እንደ ልማቱ በሙስና ላይ ተመሳሳይ አቋም ይዞ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል

ሰሞኑን አንድ ሰነድ ሳገላብጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተቋቋመበትን ዓላማ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን ለመመልከት ሞክሬ ነበር፡፡ የኮሚሽኑ ርዕይ በ2025 ዓ.ም ሙስና ለከተማ አስተዳደሩ ልማት እና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ የሚለው ነው ፤ አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሥነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ትምህርትን በማስፋፋት፣ የአሠራር ሥርዓትን በማጥናትና እንዲሻሻሉ በማድረግ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመከላከል በመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ደግሞ የእኔ ተልዕኮ ነው ሲል ያስቀምጣል፡፡

የኮሚሽኑ ዓላማ ፣የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት የሞራል እሴቶችን በመገንባት የነቃ እና ሙስናን ሊሸከም የማይችል ህብረተሰብ መፍጠር ነው፡፡ በተጨማሪም የሙስና ወንጀል እና ብልሹ አሠራርን መከላከል፣ ነዋሪው የፀረ-ሙስና ትግል ባለቤት እንዲሆን ማድረግ በፀረ ሙስና ትግል ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ሥርዓት ማስፈን እና በሕግ የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባር ለመፈጸም የሚያስችል ተቋማዊ አቅም መገንባት ነው፡፡

ይህን በአዕምሮዬ እያውጠነጠንኩ አሁናዊ የከተማዋን የመልካም አስተዳደር ገጽታ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን በዓይነ ህሊናዬ ለመቃኘት ሞክርኩኝ፡፡ በእኔ እይታ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› የሆኑ ነገሮችን እመለከታለሁ፡፡ ከተማ በትልቁ ለመለወጥ የምታደርገው የለውጥ ጉዞ እያደነቅሁኝ፤ ወዲህ ደግሞ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ደግሞ ጉራማይሌ ሁኔታዎችን አስተውላለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ሙስና ግልፅ በሆነ ሁኔታ አፍጦ ይታያል፡፡ ኮሚሽኑም መሬት አስተዳደር፣ ወሳኝ ኩነት፣ ያለ ፈቃድ የሚከወን ንግድና መንግሥትን የማጭበርበር ሁኔታዎች በከተማዋ ፈታኝ መሆናቸውን በራሱ አንደበት በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል፤ አገልግሎትን የመሸጥ ዝንባሌዎችም እንደሚስተዋሉ ደርሰንበታል ብሏል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም በተመሳሳይ አስተጋብተውታል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት ግዥ፣ ሐሰተኛ መታወቂያ፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ በቀበሌ ቤቶች እና በመሳሰሉት ላይ ሰፋ ያለ የሙስና ዝንባሌና ድርጊቶች አሉ፡፡ ይህ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ውስጥ ያለው ሁኔታ ደግሞ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይም የሚኖረው ትርጉም ቀላል የሚሆን አይደለም። ሙስና ከትንሹ ጀምሮ ሀገሪቱ በምታከናውናቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ መሆኑን ከዚህ በፊት በሜቴክ እና ህዳሴ ግድብ፣ የስኳር፣ የመንገድ፣ የመስኖ ግድቦች፣ ስታዲየሞች እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የኋሊት እየጋለብሁ ለማነፃፀር ሞከርኩ፡፡

በከተማ ደረጃ ሙስና ለመዋጋት ሲባል በርካታ ጉዳዮችን ላይ ሲሠራ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሀብት ማስመዝገብ አለባቸው በሚል በሰፊው የተነገረለት አጀንዳ ነበር፡፡ ይህ እንደ ከተማም ሆነ እንደ ሀገር በውሉ የደረሰበት ነገር ሳይታወቅ ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡ በተደጋጋሚ ከማህበረሰቡ እየሰማናቸው ካሉ ነገሮች አንዱ አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም የግድ እጅ መንሻ ወይንም ጉቦ መስጠት ግዴታ ወደሆነበት ደረጃ ተደርሷል፡፡

ይህ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ እስከ ላይኛው መዋቅር የተዘረጋ ነው፡፡ ሙስና ሰዎችን የምንቀርፅበት አካሄድ እና የሚገኘው ውጤት ድምር አለመጣጣም ነው፡፡ ሕዝቡም በጉዳዩ ላይ በሰፊው እንዲወያይ ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር ሙሰኞችን የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል፡፡ ለመሆኑ በዚህ ደረጃ ለሙስና የተጋለጥነው ለምንድን ነው? የሚለውን መመልከት ግድ ይላል፡፡

አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው ሙስና የፖለቲካው፤ ማህበራዊ ጉዳዮች እና የምጣኔ ሀብት ፖለሲ ያመጣው ችግር ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱንም ያለማክበር ሙስና እንዲንሰራፋ ምቹ ፈጥሯል፡፡ በመንግሥት አካል ውስጥ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈፃሚው በሙሉ የተናበበ እና አንዱ ሌላውን የመቆጣጠር አቅሙ ደካማ በመሆኑ ኃላፊዎች ወደ ሙስና ቅሌት እንዲመሩ ምቹ ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ ጠንካራ ያልሆነ የፌዴራል ሥርዓት ለሙስና በር ይከፍታል፡፡ ምክንያቱም ሥልጣንን ከማዕከል ወደታችኛው እርከን ይወርዳል፡፡ በዚህም ያልተማከ አስተዳደር ይፈጠራል፡፡ በፌዴራል ሥርዓት ሥልጣን በክልል፤ ዞን፣ ወረዳ፣ ከተማ አስተዳደር እና በመሳሰሉት እርከኖች ይከፋፈላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሕዝብን ሥልጣን ለራሳቸው ይጠቀማሉ፡፡ አዲስ አበባም በዚህ ተዋረድ ውስጥ ናት፡፡

እኔም እነዚህን ከላይ የተገለፁትን ሃሳቦች ከሞላ ጎደል የምቀበለው ቢሆንም ምክንያቶቹ ከዚህም አለፍ ያሉ እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡ በዚህች ከተማ ውስጥ የእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ቀጥታ ከመንግሥት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎችን መመለስ በአብዛኛው ከመንግሥት እና ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ይህን በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ ለራሳቸው ኪስ ማድለቢያ የሚያውሉ ኃላፊዎችና እነርሱ የዘረጉት አደገኛ ሰንሰለት አንዱ ችግር ነው፡፡

ሌላኛው ሙስና ላይ የሚከፈተው ዘመቻ አንድ ወቅት ሥራ ተደርጎ መወሰዱ ነው፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደር ሙስና በተመለከተ ሕግ እስከወጣ ድረስ ያለማቋረጥ ክትትል ሊደረግ ይገባል፡፡ መንግሥት በሙሰኞች ላይ እየወሰደ የነበረው ርምጃ እጅግ መቀዛቀዙ ሙስናው መሠረት ያለው ቤት እንዲሠራ አድርጎታል፡፡ ወጥነት የጎደለው ርምጃ በራሱ ለሙስና መንገድ ይከፍታል፡፡ የቁጥጥር ዘዴዎችን ከላይ እስከ ታች በጠንካራ ሁኔታ አለመዘርጋቱ ለሙሰኞች ምቹ ሁኔታ እያበጀ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡

ወደ ኃላፊነት የሚመጡ አካላትን በሁሉም የአመራር መመዘኛ መስፈርቶች በሚገባ ያለመፈተሽም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሙስና ውስጥ የሚገቡት የአመራር ጥበብና እውቀት ስለሚያንሳቸው ብቻ ሳይሆን ሙሰኞች ላይ የሚወሰደው ቀላል ርምጃ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ የሞሰሰ ኃላፊ ከሙስና በፊት እና ከዚያን በኋላ በሚል የሕይወት ምዕራፉን ይከፋፍላል፡፡ ሙስና ሰርቶ የሚገኘውን ስጋዊ ጥቅም በቀዳሚ ስሌት ውስጥ ያስገባል፡፡ በሌላ አነጋገር በቢሊዮን ዘርፈው ከሰወሩት በኋላ በሕግ ከለላ ስር ከጥቂት ዓመታት ቆይተው እንደሚወጡ ስለሚሆኑ ወደ ሙስና መሰስ ብለው ይገቡበታል፡፡

‹ፀረ ሙስና ትግሉ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው የሥነ- ምግባር መሸርሸሩ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በርካቶች ህሊናቸውን ከመፍራት ይልቅ የንዋይ አምላኪ እየሆኑ ነው፡ ፡ በቤተሰብ መካከል በራሱ አለመተማን እየታየ ነው፡፡ በብዛት የሞራል ዝቅጠት እያስተዋልን ነው፡፡ አንዱ ሥራችን ከሥነ ምግባር ዝቅጠት ውስጥ መውጣት አለበት›› ሲልም የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር በዚህ ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ላይ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንግዳ በነበሩበት ወቅት የተናገሩት እውነታ ነው፡፡

እንግዲህ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሚሽኑ በዚህ ላይ ከፍተኛ መስዕዋት ሊከፍል ይገባል፡፡ ሙስና ከነውሮች ሁሉ ነውር ነው የሚል አቋም መያዝ አለበት፡፡ በተለይም ደግሞ በ2025 ዓ.ም ከሙስና የፀዳች ተምሳሌት የሆነች ከተማን እፈጥራለሁ የሚል ርዕይ ሰንቆ ለሚንቀሳቀስ አካል መሰል ፀያፍ ተግባራት ማስቆም ግድ ይለዋል፡፡ የከተማዋ የኦዲት ምርመራ ውጤትም መሠረት አድርጎ ጠንክር ያሉ ሥራዎችን ማከናወን አለበት፡፡

ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ፣ የሕግ እና የፍትህ አካላትም ጠንካራ አደረጃጀት ሊኖራቸው ይገባል። በተለይም ሙስና እየረቀቀ ስለሚሄድ ቁጥጥሩን ከላይ እስከታች ማጠከርና በቴክኖሎጂ መታገዝ አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ሙስና ለመልካም አስተዳደር እጦት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል፡፡ በአንድም በሌላም ስልቶቹ ይለያዩ እንጂ በሙስና ላይ ከፍተኛ ዘመቻ መክፈት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡

ሙስናን ለመዋጋት የዴሞክራሲ ሥርዓትን ማጎልበት፣ ሕዝብን ማወያየት፣ በሙስና ላይ ያለውን ትግልም ማጠናከር እንዲሁም ጠንካራ የመገናኛ ብዙሃን መፍጠርና መረጃዎችን ፈልፍሎ ተደራሽ ማድረግ እና ሙስና ማጋለጥ እንደ ከተማ አስተዳደር ዋነኛ ሥራ መሆን አለበት፡፡ ሥነ ምግባር ላይ ተከታታይ ግንዛቤ መፍጠርና ቁጥጥር ሥርዓቱን ከታች ወደ ላይ እንዲሁም ከላይም ወደ ታች ማጠናከር ይገባል፡፡

ተቋማዊ በሆነ መልክ በተከታታይ ሙስና ላይ መዝመት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለሀገር መንግሥትም ሆነ ለሀገር ብሎም ለከተማ ግንባታ አደጋ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ ከተማ አስተዳደሩ በ2025 ዓ.ም ሙስና ለከተማ አስተዳደሩ ልማት እና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ የሚለው ከምኞት የዘለለ ርባና ቢስ ይሆናል፡ ፡ በአጠቃላይ እንደ ከተማ አስተዳደር በልማቱ ብቻ ሳይሆን በሙስና ላይም ጠንካራ ዘመቻ ያስፈልጋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You