ግንዛቤና ትኩረት ለሚጥል ሕመም

ወይዘሮ እናት እውነቱ የሚጥል በሽታ ታማሚ ናቸው። አብዛኛውን ሕይወታቸውን ያሳለፉት በእንግሊዝ ሀገር ነው። በኖሩበት እንግሊዝ ስለሚጥል ህመምና መደረግ ስላለበት የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ትምህርት የሚሰጠው ገና ከታዳጊዎች ጀምሮ ነው። መንገድ ላይ ሰው ቢወድቅ የስድስትና የሰባት ዓመት ልጅ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። በዛ ሀገር የሚጥል ህመም ምንም ማለት አይደለም። ብዙ ነገሮች ለታማሚዎች የተመቻቹ በመሆናቸው ህመሙ ቀሎ ነው የሚታየው። በውጪው ዓለም የሚጥል ህመም ያለበት ሰው ሲወድቅ ልክ እግር ኳስ ተጫዋች እንደወደቀ ያህል ነው የሚቆጠረው። ታዲያ የወይዘሮ እናት ምኞትም ልክ በእንግሊዝ ሀገር እንደተመለከቱት ከሚጥል ህመም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ ላይ እንድትደርስ ነበር።

የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስቷ ወይዘሮ እናት እውነቱ ዛሬ ላይ ‹‹ኬር ኢፕሊፕሲ ኢትዮጵያ›› የተሰኘና በሚጥል ህመም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን የሚሰራ ድርጅት መስርተው በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ይገኛሉ። እርሳቸው እንደሚሉት የኬር ኢፕሊፕሲ ኢትዮጵያ ሥራ በርካታ ዘርፎች ያሉት ሲሆን፤ ዋነኛው ሥራው ግን ከሚጥል ህመም ጋር በተገናኘ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው። በይበልጥ ደግሞ ድርጅቱ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው በትምህርት ቤት ሕፃናት ላይ ነው።

ድርጅቱ ከሚጥል ህመም ጋር ስኬታማ ህይወት መኖር እንደሚቻል ያምናል። በተለይ ሕፃናቶች ትምህርታቸውን ያለሃሳብ መከታተል እንደሚችሉና ተገቢውን እውቀት አግኝተው ነገ ራሳቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም እንደሚችሉ አምኖ ይሠራል። ሕፃናት እስኪያድጉ ድረስ በተወሰነ መልኩ ቤተሰብ ይንከባከባል። እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲመጣና ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ሲያጡ ብዙዎቹ የጎዳና ተዳዳሪ ይሆናሉ። በተለይ ከክልል የሚመጡ በርካታ የሚጥል በሽታ ታማሚ የጎዳና ሕፃናት በአዲስ አበባ ጤና መዋቅር ውስጥ ስላልታቀፉ ሕክምናና መድኃኒት አያገኙም። ከዚህ ችግር በመነሳት ድርጅቱ ከጤና ተቋማትና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን ሕፃናቱ መድኃኒታቸውን ማግኘት እንዲችሉ እያደረገ ነው።

ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚገልጹት፤ የሚጥል ህመም ያለባቸው ሕፃናት በርካታ ተፅእኖ ይደርስባቸዋል። የሚጥል ህመም ያለባቸው ሕፃናት የሀኪሞች ቁጥርም ዝቅተኛ ነው። አሁን ያለው የሀኪሞች ቁጥርም 7 ሲሆን፤ እነዚህ ሀኪሞች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በአብዛኛው እዚሁ አዲስ አበባ ላይ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሚጥል ህመም ታማሚዎች እንዳሉ ይገመታል። ከዚህ አንፃር በተለይ በክልል የሚገኙ የሚጥል ህመም ያለባቸው ሕፃናት በአብዛኛው የሕክምና አገልግሎት አያገኙም።

ህክምናው በክልል እንደልብ አለመኖሩ ደግሞ ከፍተኛ ጫና ያመጣል። ሕፃናቱም ያለባቸውን ህመም መግለፅ አይችሉም። ከእነርሱ ይልቅ ስለህመማቸው የሚናገሩላቸው ወላጆቻቸው ናቸው። በርግጥ ሁሉም የሚጥል ህመም ይጥላል ማለት አይደለም። የማይጥል ግን በርካታ የሚጥሉ የህመም አይነቶች አሉ። የሚያፈዙ ብዙ አይነት የሚጥል ህመሞች አሉ። ስለዚህ ሕፃናትን በደንብ ህመማቸውን የሚያስተውል የለም። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ በተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በመምህራን ላይም ከበሽታው ጋር በተያያዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ያከናውናል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሚጥል ህመም ታማሚ ሕፃናት በትምህርት ቤትም አሉታዊ ተፅዕኖ ይደርስባቸዋል። ለምሳሌ አንድ ሕፃን በህመሙ ምክንያት እንደወደቀ መጀመሪያ ከትምህርት ቤት ነው የሚወጣው። ስለዚህ ድርጅቱ በሚጥል ህመም ምክንያት ከትምህርት ቤት የሚቀሩ በርካታ ተማሪዎችን እየታገለ ዳግም ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥረት ያደርጋል። የሚጥል ህመም ሲያጋጥም ምን ማድረግ እንደሚገባ መምህራንና ተማሪዎችን በማሰልጠን ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እንደሚመለሱ ብዙ ሥራዎችን ሠርቷል።

የሚጥል ህመምን በሕፃናት ላይ ከሚያባብሱ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ስጋት እንደመሆኑ በተለይ ተማሪዎች በፈተና ወቅት በሚገባቸው ስጋት ምክንያት በተደጋጋሚ ስለሚወድቁና ይህ ድርጊት ደግሞ በመምህራን ዘንድ ውሸት እንደሆነ ስለሚታሰብ ተማሪዎቹን ከፈተና ያባርሯቸዋል። ይህ ደግሞ አመቱን ሙሉ የተማሩት ትምህርት ባከነ ማለት ነው። ህመሙ ሕፃናት ላይ ከህክምናውም፣ ከህብረተሰቡም፣ ከትምህርትም አንፃር አሉታዊ ተፅእኖ አለው።

ስለዚህ ከሚጥል ህመም ጋር በተያያዘ በሕፃናት ላይ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ የቀጣይ ሕይታቸው ጨለማ ነው የሚሆነው። ለዛም ነው ድርጅቱ በይበልጥ ሕፃናት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ ያለው። ድርጅቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋር እየሠራ ያለ ቢሆንም የሚፈልገውን ያህል ትብብር እያገኘ አይደለም።

ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚያብራሩት ድርጅቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥራውን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በአቅም ውስንነት ምክንያት በይበልጥ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ የሚጥል ህመም ታማሚ ሕፃናት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል። ይሁንና አንዳንዴ በክልሎች ለመምህራን በሚጥል ህመምና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠናዎችንና የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ይሰጣል።

በትምህርት ቤት ደረጃ ግን ድርጅቶች በአብዛኛው ሥራውን የሚያከናውነው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ100 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚጥል ህመም ዙሪያ ለተማሪዎችና መምህራን የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ሰጥቷል። መምህራንን ለብቻቸው አሰልጥኗል። ተማሪዎችም ጓደኞቻቸው ቢታመሙ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷቸዋል። በህመማቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡና በድርጅቱ ጥረት ዳግም ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ ሕፃናትም የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተመሳሳይ ወላጆችም ከሚጥል ህመም ጋር በተያያዘ ግንዛቤው ኖሯቸው ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ በየወሩ ለወላጆች ብቻ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ የእርስበርስ አቻ ግንኙነት፣ ስብሰባና ውይይት እንዲኖርና ስለልጆቻቸው ባህሪ እንዲነጋገሩ፣ እንዲማማሩና ልምድ እንዲለዋወጡ ይደረጋል። በተጨማሪም በየሳምንቱ ወላጆች የምክር አገልግሎት ያገኛሉ።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You