ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ላለፉት 42 ዓመታት ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ያገለገሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና የሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ አስከሬን ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የስንብት ስነ ስርዓት ላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እና ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ የሚከተለውን የምስክርነት መልእክት አስተላልፈዋል።
የ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ምስክርነት
ጀነራል ሰዓረ መኮንን
ጀነራል ሰዓረ በአስራ ሰባት ዓመታት በነበረው የትግል እንቅስቃሴ ዘመን ሰራዊቱን ለማዘመን እንደ ሞዴል የተጠቀምንበት ጀግና ሰው ነው። በሰራዊት ግንባታ፣ በአመራር፣ በጀግንነት፣ ውጊዎችን ጥሶ በማለፍ፣ ትጋትን የተላበሰ ጀነራል መኮንን ነው። እንዲህ አይነት ባህሪ ትውልድን ይቀርፃል። ጀነራል ሰዓረና እንደ ጀነራል ሰዓረ ያሉትን ጀነራሎች እንደ ሞዴል እየወሰድን ሰራዊታችን በነሱ ባህሪ እንዲገነባ እያደረግን ነው። በሀገር ደረጃ የታወቀ ሀገሩን መከላከል የሚችልና ለሌሎች የሚተርፍ ጀግና ሰራዊት እንዲፈጠር ከፍተኛ የሞዴልነት ሚና የነበረው ጀነራልም ነበር።
እኔም ስታገል የተገነባሁበት፣ ከተገነባሁ በኋላም ሌሎችን የገነባሁበት አንዱ ሞዴል ስራቸው የሰርዶ ውጊያ ነው። የሰርዶ ውጊያ ሀምሳ ሴንቲ ግሬድ ውሃ በኮዳ ብትይዝ ውሃው ፈልቶ ለመጠጣት የማትችልበት የአየር ፀባይ ያለው ነው። በሰርዶ ውጊያ ፀረ ህዝብ የሆነውን ሀይል ግብአተ መሬት ለማስገባት ጓዶችም ተልኳቸውን ለመወጣት ሲሉ የያዙት ውሃ በሙቀት ፈልቶ የሚያልቅበትና ብዙ ጓዶች በውሃ ጥም ያለቁበት ነው። የተቀሩት ደግሞ ግዳጃቸውን ጨርሰው የተመለሱበት ይህን አይነት መከራ ያለበት ውጊያ በፅናት የመራ ሰው ነው።
የሱን ጀግንነት ለሰራዊቱ ሞዴል መሆን የሚያስችል ነው። ይች አንዷ ዘለላ ናት እንዲህ አይነት ብዙ መከራ ያለበትን ውጊያ ያለፉ ጀግና በመሆኑ ከሰዓረ ተምረናል። እንደ ጀነራል ሰዓረ ያለ ጀግና ሰራዊት መገንባት አለበት እያልን እናስተምራለን። ሰራዊታችንም ጀግና ለመሆን መነሳሳት አለበት። ይህ የትጥቅ ትግል ጊዜ ነው።
እራስን ለህዝብ ሉአላዊነት ለህዝብ ነፃ መውጣት አሳልፎ የሰጠ ጀግና ነው። ጀነራል ሰዓረ እኛ የገነባነውን ሰራዊት እንደ ሞዴል ወስደን ስንገነባ አሁን ያለውን ሰራዊት ልክ እንደሱ ጀግና ሰራዊት ነው። ጀግና ሰራዊት ብቻም ሳይሆን መሰረቱ እርሾ ስለተጣለ የእሱን አርአያ ተከትሎ ጀግንነቱን እንደጠበቀ የሚሄድ ሰራዊት አገራችንን ይመራታል ብየ አስባለሁ።
ከደርግ ውድቀት በኋላ ጀነራል ሰዓረ በርካታ ግዳጆችን ተቀብሎ በጣም ትላልቅ የሰራዊት ክፍሎችን ሲመራ የነበረ ጀግና ነው። ኮሮችንና እዞችን መርቷል። የመራቸው ሰራዊቶችም በሱ አምሳያ ተቀርጸዋል። በኤርትራ ጦርነት ሀገራችን ጦርነቱን በድል እንድትወጣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። በትጥቅ ትግሉ የነበረው ጀግንነት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ አሳይቷል። ሀገራችን እንደዚህ አይነት መሪ ስለነበረና ስላላት ልትኮራ ይገባታል። ኮርታለችም የሚያኮራ ስራም ሰርቷል።
በቅርበት አብረን ባንሰራም በተለያዩ እዞች ውስጥ ያለን የሰራዊት አመራሮች እንተዋወቃለን። በደንብ አድርገን ደካማና ጠንካራ ጎኖቻችንን እንተዋወቃለን። ስለዚህ አጠገቡ እንዳለ ሰው አውቀዋለሁ። የግል ባህሪውም በጣም የተረጋጋ ሰው ነው። ሌላውንም ማረጋጋት ይችላል። ሰው አክባሪ ነው። ሰዓረ ጓደኛ አይመርጥም። ከሁሉም ሰው ነው የሚማረው። ከታናሹም፣ ከትልቅ ኦፊሰሮችም፣ ከወታደርም፣ ከሚኒስትርና ከሀገር መሪ ለመማርና ለመቅረብ የሚያስችል ባህሪ አለው። እንዲሁም ቀላል ሰው መሆኑን እመሰክራለሁ ።
ጀነራል ሰዓረ በጣም የተረጋጋ ከመሆኑ የተነሳ ችግሮች ለመፍታት የሚሄድበት ጥበብ ለሰራዊታችን ሞዴል ነው። በሰላሳና በአርባ ዓመት አንዴ የሚፈጠሩ እንዲህ አይነት ሰራዊትም ይሁን የሀገር መሪዎችን ማጣት በጣም ያማል። ጦርነት ኑሮ ፣ጦር ሜዳ ቢሞቱ ተፈጥሮ ነው ያጋጥማል ብሎ መውሰድ ይቻል ነበር። ከእኩዮቻቸው ጋር ተጣልተው ቢሞቱ የሰው ባህሪ ነው ይባላል። ነገር ግን ለሀገር እየሰራ ሁሉንም እያቻቻለ፣ እየመራ፣ እያሰማራና እያስተናገደ ባለበት ወቅት መገደሉ ያሳዝናል። ምን በድሎ ነው የሚገደለው? ይህ ሁኔታ በጣም ያማል። ጀነራሉ የስልጣን ጥማትም የለውም። ሰው እንዳይሞት የተፈናቀለ እንዲመለስ ሲሰሩ ነበር። እንዲገደሉ የሚያደርግ ተግባር የላቸውም።
ጀነራል ሰዓረ የሚሰራለትን አላማ በማሳካት ገዳዮችን ለማሳፈርና የእነሱ ፍላጎት እንዳይሳካ ለማድረግ ቆርጠን እንታገላለን። ሰራዊታችንም በቆራጥነት ይታገላል። እንዲሁም ሰራዊታችን አንድነቱን ጠብቆ፣ የጀነራል ሰዓረን አርማ፣ ፅናት ይዞ ኢትዮጵያ ሀገሩን ለመጠበቅ በፅናት እንድንቆም እጠይቃለሁ። የግድያው አላማም እኛን በዘር መበተን፣ መንግስት እንዳይረጋጋ፣ እንዲፈርስና በሽግግር መንግስት ስም ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚደረግ ሴራ ነው። ነገር ግን ይህ እኩይ ተግባር እንዳይሳካ እንታገላለን።
ጀነራል ገዛኢም ለዚች ሀገር የለፋና የደከመ ነው። በትጥቅ ትግሉም ከሰዓረ ባልተናነሰ ሁኔታ ያለፈ ሰው ነው። ከህገ መንግስቱ ምስረታ በኋላም የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆነው ብዙ ስራ ሰርተዋል። የሎጅስቲክ መሀንዲስ ብለን ነው የምናውቃቸው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሎጀስቲክ ባህሉን የገነባውና ፈር ያስያዘ ጀግና ነው። ፈጥኖ መዘጋጀት የሚችል ከፍተኛ የሆነ ሀይል በአንድ ጊዜ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እውነትም ለሎጀስቲክ የተፈጠረ በጣም በሳል መሪ ነው። ጓደኛው ቤት ሻይ ለመጠጣት ሄዶ መገደል አልነበረበትም። አሁን የግል ስራ ነው የሚሰራው፣ ፖለቲካውን በጣም የራቀ ነው። ለሀገሪቷ ሰርቶ ሀገሪቷ ህገ መንግስት እንዲኖራት አንድነቷ ተጠብቆ እዚህ እንድትደርስ ሚና ያለው ሰው ነው። ነገር ግን በማያውቀው ነገር መገደሉ ያሳዝናል። ሀገሪቷ አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል ያደረገ ጀግና ነው። ነገር ግን ‹‹የማይረባ ሰው ጀግና ያበላሻል›› እንደሚባለው በማይረባ ሰው ተገድሏል። ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተናል። የክልል አመራር የክልል ካቢኔ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የሚረሽን የስልጣን ጥመኞችና ስድ አደጎች ችግር ፈጥረውብናል። እንቁ መሪዎቻችንን አጥተናል። ከፍተኛ የሀዘን ድባብ ውስጥ እንገኛለን። ግን ደግሞ እናሸንፋለን።
ሌተናል ጀኔራል አበባው ታደሰ
ስለ ጀነራል ሰዓረ
ጀነራል ሰዓረ ዓላማው ፅኑ የሆነ፣ ለህዝብ ጥቅም እራሱን አሳልፎ የሰጠ፣ ከህዝብ በላይ እራሱን አይቶ የማያውቅ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ አንድ ቀን ሳይንቀባረር ህይወቱን በሙሉ ለህዝብ የሰጠ ጀነራል ነበር። ጀነራል ሰዓረ በስራው ምስጉን፣ ጦርነትን በሚገባ የሚያውቅ፣ ጦርነትን በሚገባ የሚያዘጋጅ፣ ብልህ፣ ጠንቃቃ፣ ጀግና የጀግና ጀግና ሞዴል ነበር። ሰዓረ እራሱ ብቻ ጀግና አልነበረም። ጀግና ማፍራት የሚችል ብቻ ሳይሆን መፍጠር የሚችል የጀግና ሞዴል ነበር። እውነቱን ለመናገር አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ምርጥ ኮማንደር ነው።
ሰዓረ ባለበት ሁሉ ድል አለ። ሰዓረ ጦርነት ለእሱ ፊልም ነው፤ የተረጋጋ ነው። ችግርን መፍታት የሚችል። ግን ጀግኖችን አፍርቷል፣ እሱን የሚተኩ ብዙዎች አፍርቷል። ጀነራል ሰዓረ እጅግ ሲበዛ ኢትዮጵያዊ ነው። ሃይማኖት የማይለይ፣ ዘር ብሄርን የማይለይ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነበር። እዚህ ላይ አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ ከፈለገ ይፈንዳ። ይሄ ለውጥ ከመጣ በኋላ ሰዓረ እንደ ከሀዲ ተቆጠረ። በጥቂት ቡድኖች ኢትዮጵያዊነቱን አሳልፎ እንዲሰጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ደረሰበት።
“አበባው እንደዚህ እያሉኝ ነው። ቤተሰቤ ይበተናል እንጂ ኢትዮጵያዊነቴን አሳልፌ አልሰጥም። ማንም ይምጣ ማን ለኔ መሪዬ ነው። አክብሬ እስከምሞት ድረስ በኢትዮጵያዊነቴ ሳልደራደር እሰራለሁ” አለኝ። ጀነራል ሰዓረ ቤተሰቦቹን አክባሪ፣ ጓደኞቹን ወዳጅ፣ የተበተነን ሰብሳቢ፣ ቀልድ አዋቂ፣ እጅግ ሳቂታ ነበር።
ስለ ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ
ሜጀር ጀነራል ገዛኢ የአላማ ፅናቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ደግሞ አንድን ጦርነት ከሚያሸንፈውና ወሳኝ ተብለው ከሚጠሩ ዋንኛ ስራዎች ከኋላ የሚሰራው የሎጀስቲክ ስራ ነው። ምን አልባትም በኢትዮጵያ ሳይሆን አሁን ካለው ትንሽ ወደኋላ ሄደን ሜ/ጀነራል ገዛኢን የሚያክል ሎጂስቲክስ መሪ አለ ብዬ አላምንም። በመስሪያ ቤቱ በነበረበት ወቅት ጭንቅላት አለው፣ ሀሳብ ያመነጫል፣ አርቆ ያስባል፣ አስተዋይ ነው፣
ስሜት አያጠቃውም።
ለመከላከያ የሰራው ስራ ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ መንግስት ሲሰጥ፤ ከራሳችን ሰላም አልፈን የወንድሞቻችን ሰላም ለመጠበቅ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተ አሁን ላለው የሰላም አስከባሪ መሰረት የጣለ ብልህ መሪ ነበር። ዘር የማይለይ ሁሉንም እኩል አድርገን እንድናይ ከስሜት እንድንወጣ መካሪያችን ነበር። ቤተሰቡን ወዳጅ ጠንቃቃ ብልህ አስተዋይ መሪ ነበር።
እኔ የሚገርመኝ ከልጅነታቸው ጀምሮ እራሳቸውን ለሞት ያዘጋጁ ወንድሞቻችን ምን አልባትም ሞት አሽትተው ግማሽ መንገድ ሄደው የተለማመዱ ሰዎች እስከማውቃቸው ድረስ ግን ህይወታችን ያልፋል ብለው የሚያስቡት ጥይት በግንባራቸው እንጂ በጀርባቸው ይመታናል ብለው አስበው አያውቁም ።
ሁላችን ልባችን የሰበረው ህይወታቸው ማለፉ አይደለም። የሞቱበት አግባብ ሁለተኛ ሞት በመሆኑ ነው። እኔ እንደሚታየኝ ከዚህ በኋላ ቆም ብንል። እንደ ህዝብ ቆመን ብናይ፣ ጣት ባንቀሳሰር፣ በሀሳብ መማር ካልቻልን በደም እንማር። እኔ ላስተላልፍ የምፈልግው የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለም ይሁን ከአገር ውጪ ያለም ይሁን አንድነቱን ነው የሚወደው። ሰላሙን ነው የሚወደው። ፍቅርን መቻቻልን ነው የሚወደው። ብልፅግናን ነው የሚወደው። ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም አይነት ፍላጎት የለውም። መሪዎቻችን እባካችሁ ይሄን ተረድታችሁ ምሩን። እኛም መሪዎቻችንም እንዲሁ ባለንበት ቦታ አንድ አንድ ጠጠር ወርውረን ሀገራችን ትልቅ እናድርግ።
በሀገሪቱ ውስጥ ያላችሁ የፀጥታ ሰራተኞች በሙሉ ከባድ ፈተና ውስጥ ሀገሪቱ አለች። በእጃችሁ ውስጥ ያለው እሳት በየትኛውም መለኪያ ቢሆን ከሀገራችሁና ከህዝባችሁ በታች እንጂ ከሀገራችሁና ከህዝባችሁ በላይ አይደለም። ለመለዮዋችሁ ስትሉና ለምትወድዋት ባንዲራችሁ ስትሉ በፍፁም ታማኝነት መንግስትና ሀገራችሁን እንድታገለግሉ ታላቅ አደራ አላችሁ።
ለኢትዮጵያ መንግስትም፣ ለጀግኖች ቤተሰብም መፅናናትን እየተመኘሁ፤የማይታለፍ ነገር ግን የለም። እናልፈዋለን አንበተንም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011