የሩሲያና የሰሜን ኮሪያ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከ24 ዓመት በኋላ በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከጉብኝታቸው አስቀድሞ በላኩት ደብዳቤ ሰሜን ኮሪያ ሞስኮ በዩክሬን የምታካሂደውን ጦርነት “በጽኑ መደገፏን” ማድነቃቸውን የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
በዚህ ጉብኝታቸውም ከኪም ጋር በደህንነትና ሌሎች ጉዳዮች የትብብር ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል ብሏል ክሬምሊን።
ሀገራቸው ከፒዮንግያንግ ጋር “ከምዕራባውያን ቁጥጥር ውጭ የሆነ” የንግድ እና ደህንነት ስርዓት እንደምትገነባ መናገራቸውንም ነው ዘገባው የጠቆመው።
በፒዮንግያንግ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር የተገናኙት ፑቲን፤ ሰሜን ኮሪያ “የአሜሪካን ጫና፣ ማጭበርበርና ወታደራዊ ስጋት” ለመመከት የምታደርገውን ጥረት ሞስኮ እንደምትደግፍ መናገራቸውንም የሰሜን ኮሪያው ገዥ ፓርቲ ልሳን የሆነው ሮዶንግ ሲንሙን አስነብቧል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው መስከረም ወር በሩሲያዋ ቮስቶችኒ ኮስሞድሮም ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።
ፑቲን ግን በሰሜን ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ጉብኝት ያደረጉት እ.አ.አ. በ2000 እንደነበር ሬውተርስ አስታውሷል። ኪም ባለፈው ሳምንት የሩሲያና የሰሜን ኮሪያ ግንኙነት “ማንም የማይበጥሰው” ደረጃ መድረሱን መናገራቸው አይዘነጋም።
አሜሪካ በበኩሏ የሀገሪቱ ትብብር እያደገ መሄድ እንደሚያሳስባት ገልጻለች። የሀገሪቱ ብሄራዊ የደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፤ “የሚያሳስበን የፑቲን ጉብኝት ሳይሆን የሀገራቱ ግንኙነት በየጊዜው እያደገ መሄዱ ነው” ብለዋል።
ዋይትሃውስ ሩሲያ በዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት የፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፤ ሞስኮም ለሰሜን ኮሪያ የስፔስ ቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረገች ነው የሚሉ ክሶችን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል።
ፑቲንም ሆነ ኪም የዋሽንግተንን ክስ ባይቀበሉትም ሁለቱ ሀገራት የምዕራባውያኑን ማዕቀብና ጫና በትብብር ለመፍታት የሚያስችል ግንኙነት በመመስረት ላይ ናቸው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም