ሲሪል ራማፎሳ ለሁለተኛ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ

ለቀናት መንግሥት ለመመስረት በውዝግብ ውስጥ የቆየው የደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ በመጨረሻም ሲሪል ራማፎሳን ለሁለተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመን ፕሬዚዳንት አድርጎ ተጠናቋል።

የማንዴላ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ከአፓርታይድ ማብቃት ከሦስት አስርት አመታት በኋላ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2024ቱ ምርጫ መንግሥት ለመመስረት የማያበቃውን ዝቅተኛ ድምጽ አግኝቷል።

ይህን ተከትሎ አጣማሪ መንግሥት ፍለጋ በምርጫው ከተሳተፉ የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ንግግር ሲያደርግ የሰነበተው ኤኤንሲ በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ከሚመራው ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ጋር ለመጣመር ተስማምቷል።

ፓርላመንታዊ ሥርዓትን በምትከተለው ደቡብ አፍሪካ ፓርቲዎች ለምክር ቤቱ ወንበር ከተወዳደሩ በኋላ የምክር ቤት አባላቱ ፕሬዚዳንቱን ይሰይማሉ።

ሲሪል ራማፎሳ 400 መቀመጫዎች ባሉት ፓርላማ ከኢኤፍኤፍ ፓርቲ መሪው ጁሊየስ ማሌማ ጋር ለእጩነት የቀረቡ ሲሆን 283 የድጋፍ ደምጽ በማግኘት ለሁለተኛ ጊዜ ሀገራቸውን የመምራት እድል አግኝተዋል ።

ፕሬዚዳንቱ በፓርላማው ምርጫ ከፓርቲያቸው ኤኤንሲ በተጨማሪ በ2024ቱ ምርጫ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድምጽ ካገኘው ዴሞክራቲክ አሊያንስ ሰፊ ድጋፍን አግኝተዋል። እራሱን በፓን አፍሪካኒስትነት የሚገልጸው ጁልየስ ማሌማ ዝቅተኛ የተባለውን 44 ድጋፍ አግኝቷል።

ጥምር መንግሥት የመሰረቱት አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ እና ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ በርዕዮተ ዓለም እና በፖለቲካዊ አተያይ ፍጽም የተለያዩ ቢሆንም ደቡብ አፍሪካን በጋራ ለማስተዳደር ተስማምተዋል።

ተንታኞች የነጻነት ታጋይ በነበረው ኤኤንሲ እና በለዘብተኛው ዲኤ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆን ለራማፎሳ መንግሥት መጽናት አደጋ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ለአብነት ራማፎሳ በእስራኤል ጉዳይ ጠንካራ አቋም ይዘው በዓለም ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ድረስ እንድትቀርብ እየጣሩ ቢሆንም አጣማሪው ፓርቲ ግን በዚህ ጉዳይ የተለየ አቋም ያለው ነው።

ራማፎሳ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ይህ ለደቡብ አፍሪካ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው የተለያየ አቋም ቢኖረንም በደቡብ አፍሪካዊያን ደህንነት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ ተቀራርበን እንሠራለን” ብለዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You