ከባርነት ወደ ላቀ ምሁርነት

ኢትዮጵያ፣ ደማቅ ታሪክ ያላቸው በርከት ያሉ ሰዎች አገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም፤ ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኟቸው ዕድሎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው የሚታወቅ ነው። እነኚህ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በሕዝባችን መካከል እንዲሰርጽ ለማድረግ ሲጥሩ ተስተውለዋል፤ መልካሙን ለማድረግ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩም ይታወቃል።

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልነበሩም። በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምህሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው። ከእነዚህ መካከል የኦሮሚኛ መፅሐፍ ቅዱስ ተርጓሚው ኦነሲሞስ ነሲብ አንዱ ናቸው።

ኦነሲሞስ፣ የተወለደው በ1848 ዓ.ም ኢሉባቦር ‘ሁሩሙ’ በምትባል መንደር ነበር። የልደት ስሙ ‘ሂካ’ (Hiikaa) ይባል ነበር። ስሙ በአፋን ኦሮሞ ‘ፈቺ’ የሚል ትርጉም ያለው ነው። ኦነሲሞስ፣ አባቱን ሞት የነጠቀው ገና የአራት ዓመት ህጻን ሳለ ነበር። ገና በለጋነት እድሜው ጋሻ ከለላ የሚሆነውን አባቱን ያጣው ሕጻኑ ኦነሲሞስ፣ በዘመኑ ተጧጡፎ ለነበረው ለባሪያ ፍንገላ ተጋለጠና በባሪያ ፈንጋዮች እጅ ወደቀ። ኦነሲሞስ በባሪያ ፈንጋዮች እጅ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ የኖረው ለአስራ ሁለት ዓመታት ያህል እንደ ሸቀጥ ሲሸጥ ሲገዛ በመንከራተት ነው።

ከአስራ ሁለት ዓመታት የእንግልትና የባርነት ሕይወት በኋላ ኦነሲሞስ እድል ፊቷን አዞረችለት። ዋርነር ሙዚንገር (Werner Münzinger) የተባለ የስዊድን ሰው ኦነሲሞስን ገዝቶ ነጻ አውጥቶ ለስዊዲሽ ሚሲዮን አስረከበው። በዚህን ወቅት ነበር ሂካ ተብሎ በእናት አባቱ የወጣለት ስም ወደ ኦነሲሞስ ነሲብ የተቀየረበት አጋጣሚ የተፈጠረው።

ከሂካ ወደ ኦነሲሞስ ነሲብ የተደረገው የስም ለውጥ ውስጥ ሁለት ባለታሪኮች ይነሳሉ። አንደኛው ኦነሲሞስ ነሲብን በባርነት ያሳድር የነበረ ሰው ነው። ይህ ሰው ኦነሲሞስ ነሲብን በባርነት ካሳደሩት ሰዎች ሁሉ ደጉ እሱ ስለነበር ‘ነሲብ’ የሚለው ስም ከዚህ ሰው ስም እንደተወሰደ ነው ታሪክ የሚያስረዳው።

ሌላው የስሙ መነሻ ‘ቅዱስ ‘ ኦነሲሞስ የተባለ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር የነበረ ሰው ነው። ይህ ሰው ልክ እንደ ሂካ ሁሉ ባሪያ የነበረና ከባርነት ነጻ ወጥቶ ክርስትናን የተቀበለ ሰው ስለነበር ሂካም የሱን ስም እንዲወርስ ተደረገ። በዚህም ምክንያት ሂካ ይባል የነበር ወላጆቹ ያወጡለት የልደት ስሙ ወደ ኦነሲሞስ ነሲብ ሊቀየር ችሏል።

ኦነሲሞስ ነሲብ በስዊዲሽ ሚሲዮን፦

ኦነሲሞስ፣ ከባርነት ነጻ ወጥቶ በዕለተ ትንሳኤ ተጠምቆ ክርስትናን ሲቀበል ስመ ክርስትናው ኦነሲሞስ ተባለ። ከዚህ በኋላ በምጽዋ ‘እምኩሉ’ (Émkullu) የስዊዲሽ ሚሲዮን ትምህርቱን መከታተል ጀመረ። ከዚያም ወደ ስዊድን በማቅናት በስቶኮልም Johannelund Missionary Training Institute ለአምስት ዓመታት የሚሽነሪ ስልጠናን ወሰደ።

