የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋራ ሲያካሂድ የቆየው 14ኛው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስፖርታዊ ውድድር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተጠቃሏል:: ውድድሩ በአራት የስፖርት ዓይነቶች 15 ኮሌጆችን ያፎካከረ ሲሆን፤ የውድድር ቅርጽ ለውጥ እና የስፖርት ዓይነቶችን ለማብዛት እየተሠራ እንደሆነ በአዘጋጆቹ ተጠቁሟል::
ከግንቦት 15/2016 ዓም ጀምሮ ‹‹ሙያና ክህሎት ለዘላቂ ልማት›› በሚል ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው 14ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ስፖርታዊ ውድድር የሙያ ኮሌጆችን አፎካክሮ ከትላንት በስቲያ በድምቀት ተጠናቋል:: በውድድሩ 15 የሙያ ኮሌጆች በአራት የስፖርት አይነቶች ተፋልመው አሸናፊ ኮሌጆች ተለይተዋል:: በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቮሊቦል እና ጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርቶች የኮሌጅ መምህራን እና ተማሪዎች መሳተፍ ችለዋል::
በውድድሩ ማጠናቀቅያ እለት የአሠልጣኞች (የመምህራን) እግር ኳስ ጨዋታ እና በኮሌጅ ዲኖች መከካል የአትሌቲክስ ዱላ ቅብብል ተካሂዷል:: ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ከምሥራቅ ፖሊ ቴክኒክ ያካሄዱት የመምህራን እግር ኳስ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክርን አስተናግዶ ተግባረ ዕድ 3 ለምንም በመርታት የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል:: ኮሌጁ በተማሪዎች መካከል በተካሄደው የእግር ኳስ ውድድርም ዋንጫውን ወስዷል:: በተማሪዎች መካከል በተካሄደው የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ደግሞ ኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ፣ በቮሊቦል አራዳ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ የውድድሮቹ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል::
በሙያና ቴክኒክ ኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችንና መምህራንን በስፖርት ለማሳተፍ እና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ዓላማ አድርጎ የሚካሄደውን ውድድር፣ የቅርጽ ለውጥ እና የውድድሮችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮና የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቀዋል:: በየዓመቱ በሙያ ኮሌጆች መካከል በአንድ ፆታ ብቻ የሚካሄደውን ውድድር በሴቶችም ለማስቀጠል ታቅዷል:: በተጨማሪም ለአጭር ጊዜ ውድድር ከማካሄድ ይልቅ ዓመቱን ሙሉ የሚካሄድበትን የውድድር ሂደት ለመፍጠር እየተሰራም ነው::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ የውድድሩ ዓላማ አምራች፣ ውጤታማና በአካል የዳበረ አሠልጣኝና ሠልጣኝ ማፍራት መሆኑን ይጠቁማሉ:: ውድድሩ በኮሌጆችና ተማሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግና ወንድማማችነትን ለመፍጠር የተካሄደ ሲሆን፤ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በተለያዩ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተከናውኖ በስፖርታዊ ጨዋነት እና ዓላማውን ባሳካ ሁኔታ ተጠናቋል::
የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የሙያ ኮሌጆቹን ስፖርታዊ ውድድር አጠናክሮ ለማስቀጠል ከ18 ተቋማት ጋር ተፈራርሞ እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከሥራና ክህሎት ወጣቶችን ሥራ ከማስያዝና ግንዛቤን ከመፍጠር ባለፈ ኮሌጆች የማዘውተሪያ ስፍራ እና የስፖርት ባለሙያዎችን በመያዛቸው ተቀራርበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል::
የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፤ ተማሪዎች አምራችና ውጤታማ ትውልድ እንዲሆኑ በስፖርት ዘርፍ ተቀናጅቶ ለመሥራት የረጅም ጊዜ ስምምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል:: ውድድሩ በከተማ ደረጃ እየተካሄደ 14ኛ ጊዜ ላይ የደረሰ ሲሆን ኮሌጆች በየትምህርት ክፍሉ የውስጥ ውድድሮችን በማድረግ ከተማ አቀፍ ውድድር ላይ እንዲሳተፉና ዓመቱን ሙሉ በዲቪዝዮን ደረጃ እንዲወዳደሩ ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: በዚህም መሠረት በቀጣይ ዓመት የቅርጽ ለውጥ በማድረግ ዓመቱን ሙሉ ውድድሮችን ለማካሄድ ይሠራል:: በእነዚህ ኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ የማዝወተሪያ ስፍራዎችም በአካባቢያቸው ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ክፍት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ ይገኛል::
በኮሌጆች ውስጥ እውቀት በመኖሩ የስፖርት ክፍሎች እንዲከፈቱ ቢሮው ፍላጎት እንዳለው የጠቀሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ለስፖርቱ ካሪኩለም ተቀርጾ የአጭር ጊዜ የሙያ ሥልጠና በመስጠት እንደ አንድ የሙያ መዳረሻ እንዲሆን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል::
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝና የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መክብብ ወልደሃና በበኩላቸው ቢሮው በየዓመቱ የቴክኒክና ሙያ ሳምንትን የሚያከብር መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሁነቶቹ መካከል ስፖርታዊ ውድድር እንደሆነ ገልጸዋል:: ስፖርት ኮሌጆች ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሥራ ፈጣሪ ወጣትን እንዲያፈሩ የሚያደርግ መሣሪያ በመሆኑ፣ የበቁ ዜጎችን ለማፍራት ጠቀሜታ ይኖረዋል:: በአዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ፣ ስፖርት በኮሌጆች አንድ የሥልጠና ዘርፍ ሆኖ የመጣ ሲሆን ስፖርቱን በወጥነት ለማስኬድ በእቅድ የሚመራ ይሆናል:: በአንድ ፆታ የሚካሄደውን ውድድርም ሴቶችን በማካተት፣ የቅርጽ ለውጥና ውድድር ዓይነቶችን ለማብዛት በእቅድ መያዙንም ገልጸዋል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም