በኢትዮጵያ ዋና ዋና በሆኑ ከተሞች በመተግበር ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራው በመፋጠን ላይ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማን ተሞክሮ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በከተማዋ ልማቱ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች በአንዳንዶቹ እየታየ ያለው ሥራ ከወዲሁ ለከተማዋ መልካም የሆነ ገጽታን ማላበስ ጀምሯል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በመተግበር ላይ የሚገኘው የራሱ የሆነ ዓላማና ግብ ይዞ ነው፡፡ ይኸውም ከተሞችን ውብና ፅዱ፣ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ተመራጭ፣ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻ፣ የምርምር እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራ ማዕከል ማድረግ ዋንኛው ነው፡፡
ከዚህ አኳያ የኮሪደር ልማቱ በአጠቃላይ በምጣኔ ሀብት እድገት በተለይም ከአዲስ አበባ ተጨባጭ ሁኔታ ለከተማዋና ለነዋሪዎችዋ ምን አይነት እድሎችን ይዞ ይመጣል ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች ጠይቀናል። አንደኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ ሲሆኑ፣ ሌላኛው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የአርክቴክቸር ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት መምህር የሆኑ አርክቴክ ብሥራት ክፍሌ ናቸው፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ፣ እንደሀገር ከሰላም፣ ከሰብአዊ እርዳታ ፍለጋ፣ ትላልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ካላቸው የፕሮጀክቶች ግንባታና መሰል አስፈላጊ ከሆኑ ተግባራት ጋር ተያይዞ የሚሻሙ የተለያዩ አጀንዳዎች ባሉበት በዚህ ወቅት የኮሪደር ልማት መከናወኑን በአድናቆት ገልጸዋል፡፡ ልማቱ ምጣኔ ሀብት እድገቱ ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ፋይዳ፤ የኮሪደር ልማት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ጥቅም ላይ ሲውል በሂደት የሚታይና በጥናትም የሚለይ ቢሆንም ልማቱ ይዞ የሚመጣውን እድል ግን ከወዲሁ መተንበይ ይቻላል ይላሉ፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ከነዋሪዎች ተጠቃሚነት አንጻር፤ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ከተሞች ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ የበለጠ እንዲነቃቁ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሮች ሕዝቡን ያሳተፈ የልማት አቅጣጫ በመቀየስ ለመኖሪያና ለሥራ ምቹ የሆነ አካባቢ መፍጠር ሲችሉ ደግሞ ለውጥና እድገት እንደሚመዘገብም አስረድተዋል፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ማብራሪያ፤ ከተሞች በባህሪያቸው የግብርና ሥራ የሚከናወኑባቸው አይደሉም፡፡ ከከተማ ነዋሪው የሚጠበቀው ነገር ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ በከተሞች መደበኛ ባልሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የእለት ኑሮአቸውን በመሸፈን የመንግሥትን ጫና በመቀነስ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ከአነስተኛ የንግድ ሥራ ተነስተው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱም ግብር በመክፈል የሚወጡት ኃላፊነት በሚሰሩባቸው ከተሞች ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግና በሀገር ምጣኔ ሀብት ላይም ከፍ ያለ ድርሻ ይወጣሉ፡፡ የከተማ ነዋሪ ኢኮኖሚውን ማሳደግ የሚችለው በዚህ መልኩ ነው፡፡
ሥራ መፍጠር የግሉ ዘርፍ ድርሻ ነው የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ሆኖም ግን አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት ሁሉንም ነገር ለማሟላት ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ያለፉ ተሞክሮዎችም የሚያሳዩት፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ሁሉም ነገር ማሟላት የሚጠበቀው ከመንግሥት ነው፡፡ መንግሥትም ድርሻው አድርጎ እየተወጣ ነው፡፡ መንግሥት የዜጎች ደህንነትና ሀገር እንዲጠበቅ፣ መሠረተልማትን ጨምሮ እንደ ጤና ትምህርት ያሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ምቹ በማድረግ በስትራቴጅና ፖሊሲ በመደገፍ፣ የተለያዩ እገዛዎችንም በማድረግ ዜጎች በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱም ቢሆን መደረግ የነበረበት ባለሀብቶች እንዲሰሩት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ የልማት ሥራዎች ወደፊት በዚህ መልኩ ቢታዩ የመንግሥትን ጫና ይቀንሳል፡፡ እንዲህ ያለው አቅጣጫ በአንዳንድ ሀገር የተለመደና ውጤትም ያመጡበት ጉዳይ ነው፡፡
ልማቱ እንደከተማ ምን እድል ይዞ ይመጣል ለተባለውም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ እንደመሆኗ ይህን የሚመጥን የከተማ ገጽታ ግንባታ ቀዳሚው መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡ የመኪና ፍሰቱ ምቹ እንዲሆን መደረጉ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቀድመው ከተገነቡት የሆቴል ኢንደስትሪዎችና ከሌሎች መሠረተልማቶች ጋር ተደምረው ያሉት አቅርቦቶች የከተማዋን ማደግ አመላካች ተደርጎ እንደሚወሰድ ያስረዳሉ፡፡
በዚህም ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎችን ትኩረት በመሳብ ገጽታን እንደሚገነባ፣ በሌሎች ሀገሮች እንደተለመደው በኢትዮጵያ ውስጥ መኖሪያ ቤት ገንብተው ለመኖርና በተለያየ የሥራ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያድርባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶችም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተገነቡ የሆቴል ቤቶች እየተደነቁ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ፀባይና መልክአምድር በውጭ ዜጎች ተፈላጊ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ከተማዋ ንጹና ውብ ስትሆን በጎዳናዋ ላይ በመንቀሳቀስ ለመናፈስና ለመዝናናት ምርጫቸው እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር ዜጎች ተፈላጊነቷ ሲጨምር የምታገኘው የውጭ ምንዛሪም በዚያው ልክ እንደሚጨምርና ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በማቃለል ለኢኮኖሚ እድገት ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የሚፈለገው ውጤት ላይ ለመድረስ ግን ራዕይ ያለው የከተማ አስተዳደር ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ‹‹አሁን ላይ ሰው ዱባይ መሄድን እንደትልቅ ነገር አድርጎ ያያል፡፡ ዱባይን ለማየት የሚፈልጉ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ አዲስ አበባ ከተማንም እንደ ዱባይ በተመሳሳይ ተፈላጊ ከተማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዱባይ አሁን የምትገኝበት ደረጃ ላይ የደረሰችው በ40 ዓመት ታሪክ ውስጥ ነው፡፡ ለስኬታማነቷም ከሚጠቀሱት አንዱ ጥሩ የከተማ አስተዳደር መገንባት መቻሏ ነው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የአርክቴክቸር ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት መምህር አርክቴክ ብሥራት ክፍሌ በበኩላቸው፤ በጥናትና በተለያየ መንገድ ወደፊት መታየት አለበት የሚለውን የዶክተር ቆስጠንጢኖስን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ የኮሪደር ልማቱ ለእግረኞች ቅድሚያ የሰጠና ለብስክሌት የሚሆን አመራጭንም ያካተተ መሆኑ ልማቱ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ የተጓዘ መሆኑን እንደሚያሳይና ይህንንም በመልካም ጎኑ እንዳዩት ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ ቀድሞ የተከናወኑ ፓርኮች ላይ ውበት በመጨመር መልካም ገጽታ እንዲኖረው በማድረግ ሊኖረው የሚችለውንም አስተዋጽኦ ከወዲሁ መገመት እንደሚቻል ገልጸዋል። ከዚህ አንጻርም የኮሪደር ልማቱ ብዙ በረከቶችን ይዞ ሊመጣ የሚችል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ከተማዋ ላይ እንዲህ ያሉ ለውጦች መኖራቸው ቀደም ሲል በተለያየ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ የንግድ ተቋማት አገልግሎታቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው፣ የተሻለ አገልግሎት ሲኖራቸው ደግሞ ገቢያቸውም ከፍ እንደሚል፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ገቢ ሲጨምር ከተማ አስተዳደሩ ከነጋዴው የሚሰበስበው ግብርም እንደሚጨምርና ይህም በከተማዋ ምጣኔያዊ ሀብት ላይ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡ እንደርሳቸው ገለፃ የተሻለ ገቢ ኖሮት ያደገ ከተማ ደግሞ የነዋሪውን ፍላጎት በቀላሉ በማሟላት ክፍተቶችንና ቅሬታዎችን ይቀንሳል፡፡
