አንዳንድ ነገሮች አጀንዳ የሚሆኑት ሰዎች ያንን ነገር ትኩረት ሰጥተው ልብ ስለሚሉት ነው፡፡ ‹‹ሰው የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩትን ያህል ይስቃል›› እንደሚባለው አንድ ነገር በብዛት የሚሰራጨው የሰዎችን የውስጥ ስሜት ስለሚነካካ ነው፤ አለበለዚያ ማንም ልብ አይለውም፡፡
ሰሞኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣው ‹‹ኑሮ የከበዳቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓት በቤተ እምነቶች እያሳለፉ መሆኑ ተነገረ›› የሚለው የዜና ርዕስ በማህበራዊ ገፆች በቀልድም በቁም ነገርም አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ የዜናውን ዝርዝር ስታዩት ግን አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰጡት አስተያየት ነው እንጂ በጥናት የተረጋገጠ አይደለም፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ያላቸው የእረፍት ሰዓት በምሳ ሰዓት ስለሆነ ምናልባት በዚያ ሰዓት ወደ ቤተ እምነት ሲሄዱ አይተው ሊሆን ይችላል፡፡ ምሳ አልያዛችሁምና ከቢሮ ውጡ የሚል የለም እኮ! እንዲያውም ሲባል የምንሰማው በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ቢሮ ውስጥ የምግብ ትርፍራፊ እንዳይኖር፣ የቢሮው ጠረን ምግብ ምግብ እንዳይል (የሥራ ቦታ ስለሆነ) የሚከለክሉ እንዳሉ ነው፡፡ ምግብ ካልያዛችሁ ብሎ ‹‹ውጡ!›› የሚል የለም፡፡
እንዲያውም እኔ የማውቀው በተቃራኒው ነው፡፡ ምሳ የሚቋጥሩ ሰዎች ባለትዳር የሆኑ እና ገንዘብ ለመቆጠብ የሚያደርጉት ነው ተብሎ ነው የሚቀለድ፤ ምሳ የማይዙት ደግሞ ላጤ የሆኑ እና ውጭ በየካፌውና በየሆቴሉ የሚመገቡ ተደርጎ ነው የሚታሰበው፡፡ በመሰረቱ ሁለቱም ትክክል አይደለም፡፡ ምሳ መቋጠርም ሆነ አለመቋጠር ከግል ፍላጎት ጋር የሚያያዝ እንጂ የኑሮ ደረጃ መለኪያ አይደለም፤ እንዲያውም ለጤና የሚሻለው የቤት ምግብ መያዝ ነው፡፡ በቢሮ ውስጥ ባለው ልማድ ግን ምሳ ያልቋጠረ ሰው እንደ ልዩ ድሃ የሚታይ አይደለም ለማለት ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ዋናው ጉዳይ ግን ይህ አይደለም፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊው ይህን አስተያየት ቢሰጡም ባይሰጡም፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ይህን ዜና ቢሰራውም ባይሰራውም፤ የመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ችግር አጀንዳ ነበር፤ መቀለጃ ነበር፡፡ በወር ደሞዝ የሚኖር ሰው ምን ያህል ችግር ውስጥ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የቤት ኪራይ ከተከራዩ የደሞዝ ጣሪያ በላይ እየሆነ መሆኑን ማንም ያውቃል፡፡
ይህ አጀንዳ፤ አጀንዳ ከመሆኑ በፊትም በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ይቀለዳል፡፡ በፊልሞች፣ በመድረኮች፣ በመገናኛ ብዙኃን ከኑሮ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ቀልዶች ይዘታቸው የመንግሥት ሠራተኛን በችግረኛነት የሚስሉ ናቸው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ለምን ድሮ የነበረው ክብር አሁን ጠፋ? ጉዳዩ በሠራተኛው ድህነት ብቻ ወይስ በሌላ?
የኑሮ ውድነቱ እንዳገር ስለሆነ ምንም ትዝብትም ሆነ አስተያየት አያስፈልገውምና እንለፈው፡፡ የኑሮ ውድነቱ በየመገናኛ ብዙኃኑና በየመድረኩ አጀንዳ ስለሆነ ብዙ ተብሎበታል፡፡ አንድ ግን ልብ ያልተባለ የሚመስለኝ ነገር አለ፡፡ እዚህ ላይ ደፈር ብለን የመንግሥት ሠራተኛውን እና የራሱ የመንግሥትን ችግሮች ልንናገር ይገባል፡፡ ማስመሰልና መደባበቅ ወደ ዕድገትና ሥልጣኔ አይወስድም፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች ሊሆኑ የሚገባውን ያህል የነቁ እና የሠለጠኑ አይደሉም፡፡ አርዓያ መሆን ሲገባቸው መሆን አልቻሉም፡፡ የድሮውን እናስታውስ፡፡ ከአሥርት ዓመታት በፊት ‹‹የቢሮ ሠራተኛ›› የሚለው ትርክት ትልቅ ክብር ያለው እና ብዙዎች የሚመኙት ነበር፡፡ እንዲያውም የዚያ ልማድ ተፅዕኖ አድርጎባቸው ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው የመንግሥት ሥራ ሲቀጠሩ እጅግ በጣም ደስ ይላቸዋል፡፡ በገቢ የተሻለ ሌላ ሥራ ላይ ከሚሰማራ ይልቅ በገቢ አነስተኛ ሆኖ የመንግሥት ተቋም ውስጥ ሲቀጠር እንደ ልዩ ክብር ይታይ ነበር፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት የመንግሥት ተቋም ሠራተኛ መሆን፤ የመማር፣ የመሰልጠን፣ የማወቅ፣ በአጠቃላይ ከሌሎች የተሻለ ሁሉን አዋቂ ተደርጎ ይወሰድ ስለነበር ነው፡፡ እንኳን ሌላ ቀደም ባለው ጊዜ የግል ንጽህና ሳይቀር የሚኮረጀው ከመንግሥት ሠራተኛ ነበር፡፡ አስተዋይነት፣ ጨዋነት፣ ግርማ ሞገስ፣ ስክነት የመሳሰሉት አሉ ተብሎ የሚጠበቀው ከመንግሥት ሠራተኛ ነበር፡፡ እነዚህ ነገሮች ይኖሩታል ተብሎ የሚታመነው ደግሞ በምንም ሳይሆን የተማረ ስለሆነ ነው፡፡
በአሁኑ ዘመን ግን ትምህርት ስለተስፋፋ አብዛኛው ዜጋ የተማረ ነው፡፡ ወዲህ ደግሞ ቴክኖሎጂው ምቹ ስለሆነ ሁሉንም እኩል የማድረግ ዕድሉ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው፤ እንኳንም ሆነ የሚያሰኝ ነው፡፡
ችግሩ ግን ወዲህ ነው! ደፈር ብለን እንናገር ከተባለ የመንግሥት ሠራተኛው ያለው ንቃት እና ብቃት ከነጋዴ እና ከገበሬ እያነሰ ነው፡፡ ለሥልጣኔ የበለጠ አርዓያ መሆን ሲገባው የዝርክርክነትና የግዴለሽነት ማሳያ እየሆነ ነው፡፡ አንድ የግል ንግድ ቤት ውስጥ የማይታይ ብልሹ ድርጊት የመንግሥት ተቋም ውስጥ ይታያል፡፡ ለሁሉ ነገር ሞዴል መሆን ሲገባው ጭራሽ በተቃራኒው በግለሰቦች ቤትና ተቋም ውስጥ ባሉ ሥልጣኔዎች የተበለጠ ሆነ፡፡ የሚታዩት ችግሮች ደግሞ የገንዘብ ሳይሆን የአስተሳሰብ ችግሮች ናቸው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ግዴለሽነት ስላለ ነው፡፡ በዕውቀትና በአስተሳሰብ እየተበለጡ መጡ፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ አዋቂና አስተዋይ የሆነ ሰው ሲያጋጥም የሚመከረው ምክር ከመንግሥት ቤት እንዲወጣ ነው፡፡
በሕክምናው እና በትምህርቱ ዘርፍ ልብ በሉ! የተሻለ ዕውቀት ያለው ‹‹የግል ትምህርት ቤት ነው፣ የግል ሆስፒታል ነው›› የሚለው ትርክት ስር እየሰደደ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አደገኛ ትርክት ነው፡፡ የመንግሥትን ተቋማት እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ የልጆችንም ስነ ልቦና ይጎዳል፡፡ ምኞታቸው የመንግሥት ተቋም ውስጥ ገብቶ አገር ማገልገል ሳይሆን ገንዘብ ነክ ነገር ብቻ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ይህ ለምን ሆነ? ከተባለ ግን የመንግሥት በቂ ክትትል አለመኖርና ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት ነው፡፡ ከአካዳሚ የትምህርት ደረጃ ባሻገር የሠራተኞችን ስነ ምግባርና ሰብዓዊነት የመለየት አሰራር ስለሌለ ነው፡፡ ቢሮ ውስጥ መጮህ፣ ንፅህናን አለመጠበቅ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ ቀላልና ተራ ችግሮች ቢመስሉም አለመሰልጠንን ያሳያሉ፡፡
ወዲህ ደግሞ ከራሱ ከአመራሩ ጀምሮ በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተተበተበ ስለሆነ ነው፡፡ ከአንድ ቦታ በስርቆት የተባረረ አመራር ሌላ ቦታ በሌላ ኃላፊነት (ምናልባትም በተሻለ) ሊመደብ ስለሚችል ነው፡፡ ይህ ለብዙ ዓመታት ሲወቀስ የቆየ ችግር ነበር፡፡ ሥልጠና ሲሰጥ እንኳን ከመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴዎጂዎች ጋር የተያያዘ ጉዳዮች ይበዙበታል፡፡ መሰልጠንን፣ ሰብዓዊነት ቀረጻን፣ በአጠቃላይ ስነ ምግባር ተኮር የሆኑ ሥልጠናዎች አይሰጡም፡፡ ሠራተኞች ‹‹ብቁ›› የሚባሉትም ምናልባትም የማያረፍዱ ወይም ከሥራ የማይቀሩ በመሆናቸው እንጂ በጨዋነትና በስነ ምግባር ማበረታቻ ሲደረግ ብዙም አይታይም፡፡
በመሰረቱ የመንግሥት ሠራተኛ ለእነዚህ ነገሮች ማበረታቻ የሚያስፈልገው መሆን አልበረበትም፤ አገር ሊቀይር አገር የተረከበ ዜጋ ነው፡፡ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ምናልባትም ከመጀመሪያ ዲግሪ በታች የትምህርት ደረጃ ብዙም የለም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁት አገር ሊረከቡ ቃለ መሃላ ፈጽመው ነው፡፡ ስለዚህ የነቁ እና የበቁ መሆን አለባቸው፡፡
በአጠቃላይ ግን ችግሩ ከራሱ ከሠራተኘውም ከመንግሥት አመራሮችም ሥር የሰደደ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ የተለመደውን ትርክት መቀየር አንችልም፤ ስለዚህ ሁሉም በቆራጥነት መሥራት አለበት፡፡ አዲስ የንቃትና የብቃት ባህል መገንባት አለበት፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው የድህነትና የኋላቀርነት መቀለጃ መሆን የለበትም! ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ‹‹ለምን እንዲህ አሉኝ!›› እያሉ መፎከር ሳይሆን ለመለወጥ መዘጋጀት ነው፡፡ የንቃት እና የብቃት፣ የሥልጣኔ እና የሰብዓዊነት፣ የአስተዋይነትና የትህትና አርዓያዎች መሆን አለብን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም