አደጋም ሆነ ህመም ቀጠሮ ይዞ አይመጣም። ደም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ወዲያውኑ ደም ለመስጠት በጊዜው በደም ባንክ ደም ተዘጋጅቶ ቢቀመጥ ተመራጭ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ። ለዚህ ደግሞ ህይወታቸው ለአደጋ የተጋለጠ ወገኖችን ለመታደግ አስቀድሞ ደም መለገስ ያስፈልጋል። ቀድሞ የተለገሰ ደም ህይወታቸው ለአደጋ የተጋለጡና ደም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖችን ይታደጋል። ጤነኛ ነኝ የሚል ሰውም የሰው ነገር አይታወቅም አንድ ቀን በአደጋና በሌሎች በሽታዎች ምክንያት ደም ሊያስፈልገው ይችላል። እርሱ ባያስፈልገው እንኳን ከቤተሰቡ አንድ ሰው ሊያስፈልገው ይችላልና በቀናነት ደም መለገስ ተገቢ ይሆናል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር የሚታተመው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 78ኛ ዓመት ምስረታን መሰረት በማድረግ ሰራተኞችና አመራሮች በደም ልገሳ መርሀ ግብር ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። የድርጅቱ ባልደረባ ወይዘሮ ሰርተሽኩሪ አስናቀ፤ በደም ልገሳ ሲሳተፉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። በአንድ አጋጣሚ የታመመ ዘመድ ለመጠየቅ ሆስፒታል በተገኙበት አጋጣሚ ብዙ ህመምተኞች ደም የሚያስፈልጋቸው መሆኑን መስማታቸው ደም ለመለገስ እንደተነሳሱ ያሳታውሳሉ። ‹‹ወገን ሊደገፍ ይገባል›› በሚል እሳቤም ደም ለመለገስ ፍላጎት እንዳደረባቸው ይጠቅሳሉ።
ሰው ቅን ነገርን ማሰብና መተግበርም አለበት የሚሉት ወይዘሮ ሰርተሽኩሪ፤ በጎ ነገር ማድረግ በኢትዮጵያዊ ባህልም የሚደገፍ ተግባር ነው ባይ ናቸው። ‹‹ዛሬ ጤነኛ ልንሆን እንችላለን። ነግ በእኔ ማለት ይገባል። የምንለግሰው ደም ለማን እንደሚውል አናውቅም ምናልባት እኛ ላይ ወይም በቅርብ ቤተሰቦቻችን ላይ አደጋ ይከሰት ይሆናል›› በማለትም የደም ልገሳውን አስፈላጊነት ይገልጻሉ። ‹‹በወሊድ፣ በመኪና አደጋና በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ወገኖቻችንን ህይወት ለማትረፍ ደም ሊያስፈልግ ስለሚችል ደም በመለገስ መልካም ተግባር ነው። ደም በመለገሴ አንድ ሰው ከህይወት ማትረፍ ይችላል ብዬ በማሰብም እርካታ ተሰምቶኛል›› ብለዋል።
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ ወርቁ ማሩ ደም ሲለግሱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ያመለክታሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ትኩረት ሰጥተው ደም ለመለገስ ወደ ጤና ተቋም ባለመሄዳቸውና ደም እንዲለግሱ የሚያስችላቸው ሁኔታ በቅርበት ባለመፈጠሩ መሆኑን ይገልጻሉ። የጤና ባለሙያዎች ደም ለመሰብሰብ ወደ ተቋማቸው መምጣታቸው ደም ለመለገስ እንዳነሳሳቸውም ይጠቁማሉ። ደም መለገሳቸው የሚያደርስባቸው ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለ መገንዘባቸውንም ተናግረዋል። ‹‹ደም በመለገሴ ለሌሎች ሰዎች ህይወት እንደመስጠት ነው የሚሰማኝም በዚህም ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል።
ደም ልገሳ ምንም አይነት ጉዳት አያስከትልም እንዲያውም ተግባሩ ለሌሎች ህይወት እንደመስጠት ነው የሚሉት አቶ ወርቁ፤ ህብረተሰቡ በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ ደም ቢለግስ መልካም ነው ይላሉ። ደም ለመለገስ ቢፈልጉ እንኳን በቅርበት ወደ የትኛው የጤና ተቋም ሄደው መስጠት እንዳለባቸው ግንዛቤ ስለሌላቸው የሚመለከተው አካል ህብረተሰቡ ደም የሚለግስበት ሁኔታውን እንዲያጠናክሩ ቢያደርግ መልካም ነው ሲሉም መክረዋል።
በተደጋጋሚ ጊዜ ደም መለገሳቸውን የሚያስታውሱት ወይዘሮ ሄለን እስክንድር በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ይሰሩ በነበረው ተቋም በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በመዘጋጀቱና የደም አይነታቸውም ለሁሉም የሚያገለግል መሆኑን ስለተገነዘቡ የሰው ህይወትን ለመታደግ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ።
በአደጋም በተለያየ ህመም ምክንያትም ደም የሚያስፈልጋቸው በርካታ ሰዎች በየህክምና ማዕከሉ መኖራቸውን የሚያነሱት ወይዘሮ ሄለን፤ ከዚህ አኳያም በአገሪቱ የደም እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠቁማሉ። ‹‹እኔ አንድ ጊዜ የምለግሰው ደም የሶስት ሰዎችን ህይወት ያድናል። በዚህ መረዳትም እስከቻልኩኝ ድረስ ደም እለግሳለሁ›› በማለት ነው ቃል የሚገቡት።
በየአካባቢው ደም ለመለገስ ፍቃደኛ የሆኑ ሰዎች አሉ። ደም ባንክ አገልግሎት ያለበት ቦታ ድረስ ሄደው ለመለገስ የማይመቻቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። አገልግሎቱ ለእነዚህ ደም ለመለገስ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በየተቋማትና በየትምህርት ቤቶች ባለሙያዎችን በመላክ ደም የሚሰበስብበትን ሁኔታ ቢያመቻች የተሻለ ይሆናል ሲሉም ይገልጻሉ። በተመሳሳይ ህብረተሰቡም ጤነኛ እስከሆነ ድረስ የሚለግሰው ደም የሰው ህይወት የሚታደግ መሆኑን በማሰብ ቢለግስ ጥሩ ነው ሲሉም ወይዘሮ ሄለን ይመክራሉ።
የፕሮዳክሽንና ኦንላይን ሚዲያ ስራ አስፈጻሚ አቶ አርዓይ ጌታቸው፤ ደም ሲለግሱ የመጀመሪያቸው መሆኑን ይጠቁማሉ። ደም ለመለገስ አስበውም ሆነ አቅደው እንደማያውቁና እድሉን አለማግኘታቸውንም ያክላሉ። እድሉ በቅርበት ሲገኝ መጠቀም አለብኝ ብለው ለመለገስ ተነሳስተዋል።
‹‹ደም ስለግስ አስብ የነበረው የአንድ ሰው ደም ለሶስት ሰዎች ይሆናል፣ የማላውቃቸው ሶስት ሰዎች በጣም ባስፈለጋቸው ሰዓት የእኔ ደም እንደሚደርስላቸው አስብ ነበር›› የሚሉት አቶ አርዓያ፤ ደም በመለገስ የሚፈጠር እርካታና ደስታ መኖሩን ያምናሉ። ይህም በገንዘብ የማይገዛ በምንም የማይተካ ነው ባይ ናቸው።
የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት በተለያዩ ቦታዎች በመገኘት የሚያደርገው ደም የመሰብሰብ ተግባሩን ሊያስፋፋ ይገባዋል። ዛሬ ደም መስጠት የሚችል ሰው ነገ ደም ሊያስፈልገው ይችላል። እርሱ ባያስፈልገው እንኳን ከቤተሰቡ አንድ ሰው ሊያስፈልገው ይችላል። በመሆኑም ሁሉም ህብረተሰብ በዚህ እሳቤ መሰረት ደም መለገስ አለበት። የሚሰጠው ደም ለነገ ለሚያስፈልገው ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ህይወትን የሚታደግ መሆኑን በመገንዘብ መስጠት ይገባል ብለዋል።
በብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት የደም ልገሳ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ሲስተር ሀና ለገሰ፤ በተለያየ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች በመዘዋወር ከበጎ ፍቃደኞች ደም እንደሚሰበስቡ ይጠቁማሉ። ‹‹ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ አሁን ተቀይሯል። በተለይ በአዲስ አበባ በበጎ ፍቃድ ደም የሚለግሱ ሰዎች እየጨመሩ መጥተዋል። በአሁኑ ጊዜ ደም በተሰጣቸው ታካሚዎች ቤተሰቦቻቸው የሚሰጡት ምትክ ደም ቀርቶ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ደም ነው ጥቅም ላይ የሚውለው ›› ይላሉ።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ቅርጫፍ የለውም። ብዙ በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሽ መኖራቸው ታሳቢ በማድረግ አገልግሎቱን የማስፋት ስራ ተጀምሯል። በቅርቡም የካ ክፍለ ከተማ ደም መስጫ ማዕከል ተቋቁሟል። በቀጣይም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለማስፋፋት ታቅዷል።
አደጋም ሆነ ህመም ቀጠሮ ይዞ አይመጣም። ስለዚህ ደም ስንሰጥ የምንለግሰው ነገ ለኔ ወይንም ለቤተሰቤ ሊሆን ይችላል ብለን መሆን አለበት። ድንገተኛ አደጋ ሲደርስ ደሙ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ተዘጋጅቶ ቢቀመጥ ይመረጣል። ደም መለገስ የህሊና እርካታ ያጎናጽፋል፣ የደም አይነትና የምርመራ ውጤትንም ለማወቅ ይረዳል። ደም ለጋሾች ከሚለግሱ ሰዎች አንጻርም በልብ ድካም የመያዝ እድላቸውም አነስተኛ ነው።
ደም መለገስ ምንም አይነት የጤና ችግር አያስከትልም። ብንለግስም ባንለግስም ተወግዶ አዲስ ደም ይመረታል። ስለዚህ ብንለግስ ህይወት እናድናለን። ባንለግስ ደግሞ ይወገዳል። በመሆኑም በሚተካው ደም የማይተካውን የሰውን ህይወት እንታደግ መልዕክታቸው ነው ሲስተር ሀና።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደሚሉት፤ በጎ ዓላማ የሚመነጨው ከቀና ልቦና ነው። ቀና ሃሳብ ከሆነ ደግሞ ተግባሩ መቀጠል አለበት። የደም ልገሳ የዘመቻ ስራ ወይም አድርጉት ተብሎ በአዋጅ የሚሰራ አይደለም። የምንለግሰው ደም ለማናውቃቸው ግን ለተቸገሩ ወገኖች የሚውል ነው። ስለዚህ በተቋም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ደም መለገስ የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባል።
‹‹ በተለገሰ ደም የሰው ህይወት የሚድን ከሆነ በግሌም ደም መለገሴን እቀጥላለሁ። በምመራውም ተቋምም ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎት አለኝ። ለዚህም ፍላጎት ያላቸው አመራሮችና ሰራተኞች አሉ። ይህ መልካም ተግባርም የደስታ ስሜትን ይፈጥራል። በሰራተኛው መካከልም መቀራረብን ያመጣል። መደበኛ ስራ ከመስራት ባሻገር በእንዲህ አይነት ማህበራዊ ህይወት ላይ መሳተፍም ማህበራዊ ትስስርን ስለሚያጠናክር ተግባሩን አጠናክረን እንቀጥላለን›› ሲሉ ገልጸዋል።
እንደአገር የሚሰሩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች፤ የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላና አካባቢ ማጸዳት ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ስራዎቹም ከተቋም ለውጥ ጋር በማስተሳሰር እየተከናወነ ይገኛል። የደም ልገሳውም ሆነ ቀደም ሲል የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የአዲስ ዘመን ጋዜጣን 78ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተከታታይ እየተካሄዱ ያሉ ስራዎች አካል መሆኑን ናቸው። በማጠቃለያ መድረኩም ድርጅቱ የጀመራቸው የለውጥ ስራዎች የሚተዋወቁበት እንደሚሆን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመው በኢትዮጵያ የህትመት ሚዲያ አጠቃላይ ጉዞ፣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የለውጥ ሂደትና ሌሎች ጉዳዮች የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡም ጠቅሰዋል።
‹‹ለኢትዮጵያዊነት ደግነትና ልገሳን እንዴት ታስተምራለህ? በማለት የሚጠይቁት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ መረዳዳትና መደጋገፍ በሁሉም አካባቢ ባህል መሆኑን ያመለክታሉ። ለዚህ ተግባር የመሪነት ሚና ሊታከልበት ይገባል። በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የደም ልገሳ መርሀ ግብርን በቀናነት በማስተባበር ባህሉን ሊያስቀጥሉት ይገባል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2011
ዘላለም ግዛው