“The Swedish Mission in Ethiopia» በሚል ርዕስ መፅሐፍ የጻፉት ዓለም እሸቴ እንደገለፁት፤ ቀዳሚዎቹ የሉንድሃል ተማሪዎች ኦነሲሞስን ጨምሮ በቁጥር ስድስት ሲሆኑ፣ ትምህርት ቤቱ፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በካታኪዝም፣ በአጠቃላይ ታሪከ፣ በጂኦግራፊ፣ በአርትሚቲክ እና በቋንቋ (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ስዊድንኛ፣ ጀርመን) ተማሪዎችን ያሠለጥናል፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስም እንደ እንድ የማስተማሪያ መጽሐፍ ያገለግላል ሲሉ ጽፈዋል።

ኦነሲሞስ፣ ትምህርት በመቅሰም ረገድ ልቡናው ብሩህ እንደ ነበር በትጋቱና ባስመዘገበው ውጤት አሳይቷል። ታዲያ በዚህ ወጣት ውስጥ ያለውን ዕውቀት የመሻት ጉልበት የተገነዘቡ የውጭ አገር መምህራን ልጁን ምፅዋ በሚገኘው የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ብቻ ሊገቱት አልፈለጉም፤ እናም ለበለጠ ትምህርት ባህር ተሻግሮ ይጓዝ ዘንድ እድል ከፈቱለት፡፡

ከስዊድን ስልጠናውን አጠናቆ ወደ ምጽዋ ከተመለሰ በኋላ ኦነሲሞስ ለሚሲዮናዊ ተልዕኮ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ጓዙን ጠቅልሎ ተነሳ። ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርግ ያሰበው ጉዞ እንዳሰበው ቀላል አልነበረም። በዚህ ምክንያት በኤርትራ በእምኩሉ የሚሽን ትምህርት ቤት ለረዥም ጊዜ ለመቆየት ተገደደ።

ፕሮሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ “Pioneers of Change in Ethiopia” በሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በገለጹት መሠረት፤ በወቅቱ አፄ ዮሐንስ በሚሲዮናውያን ላይ አድርገውት በነበረው የእንቅስቃሴ እገዳ ምክንያት ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ መካከለኛ የአገሪቱን ክፍል ሰንጥቆ መጓዝ የማይደፈር በመሆኑ የነሲሞስ ቡድን አቅጣጫውን በሱዳን በኩል በማድረግ ወደ ወለጋ የመግባትን እቅድ ከአምስት ኢትዮጵያውያንና ከሁለት ስዊድናውያን ጋር አዘጋጀ፡፡

እቅዱንም በተግባር ለመተርጎም ጉዞ ተጀመረ፤ እጅግ ብዙ ተጓዙ። አያሌ በረሃዎችንም አቆራረጡ። በቀይ ባሕር የተደረገውን የባሕር ጉዞ ጨምሮ መንገዳቸው ሁለት ወር ፈጀ። በመጨረሻም ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ድንበር ቢቃረ- ቡም በጊዜው በነበረው የአካባቢ ግጭትና የፀጥታ መታወክ ምከንያት ካሰቡት ሳይደርሱ እቅዳቸው ጨነገፈ።

ታዲያ በመገባደጃው ጠርዝ ላይ የውሃ ሽታ በመሆኑ ሁሉም ጥልቅ ሃዘን ተሰማቸው፤ በእጅጉም ልባቸው ተስበረ። ሃዘኑ ብቻ ሳይሆን የበረሃው ንዳድ ጠንቅ ፅኑ በሆነ ደዌ ሁሉንም ያስቃይና ያንገላታ ጀመር፤ ከመካከላቸው የቡድኑ መሪ የነበሩ ስዊድናዊው ጂ. ኢ. አርሄኒየስና የኦሮሞው ተወላጅ ወጣቱ ፊሊጶስ በረሐው ውስጥ ሕይወታቸው ሲያልፍ የተረፉት ከብዙ ስቃይና ድካም በኋላ ወደ ምፅዋ ተመለሱ፤ ያም ሆኖ የበረሃው በሽታና መዘዙ ኦነሲሞስንና ትሩፋቱን ለረጅም ጊዜ የሕማም ስቃይ ዳርጓቸዋል፡፡

የመጀመሪያው ጉዞ በእቅዱ መሰረት ባይከናወንም ኦነሲሞስ ተስፋ አልቆረጠም፤ በእምኩሉ የማስተማር ሥራውን ቀጠለ። አብሮም የተለያዩ መጻሕፍትን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ በመመለስ ለተከታዩ ጉዞ ይሰናዳ ጀመር። በዚህ መካከል ማሠልጠኛ ተቋሙ የመንፈሳዊ መጻሕፍትን ኀትመት ለማሳደግ በ1878 ዓ.ም አነስተኛ የማተሚያ መኪና ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት Songs and Psalms (Galata Waaqayoo Gofta Maccaa) የተስኘው የኦነሲሞስ ሥራ የማተሚያ ቤቱ የመጀመሪያ ሥራ በመሆን የኀትመትን ብርሃን አየ፡፡

ኦነስሞስ ከጀመሪያው ጉዞ ሁለት ዓመታት በኋላ እንደገና ከጥቂት ሰዎች ጋር የሸዋን ግዛት አቋርጦ ወደ ምዕራብ ለማለፍ ጥረት ቢያደርግም የይለፍ ወረቀት በመነፈጉ ወደ እምኩሉ መመለስ ግዴታ ሆነበት። ተደጋጋሚ የሆነው ይህ ስኬት አልባ ጉዞ ብዙዎችን ሲያሳዝን የኦነሲሞስን እምነት ግን በአያሌው ፈትኗል።

ከምጽዋ በመነሣት አንዴ በሱዳን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጅቡቲ፣ እንዲሁም በመሀል ሀገር በማድረግ ከሚሲዮናውያኑ ጋር ወደ ወለጋ ለመዝለቅ ያደረገው ያላሰለሰ ጥረት በመሃል አገር ሹሞች መጨናገፉ የኦነሲሞስን ልብ በእጅጉ የጎዳው ሆነ፤ ቢሆንም ተስፋ ቆርጦ ግን አልተቀመጠም።

ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቀውንና እጅግ አድካሚ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ይከውን ጀመር። ቀደም ሲል፣ አራቱ ወንጌላትን ጨምሮ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በአንዳንድ ፀሐፊዎች አማካይነት ወደ ኦሮምኛ የተተረጎሙ ቢሆንም፣ እንደ ኦነሲሞስ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመተርጎም የተነሳ ግን አልነበረም። ኦነሲሞስ፣ ይህን ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ የተለያዩ መጻሕፍትን የጻፈና ወደ ኦሮምኛ ቋንቋም የተረጐመ ነው፤ በወቅቱም አቻና ተስማሚ ቃላትን በማፍለቅ ረገድ ልዩ የቋንቋ ተሰጥኦ በነበራት (በአሰቴር ገኖ) በተባለች እንስት ራዳትነት ተግባሩን ከግቡ ሊያደርስ በቅቷል።

ከፍተኛ ጥንቃቄ የጠየቀው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ከፍጻሜ ለመድረስ በርካታ ዓመታትን ወስዷል። የአዲስ ኪዳን ትርጒም ከሰባት ዓመታት ጽኑ ምጥ በኋላ ተወለደ፤ ብዙም ሳይቆይ የብሉይ ኪዳን ትርጒም ተጀምሮ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በተፀነሰ በ13ኛ ዓመቱ ለፍሬ በቃ። የመጽሐፉ መጠናቀቅ ለብዙዎች ደስታን ከማጎናጸፍ ባለፈ ለተከታዩ የወንጌል ጉዞ የውስጥ ጥንካሬን፣ በተለይም በገዛ ቋንቋው መጽሐፉ ለቀረበለት ሕዝብ የእውነትና የዕውቀትን ፈለግ በማመላከት ረገድ ዐቢይ የሆነውን ሚና ተጫውቷል።

የኦነስሞስ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ከጊዜ በኋላ እልባት ላይ ደረሰ:: ሙለው የኦሮምኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተጠናቅቆ እንዳበቃ ኦነሲሞስ ጥቂት ባልደረቦቹን ይዞ ታኅሣሥ 1895 ዓ.ም መንገዱን ወደ አዲስ አበባ አቀና፤ ከረጅምና አድካሚ ጉዞ በኋላ 1896 ዓ.ም መባቻ ላይ አዲስ አበባ ደረሱ።

በወቅቱ አፄ ምኒልክ ወደ ሆለታ ወርደው ስለ ነበር እስኪመለሱ ድረስ አዲስ አበባ ተቀምጦ መጠበቅ ግድ ሆነበት፤ በነዚያ የጥበቃ ቀናት መካከል ግን ሥራ ፈቶ አልተቀመጠም፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ አቡነ ማቴዎስ ዘንድ በመቅረብ፣ «የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች» የተሰኘ ሥራውን አበረከተ:: አቡኑም፣ «መልካም! መልካም!» የተሰኘውን ቃል ሰነዘሩ። ቀጥሎም በኦሮምኛ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ አቀረበ። ንጉሡ ወደ አዲስ አበባ እስኪመለሱም አቡኑን በተደጋጋሚ በመጎብኘት ስለ መንፈሳዊ ጉዳይ አውግተዋል።

አፄ ምኒልክ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ አቡነ ማቴዎስ፣ ኦነሲሞስ ነሲብ የመጣበትን ጉዳይ ለንጉሡ ያቀርብ ዘንድ ሁኔታውን አመቻቹ። ኦነሲሞስም ወደ ወለጋ ዘልቆ ለማስተማር የሚያስችለውን ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ንጉሡን ጠየቀ። ከመጀመሪያው እትም አንዱ የሆነውን የኦሮምኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለአፄ ምኒልክ ገፀ በረከት አቀረበላቸው። ንጉሡም በደስታ ተቀበሉ። ወደ ወለጋ ሄዶ እንዲያስተምርም ተፈቀደለት።

ኦነስሞስ ወለጋ መግባቱ፣ እንዲሁም የቀለምና የሃይማኖት ትምህርትን ለማስተማር እድል በማግኘቱ ደስተኛ ሆኖ ለጥቂት ጊዜያት ቢቆይም በእምነቱ ሳቢያ የደረሰበት ስደት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ ተቃዋሚዎቹ ከወለጋ አዲስ አበባ እያመላለሱ ሙግት ከመግጠምም አልፈው ንብረቱ እንዲወረስና በእግረ ሙቅም ታስሮ ወህኒ እንዲወርድ አድርጎታል። በአጭሩ ኦነሲሞስ ለእምነቱም ሆነ ለነፃው ኑሮ አንጻራዊ ዕረፍት ያገኘው በ1909 አካባቢ ከልጅ ኢያሱ ባገኘው የእምነት ነጻነት በኋላ ነበር።

ኦነሲሞስ፣ ከወንጌል ሥራው በተጓዳኝ የቀለም ትምህርት እንዲሁም ከነበረው መጠነኛ የሕክምና እውቀት በመነሳት ሕሙማን በነጻ ያገለግል ነበር። ምንም እንኳ መደበኛ ትምህርት ቤት ባይኖርም፣ ኦነሲሞስ የባላባት ልጆችን በመሰብሰብ መጻፍና ማንበብ ማስተማር ቀጠለ። በርካታ ልጆችም በአማርኛ የተጻፉ የወንጌል ክፍሎችን ለማንበብ በቅተዋል፤ ይህም ኦነሲሞስ በማኀበረሰቡ ዘንድ የነበረውን መከበር ከፍ አድርጓል፡፡

ታዲያ በነዚህ ሁሉ ማኀበራዊና መንፈሳዊ ትግሎች መካከል በጽናት የተራመደ፣ ስደት፣ ግዞትና መገፋት ቢፈራረቁበትም እስከ መጨረሻዋ ርምጃ ድረስ የተጓዘ፣ ራሱንም ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ለውጥ የሰጠው፤ ከአገሩ ከወጣ ከሰላሳ አምስት ዓመታት በኋላ የአከባቢውን ልጆች በእውቀት ብርሃን አይናቸው እንዲገለጥ ብዙ ጥረት ያደረገው ኦነሲሞስ፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ነቀምቴ ወለጋ ሳለ በሰማንያ አንድ ዓመቱ ነበር።

እኛም ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና እንዲሁም በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር ለቻሉ ግለሰቦች ታሪካቸውን በመጥቀስ ለአበርክቷቸው ክብር እንሰጣለን። በዚህ የባለውለታዎቻችን ዓምድ ላይም ለአንባቢያን እናቀርባለን። እውቁ የመፅሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ኦነስሞስ ነሲብንንም ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሰገንን። ሰላም!

ለዚህ ፅሑፍ እንደ ምንጭነት የተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆችን ተጠቅመናል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You