እንደ መምህር አርክቴክ ብሥራት ገለጻ፤ የመንገድ መሠረተልማቱ ትራንስፖርት ፍሰቱን ከማሳለጥ በተጨማሪ፤ በኮሪዶሩ ግራና ቀኝ በርካታ አገልግሎቶች እንዲኖሩ፣ አገልግሎቱንም ተከትሎ የተጠቃሚው ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ በገቢ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡
ከመንገዱ በስተጀርባ የሚኖረውን ነዋሪ የሚመጥን አገልግሎት በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ሌላው አማራጭ እንደሆነ የሚጠቅሱት መምህር አርክቴክ ብሥራት፣ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ምቹ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ አነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተው ይንቀሳቀሱ የነበሩና ለኮሪደር ልማቱ ተብሎ ከአካባቢያቸው የተነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተሻለ ሁኔታ ሥራቸውን የሚሰሩበት ሁኔታ በማመቻቸት ማመጣጠን የሚቻልበትን እድል በመፍጠር ሁሉም አይነት ነጋዴ ለከተማዋ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚቻልና ዘላቂ የሚባል መፍትሄ የሚያመጣም ተደርጎ እንደሚወሰድ ከነዋሪ አንፃር ያለውን ተጠቃሚነት አስረድተዋል፡፡
ከከተማዋ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንፃርም መምህር አርክቴክ ብሥራት፣ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ሙሉ ለሙሉ የእግረኛ መንገድ ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ አዲስ አበባ ከተማን ሙሉ ለሙሉ መቀየር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄን ያልኩበት ምክንያት እስከዛሬ ስንጠቀምባቸው የነበሩት የእግረኛ መንገዶች በቅጡ የተሰሩ ባለመሆናቸው እግረኛውን ምቾት የሚነሱ ናቸው፡፡ ቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃዎቹ በደረቅ ቆሻሻ የተደፈኑ፣ ክዳን ባለመኖሩ ለአደጋ የሚያጋልጡ፣ ብዙ እንከን ያለባቸው ናቸው” ብለዋል፡፡
አሁን ላይ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት የእግረኛ መንገድ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ምቾቱ ለነዋሪው ብቻ ሳይሆን ለጉብኝት ወደመዲናችን የሚመጡ ሁሉ የሚደሰቱበት ይሆናል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያን ንጹህ አየር የሚናፍቁ የውጭ ሀገር ዜጎች በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳና ላይ እንደልባቸው ይንሸራሸራሉ፡፡ የውጭ ዜጎችን መሳብ ደግሞ ጥቅሙ ዘርፈብዙ ነው፡፡ አንዱ የገጽታ ግንባታ ሲሆን፣ ሌላው የገቢ ምንጭ በመሆኑ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በውስጥ የገጠማት የሰላም ችግር በዘላቂነት ተፈትቶ ሙሉ ለሙሉ ወደሰላሟ ስትመለስ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች የጎብኝዎች መናኻሪያ እንደምትሆን እምነታቸው እንደሆነ የሚገለጹት መምህር አርክቴክ ብሥራት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የቱሪዝም መዳራሻ ሆና የምትታወቀው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ሀብቷ፣ በመልካምድሯ፣ በታሪኳ፣ በባህሏና ሌሎችም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለቱሪዝም ምቹ የሆነ የመንገድ መሠረተልማት አላት በሚለው እንድትታወቅ ዕድሎች እየተፈጠሩ ነው›› በማለት የመንገድ መሠረተልማቱን የወደፊት እድሎች ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተመረጡ ዋና ዋና ከተማ በመከናወን ላይ ያለው የኮሪደር ልማት በባለሙያዎቹ እንዲህ ተስፋን አሳድሯል፡፡ የገቢ ምንጭ ሆነው በከተሞቹና በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ሚና እንዲኖራቸው ልማቱ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ በክትትልና ቁጥጥር የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የቤት ሥራ መኖሩን በገለጻቸው አብራርተዋል፡፡ ነዋሪው የተሰራውን ልማት በባለቤትነት እንዲጠብቀው የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ከከተማ አስተዳደሮቹ የሚጠበቅ ኃላፊነት እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም