ለሕፃናት ሁለንተናዊ እድገት የላቀው የሴቶች ሚና

ትውልድ ለማሰቀጠል ዋናው መሰረት እናትነት ነው። በሴትነት ውስጥ የተሰጠ ታላቅ ፀጋ እናትነት ከፀጋነቱም በላይ በርካታ ኃላፊነቶችን በውስጡ የያዘ ስለመሆኑ ይታወቃል። ለዚህም መሰለኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕፃናት የተሟላ እድገት በሴቶች እጅ ነው የሚሉን።

ይህ ጉዳይ የተነሳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበጀት ዓመቱ ሁለት ጊዜ የሕፃናት ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ ቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ጥበቃ እና መብት ደኅንነታቸው ከማስከበር አኳያ ሁለት ጊዜ ደማቅ ፌስቲቫሎችን ያካሂዳል የሚለውን ጉዳይ ለጋዜጠኞች በተናገረበት ወቅት ነው፡፡ ቢሮው እንደሚለው ኅዳር 11 ዓለም ዓቀፍ የሕፃናት ቀን እና ሰኔ 9 የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ሲያከብር በቢሮው የተከናወኑ ተግበራትን ሊያሳይ ብሎም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤን ሊፈጥር የሚያስችል መርሃ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑን ተናገሯል።

በያዝነውም ዓመት የአፍሪካ የሕፃናት ቀንን በአፍሪካ ለ34ኛ እንደ ሃገር ለ33ኛ ጊዜ “የሕፃናትን ትምህርት፣ ተሳትፎ እና ጥራት ለማሳደግ ጊዜው አሁን ነው” በሚል መሪ ቃል በየክፍለ ከተማው እና እንደ ማዕከል በቢሮው በተለያዩ ውይይቶች፣ የግንዛቤ መስጫ መድረኮች እና አዝናኝ መርሃ ግብር ኩነቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የበዓሉን መከበር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የቢሮው ሕፃናት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ተስፋዬ የከተማው አስተዳደሩ ለነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፤ ቢሮውም በከተማ አስተዳደሩ የተሰጠው ተልእኮ መሰረት በማድረግ ከቀዳማይ ልጅነት ጀምሮ እስከ ሕፃናት አስተዳደግ፣ መብትና ደህንነት ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ ማለት አንዲት እናት በማህፀኗ ልጅ ካደረ ጀምሮ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ፅንሱ ጉዳት እንዳይደርስበት የተለያዩ ድጋፍ የሚደረጉበት ሁኔታ መኖሩን አመላክቷል። እናት ደህና መሆኗ ለልጅ ጤና ነውና ነፍሰጡሯ የተመጣጠነ ምግብ አግኝታ በቂ የሕክምና ክትትል አድርጋ በኢኮኖሚ እየተደገፈች ትወልድ ዘንድ የከተማ መሰተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በጅቶ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በእርግዝና ጊዜ የተጀመረው ድጋፍ ሕፃኑ ተወልዶ ምግብ እስኪጀምር ለአጥቢ እናት ድጋፍ እየተደረገ ይቆያል። ከዛም በኋላ ልጁ ተጨማሪ ምግብ ሲያስፈልገው ተጨማሪ አልሚ ምግቦች እየቀረበለት በአካልም በአእምሮም የጎለበተ ልጅ እንዲሆን በከተማ መስተዳደሩ ታስቦ የተዘጋጀ ፐሮጀከት ድጋፉን ያስቀጥላል ብለዋል።

እናትም ልጄም ምን ላብላው ብላ ሳትሳቀቅ የምግብ አቅርቦት ከመኖሩም በሻገር፤ በድህነት ቅነሳ አገልግሎትም እናት ተገቢውን ደጋፍ እያገኘች ሳትቸገር ለልጇ በቂ ፍቅርና ክብካቤ እየሰጠች ታሳድጋለች። ከዚህም በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ስለ ሕፃናት አስተዳደግ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የተለያዩ ድጋፎችን እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ወይዘሮ እመቤት አክለውም የሕፃናት መብትና ደህንነት በማስጠበቅ፣ ክብካቤና አስተዳደግ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ግንዛቤ በማሳደግ ማረም ተገቢ በመሆኑ በዓመት 2 ጊዜ የሕዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያስችሉ የዓለም ሕፃናት ቀን እና የአፍሪካ ሕፃናት ቀንን ምክንያት በማድረግ ፌስቲቫል እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመትም ሕዳር 11 የዓለም ሕፃናት ቀን በተለያዩ ሁነቶች በርካታ የከተማችን ነዋሪ እና ሕፃናት በማሳተፍ የተከበረ መሆኑን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ለ34ኛ በሀገራችን ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረው የአፍሪካ ሕፃናት ቀን በተለያዩ ሁነቶች የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት እንደሚከበር አብራርተዋል፡፡

በቢሮው የሕፃናት መብት ደህንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ታፈሰ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕፃናት ቀን በነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ቀረፃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባለው በሕፃናት ትምህርት ተሳትፎና ጥራት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሕፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት የተሟላ ሊሆን የሚችለው መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ልክ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩበት ነው ብለዋል፡፡

የሕፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ አቶ አናንያ ያዕቆብ በበኩላቸው የዘንድሮው የአፍሪካ ሕፃናት ቀን የተለያዩ አካላትን ያሳተፉ የምክክር መድረኮች፣ ፓናል ውይይት እና ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ሕፃናትና ወላጆች (አሳዳጊዎች) ያሳተፈ ፈስቲቫል ከከተማው ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ ጋር በመቀናጀት እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ እመቤት ሕፃናት በየትኛውም ረገድ ቢሆን መብት ደኅንነታቸው ተጠብቆ፣ ምቹ አካባቢ ተፈጥሮላቸው፣ በዕውቀትና በሥነምግባር የተነጹ እንዲሆኑ እና ለነገ ጥሩ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል ዛሬ ብዙ ልንሠራ ይገባል፡፡ በዚህም ምክንያት የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በከተማዋ ለሚገኙ ሕፃናት መብታቸውን ከማስጠበቅ እና ደኅንነታቸውን ከማረጋገጥ አንጻር በርካታ ሥራዎች እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡

ከተከናወኑት ተግባሮች መካከልም ማንኛውም ሕፃን የልደት ምዝገባ ምስክር ወረቀት የማግኘት መብቱ እንዲረጋገጥ በማድረግ 155ሺ063 የሕፃናት ምዝገባ ተደርጓል። ሕፃናት በጤና እንዲኖሩ አስፈላጊ ክትባቶችን ስለመከተባቸው በመከታተል 477 ሺ 220 ለሚሆኑ ሕፃናት ከትባቶች መዳረሳቸውን ለማወቅ አንደተቻለ አብራርተዋል።

ሕፃናት ከጉልበት ብዝበዛ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ እና መሰል ጥቃቶች ነጻ እንዲሆኑ መሥራት፤ ሕፃናት በወላጆች እና በአሳዳጊዎቻቸው በተሻለ አያያዝና አስተዳደግ በሥነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ግንዛቤ መስጠት፣ ማሠልጠን 7ሺ 820 ቤተሰቦች ስልጠና አግኝተው ልጆቻቸውን በተገቢው መልኩ እንዲያሳድጉ ማድረጋቸውም ወይዘሮ እመቤት አስረድተዋል።

ትምህርት ቤቶች ከሕፃናት ጥቃት እና ከአድልኦ ድርጊት ነጻ እንዲሆኑ እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናት እንደአስፈላጊነቱ የትምህርት ድጋፍ በማድረግ ማስተማሪ ስራ እየሰራ መሆኑን እንደሚከታተሉ ያስረዱት ወይዘሮ አመቤት ሕፃናት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትክክለኛው ዕድሜ መጀመራቸውን ማረጋገጥ እና መሰል የመብት ማስጠበቅ ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምጣኔን፣ ያለዕድሜ ጋብቻ ምጣኔን፣ ከሕፃናት ጥቃት እና መድልኦ ነጻ ስለኾኑ ትምህርት ቤቶች ምጣኔ፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የትምህርት ድጋፍ ስለማግኘታቸው እና በአዎንታዊ አስተዳደግ ተይዘው ስላሉ ሕፃናት ምጣኔ በ119 ወረዳዎች መረጃ በመሰብሰብ የዳሰሳ ጥናት መሥራት መቻሉንም ተናግረዋል።

ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሕፃናትን ጉዳይ በዕቅዶቻቸውና በፕሮግራሞቻቸው አካተው እንዲተገብሩ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ እመቤት በዚህ ተግባር ተቋማቱ ዐቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የዐቅም ግንባታ ሥልጠና የመስጠት፣ ክትትል ድጋፍና በማድረግ በግብረ-መልስ ሥራዎቻውን ማጠናከር፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ ሕፃናት አያያዛቸውና አስተዳደጋቸው በስታንዳርዱ መሠረት ተገቢውን አገልግሎት ማግኘታቸውን የሚያሳይ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን በማከናወን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ በማገዝ የሕፃናት መብት ተጠቃሚነት ላይ አበክሮ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለልጅ እናት ካልሆነም የተማሏ ቤተሰብ በማስፈለጉ ወላጅና አሳደጊ የሌላቸውን ልጆች በአማራጭ የሕፃናት ድጋፍ ክብካቤ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን የቢሮው ሕፃናት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ተናግረዋል።

በአማራጭ የሕፃናት ድጋፍ ክብካቤ አገልግሎቱም በሃገር ውስጥ ጉዲፈቻ 181 ሕፃናት፣ በአደራ ቤተሰብ አገልግሎት 50 ሕፃናት ቤተሰብ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

አክለወም በዚህ ዓመት ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም የተከበረው የአፍሪካ ሕፃናት ቀን “የሕፃናትን ትምህርት፣ ተሳትፎ እና ጥራት ለማሳደግ ጊዜው አሁን ነው” በሚል መሪ ቃል መሠረት መጪው ጊዜ ዛሬ በልጆች ትምህርት ላይ የተመሠረተ እንደመኾኑ መጠን በሕፃናት ትምህርት ላይ አጠንክረን ልንሠራ ይገባል የሚል ሀሳብ የያዘ መሆኑንም ጠቆመዋል፡፡

ትምህርት ለአንድ ሃገር የነቃ ማኅበረሰብ ከመፍጠር፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማምጣት፣ ማኅበረሰባዊ ትብብር ከማጠናከር የዕውቀት ሽግግር ከማድረግ፣ አኗኗርን ከማዘመን እና የማኅበረሰቡን የኑሮ ስልት ከማቅለል አንጻር ከፍተኛውን ድርሻ ይወጣል፡፡

ትምህርት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ መኾን ያለበት ዓለም ዐቀፋዊ፣ መሠረታዊና ሰብአዊ መብት ነው። የሕፃናት ትምህርት ማሳደግ ሲባል መደበኛ ትምህርት የማግኘት እና በትክክለኛው ዕድሜአቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጀመር የመማር ዕድላቸውን ማሳደግ ማለት ነው። በተጨማሪም ለትምህርት ቤቶች ተጨማሪ የማስተማሪያ ግብዓቶችን መስጠት፣ የተሻሉ የሠለጠኑ መምህራንን መቅጠር፣ የወላጆች ተሳትፎን ማሳደግ፣ ከጥቃት ነጻ እና ምቹና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የት/ቤት አካባቢ መፍጠር፣ ከትምህርት የተገለሉ እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው የሕፃናትን በአካቶ ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተግባራዊ ማድረግ ነው።

የሕፃናትን የትምህርት ተሳትፎ ማሳደግ፡ ተማሪዎች ሃሳባቸውን፣ ፍላጎታቸውን እና ስሜታቸውን እንዲያካፍሉ በማገዝ፤ ሰሚ የማግኘት፣ ክብር እንዲሰማቸው ማድረግ እና በክፍል ውስጥ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ እንዲሳተፉ በማበረታታት የበለጠ ንቁ ተሳታፊ ማድረግ ነው፡፡

የሕፃናት የትምህርት ጥራትን ማሳደግ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት ማዘጋጀት እና ማቅረብ፣ ዘመናዊ የማስተማሪያ ቴክኖሎጂዎችን እና የትምህርት ግብአቶችን ማካተት፣ ቀጣይነት ያለው የመምህራን ሙያዊ ዕድገት ማረጋገጥ፣ የሕፃናት/የተማሪዎችን ፍላጎቶች መለየት እና ፍትሐዊ እና ሁሉን ዐቀፍ የትምህርት ዕድሎችን የሚያበረታቱ እርምጃዎችን መተግበር ነው።

ስለዚህም የሕፃናትን ትምህርት፣ ተሳትፎ እና ጥራት ማሳደግ ፍትሐዊነትን፣ ዘላቂ ልማትን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን፣ ጤናን እና ደኅንነትን፣ ዲሞክራሲያዊ እሴቶችን ለማሳደግ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ወሳኝ ጠቀሜታ አለው። ስለሆነም ሁሉም ሕፃናት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ፣ በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ሁሉ በንቃት እንዲሳተፉ ዛሬ ላይ የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል።

የሀገር ተረካቢ የሆኑት ሕፃናት ተወልደው በትምህረት ጎልብተው ሙሉ ሰው እስኪሆኑ ድረስ በተለያየ ደረጃ የሁሉም ማኅበረሰብ የተለያዩ ድጋፎች ለደረግ ይገባል። ልጅ የተማላ ጤናን ይዞ እንዲያድግ እናት የበለጠውን ኃላፊነት ብትወሰድም ቅሉ ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱ ግድ መሆኑን ወይዘሮ እመቤት አስረድተዋል። እኛም ሀገር ተረካቢው ትውልድ በአእምሮም በአካልም የጎለበተ ይሆን ዘንድ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ እየጠየቀነ የዛሬውን አበቃን። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You