ቤንሻንጉል ጉሙዝ ከታዳጊ ክልሎች አንዱ ነው። የማእድናት ባለፀጋ ከሆኑትም ቀዳሚው ሲሆን፤ ፀጋዎቹን ወደ ሀብት ካልቀየሩትም እንደዚሁ ቀዳሚ ሆኖ ይገኛል።
በእስከ ዛሬው የአገሪቱ ተጠቃሚነትና የመልማት ታሪክ ተግፍቶ መቆየቱ፤ በተለይም ከ1983 ጀምሮ ከባለቤትነትና ተሳታፊነት፤ እንዲሁም ውሳኔ ሰጪነት መድረክ በመገፋት በ″አጋር ድርጅት″ነት መቆየቱ በክልሉና ህዝቡ ላይ የተፈፀመ ፖለቲካዊ ግፍ መሆኑ በሚመለከታቸው ሁሉ የተነገረለት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ከአየር ንብረትና ውሀ ሀብት ጀምሮ ያልታደለው ነገር የለም።
በሰው ሀብት በኩል የወጣት ምድር ሲሆን፣ ከልማት አኳያም መልማት የማይችል ቦታ የሌለው ከመሆኑ ባሻገር ያልለማውና እስከ ዛሬ ያለ ጥቅም የኖረው፤ እንዲሁም ኑ ብሉኝ፣ ኑ ብሉኝ • • • የሚለው ስፍራ ይበልጣል። ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ፣ ክልሉ ወደ ልማት ሀዲድ ውስጥ በመግባት እየገሰገሰ ስለ መሆኑ ይነገርለታል። ክልሉ የማእድንና ግብርናው ዘርፎች በቆሰቆሱት ኢኮኖሚ ሞቅ ደመቅ እያለ መሆኑ በግልፅ ይታያል።
በተመቻቸ መልክአምድሩ ሳቢያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በእቅፉ ያስገባ የወደፊት የአገሪቱ የኢኮኖሚ እምብርት መሆኑም ከወዲሁ እየተስተጋባለት ያለ የአገሪቱ አካል ነው። ክልሉ የተከሰተውን የሠላም እጦት፣ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ሁሉ ወደ አንፃራዊ ሠላም በመመለስ ለውጥና ብልፅግናን የማምጣት ጉዞውን እንደ ተያያዘውም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሃሰን ይናገራሉ። አብረን እንዝለቅ።
አዲስ ዘመን:- በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች እየተመዘኑ ያሉት ሀገሪቱ ውስጥ ከተከሰተው ለውጥ አኳያ ነውና፤ ከለውጡ በፊትና በኋላ ያለውን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ባጭሩ ቢገልፁልን።
አቶ አሻድሊ:- ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በክልላችን የተመዘገበው ትርጉም ያለው ለውጥ ነው፡፡ ከኢህአዴግ በፊት በነበሩ የአስተዳደር ሥርዓቶች የተረሱ አካባቢዎች የነበሩ ሲሆን፣ አንዱም ይህ የእኛ ክልል ነው። ከመንግሥት የራቀ አካባቢና ሕዝብ ነበር። ሩቅ ነው በሚል ብቻ፣ ኋላ ቀር ነው ከሚል የተሳሳተ እሳቤ በመነሳት ከሀገሪቱ ጥቅም ተገልሎ የኖረ ክልል ነው። ሕዝቡም በባህላዊ አስተሳሰብና አሠራር ውስጥ እንዲቆይ የተደረገ ሕዝብ ነው።
ይህንን እቀይራለሁ ብሎ በ1983 ዓ•ም ወደ ሥልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግሥት ተግባሩ ሁሉ የይስሙላ ነበር። ከእነ ጭራሹ እኛን ከሀገር ባለቤትነት ወደ ዳር በመግፋት “አጋር ድርጅት” በሚል ሰየመን። እስከለውጡም ድረስ የነበርነው በአጋር ድርጅትነት ነው። የነበረው በሕዝብ ላይ የተቀለደበት ሁኔታ ነበር። ሕዝቡ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ላይ እንዲወስን አልተደረገም፤ አልተፈቀደለትም ነበር።
ሕዝቡ ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የተጋለጠበት ሁኔታ ነበር። ፌዴራል ላይ ሆነው ሕዝቡንና አካባቢውን በእጅ አዙር የሚያስተዳድሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ መሬት እንኳን ሳይቀር ወደ ላይ ተስቦ በተወሱ ባለሥልጣናት አማካኝነት ለባለሀብት ተብዬዎች የሚሸነሸንበት ሁኔታ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢንቨስተሮች የተባሉ ሰዎች የወሰዱትም ለዚያ ነበር፡፡ መሬት ተነጥቆ ካርታቸው እንዲመክን የተደረገውና ለአንዳንዶቹም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው የነበረው ለዚያ ነበር። ክልሉንና ሕዝቡን በአጋር ስም አግልሎ ሲካሄድ የነበረው ልማት ሳይሆን ዘረፋ ነበር።
ክልሉ ራሱን ማስተዳደር አይችልም በሚል ድምዳሜ በራሱ ጉዳይ ነጻ ሆኖ አይሠራም ነበር፡፡ በትእዛዝ ለእነ እከሌ፣ ለእነ እከሊት መሬት ስጥ እየተባለ መሬት ሲሰጥና ሲሸነሽን የነበረው በሞግዚትነት ነበር። ሲኖር የነበረው አቅም ለሌለው ሁሉ መሬት እየተሰጠው፤ ገንዘብ የሌለው ሁሉ ገንዘብ ከባንክ እየወሰደ ምንም ሳይሰራበትና ሳያለማበት ነው። ይህ በበኩሉ በአካባቢው እድገት ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል። ክልሉን ወደ ኋላ አስቀርቷል። እንደ ሌሎች ክልልች እንዳይለማ አድርጎታል። ከለውጡ በኋላ ግን ወደ ላይ ተስቦ የተወሰደው መሬትና የመሬት ጉዳይ ወደ ክልሉ እንዲመለስ ተደርጎ ለባለሀብቶች በመሰጠቱ ምክንያት በርካታ ባለሀብቶች ወደ ሥራ ገብተዋል። ምርታማም በመሆን ላይ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ከለውጡ ወዲህ እንደ አንድ የሀገሪቱ አካል በመሆን እየተሳተፍን እንገኛለን። የቤኒሻንጉል ሕዝብ እውነትም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አስተሳሰብና ማንነትን ያዳበረው ገና አሁን ነው። እራሱን በራሱ በትክክል ማስተዳደር የጀመረው ከለውጥ በኋላ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ያለው አሁን ነው፡፡ የራሱን ሀብት መጠቀምና መልማት የጀመረው ከለውጡ በኋላ ነው። በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍረው የነበሩትን መብቶች በትክክል መጠቀም የቻልነው ከለውጡ በኋላ ነው። ክልላችን በእነዚሁ ዓመታት ውስጥም ከራሱ አልፎ እንደ ሀገር ለፌዴራል መንግሥት ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በፊት በሀገር ደረጃ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ አንገኝም፤ አንሳተፍም ነበር። የኖርነው ተገልለን ነው። በሀገር ደረጃ ይደረጉ የነበሩ ውሳኔዎች ይደርሱን የነበረው በተዘዋዋሪ ነበር። ክልሉ ሲመራ የነበረው አማካሪ ምናምን እየተባለ ነበር። ከለውጡ በኋላ ግን ይህ ሁሉ ቀርቶ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ በተወካዮቹ አማካኝነት፣ እንደ ፓርቲም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋል፤ ውሳኔም ይሰጣል። ለውጡ ይህንን ያህል ተጨባጭ ለውጥ ይዞ የመጣው።
እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ሕዝብ፣ ለውጡ ትልቅ ስፍራ፣ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ የክልሉ ሕዝብ እውነትም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አመለካከት እንዲኖረው ያደረገ፤ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ወሳኝ መሆኑን ያረጋገጠበት ለውጥ በመሆኑ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
አዲስ ዘመን:- ከኢኮኖሚያዊ እድገት አኳያ ያለውንስ እንዴት ይገልፁታል?
አቶ አሻድሊ:- የለውጡ ሃይል ገና ወደ መንግሥታዊ ሃላፊነት ሲመጣ የኢኮኖሚ ፍትሃዊነት እንዲኖር ይፈልግ ነበር። በዚሁ መሠረትም እኩል የማደግ እድል ለሁሉም ክልሎች ሰጥቷል። በዚህ እድል ተጠቅመን እየሠራንና እያለማን፤ ከተረጂነት ወደ አምራችነትም እየተቀየርን እንገኛለን።
እንደሚታወቀው በክልላችን ሊታረስ የሚችል፣ ሊያመርት የሚችል፤ በአጠቃላይ ለእርሻ ምቹ የሆነ ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አለ። ይህ ማለት በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሌለ መሬትና አቅም ነው። እዚህ ግን በኢትዮጵያ በአንድ ክልል ያለ ሀብት ነው፤ ትልቅ አቅም አለ ማለት ነው። ይህ ወደ ሥራ ቢገባበትና ቢለማ ከክልል፣ ከሀገርም አልፎ ለውጭ ገበያም በመትረፍ የሀገርን ኢኮኖሚ ይጠቅማል ማለት ነው።
ከለውጡ በኋላ ወደዚህ፣ ወደ ማልማቱ ሥራ እየተገባ ነው። አሁን ባለሀብቶች በዘርፉ እየተሰማሩ ይገኛሉ። ለመሥራት የሚያስችላቸውንም ገንዘብ ከባንክ እየወሰዱ ይገኛሉ። እስካሁንም ከ900 ሄክታር መሬት በላይ ወስደዋል። ወደ ሥራም እየገቡ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰአት ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እየለማ ይገኛል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢኒሼቲቭ መሠረት ስንዴ ዘርተንባቸው የማናውቃቸውን ቦታዎች በመለየት በተለያዩ አካባቢዎች በማምረት ላይ እንገኛለን። ለአርሶ አደሩ ድሮ ውስን ተደርጎ ይሰጠው የነበረው ግብዓት ከለውጡ በኋላ ተገቢውን፣ የሚፈልገውን ግብዓት እያገኘ ነው።
ከለውጡ በፊት ይህንን የሚያክል አቅም ያለው ክልል ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ አምርቶ አያውቅም ነበር። ከለውጡ በኋላ ግን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በአርሶ አደር ብቻ ለምቷል። ይህ ቀላል ግምት የሚሰጠው ለውጥ አይደለም። በዚህ ከቀጠለ ክልሉ የወደፊቱ የሀገሪቱ የልማት ኮሪደር የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።
አዲስ ዘመን:- በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አሉ? ካሉ ቢገልፁልን።
አቶ አሻድሊ:- በዚህ ዘርፍ አቅሙ እያለ ያልተሠራበት ዘርፍ ነው። ባምቡ ፋብሪካ፣ እምንበረድ እና ሌሎች ከእምነበረድ ጋር የተያያዙ ዘርፎች ወደ ሥራ የተገባባቸውና እየተገባባቸው ያሉ ናቸው። የዱቄትና ሌሎች ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ ገብተው በምርት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ብዙ መሥራት እየተቻለ በሰላም እጦት ምክንያት እንደተፈለገው መሄድ አልተቻለም። በተለያዩ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ከ900 በላይ ባለሀብቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነበሩ። ያልገቡ አሉ። መግባት ሳይችሉ የቀሩት በዚሁ በሰላም ማጣት ችግር ሲሆን፤ አሁን በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ግን ወደ ሥራ በመግባት ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን:- ክልሉ በማዕድን ሀብትም ይታወቃልና በዛ በኩል ያለውን ገፅታ ቢገልጹልን ?
አቶ አሻድሊ:- ገና በጥናት ያልተደረሰባቸውን ሳይጨምር፣ ክልላችን ከሁሉም በበለጠ በማዕድን ሀብት የበለፀገ ክልል ነው። ይህ ሀብት ከለውጡ በፊት እንዲነካ ሁሉ አይፈልግም ነበር። የፖሊሲ አቅጣጫም ሆነ የሕግ ማእቀፍ ሁሉ አልነበረውም። ዛሬ ያ ሁሉ ቀርቶ የማእድን ሀብቱን መጠቀም ጀምረናል። ለፌዴራልም ገቢ በማስገባት ላይ እንገኛለን።
ለምሳሌ በ2013 ዓ•ም 30 ኩንታል (3000 ኪሎ ግራም)፤ በ2014 ዓ•ም ደግሞ ሁለት ሺህ 300 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል። ይህ በጥቁር ገበያ በኩል እየሄደ ያለውን ሳይጨምርና በማህበራት በኩል በተደራጁ ወጣቶች አማካይነት ከተሠራው የተላከ ብቻ ነው።
በአሁኑ ሰአት ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃም ተጠቃሚ እየሆኑ፤ አካባቢያቸውን የማልማት ተግባራት ላይም እየተሳተፉ ይገኛሉ። አሠራራቸውም ከኋላ ቀር አሠራር እንዲላቀቅ እየተደረገ
ሲሆን፣ ወደ ዘመናዊ አሠራርና ቴክኖሎጂ አጠቀቃቀም በመሸጋገር ላይ ናቸው።
ወጣቱ ከአህያ ወደ ሞተር፤ ከሞተር ወደ መኪና እየተሸጋገረ ይገኛል። በሶስት ዓመታት ውስጥ ብቻ፣ ከለውጡ በኋላ ከ300 በላይ መኪኖችን የገዙ ወጣቶች ያሉባቸው አካባቢዎች አሉ። በኩምሩህ አካባቢ ብቻ ከ80 በላይ መኪኖች ተገዝተው ሥራ ላይ ናቸው። ሸርቆሌ አካባቢ ከአራትና አምስት ዓመት በፊት አንድ ብስክሌት እንኳን ያልነበረበት ሁኔታ ነበር። ዛሬ ሞተርና መኪና እንደ ልብ ነው። ካማሼ አካባቢ የድንጋይ ከሰል በስፋት እየተመረተ፣ ሀገር ዶላር እያዳነች፤ የአካባቢው ህብረተሰብም በከፍተኛ ደረጃ በመለወጥ ላይ ነው።
በአሁኑ ሰአት በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ማየት ተችሏል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከሁሉም በላይ በማእድኑ ዘርፍ እየታየ ያለው ሰፊ እንቅስቃሴና እየተገኘ ያለው ውጤት ነው።
ዛሬ፣ እንኳን መኪና ሊገዙ መኪና እንኳን አይተው የማያውቁ አካባቢዎች በዚህ ደረጃና ፍጥነት ባለ መኪና መሆናቸው ሲታይ በክልሉ ከፍተኛ ለውጥ ስለ መኖሩ ተገቢ ማሳያ ነው። አሁንም ከማህበራቱ በዘለለም፣ ወጣቶቻችን ተደራጅተው ከባለሀብቱ ጋር በመሆን በ70/30 (ማሽኖችና የመሳሰሉት ከባለ ሀበቱ) አሠራር እየሠሩ ይገኛሉ። ይህም የማእድን ሀብት አላቂ ከመሆኑ አኳያ ባለ ሀብቱ ብቻ አምርቶ እንዲሄድ ስለማያደርገውና የአካባቢው ማህበረሰብም ተጠቃሚ ስለሚሆን የተሻለ ተጠቃሚነትና ኢኮኖሚያዊ እድገት እየመጣ መሆኑ ግልፅ ነው።
በክልሉ፣ በተለይም በከተሞች ዛሬ ቁጠባ ባህል እየሆነ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ባንክ ማስቀመጥ የተለመደ ብቻ ሳይሆን ተገቢነቱን አምኖ የተቀበለ ማህበረሰብ በስፋት ተፈጥሯል። በአካባቢ ልማት እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች ብዙ ናቸው። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ከፌዴራል ጀምሮ ባለው መስተዳድር የአካባቢው የማእድን ሀብት ማህበረሰቡን ሊቀይር የሚችል አቅም ያለው መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ በመሆኑ ነው።
በአሁኑ ሰአት እነዚህ ወጣቶች ከተሞች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ጀምረዋል። ካማሽ ዞን ላይ የድንጋይ ከሰል ማምረት ተጀምሯል። የድንጋይ ከሰል ሃይል (ኢነርጂ) ነው፤ አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን አዋጭም ነው። እነዚህንና እነዚህን በመሳሰሉ ተግባራት ከለውጡ በኋላ የህብረተሰቡ ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ እየተለወጠ ይገኛል። የሰላም እጦት ችግር ባያጋጥመንና ትኩረታችንን ባይወስድብን ኖሮ ከዚህ በተሻለ በመሥራት የትና የት በደረስንም ነበር።
እየተመረተ ባለው እምነበረድ ምክንያት ሰፊና እያደገ የሚሄድ የሥራ እድል ተፈጥሯል። ህብረተሰቡ ሀብት እያፈራ ነው። በሂደት ወደ ኢንዱስትሪውና ግብርናው ዘርፍ እንዲገቡ ነው አቅጣጫ አስቀምጠን እየሠራን ያለነው። በየዞኑና ወረዳዎች ያሉ አካባቢዎች እየለሙ ነው። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በተለይ የክልሉ መንግሥት ከአጋር ድርጅትነት ወደ ወሳኝና ውሳኔ ሰጪ ድርጅትነት መቀየሩን ተከትሎ ነው። ይህ የህብረተሰቡን ሞራል እጅጉን ገንብቶታል። ተጎድቶ ነበረውን ስሜቱን መልሶ አድኖታል። የሥራ ሞራሉ፤ ሰርቶ የመለወጥና የማደግ ፍላጎቱን ሁሉ ከፍ አግርጎታል። ለውጡ ቀላል አልነበረም፤ አይደለምም።
ሌላው የክልሉ የማእድን ሀብት እጣን ነው። በፊት አንድ ወይም ሁለት ባለ ሀብቶች ብቻ ነበሩ እንደፈለጉ የሚያደርጉት። አሁን ክልሉ በእውነተኛው ራሱን ማስተዳደር ከጀመረ፣ ከለውጡ ወዲህ ግን በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፤ አሁን ማህበረሰቡ ተደራጅቶ እየሠራ ይገኛል። ወጣቶች አንድ ኩንታል እጣን 40 ሺህ ብር በመሸጥና ተጠቃሚ መሆን ላይ ናቸው። ይህ ሁሉ የመጣው ከለውጡና የለውጡ ሃይል ሁሉም ክልሎች እኩል የመልማት መብት አላቸው ብሎ ከማመኑ፤ ከሚያፈልቃቸው አዋጭና ጠቃሚ ሃሳቦች፤ እንዲሁም የማይናወጥ ጠንካራ የመበልፀግ አቋም ከመያዙ፤ የክልሉ አመራርም በማእድኑ ዘርፍ በሚገባ ከተሠራ በክልሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ ከማመኑና በዛው ልክ በመሥራት ላይ በመሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ፣ ያለ ምንም ሞግዚት ራሳችን፣ የፌዴራሉን እቅድ በተንተራሰ መልኩ የራሳችንን አካባቢ በራሳችን እቅድና ፕሮግራም ማልማት ከመቻላችን የመጣ ከፍተኛ ለውጥና እድገት ነው።
አዲስ ዘመን:- በማህበራዊው ዘርፍስ ያለው ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አሻድሊ:- ከትምህርቱ ዘርፍ ለመጀመር ያህል፣ በክልሉ ከለውጡ በኋላ ትምህርት ተስፏፍቷል። ተደራሽነቱም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ጥራትን ለማምጣትም እየተሠራ ነው።
በአሁኑ ሰአት በሁሉም አካባቢዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ማእከላዊ በሆኑ ቦታዎች ላይ እየተገነቡ ነው። በ“ትምህርት ለትውልድ” ሀገራዊ እንቅስቃሴ መሠረትም እየተሠራ ይገኛል። በትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራሞች ተጀምረዋል፤ ለውጥም እየታየ ይገኛል። አዳሪ ትምህርት ቤትም በመገንባት ላይ ነው።
ወደ ጤናው ሴክተርም ስንመጣ በተመሳሳይ ሁኔታ ለውጦች አሉ። ከለውጡ በፊት መከላከል ላይ ብቻ ያተኩር የነበረው የህክምና ፖሊሲያችን በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ መሻሻልን አምጥቶ መከላከልና ማከም ላይ እየሠራ ይገኛል።
በክልላችን አምስት የመጀመሪያ ደረጃ (ፕራይመሪ) ሆስፒታሎች እየተገነቡ ሲሆን፣ አራቱ ተጠናቅቀዋል። በርካታ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ተሠርተዋል፤ ነባሮቹም እየተጠናከሩ ነው። አጎበር በማሰራጨት ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ህክምናን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የጤና መድህን ላይ በስፋት እየተሠራና ህብረተሰቡን መቶ በመቶ የጤና መድህን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ለውጥም እየመጣ፣ ውጤትም እየተመዘገበ ይገኛል።
ከቱሪዝም አኳያም የውሃ ሀብት በብዛት ያለን በመሆኑ ወንዞች ላይ እየሠራን ነው። ተራሮች አሉ፤ በእነርሱ ላይም እየሠራንባቸ ነው። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያም እየተሠሩ ያሉ በርካታ ሥራዎች አሉ። ወደ ፊት ትልቅ ከተማ ይገነባል ተብሎም ይጠበቃል። ቤተመንግሥቶች አሉ፣ እየተጠበቁና ለቱሪዝም ዘርፉ አገልግሎት እንዲውሉ እየተደረጉ ናቸው።
አዲስ ዘመን:- ከመሠረተ-ልማት አኳያ የተሠሩ ሥራዎች ካሉ ቢገልጹልን፡፡
አቶ አሻድሊ:- በከተማ ውስጥ በአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት የአስፓልት መንገድ እየተሠራ ይገኛል። ከለውጡ በፊት ያለ ጥናት ወደ ግንባታ የተገባበት ስታዲዮም እንደ ገና እንዲጠና ተደርጎ በካፍ ስታንዳርድ መሠረት መልሶ የመገንባቱና ማጠናቀቁ ሥራ በመጀመር ላይ ይገኛል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጽሐፍ (መደመር) በተገኘ የ300 ሚሊዮን ብር ገቢ በከተማችን ውስጥ ዘመናዊ ሙዚየም በመገንባት ላይ ነው። ግሽበትና ካሳ ፈተና ቢሆንብንም እስካሁን የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ያለ ማቋረጥ እየሠራን እንገኛለን። የሰላም መደፍረስ ቢረብሸንም ልማትን አላቆምንም። በርካታ በፌዴራል የተጀመሩና ተቋርጠው የነበሩ የመንገድ ሥራዎች እንዲጀምሩ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን ወዘተ በተመለከተ አስቀድሜ እንደገለፅኩት በስፋት እየተሠሩ ነው።
አዲስ ዘመን:- በአረንጓዴ ዐሻራ ዙሪያ ምን ያህል ተሠርቷል?
አቶ አሻድሊ:- በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ በስፋት እየሠራን እንገኛለን። አረንጓዴ ኢኮኖሚ (ግሪን ኢኮኖሚ) እየገነባን ነው። በዓመት በአማካይ 50 ሚሊዮን ችግኞችን እንተክላለን። የገቢ ምንጭ የሆኑትን፣ እንደነ ማንጎ፣ አቡካዶና የመሳሰሉ አትክልቶችንም እየተከልን ነው። በክልሉ አራት የከተማ አስተዳደሮች አሉ። በሁሉም የማፅዳትና ማስዋብ ሥራዎችን ያለ ማቋረጥ እየሠራን እንገኛለን። በሠራነው ልክም ውጤታማ እየሆንን ነው።
አዲስ ዘመን:- ሀገራዊ አጀንዳ በሆነው የሌማት ትሩፋት ዘርፍስ የተሠሩ ሥራዎች ይኖሩ ይሆን?
አቶ አሻድሊ:- አዎ! ተጠቃሽ ሥራዎች አሉ። በክልላችን አሶሳ ከተማ ውስጥ ሁሉን አካታች የሆነ ሞዴል ማእከል ተፈጥሯል። የተገነባውም በክልል ፕሬዚዳንት ልዩ ጽሕፈት ቤት ድጋፍና ክትትል ነው፤ አሁንም ድጋፍና ክትትሉ አልተቋረጠም። በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። የዋጋ ግሽበትን ከመከላከልና መቆጣጠር ባሻገር፤ ነዋሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ ነው። ዶሮ፣ እንቁላል፣ ማር፣ አይብ ወዘተ ለገበያ በመቅረብ ላይ ይገኛል። ገበያን የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ ለውጥም ተገኝቶበታል። ዘርፉ የግል ባለሀብቶችም እንዲገቡበት እየተደረገና እየተስፋፋ ይገኛል። ሌሎች፣ እስከ ገጠር ወረዳና ቀበሌዎች ድረስ እሱን በሞዴልነት እንዲከተሉትና እነሱም እሱን መሰል ማእከል እንዲገነቡ እየተደረገ ነው። 25 ሺህ የአንድ ቀን ጫጩት መያዝ የሚችል ማእከል (ኢንኪዩቤተር)ም በመገንባት ላይ ነው።
ከሌማት ትሩፋት አንዱ የሆነው የዓሳ ልማትም እየተሠራባቸው ካሉት ተግባራቶቻችን አንዱ ሲሆን፤ በተለይ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የዓሳ ልማቱ በጥሩ ሁኔታ እየተሠራበት ይገኛል። ወጣቶች እየተደራጁ በመሥራት ላይ ናቸው። ከፍሪጅ ጀምሮ እስከ እንዴት ፕሮሰስ አድርጎ ለገበያ (ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ) ማቅረብ እስከሚቻልበት ሁኔታ ድረስ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል መሠረተ ልማት እየተካሄደ ነው። በተለይ ከአቅርቦትና ገበያን ከማረጋጋት አኳያ ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየታዩ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን:- ወደ ሠላም እና ፀጥታው ዘርፍ እንምጣና የነበሩትን ተግዳሮቶች፤ እንዲሁም፣ አሁን ያለውን ተጨባጭ የሠላም፣ ፀጥታና ደህንነት ሁኔታ ቢገልፁልን?
አቶ አሻድሊ:- ከለውጡ በኋላ ወይም የለውጡን መምጣት ተከትሎ ጥቅሜ ይቀራል በሚል ያኮረፉና ወደ ጦርነት ሳይቀር የገቡ ኃይሎች አሉ። እነዚህ ኃይሎች የፈጠሩት ቀውስ በክልሉ ሰላም እንዲደፈርስ አድርጎ መቆየቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በተከፈለው ውድ መስዋእትነት አሁን በክልላችን አንፃራዊ ሰላም ሊገኝ ችሏል። በአሁኑ ሰአት በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች መንቀሳቀስ ይቻላል። ትንሽ ችግር ያለው ከአጎራባች ክልሎች ጋር ለመገናኘት አለመቻሉ ነው። በአጎራባች ክልሎች አሁንም የፀረሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ አለ። ከአሶሳ ወደ ባህር ዳር፤ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ትንሽ ችግር አለ። በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎችም እንደዛው። ይህ ደግሞ ሸቀጦችን ከማሳለጥ አኳያ የራሱ የሆነ ችግር ፈጥሯል። ልማት ላይ ሳይቀር እንቅፋት እየሆነ ነው። ሁሉም በእርግጠኝነት በቅርቡ መፍትሄ ያገኛል ብዬ አስባለሁ።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ ነው። ከጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ጋርም እጅና ጓንት በመሆን ሥንሰራ ነው፡፡
አኩርፈው ጫካ ከገቡት፣ ወደ ጎረቤት ሀገር በመሄድ ተመልሰው ሀገራቸውን ሲወጉ ከነበሩት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ያልተቋረጠ ውይይት በማድረግና ስምምነት ላይ በመድረስ፤ ወደ ሰላም እንዲመለሱና በልማት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል። በተደረጉት ስምምነቶች ምክንያትም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት፣ በተለያዩና ባላመኑባቸው ምክንያቶች ወደ ጫካ ገብተው የነበሩት ሲሆኑ፣ ወደ ሰላም ተመልሰው በልማት ሥራዎች ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ። ይህ ትልቅ ስኬት ነው ብለን ነው የወሰድነው።
የጠረፍ አካባቢ እንደ መሆኑ መጠን፣ ክልሉ ረዘም ላለ ጊዜ የፀጥታ ችግር ውስጥ መቆየቱ ጎድቶናል። አሁን አንፃራዊ ሰላም አግኝተናል። የመልሶ ግንባታ ሥራዎችንም እየሠራን እንገኛለን። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ብዙ እያገዘን ሲሆን፣ በራሱ ወጪ ትምህርት ቤትና መንገዶችን ሁሉ እስከ መሥራት የዘለቀ ድጋፍን አድርጎልናል። በአማራ በኩል ያለውን ችግር ለመቅረፍም ከክልሉ ሥራ ሃላፊዎች ጋር እየሠራን እንገኛለን። በእነሱም በኩል ድጋፍ አለን።
ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የጋራ (ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ) ጽሕፈት ቤት አቋቁመን እየሠራን እንገኛለን። የጽሕፈት ቤት ህንፃ (ጂ+4) ግንባታውም እየተገባደደ ይገኛል። አብሮና በጋራ በመሥራት ሰላም ማምጣት ይቻላል በሚል እሳቤ የተቋቋመ ጽሕፈት ቤት ነው።
መንግሥት “ያ የኔ፣ ያ ያንተ ችግር ነው” ከመባባል ይልቅ “የአንዱ ችግር የእኔም፣ የሁላችንም ችግር ነው” ብሎ በመውሰድ በጋራ ችግሩን ለመፍታት መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ ይዟል። በዛ መሠረት ነው ይህ በጋራ የመሥራት ነገር የመጣው።
እንደ ሀገር ሁሉ፣ እንደ ክልልም እኛንም ፈተና ውስጥ የከተቱን በርካታ የሰላም እጦት ችግሮች አጋጥመውናል። በተለይ የሰላም ማጣት ከፍተኛ ፈተና ሆኖብን ነበር። ይሁን እንጂ፣ በዛ ውስጥ ሆነን ነው ብልፅግናን ማምጣት የቻልነው። የብልፅግና መንግሥት ችግሮችን፣ ፈተናዎችን ወደ እድሎች መቀየር የሚችል መንግሥት በመሆኑ እነዛን ሁሉ አልፈን ነው እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ የቻልነው።
አዲስ ዘመን:- የሥራ እድልን በተመለከተ እርስዎ በሚያስተዳድሩት በዚህ ክልል ያለውን ተጨባጭ እውነታ ቢነግሩን።
አቶ አሻድሊ:- በአጠቃላይ በተለያዩ መስኮች (ዘርፎች) ከ34 ሺህ በላይ የሥራ እድል ተፈጥሮ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ተጠቃሚዎችም ከራሳቸው አልፈው አካባቢዎቻቸውን ሁሉ መቀየር ችለዋል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ብስክሌት እንኳን የማያውቁ አካባቢዎች ዛሬ ባለ መኪናዎች የሆኑት በክልሉ በተፈጠረው የሥራ እድል አማካኝነት ነው።
ከለውጡ በኋላ ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 11 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አሉ፤ ሰባቱ አነስተኛ ናቸው። በእነዚህ አማካኝነት በአመት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት የተጀመረ ሲሆን፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ በቆሎ እና ሌሎች ምርቶችም እየተመረቱ ይገኛሉ። አሁን ያለው ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገረ አርሶ አደር ነው። ይህን እያስፋፉ መሄድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። በእርግጠኛነት መናገር የሚቻለው የሰላም ችግሮቻችንን ሙሉ ለሙሉ ካስወገድን በጥቂት ዓመታት ውስጥ የፈለግነው የብልፅግና ምእራፍ ላይ እንደርሳለን። ራሳችንን ከመቻልም አልፈን ለሌላውም በመትረፍ ለሀገራችን ብልፅግና የበኩላችንን እንወጣ ለማለት እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቶ አሻድሊ፡- እኔም እዚህ ድረስ በመምጣት ይህንን እድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም