‹‹ጤናችን በምርታችን!››

የጤና ሥርዓቱን ከሚያሳልጡና በሕክምና ሂደት ከፍተኛ ሚና ከሚጫወቱት ውስጥ የሕክምና ግብዓቶች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ:: እነዚህ የሕክምና ግብዓቶች በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ስለማይመረቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ:: ይሁንና በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የሕክምና ግብዓቶች እዚሁ በሀገር ውስጥ ተመርተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ:: በተለይ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአዲስ አበባ መከፈትን ተከትሎ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ አልሚዎች በፓርኩ ሼዶችን በመገንባት ለሕክምና የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ግብዓቶችንና መድኃኒቶችን ማ ምረት ጀምረዋል::

ይህም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ይገቡ የነበሩ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷል:: በሂደትም በፓርኩና ከፓርኩ ውጪ የሕክምና ግብዓቶችንና መድኃኒቶችን የሚያመርቱ ሀገር በቀል አልሚዎች እየጨመሩ መጥተዋል:: የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት አምራቾችን ለማበረታታትና በዘርፉ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳደግም ነው ጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽን ‹‹ጤናችን በምርታችን!›› በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ሰኔ 15 እስከ 20 ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ የሚያካሂደው::

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ እንደሚናገሩት፣ የጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ ተግባራዊ እያደረጋቸው ካሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርቶችን ማሳደግ ነው:: የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርቶችን ከማሳደግ አንፃር በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን የመደገፍ፣ የማገዝና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የመሳብ ሥራዎች በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተከናወኑ ይገኛሉ:: ከነዚህ ዘርፎች መካከል ደግሞ ጤና ሚኒስቴር የሚከታተለውና የሚደግፈው የፋርማሲዩቲካል ዘርፉን ነው::

በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ የሀገር ውስጥ መድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶችን ምርት በማሳደግ የጤና አገልግሎት ሽፋንን በተፈለገውና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል:: የሀገርን ኢኮኖሚ ዘላቂ ከማድረግ አንፃር ያለው ተፅዕኖ በማሳደግና የሀገርን ደኅንነትና ሠላም ከማረጋገጥ አንፃር የሕክምና ዘርፉን በተለይ ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ቁልፍ ተግባር ነው:: በ2014 ዓ.ም በተደረገው የመንግሥት ተቋማት መልሶ ማደራጀትና ማስተካከያ ላይ የጤና ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስዶ የፋርማሲዩቲካል አምራች ዘርፉን የመደገፍና የማገዝ ሚና ተሰጥቶታል::

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደሚያብራሩት፣ በአፍሪካ ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነው መድኃኒት ከውጪ ሀገራት ነው የሚገባው:: በኢትዮጵያም 90 ከመቶ የሚጠጋው መድኃኒት በተመሳሳይ በውጪ ምንዛሪ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል:: በተለየ ሁኔታ አንዳንድ መድኃኒቶች ደግሞ መቶ ከመቶ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው:: ለምሳሌ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ለክትባት አገልግሎት አብዛኛዎቹን መድኃኒቶችና የክትባት ግብዓቶችን የሚያስገቡት ከውጪ ሀገራት ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃም ከ25 ከመቶ በላይ የክትባት አገልግሎት ተጠቃሚ አፍሪካ አሕጉር ነው:: 99 ከመቶ የሚሆኑት የክትባት አይነቶች ወደሀገር ውስጥ የሚገቡት ደግሞ ከአፍሪካ ውጪ የተመረቱ ምርቶች ናቸው::

ይህም በገንዘብ ሲሰላ በአፍሪካ በዓመት ከ42 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለመድኃኒት ግዢ ወጪ ይሆናል:: ኢትዮጵያም በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን የመድኃኒት ግዢ ይፈፀማል:: አብዛኛውን ማለትም 90 ከመቶ የሚጠጋው መድኃኒትም ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ነው:: በ2015 ዓ.ም ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት በኩል ለመድኃኒት ግዢ ወጪ ሆኗል:: በዚህን ያህል ወጪ የመድኃኒት ግዢ ከውጪ ሀገራት መፈፀም የሚፈለገውን የጤና አገልግሎት በፍትሐዊነትና በጥራት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተግዳሮት ፈጥሯል::

ይህንን ለማሻሻል እንደኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደአፍሪካ የተቀመጡ ኢኒሼዬቲቮች አሉ:: አንደኛው ከውጪ ሀገር በግዢ የሚገቡ መድኃኒቶች እንዳሉ ሆነው የአፍሪካ ሀገራት በተለይም ደግሞ በአፍሪካ ሲ ዲ ሲ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ የተመረጡ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የአፍሪካ ሀገራት የተቀናጀ የግዢ ሥርዓት ተዘርግቶላቸው መድኃኒቶችን እንዲገዙ ማድረግ ነው:: ይህም የሀገር ውስጥ ምርትን ከማሳደግ አንፃር ትልቅ ሚና አለው:: በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት እስከሚያድግ ድረስ ከውጪ ሀገር የሚገዙ ምርቶች ላይ በውድድርና በተሻለ ዋጋ የመግዛት አቅምን ያሳድጋል::

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ምርትን ማምረት ብቻ ሳይሆን የሚመረተው ምርት ጥራታቸውን የጠበቁና የኅብረተሰቡን ጤና የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው:: በዓለም አቀፍ ደረጃም ደረጃቸውን ያሟሉና ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው:: ለዚህም የቁጥጥር ሥርዓቱ በጣም ጠንካራ መሆን አለበት:: አፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ኢኒሺዬቲቭ መሠረት የቁጥጥር ሥርዓቱ ወጥና ተመሳሳይ እንዲሆን፣ በአንድ አካባቢ ላይ የተመረተው ምርት በሌላ አካባቢ ላይ ተቀባይነት እንዲኖረው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር ዘርፈ ብዙ ኢኒሺዬቲቮች ተቀርፀው በኢትዮጵያም በአፍሪካም እየተተገበሩ ነው::

እ.ኤ.አ በ2040 ቢያንስ 60 ከመቶ የሚሆነው የመድኃኒት ምርት በአሕጉር ደረጃ መመረት አለበት የሚል ግብ ተቀምጦ እየተሠራበት ይገኛል:: ይህን ግብ እንደሀገር ተቀብሎ ከማስፈፀምና የተቀመጡ ኢኒሼዬቲቮችን ውጤት ባለው መልኩ ከመምራት አንፃር እንደሀገር ምቹ ሁኔታዎች አሉ:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከፍተኛ መሆንም በዘርፉ ከፍተኛ ገበያ እንዳለ ይጠቁማል:: በዛው ልክ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትም እየሰፋ በመምጣቱና የኅብረተሰቡን የጤና አጠቃቀም በተለይ ደግሞ የጤና መድኅን ሥርዓት ከተጀመረ ወዲህ በቀላሉ የሕክምና ወጪውን ሳይሰጋ ሕክምና መጠቀም ዕድል እየተፈጠረ በመሆኑ የሕክምና አጠቃቀሙ ላይ እያደገ የመጣ ትልቅ የገበያ ዕድል እንዳለ ያሳያል::

ከአፍሪካ አሕጉር አንፃር የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ በኮቪድ ወቅት ያጋጠመውን የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ መድኃኒቶችን ለተለያዩ ሀገራት ሲያቀርብ ነበር:: ይህም በሀገር ውስጥ መድኃኒቶችን ማምረት ቢቻል በቀላሉ የካርጎ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ወደተቀረው የአፍሪካ ሀገራት ማዳረስ የሚቻልበት አቅም አለ:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምቹ መሠረተ ልማትን ማዘጋጀት ያስፈልጋል:: ሕክምና ምርት እንደሌላው ምርት ባለመሆኑና ጥንቃቄና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት የሚያስፈልገው በመሆኑ የሚመረትበት አካባቢ ምቹ መሆን አለበት:: የመሠረተ ልማት በበቂ ሁኔታ መሟላት አለበት::

ከዚህ አንፃር ራሱን የቻለና ሁሉንም መሠረተ ልማት ያሟላው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቷል:: በዚህ ፓርክ በመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት ማምረት ሥራ መሠማራት የሚፈልግ ማንኛውም አልሚ ቢመጣ የሚጠበቅበትን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ማምረት እንዲችል እንደሀገር የተቀመጡ ምቹ ሁኔታዎች አሉ:: እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ምቹ ሁኔታዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ያሉ ፖሊሲዎች፣ አሠራሮች፣ አደረጃጀቶችና መዋቅሮች መጠናከር አለባቸው:: ኢንዱስትሪን በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚያበረታታ ሀገራዊ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል::

ይህን ተከትሎ የጤና ፖሊሲ ውስጥ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ፍትሐዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል:: ይህንኑ ተከትሎ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚደግፍ ሀገራዊ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቷል:: የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ደግሞ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፉን በምርምርና በአቅም ግንባታ ይደግፋል፤ ያግዛል:: በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች የትም ሀገር ቢሄዱ ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሀገር ውስጥ የቁጥጥር አቅም ጠንካራ መሆን አለበት:: ይህን ቁጥጥር የሚያደርገው ደግሞ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው:: ይህም አምራች ዘርፉን የበለጠ ለማገዝና ምርቱ የበለጠ ጥራት ኖሮት ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር እየተሠራ ያለ ሥራ ነው::

ይህ ሁሉ ሥራ እየተሠራ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ይታያል:: ይህን ለማስተካከል ከግዢ ሰንሰለቱ ጀምሮ የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሀገር ውስጥ ምርት አንፃር አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ 25 የሚሆኑ በከፍተኛና በመካከለኛ ደረጃ የመድኃኒት ምርትን የሚያመርቱ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች አሉ:: ከሃምሳ የሚበልጡ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚያመርቱ የመድኃኒት አምራች ድርጅቶች አሉ::

የነዚህን አምራቾች አቅም በመጠቀምና መንግሥት በወሰደው ሪፎርም ከ8 ከመቶ የማይበልጥ የሀገር ውስጥ ምርት ሲያቀርቡ የነበሩ አምራቾች አሁን ላይ 37 ከመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል:: ይህ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተቀመጠው ግብ አንፃር ከፍተኛ ቢሆንም አሁንም ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል::

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደሚገልፁት አሁን የሚካሄደው ኤግዚቢሽን የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት ተደራሽነትን ይበልጥ ለመፍታት የሚያስችል፣ የሀገር ውስጥ መድኃኒትና ሕክምና ግብዓቶችን የሚያሳድግና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ዕድል የሚፈጥር ነው:: በዚህ ኤግዚቢሽንም ከ150 በላይ አምራቾች ይሳተፋሉ:: የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የሚሠሩ፣ ዘርፉን የሚደግፉና የሚያግዙ የፈጠራ ሥራዎች ይቀርባሉ:: ይህን ዘርፍ የሚደግፉ የፋይናንስ ተቋማትና ዘርፉን የሚቆጣጠሩ ተቋማትም ይሳተፋሉ:: የመድኃኒት የቁጥጥር አቅም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለዓለም የሚታይበትም ጭምር ነው ኤግዚቢሽኑ::

ይህ ኤግዚቢሽን አምራቾችና አቅራቢዎች በግብዓት፣ በአሠራርና በሌሎችም የእርስ በርስ ትስስር የሚፈጥሩበት፣ ከዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ጋርም የሚተዋወቁበትና በትስስር የሚሠሩበት፣ የቴክኖሎጂ ልውውጥ የሚያደርጉበትና አምራችነታቸውን የሚያሳድጉበት ነው:: በዚህ የፋርማሲዩቲካልና የሕክምና ግብዓት ዘርፍ ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ለማሳየትና ለማሳወቅ የሚያስችል ነው:: የሀገር ውስጥ ምርት ምን ያህል ጥራቱን ጠብቆ እየተመረተ እንደሆነና ሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም ምን ያህል ሀገራዊና ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ አንፃር ሚናው ምን እንደሚመስል ኅብረተሰቡ እንዲረዳ ለማድረግ የሚያችልም ነው ኤግዚቢሽኑ::

በተጨማሪም በዚህ ኤግዚቢሽን ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ምርምና ጥናት አቅራቢዎች ይገኛሉ:: ከዚሁ ጎን ለጎን የተለያዩ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ:: በዘርፉ እየገጠሙ ያሉ ማነቆዎች ባለቤት ኖሯቸው፣ አቅጣጫ ተቀምጦላቸው ችግሮቹ እየተፈቱ የሚሄዱበትንና ፖሊሲ አቅጣጫና አሠራር ሥርዓትን ለመቀየር የሚመከርበትና ውይይት የሚደረግበት ኤግዚቢሽን ነው::

የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግና ማበረታታት ከጤና ባሻገር የሀገር ኢኮኖሚን በማሳደግና ደኅንነትን ከማረጋገጥ አንፃር ፋይዳው ከፍተኛ ነው:: እስካሁን ባለው ሂደት መድኃኒትና የሕክምና ግብዓት ግዢና ጨረታ ሕግ ነፃ የውድድር መስፈርትና ሥርዓት ስለሚኖረው አምራቾች በማንኛውም ገበያ ውስጥ ገብተውና ተወዳድረው እንዲያሸንፉ ይጠበቃል:: በዚህ ሰዓት ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ካለመገኘት አንፃር አምራቾች ሊገጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶች አሉ:: እነዚህንም ችግሮች ጤና ሚኒስቴር አጥንቶ ለይቷል::

አምራቾች በዋጋ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመምጣት የሚያመርቱበት ሥነ ምሕዳር፣ ቴክኖሎጂ፣ የሚያመርቱት ምርት ብዛትና ጥራት፣ የሚጠቀሙት የሰው ኃይል፣ የሚያገኙት የሕክምና ግብዓት ወሳኝ ነው:: ከነዚህ ጋር በተያያዘ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት የሀገር ውስጥ ምርት እያደገ እንዲመጣ ማድረግ ካለልተቻለ በገበያ እኩል ተወዳዳሪና ተሳታፊ ሊሆኑና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አይችሉም::

ለዛም ነው በዚህ ዓመት ከሀገር ውስጥ ሕክምና ግብዓት አምራች ማኅበር ጋር በመሆን ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ በመስጠት ከ93 ከመቶ በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ምርቶች በውድድር ግዢ ተፈፅሟል:: ይህ በመደረጉም አቅርቦታቸው ከ8 ወደ 37 ከመቶ አድጓል:: ይህም ሊሆን የቻለው የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለብቻቸው እንዲወዳደሩ በመደረጉ ነው::

የግብዓት እጥረትም የአምራቾቹ ሌላኛው ችግር የነበረ በመሆኑ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን አዲስ መመሪያ ወጥቶ ግብዓቶችን ከውጪ ሀገር እንዲያመጡ ከ35 እስከ 55 ከመቶ የሚሆን የውጪ ምንዛሪ ቅድመ ክፍያ እንዲሰጣቸው ተደርጓል:: በዚህ ኤግዚቢሽንም ከሕክምና ግብዓት አምራች ማኅበራት ጋር በመሆን ተግዳሮቶችን ለመፍታት ውይይቶች የሚካሄዱ ይሆናል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You