ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ከመደረሱ በፊት ዩክሬን ‘ከግዛቶቼ’ ወታደሮቿን ልታስወጣ ይገባል ሲሉ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ።

ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው፤ የሩሲያ ኃይሎች ክሪሚያን ጨምሮ ከሁሉም የዩክሬን ግዛቶች ለቀው ካልወጡ ሀገራቸው ከሞስኮ ጋር እንደማትደራደር ተናግረዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ጨምረውም የሰላም ስምምነቱ ከመጀመሩ በፊት ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የመሆን ፍላጎቷን መተው አለባትም ብለዋል።

ፑቲን ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች የገለጹበትን መግለጫ ያወጡት ከ90 ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች ትናንት ቅዳሜ በስዊዘርላንድ ተገናኝተው በዩክሬን ሰላም ላይ ለመምከር በዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ነው። በዚህ ጉባኤ ላይ ሩሲያ አልተጋበዘችም።

ፑቲን አርብ ዕለት በሞስኮ ከሚገኙ አምባሳደሮች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፤ የዩክሬን መንግሥት በከፊል በሩሲያ ከተያዙት አራቱ ክልሎች ከዶኔስክ፣ ሉሃንስክ፣ ኼርሶን እና ዛፖሬዢያ ለቆ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ፑቲን ጨምረውም ዩክሬን የሩሲያን የጦር ግስጋሴ ለመግታት የኔቶን ወታደራዊ ጥምረት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት በይፋ ማቆም አለባትም ብለዋል።

“ኪዬቭ በእነዚህ ቅደመ ሁኔታዎች ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ዝግጁ ስትሆን በእኛ በኩል ወዲያውኑ ተኩስ እንዲቆም እና ድርድር እንዲጀመር ትዕዛዝ እናስተላልፋለን” ብለዋል ፑቲን።

የዩክሬን የፕሬዚዳንት አማካሪ ሚካኼሎ ፖዶልያክ ፑቲን ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታ “አሳፋሪ” ብለውታል።

አርብ ዕለት ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ለጣልያኑ ስካይ ቲጂ24 ቴሌቪዥን ሲናገሩ “ይህ መልዕክት ሒትለር በመጨረሻው ሰዓታት ካደረገው ንግግር ጋር ተመሳሳይ ነው። ሒትለር በንግግሩ የቼኮዝላቫኪያን ክፍል ስጡኝ ብሎ ነበር” ብለዋል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን በበኩላቸው፤ ሩሲያ ያቀረበችውን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አድርገው፤ ፑቲን የዩክሬንን ሉዓላዊ ግዛት በሕገ ወጥ መንገድ ይዘዋል ሲሉ ከሰዋል ።

“ሰላም ለማምጣት በሚል ፑቲን ዩክሬንን ለመጨቆን ምንም ሥልጣን የለውም” ብለዋል። የኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልትንበርግ በበኩላቸው፤ ፑቲን ያቀረቡት ሃሳብ “በቅንነት የቀረበ አይደለም” ብለውታል።

የሩሲያ የፖለቲካ ተንታኝ ታቲያና ስታኖቫያ እንደሚሉት፤ የፑቲን ዕቅድ ስምምነት ላይ የማያደርሱ ጥያቄዎችን በማቅረብ የሰላም ንግግሩ ከመጀመሩ በፊት የንግግሩን ዋጋ ለማሳነስ ያለመ ነው።

ዜሌንስኪ ትናንት ቅዳሜ ዕለት የሚካሄደውን ጉባኤ የሚሳተፉ ሲሆን፣ ሰፊ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል።

የጉባኤው ዓላማ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በተባበሩት መንግሥታት ስምምነቶች መሠረት የዓለም መሪዎች ለዩክሬን ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የመወያያ መድረክ መክፈት እንደሆነ የስዊዝ መንግሥት ገልጿል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሐሪስ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ፣ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ላይን ይሳተፋሉ።

ሩሲያ በጉባኤው ላይ ያልተጋበዘች ሲሆን፤ ቻይናም ጥሪ ቢቀርብላትም ሩሲያ ባልተገኘችበት ጉባኤ ላይ እንደማትሳተፍ ገልጻለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You