የግንቦት ወር የዘመነ ደርግ እና የዘመነ ኢህአዴግ ክስተቶች ይበዙበት ነበር። እነሆ የሰኔ ወር ደግሞ በዘመነ ብልጽግና በተከሰቱ ክስተቶች የሚታወስ ሆነ። አንደኛው ከስድስት ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር በተጠራ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የታጣለው ቦምብና ግርግሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከአምስት ዓመታት በፊት (በሰኔ 16ቱ ክስተት በዓመቱ ማለት ነው) ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም የተከሰተው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና በአዲስ አበባ ደግሞ የከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግድያ ነው።
በዛሬው “ሳምንቱን በታሪክ” ዓምዳችን 6 እና 5 ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብለን እነዚህን ሁለት ክስተቶች እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ።
ከ5 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ደራሲ አውግቸው ተረፈ አረፈ። አውግቸው ተረፈ በሚለው ስሙ ቢታወቅም ይህ ግን የብዕር ስሙ እንደሆነ ይነገራል። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ኅሩይ ሚናስ ነው። ከመጽሐፍ ሻጭነት ተነስቶ ታዋቂ ደራሲ የሆነው አውግቸው ተረፈ ከ20 በላይ መጻሕፍትን በወጥና በትርጉም በመጻፍ በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከቀዳሚዎቹ አዘንዱ በመሆን ይታወሳል።
ከ809 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት፣ ሰኔ 12 ቀን 1207 ዓ.ም ቅዱሥ ንጉሥ ላሊበላ አረፈ። ንጉሥ ላሊበላ የተወለደበትም (ታኅሳስ 29) ሆነ ያረፈበት ቀን ሃይማኖታዊ ንግሥ ያለበት ስለሆነ በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ይከበራል። ንጉሥ ላሊበላ ከሰውየው በላይ ሥራዎቹ ስለሚታወሱ በላሊበላ ቅርስ እነሆ ለሚሊኒየም ዓመታት ይታወሳል።
ከ96 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሳስ 12 ቀን 1920 ዓ.ም ሐኪምና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ተወለዱ። (ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን በቅርቡ በዝርዝር አስታውሰናቸዋል።)
ከ9 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ጋዜጠኛ ዳሪዮስ ሞዲ አረፈ። ዳሪዮስ ሞዲ በሬዲዮ ጋዜጠኛነት ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እውቅ የዜና አንባቢ ነው። ዳሮዮስ በነጐድጓዳማ ድምፁ የሚታወስ ሲሆን ሰኔ 13 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከኢትዮጵያ ለቀው ሲወጡ፤ እንዲሁም ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ባነበባቸው ዜናዎች በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል።
ከ43 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 14 ቀን 1973 ዓ.ም አፄ ዮሐንስ 4ኛ ከደርቡሽ ጋር በተዋጉበት ቦታ (በኋላ ‹ዮሐንስ› ተብሎ በተሰየመው) ተራራ አናት ላይ ‹‹ዮሐንስ 4ኛ ከደርቡሾች ጋር የተዋጉበት ስፍራ›› ብሎ የደርግ መንግሥት መታሰቢያ አቆመላቸው።
ከ26 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 14 ቀን 1990 ዓ.ም ዶክተር እሸቱ ጮሌ አረፉ። እሸቱ ጮሌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማህበር መሥራችና ፕሬዚዳንት የነበሩ ሲሆን፣ ከኢኮኖሚክስ ምሁርነቱ ባሻገር የፍትሕና ዴሞክራሲ ተሟጋች ነበሩ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስማቸው አዳራሽ (እሸቱ ጮሌ አዳራሽ) ሰይሞላቸዋል።
ከ70 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 15 ቀን 1946 ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለጉብኝት ወደ ሜክሲኮ በሄዱበት ወቅት የሜክሲኮ መንግሥት በሀገሪቱ ዋና ከተማ ላይ በኢትዮጵያ ስም የሚጠራ አደባባይ ሰየመ።
ከ116 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በዛሬዋ ቀን ሰኔ 16 ቀን 1900 ዓ.ም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የሞተን ሰው በአግባቡ መቅበር እንደሚገባ የሚገልጽ አዋጅ አወጁ። አዋጁም የሚከተለው ነበር።
‹‹ሰው ሲሞት መቅበር ከጥንት የመጣ ልማድ ነበር፤ አሁን ግን በየቦታው የሚታየው የሰው አጽም ብቻ ሆነ። የጥንቱ ልማድ መቅረቱስ ለምንድነው? አሁንም በየገዳማቱና በየአድባራቱ በሌላውም ሥፍራ ሳይቀበር የተገኘ የሰው አጽም፣ የክርስቲያንም ሆነ የሌላ፣ በየግዛትህ በየአጥቢያ ቦታ እያስፈለግክ በሥርዓት ቅበር። ከእንግዲህ ወዲህ ግን በየግዛቱና በየአጥቢያው የሰው አጽም ሳይቀብር የተገኘ ሰው ብርቱ ቅጣት ይጠብቀዋል።››
ቀጥለን በዝርዝር ወደምናየው የዚህ ሳምንት ታሪክ እንለፍ።
የሰኔ 16 የዶ/ር ዐቢይ የድጋፍ ሰልፍ ክስተት
ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተመረጡ በሦስተኛው ወር አካባቢ የድጋፍ ሰልፍ ተዘጋጀ። ዕለተ ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፉ እንደሚደረግ አስተባባሪ ኮሚቴው አሳወቀ።
በተባለው ቀንና ቦታ የጠጠር መጣያ እስከሚጠፋ ድረስ ከአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ (ዙሪያ) በመጡ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች መስቀል አደባባይ ተጥለቀለቀ።
በዚያ ክስተት ውስጥ ዓመቱን ሙሉ መነጋገሪያ ሆኖ የከረመውና በታሪክም የሚመዘገበው አስደንጋጭ ክስተት ግን ተከሰተ። ክስተቱን እናስታውስ።
ዶ/ር ዐቢይ ንግግር አድርገው ጨረሱ። መድረክ መሪው ማይኩን ከዶ/ር ዐቢይ ተቀብሎ በአማርኛ የተናገረውን በእንግሊዝኛ እየደገመ ሳለ፤ በቀጥታ ሥርጭት ለሚከታተሉ ብዙም ያልተሰማ፣ በጭብጨባና ጩኸት ለታጀበው ታዳሚ እምብዛም ጉልህ ያልሆነ የፍንዳታ ድምጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ባለሥልጣኖቻቸው ካሉበት መድረክ አቅራቢያ ተሰማ። ዳሩ ግን፣ በዚያው ቅጽበት ፍንዳታው ቦንብ መሆኑን ያወቁት በመድረኩ ላይና እዚያው አቅራቢያ የነበሩት ብቻ ናቸው።
የፍንዳታው ድምጽ ወደ ተሰማበት አቅጣጫ ለመመልከት ጠቅላይ ሚኒስትሩና በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው የነበረ ሲሆን፣ በዚያው ቅጽበትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠባቂዎች ዶ/ር ዐቢይን ዙሪያቸውን በመክበብ እያጣደፉ ከመድረክ ይዘዋቸው በመውረድ ወደ መኪናቸው ወስደው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቀኑ።
ቦንቡ በፈነዳበት የመድረኩ አቅራቢያ ትርምስ በመፈጠሩ የጸጥታ ሠራተኞች ተሰማርተው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ጥረት ያደርጉ ነበር። ይህም ሆኖ ከመድረኩ እርቀው የነበሩ የሰልፉ ታዳሚዎችና በቴሌቪዥን በቀጥታ ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎች ግን ምን እንደተከሰተ አላወቁም ነበር።
በመድረኩ ላይ ይካሄድ የነበረውን ሥነ ሥርዓት በቀጥታ ሲያስተላልፉ ከነበሩት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል ቀዳሚው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የነበረ ሲሆን፣ ከፍንዳታው መከሰት በኋላ ያቀርባቸው የነበሩት ምስሎች ከመድረኩ የራቁትን ብቻ ነበር።
የፍንዳታው ክስተት በማህበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን በኩል ከተገለጸ በኋላ በአጠቃላይ በሕዝቡ፣ በተለይ ደግሞ በአደባባዩ ታድመው በነበሩ ሰዎች ላይ ድንጋጤና ቁጣን ቀሰቀሰ። አንዳንዶችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት የደረሰ ስለመሰላቸው ስሜታዊ እስከመሆን ደርሰው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጽህፈት ቤታቸው በተመለሱ በደቂቃዎች ውስጥ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ደህና መሆናቸውንና በቦንብ ጥቃቱ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በማሳወቃቸው ወዳልታወቀ አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል ተብሎ የተሰጋው ቁጣ ረገብ ማለት ችሏል። ቢሆንም ግን በታዳሚው መካከል የተወሰኑት ከጥቃቱ ጋር ሊገናኙ ይችላሉ ባሏቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቧል።
በክስተቱ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በመስቀል አደባባይና በአካባቢው ተቋርጦ ነበር። በዚህም ምክንያት በዕለቱ የስልክ ግንኙነት ማድረግ አዳጋች ሆኖ ነበር።
የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሁነቱን ከመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ሥፍራዎች ምስሎችን እያሳየ የነበረ ሲሆን ከፍንዳታው በኋላ ግን የተወሰኑ ካሜራዎቹ ምስል ማስተላለፍ እንዳልቻሉ በሥፍራው የነበረ የጣቢያው ባልደረባ እንደነገረው ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቧል። ምክንያቱም የካሜራዎች ገመዶች ባልታወቁ ሰዎች በመቆረጣቸው እና በካሜራዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ ነበር።
ከፍንዳታው ዕለት ከሰዓት በኋላ አንስቶ ባሉት ተከታታይ ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሆስፒታል በመሄድ ጠይቀዋል፤ በተጨማሪም የደም ልገሳ አድርገዋል።
በተከታታይ ቀናትም ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፤ በድርጊቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ የፖሊስና የደህንነት ኃላፊዎችና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው መነገር ጀመረ።
የሀገር ውስጥ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት የሚያደርጉትን ምርመራ ለማገዝ አሜሪካ ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር የታወቀው የኤፍ. ቢ. አይ ባለሙያዎችም ተልከዋል።
በወቅቱ በትንሹ ለሁለት ሰዎች መሞትና ለበርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ምክንያት ለሆነው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት ቢደርስ ኖሮ ከባድ ምስቅልቅልን ሊያስከትል ይችል ለነበረው የሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የቆየ ቢሆንም ጥቃት አድራሾቹና ሂደቱ ግን አሁን ድረስ በግልጽ አልታወቀም። እነሆ ክስተቱ ግን ታሪክ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል።
የሰኔ 15 የከፍተኛ አመራሮችና የጦር መኮንኖች ግድያ
የመስቀል አደባባዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ የቦምብ ፍንዳታ በተከሰተ በዓመቱ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን፤ እንዲሁም ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራ ተገደሉ። እነዚህን ከፍተኛ አመራሮችና የጦር መኮንኖች በጥቂቱ እናስታውስ።
ዶክተር አምባቸው መኮንን
ዶክተር አምባቸው መኮንን ሲሳይ ደቡብ ጎንደር፣ ጋይንት ተወልደው አደጉ። በልጅነታቸው የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርቶችን አብልጠው ይወዱ እንደነበርና ምኞታቸውም መምህር መሆን እንደነበር በወቅቱ የተገለጸው ታሪካቸው ያሳያል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለማቋረጥ ተገደዋል። ከዚያም ትግሉን ከተቀላቀሉ ከ5 ዓመታት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በርቀት አጠናቀዋል።
የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ነው። የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደቡብ ኮሪያ በሚገኘው ኬዲአይ የፐብሊክ ፖሊሲና አስተዳደር ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በቅድመ ምረቃም ሆነ በድህረ ምረቃ ያጠኑት የትምህርት ዘርፍ ምጣኔ ሀብትን ነው።
ከኮሪያ ተመልሰው ለ11 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አቅንተዋል። ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም እንዲሁ በምጣኔ ሀብት ዙርያ ከእንግሊዙ ኬንት ዩኒቨርሲቲ ነው ያገኙት።
ዶክተር አምባቸው ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ከወረዳ ጀምሮ በተለያየ እርከን አስተዳደራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል በአማራ ክልል የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፤ እንዲሁም የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነቶች ይገኙባቸዋል።
በፌዴራል ደረጃ ደግሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ለአንድ ዓመት ያህል አገልግለዋል። ከዚያ በኋላም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር በመሆን ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ ሠርተዋል።
ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከሕዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሠረተ ልማት አማካሪ፤ ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ህልፈተ ሕይወታቸው ድረስ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።
ጄኔራል ሰዓረ መኮንን
ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከአስር አለቃ መኮንን ይመር እና ከወይዘሮ ሕይወት ይህደጎ በትግራይ ክልል፣ ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ አስገዳ ጽምብላ ወረዳ፣ እንዳባጉና ከተማ 1954 ዓ.ም ተወለዱ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በእንዳባጉና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል፤ እንዲሁም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽሬ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ነገር ግን በመማር ላይ እያሉ የደርግን ሥርዓት ለመታገል በሕወሓት የሚመራው የትጥቅ ትግል እየተካሄደ ስለነበር ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በ1969 ዓ.ም የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ። በጉንደት ሥልጠና ማዕከል ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው እስከ ታኅሳስ 1971 ዓ.ም ድረስ በሕወሓት 91ኛ እና 73ኛ ሻምበሎች በተዋጊነት እና በጓድ መሪነት አገልግለዋል።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ ያለው የጄኔራል ሰዓረ መኮንን ታሪክ የወታደርነትና የጦር መሪነት ታሪክ ነው።
በነበራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በ1988 ዓ.ም በሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ ጀምረው በ2010 ዓ.ም የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ ደርሰዋል። በነበራቸው የትጥቅ ትግል ተሳትፎ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳልያን ጨምሮ በርካታ ኒሻኖችን ከኢፌዴሪ መንግሥት ማግኘታቸውም የሚታወስ ነው።
ጄኔራል ሰዓረ ባላቸው ከፍተኛ የመማርና ራስን በትምህርት የማሳደግ ፍላጎት በ ‹ማኔጅመንት› የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፤ እንዲሁም በ ‹ትራንስፎርሜሽን› እና ‹ሊደርሽፕ› ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪኒዊች ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ጀኔራል ሰዓረ ባላቸው ከፍተኛ የማንበብ ልምድ የሚታወቁና ለሌሎችም አርዓያ የነበሩ መሆናቸው በወቅቱ የተነገረው ታሪካቸው ያሳያል።
ባለትዳር እና የአንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆች አባት የነበሩት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፤ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ ከተደረገው ግድያ በኋላ ‹‹በጠባቂያቸው ነው›› በተባለ የጥይት ተኩስ ተገድለዋል።
በዚሁ ዕለትና በዚያው ሰዓት ከጄኔራል ሰዓረ መኮንን ቤት የነበሩትና ከመከላከያ በጡረታ የተሰናበቱት ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ተገድለዋል።
በተመሳሳይ፣ በዚሁ ዕለት የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ የነበሩት አቶ እዘዝ ዋሴ በዚያው በባህር ዳር ተገድለዋል።
አቶ ምግባሩ ከበደ
ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆነውና ያረፉበት ቀን የሚለየው የአቶ ምግባሩ ከበደ ነው። አቶ ምግባሩ ከበደ ያረፉት ከሁለት ቀን በኋላ ነው።
አቶ ምግባሩ ከበደ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በ1966 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን ሥራ የጀመሩት የወረዳና ዞን ዐቃቢ ሕግ በመሆን ነበር።
የምስራቅ ጎጃም ዞን አቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ፣ የደብረ ማርቆስ ከንቲባ፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ፣ የአዴፓ የገጠር ፖለቲካና አደረጃጃት አማካሪ፣ የአደፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኃላፊ በመሆን ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል።
አቶ ምግባሩ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተፈፀመው ጥቃት በጥይት ተመተው በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ነው ሕይወታቸው ያለፈው።
ከእነዚህ ቀናት በኋላ በዚያው ሳምንት፤ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ግድያ መርተዋል የተባሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በድርጊቱ ተጠርጥረው በፀጥታ ኃይሎች እየተፈለጉ ባለበት ‹‹ለማምለጥ ሞክረዋል›› በሚል በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውም የዚሁ ታሪክ አካል ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም