢው ላይ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የተሄደው ርቀት ጊዜ የወሰደ፣ የፖለቲካ ውሳኔና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አበበ፤ በዚህ ሀገር በቀል እውቀት አካባቢው ላይ ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የተካተቱበት የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ከቀበሌ እስከ ዞን በማዋቀር ትኩረት ተሰጥቶት የተሠራ ሥራ መሆኑን አመልክተዋል።

የፀጥታ መደፍረስ ተፈጥሮ በነበረበት ወቅት ግለሰብ ከግለሰብ፣ መንደር ከመንደር፣ ቀበሌ ከቀበሌ፣ ወረዳ ከወረዳ መሻከሮች ተፈጥረው እንደነበር፣ የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን፣ ሰዎች ወጥተው ለመግባት ከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቃቸውን፣ የስርቆትና ዘረፋ ወንጀል መስፋፋቱን፣ በአጠቃላይ የአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተገድቦ እንደነበር አስታውሰዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን ቴፒ ከተማና የኪ ወረዳ ውስጥ አጋጥሞ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ፈተና ተሻግሮ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ልማታዊ ሥራዎች ተጠናክረዋል።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You